Saturday, 21 December 2019 13:11

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ተቋቋመ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  የሙዚቃ ባለሙያዎችን መብት ለማስከበርና ሥራዎቻቸውን ካልተገባ ብዝበዛ ለመታደግ ያስችላል የተባለ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ተመስርቷል፡፡ ለዚህ ማህበር እውን መሆን ከፍተኛ መስዋዕትነትን በከፈለውና በቅርቡ በሞት በተለየው እውቁ የሙዚቃ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ ስም የሙዚቃ ማዕከል ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ የማህበሩ የቦርድ አባል ሆኖ ከተመረጠው የኤልያስ መልካ ቅርብ ጓደኛ ከነበረው ኃይለ ሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩት) ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡



               ማህበሩን ለመመስረት እስካሁን የሄዳችሁበትን ርቀትና ያለፋችሁበትን ፈተና የሚያስቃኝ ዘጋቢ ፊልም ለዕይታ አቅርባችኋል:: እስኪ አጠቃላይ ሂደቱን ግለጽልኝ…
እኛ ትግል የጀመርነው ህጉን ይዘን፣ ከአዋጁ አንፃር ነው፡፡ እንደሚታወቀው፤ ስንቃወም የነበረው የሰውን መደራጀት አልነበረም፡፡ እኛ ባለቤቶቹ እያለን ሌላ አካል ወክሎን ሲሰራ የነበረው ነገር፣ ትክክል አልነበረም እያልን ነበር:: “ምክንያቱም ሙዚቃ ምንም ላይ ሳይለጠፍ፣ ብቻውን መደራጀት ይችላል፡፡ ብቻውን እንዲደራጅ አዋጁም ይፈቅዳል፣ ሁሉም የሙያ ዘርፍ በየራሱ ተደራጅቶ የራሱን ሮያሊቲ እንዲሰበሰብ ነው አዋጁ የወጣው፣ ይህን ነገር ተረዱልን፤ የጋራ አስተዳደር ማህበራት ነው የሚለው አዋጁ” እያልን ስንጮህ ከርመናል:: ይሄ ነገር ብዙ አድክሞናል፤ በተለይ ኤልያስ መልካ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ እዚህ ላይ ደርሰናል:: ዋናው ነገር የሮያሊቲ ክፍያን ማስጀመር ነው፤ ትልቁ ግብ፡፡ ባለሞያው ሲጐዳ የነበረው የሮያሊቲ ክፍያ ባለመጀመሩ እንጂ ስላልሰራ ወይም ስለሰነፈ አልነበረም፡፡
እንዳየነው ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጥሩ ጥሩ ህግ አለ፡፡ ነገር ግን ህጉ ተግባር ላይ የለም፡፡ ለምሳሌ የንግድና ኢንዱስትሪ ህግ ላይ ፈቃድ በሚሰጡ አዋጆች ውስጥ ህጉ አለ፡፡ አንድ ቤት ሙዚቃ የሚያጫውት ከሆነ፣ ፈቃድ እንዲኖረው፣ ፊልም የሚያሳይም ከሆነ እንደዛው ማድረግን የሚጠይቁ ሮያሊቲን የተመለከቱ ህጐች አሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ህጐች ተግባር ላይ አልዋሉም፡፡ እነዚህን ህጐች ተግባር ላይ ለማዋል አንድም ባለሞያው መነሳት ነበረበት፡፡ ለምን ማንም ቢሆን ለመብቱ መጀመሪያ መነሳት ያለበት ራሱ ነው፡፡ … ይህ ጥያቄ ሲነሳ የነበረው ከነጋሽ ፍሬው ጀምሮ ነው እስካሁን ምላሽ ሳያገኝ ቆየ፡፡ አሁን ግን “መብታችን ይከበር” ብለን እኛው ራሳችን ተነሳን፡፡ ባደረግነው ትግልና ጥረት፣ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በኩል ማህበሩ ተመስርቷል ማለት ነው፡፡
