Saturday, 21 December 2019 12:37

አዲስ መጽሐፍ ሰኞ በገበያ ላይ ይውላል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀሱ ቀደምት ጋዜጠኞች ተርታ በሚሰለፉትና በርካታ መጻሕፍትን ለንባብ በማብቃት በሚታወቁት አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ነቢዩ ኢያሱ የተጻፈውና በኢትዮጵያውያን የስደት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥነው “Dreamers of the Horn - The Story Behind Ethiopian Migration” የተሰኘው መጽሓፍ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በገበያ ላይ ይውላል፡፡
ለረጅም አመታት በውጭ አገራት የኖሩት ደራሲና ጋዜጠኛ ነቢዩ ኢያሱ፣ የራሳቸውን የስደት ተሞክሮ መነሻ በማድረግ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያዘጋጁት መጽሐፉ፤ በኢትዮጵያውያን ስደት ዙሪያ ታሪካዊ ሰነዶችን ያካተተና በጥናት የተደገፈ ሲሆን፣ በየዘመናቱ ዜጎችን ለስደት ሲዳርጉ የነበሩ ምክንያቶችን፣ የስደት ጉዞዎችን አስከፊነት እንዲሁም በዓለም ዙሪያ የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን የሚገኙበትን ወቅታዊ ሁኔታና እያሳለፉት ያለውን የስደት ህይወት በጥልቀት የሚተነትን እንደሆነ ተነግሯል፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛ ነቢዩ ኢያሱ ከራሳቸው የረጅም አመታት የስደት ሕይወት ተሞክሮ በተጨማሪ በአውሮፓ፤ በአሜሪካና በአፍሪካ አህጉራት በመዘዋወር ያካበቱዋቸውን ልምዶች እንደ ትልቅ ግብአት በመጠቀም ባዘጋጁት በዚህ መጽሐፋቸው፤ በጋዜጠኝነት ሕይወታቸው ያጋጠሟቸውንና ከዚህ ቀደም ተሰምተው የማይታወቁ በርካታ አዳዲስና አነጋጋሪ መረጃዎችን አካትተው ማቅረባቸውም ታውቋል፡፡
በስምንት ምዕራፎች ተከፋፍሎ፣ በ474 ገፆች የቀረበው መጽሐፉ፤ የእንግሊዝኛ ቋንቋን አንብበው መረዳት ለሚችሉ እንዲሁም የአማርኛ ቋንቋ ለሚቸግራቸው በውጪ አገራት ያደጉ ትውልደ ኢትዮጵውያን (ዲያስፖራዎች) የስደትን አስከፊነት እንዲረዱ በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን በእንግሊዝኛ ቋንቋ መዘጋጀቱ አንድም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በመማሪያ መጽሐፍነት እንዲያገለግል በሌላ በኩል ደግሞ የውጪው አለም ስለ ኢትዮጵያውያን የስደት ምክንያት፣ ሰቆቃና መከራ ትክክለኛውን ዕውነታ በሚገባ እንዲረዳ ለማስቻል በማሰብ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጃፈር መጻሕፍት መደብር አሳታሚነትና አከፋፋይነት ለንባብ የሚበቃው “Dreamers of the Horn - The Story Behind Ethiopian Migration”፣ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ በአዲስ አበባና በሁሉም የክልል ዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ መጽሐፍት መደብሮችና አዟሪዎች በ200 ብር ለገበያ ይቀርባል ተብሏል፡፡
ደራሲና ጋዜጠኛው ከዚህ ቀደም በአማርኛ ቋንቋ ጽፈው ካሳተሟቸው ተወዳጅ መጻሕፍት መካከል “አፍሪካና አምባገነን መሪዎችዋ”፣ “አረቦችና እሥራኤል”፣ “የእሥራኤል የስለላ መረብ”፣ “የሕሊና ባርነት”፣ “ስደት” እንዲሁም “ተስፋ-ክሕደትና ሰቆቃ” የተሰኙት ይገኙባቸዋል፡፡
ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ለረጅም አመታት በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ የቆዩት አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ነቢዩ ኢያሱ፤ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅነት፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የፕሮግራም ዋና ክፍል ኃላፊነት እንዲሁም “የአፍሪካ ቀንድ” የተሰኘው መጽሔት ዋና አዘጋጅነት ያገለገሉ ሲሆን፣ የደርግ መንግስትን ውድቀት ተከትሎ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ሳቢያ አገራቸውን ጥለው በተሰደዱባትና ከሁለት አሥርተ ዓመታት በላይ በስደት በኖሩባት አሜሪካ፣ በኢሳት ቴሌቪዥን ጥናታዊ ዝግጅትቶችን በመደበኛነት በማዘጋጀትና በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡


Read 2942 times