Saturday, 21 December 2019 13:14

የቦርድ ሊቀ መንበሩ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

     ኤልያስ የሆስፒታሉ እንግዳና መቀበያ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ ስሙ እስኪጠራ እየተጠባበቀ ነው፡፡ ይህ አዲስ ሆስፒታል ከተቋቋመ አመት እንኳን ያልሞላው ቢሆንም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዝነኛ ለመሆን የበቃው በምንም ሳይሆን፣ አሉ የተባሉ አገሪቱ ያፈራቻቸውን ሃኪሞች በውድ ገንዘብ መቅጠር በመቻሉ እንደሆነ ኤልያስ ከሁነኛ ሰው ሰምቷል። ሌላው ይህን ሆስፒታል ልዩ የሚያደርገው የፕላስቲክ ሰርጀሪ ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ብቸኛው ሆስፒታል በመሆኑም ጭምር ነው፡፡ የኤልያስ አመጣጥም ዋናው ምክንያት ይኸው ነበር፡።
ከወር በፊት መልካም መልካም የነበረው ፊቱ፤ የተጨማደደ የጨርቅ ኳስ ስለመሰለ፣ የተጠየቀውን ከፍሎ የቀድሞ ገፅታውን ለማስመለስ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ የሕክምናው ቦርድ ሊቀመንበር ከመጀመርያው እንዳልወደደው መግለጽ እንወዳለን፡፡ ‹‹የባንክ ሂሳብ ደብተርህንና አንዳንድ ማንነትህን የሚገልጽ ማስረጃ አምጣ?” ባለው መሰረት፤ መታወቂያውንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰሜን ቅርንጫፍ የቁጠባ ሂሳብ ደብተሩን ይዟል፡፡ የባንክ ደብተሩ ተቀማጭ ሂሳብ፣ አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃምሳ ስድስት ሺህ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም ጥሪት እንዳለው ያሳያል። እንግዲህ ህክምናው ምን ያህል ወጪ እንደሚፈጅ አሁን ነው የሚለየው፡፡ መቼም ይሄን ገንዘብ አንድ የሕንጻ ጥበቃ ሰራተኛ ‹እንዴት በስድስት ወራት ውስጥ ሊያፈራ ቻለ? ብሎ መጠየቅ ከማንኛውም ማሰብ የሚችል ሰው የሚጠበቅ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ እኛም ይህንን ለማብራራት ዝግጁ ነን፡፡
የወር ደሞዙ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር የሆነው የሰላሳ አምስት አመቱ ኮበሌ ኤልያስ ተሰማ፤ ከቤት ኪራይ፤ ከምግብና ከአረቄው (አንዳንድ ወጪዎቹን ሳይጨምር) ውጭ ከደሞዙ ምንም አይተርፈውም፡፡
ሕንጻው ስር ካለው ምድር ቤት፣ ሁለት ፎቆች ወደ ታች - ሶስት መቶ መኪኖች ሲያድሩ ጠባቂው እሱ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ከሕንጻው ሰባተኛ ፎቅ ላይ የሚኖር ሃብታም፤ ጀሪካንና የፕላስቲክ ቱቦ ይዞ መጣና የመኪናውን የነዳጅ ታንከር ከፍቶ ጎማውን ወደ ታንከሩ ሰዶ፣ በአፉ ነዳጁን በመሳብ ወደ ጀሪካኑ ሲቀደ ተመለከተ፡፡ ቱጃሩ ወደ አስር ሊትር ያህል ቀዳና ጀሪካኑን ይዞ ወደ ፎቅ ወጣ። ከዚያ ቀን በኋላ የኤልያስ የሲሳይ በር ተከፈተ ማለት ይቻላል። ከሚጠብቃቸው መኪኖች ውስጥ እሩብ ያህሉ የነዳጅ ታንከራቸው ቁልፍ የለውም፡፡ በቀን ከሃምሳ መኪኖች ከአንድ ሊትር እስከ አምስት ሊትር መቅዳት ጀመረ፡፡ ከግብረ አበሮቹ ጋር ከህንጻው እያወጣም አንዱን ሊትር በሃያ ብር ይቸበቸብ ያዘ፡፡ ይሄም በጣም አስደሳችና የማይነጥፍ የገቢ ምንጭ ሆነለት፡፡ ለስድስት ወራት ያህል ሁኔታው ሳይቋረጥ ቀጠለ፡፡ ልክ የዛሬ ወር ያልተጠበቀ ነገር ተፈጠረ፡፡ የገቢ ምንጩ ድንገት ተቋረጠ፡፡ ነገሩ እንዲያው ዝም ብሎ አልነበረም የቆመው፡፡ የሱ ያልነበረው ነገር ከሱ ሲሄድ፤ የሱ የነበረውንም ይዞበት ጭምር ነው የሄደው፡፡
አንድ ቀን እንደለመደው አንዱን መኪና ከፍቶ ጎማውን ወደ ታንከሩ ካስገባ በኋላ ነዳጁን ሲመጥ፣ አፉና ፊቱ ላይ ተደፋ፡፡ ያኔ ፊቱ በእሳት ተጠበሰ፡፡ የላይኛው ከንፈሩ፣ አፍንጫውና አገጩ እንዳልነበሩ ሆኑ፡፡ መልከ መልካሙ ኤልያስ፤ ሌላ አሰቃቂ ፍጡር መሰለ፡፡
ቀን ላይ ባለመኪናው አንድ ጀሪካን ነዳጅ ይዞ ወደ አንድ የሕንጻ መሳርያ ጎራ ብሎ ነበር፡፡ የገዛውን ገዝቶ ሲወጣ፣ አጠገቡ የሱ አይነት ቢጫ ጀሪካን ሰልፈሪክ አሲድ የያዘ የሌላ ገበያተኛ ጀሪካን መሬት ላይ ተቀምጧል፡፡ ባለመኪናው ሂሳብ ሲከፍል ሌላው ገበያተኛ፣ የባለመኪናውን ነዳጅ የያዘ ጀሪካን የራሱ መስሎት ይዞት እብስ አለ፡፡ ባለመኪናው ከፍሎ ሲጨርስ፣ አሲድ የያዘውን የሱ ያልሆነ ጀሪካን ይዞ ከሱቁ ወጣ፡፡ መኪናውን ምድር ቤት ሕንጻው ጋ አቁሞ፣ ወደ ቤቱ ከመሄዱ በፊት በጀሪካን የነበረውን አሲድ ወደ መኪናው የነዳጅ ታንከር ገለበጠው፡፡ እንግዲህ ያንን አሲድ ነበር ኤልያስ የተጋተው፡፡
***
ሆስፒታሉ ውስጥ ተራውን ሲጠብቅ የነበረው ኤልያስ፤ ስሙ ተጠራና የቦርዱ ሊቀ መንበር ወዳለበት ዘጠኝ ቁጥር ቢሮ አመራ:: ፊቱ በስካርቭ ቢሸፈንም ጉዳቱ ክፉኛ ስለነበር፤ ሊደብቀው አልቻለም፡፡ ሰው ሁሉ አፍጦ ያየዋል፡። ወደ ቢሮው ገባና ወንበር ላይ ተቀመጠ፡፡
ጉረኛው የሆስፒታሉ የቦርድ ሊቀ መንበር ገና እንዳየው ነበር የጠላው፡፡ ሃይሉንና ስልጣኑን እሱ ላይ ለማሳየት ቆርጦ የተነሳ ይመስላል፡፡ ነገሩ ሥራው፤ እንደ ትልቅ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ያደርገዋል፡፡ ግን ይህ ሆስፒታል ከሌሎች በምን ይበልጣል? በምንም፡፡ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ህክምና ስላለው ብቻ እንጂ ሌላ ምን አለው? ምንም!
‹‹ጉዳቱ ከባድ ስለሆነ ሕክምናው ቀላል አይደለም›› አለ ጉረኛው የቦርድ ሊቀ መንበር፤ መነጽሩን ወደ ላይ ገፋ እያደረገ፡፡ ‹‹ባደረግነው ምርመራ ብዙ ድካምና ጥበብ የሚጠይቅ ሕክምና የሚያስፈልገው እንደሆነ ደርሰንበታል። ስለዚህ ሕክምናው የሚጠይቀው ወጪ ይህን ያህል ነው” አለና፤ ትልቅ አሃዝ የተጻፈበት ወረቀት ሰጠው - እየተጀነነ፡፡ ኤልያስ ወረቀቱን ተቀብሎ በግርምት አትኩሮ ተመለከተው፡፡ ሊቀ መንበሩ የባንክ ደብተሩን አልተመለከተም፡፡ ታዲያ እንዴት ይህንን ቁጥር ሊጽፍ ቻለ? አንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሃምሳ ስድስት ሺህ ብር ከሃያ አምስት ሳንቲም፡፡ ኤልያስን ወደ ተፈጥሮ መልኩ ለመመለስ የተጠየቀው ገንዘብ የባንክ ደብተሩ ላይ የሰፈረው ነው - እቅጯን!       

Read 2061 times