ዘጋቢ ፊልሙን ማህበሩን ለመመስረትና መብታችሁን ለማስከበር የሄዳችሁትን ርቀትና ያለፋችሁትን ፈተና የሚያሳይ ነው፡፡ እስቲ ስለ ዘጋቢ ፊልሙ አሰራር ንገረኝ…
ዘጋቢ ፊልሙን የሰራንበት ምክንያት፣ እኛ ብዙ ጊዜ ብንናገርም ብንሟገትም፣ ብዙዎቹ የችግሩን ሊረዱት አልቻሉም፡፡ በተለይ የመንግስትና አንዳንድ አካላት ማለቴ ነው:: ስለዚህ ሁሉም እንዲረዱት ዘጋቢ ፊልሙን መስራት ነበረብን፡፡ “ፍትህ ያጣች ነፍስ” ይሰኛል፡፡ የሰራነው እኔ፣ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) እና ኤልያስ መልካ ነን፡፡ ለምሳሌ ትረካውን የፃፈው ኤልያስ መልካ ነው፡፡ ሱራፌል የሚባል ልጅም ሆነን የኖረው በሞቱ ሲለመን ነበር የቆየው፡፡ ይሄ ነገር ኖርማል ሆነና ተለመደ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ይሄ መቅረት አለበት፡፡ ሲዲ ኮፒ መደረጉ ብቻ ከአይደለም፡፡ አርቲስቱንና ሙዚቃውን የጐዳው ዋናው ነገር፣ ሰው ሙዚቃ ሰርቶ ለሙዚቃ ነጋዴዎች በውል የሰጠው ስራ፣ ውሉ ሲያልቅ ለባለቤቱ አለመመለሱ ነው፡፡  ከዚያ ደግሞ ሮያሊቲ ክፍያ አለማግኘቱ ነው:: አንድ የመንግስት ሰራተኛ በጡረታ ሲገለል፣ ምንም አይነት የስራ ደረጃ ላይ ይሁን በዛም አነስ ጡረታ አለው፡፡ የእኛ ጡረታ ግን ምንድነው?   ጡረታችን የሮያሊቲ ክፍያ ነው፡፡ ስራችን በንግድ ቤት ይሰማል፤ ብዙ ነገር ያሻሽጣል፣ ሰዎች ይማሩበታል፣ ከዚያ ወጣት በዚያ ስራ ሲለማመድ ቆይቶ ወደ ራሱ ስራ በመምጣት፣ ያ ወጣት ራሱን ችሎ ይኖርበታል፡፡ ብዙ ነገር አለው፤ ነገር ግን በዚህ ሁሉ ባለቤቱ ተጠቃሚ ሳይሆን ጥሩ ሕይወት ሳይኖር ያልፋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የመጀመሪያው ስራ፤ ሰው ግንዛቤ አግኝቶ ማህበሩን መመስረት ነበር፤ ተሳክቷል፡፡ ዘጋቢ ፊልሙም የዚህ አንዱ አካል ነው፡፡
ኤልያስ ከህመሙ ጋር እየታገለ ቆይቶ ማህበሩ ሳይመሰረት ቢያልፍም፤ የሱ መታሰቢያ ሆኖ በልደቱ ቀን ተመስርቷል፡፡ በልደቱ ቀን እንዲመሰረትና የሱ መታሰቢያ ይሁን የሚለው ሀሳብ እንዴት ታሰበ?
ኤልያስ ማለት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ሁሉ ነገሩን የሰጠ ነው፡፡ እናም ከልቡ ታማኝ ሆኖ ለሙዚቃ የኖረ ሰው ነው፡፡ አልፎም ተርፎ ለሙዚቀኞች መብት ሲታገል ነው ያለፈው፡፡ እኔ እስከ መጨረሻው ህልፈት ድረስ አጠገቡ ነበርኩኝ፡፡ እረፍት አያደርግም ነበር፤ እኔ አውቃለሁ፡፡ በተለይ ላለፉት ሶስት ዓመታት ያሳለፍናቸው ጊዜያት፤ ከባድና ፈታኝ ነበሩ:: እንዳልሽው እሱ ከበሽታው ጋር እየታገለ፣ አልፎም ደግሞ መብቱን ከሚነጥቁ አካላት ጋር እየታገለ ነበር ያሳለፍነው፡፡ ሁላችንም የራሳችን ጉዳይ ስለነበር፣ አብረን ትግሉና ፈተናው ውስጥ ነበርን፡፡ ለኤሊያስ መታሰቢያ መሆኑና በልደቱ ቀን ማህበሩ መመስረቱ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም፡፡ ይህንን ሀሳብ ያመጣነው እኛው ነን፡፡ ለህብረቱም ያቀረብነው እኛው ነን፡፡
ትላንት ረጅሙን ሰዓት የወሰደው የቦርድ አመራሮች ምርጫ ነው፡፡ እስቲ የምርጫውን ሂደት ንገረኝ?
እውነትሽን ነው፤ ብዙውን ሰዓት የፈጀው የቦርድ አመራሮች ምርጫና ድምጽ ቆጠራው ነው፡፡ ይሄ ስራ የመጀመሪያ እንደ መሆኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ በጣም በጥንቃቄ መስራት ነበረብን:: የሰው ሀይል እጥረት ስለነበረም ይሆናል፤ ብቻ ረዝሞ ነበር፡፡ ነገር ግን በስተመጨረሻ በግልጽነት 11 አባላት ተመርጠዋል፡፡ አብዛኛው የህብረቱ አባላት፤ ይሄ ማህበር እውን እንዲሆን የተደረገውን ትግልና ሂደት በደንብ ያውቅ ስለነበር ማህበሩን ቢመሩ የተሻሉ ናቸው የተባሉትን ህብረቱ መርጧል::  በዚህም መሰረት፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ንዋይ ደበበ፣ ጌቴ አንለይ፣ እኔ፣ ብሩክታዊት ጌታሁን (ቤቲ ጂ)፣ ሔኖክ መሀሪ፣ ሞገስ ተካ፣ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ)፤ ሀይልዬ ታደሰና አቤል ሙሉጌታ… ብቻ 11 ነን የተመረጥነው፡፡ ማን ሰብሳቢ ማን ፀሐፊ ይሁን የሚለው በዚህ ሁለት ሶስት ቀናት ውስጥ ይሰራበትና ይፋ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ኤልያስ ያቋቋመው “አውታር መልቲ ሚዲያ” የተሰኘው ድርጅት የወደፊት ዕጣ ፋንታ ምን ይሆናል?
አውታር የተቋቋመው ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር (በፒኤልሲ) ሲሆን ኤልያስ አንዱ ባለድርሻችን ነበር፡፡ በእኔ፣ በዳዊት ንጉሴ፣ በጆኒራጋና በኤልያስ መልካ የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱ እንግዲህ ይቀጥላል፡፡ እንደውም በቅርቡ አዲስ ስርአትም ዘርግተዋል፡፡ በጣም ደስ የሚል፣ ከአገሪቷ ሲስተም ጋር ተስማሚ የሆነ ሲስተም ነው የተሰራው፡፡ አውታር ይቀጥላል፤ የኤልያስን ሌጋሲም ያስቀጥላል:: ከእርሱ ጋር ተያይዞ የምናስባቸውና ወደፊት ይፋ የምናደርጋቸው ነገሮች ስላሉ በደንብ ይቀጥላል፡፡
በብሄራዊ ቴአትር በተከናወነው የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ “ኤልያስ የጀመራቸው ስራዎች በመሞቱ ብቻ አይቆሙም፤ ይቀጥላሉ” ብለህ ስትናገር ሰምቻለሁ፡፡ እጃችሁ ላይ ምን ምን ስራዎች አሉ? እንዴትስ ነው የምታስቀጥሏቸው?
ኤሊያስ ስራ ጀምሮላቸው የነበሩ 33 አዳዲስ ወጣት አርቲስቶች ነበሩ፡፡ እናም እነዚህ ልጆች ስራቸው በሥነ ሥርዓት እንዲሰራና እንዲያልቅ የኤሊያስ መልካ ጓደኞች፣ አቀናባሪዎችና የድምጽ ባለሙያዎች ማለትም እነ ሰለሞን ኃ/ማሪያም፣ አቤል ጳውሎስ፣ ዳግማዊ አሊና እነ ማሩ (የእርሱን ነገርና ፍላጎት በቅርበት የሚያውቁ ስለሆኑ) እያገዙን ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች እሱ ጀምሯቸው የነበሩ ስራዎች ተጠናቅቀው ለሕዝብ እንዲቀርቡ፣ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ሌላው በኤሊያስ ስም የሙዚቃ ማዕከል እንዲቋቋም ከፍተኛ ጥረት እያደረግን ሲሆን ጉዳዩ ወደ አዲስ አበባ ባህል ቱሪዝምና ኪነ ጥበባት ቢሮ ደርሷል::
ፕሮፖዛሉን ያስገባው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፎች ማህበራት ህብረት ነው፡፡ ይህም በጥሩ ሁኔታ እንደሚሳካና ከሀላፊዎቹ መልካም ምላሽ እንደሚገኝ እምነታችን ነው:: በአጠቃላይ መልካም ጉዞ ላይ ነን፡፡ ከምንም በላይ ኤሊያስ በሕይወት እያለ የልፋቱን ውጤት ቢያይ ምኞታችን ነበር፤ ነገር ግን ይህ አልሆነም:: ይሁን እንጂ እኛ የእሱን አሻራዎች ጠብቀው የሚያቆዩና የሚያስታውሱ ነገሮች እንዲኖሩ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡
በተረፈ ለሙዚቀኞች እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ ትግላችን፣ አብራችሁን ሆናችሁ ስታግዙን ለነበራችሁ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞችም ከልብ እናመሰግናለን፡፡


Read 1183 times