Saturday, 14 December 2019 13:08

ድንቅ ልብ ወለድ በግዕዝ!

Written by  ጽጌ መዝገቡ (መሪጌታ)
Rate this item
(2 votes)

   የመጽሐፉ ርእስ፡- ጦማረ መዋቲ
ደራሲ፡- ነጋሢ ግደይ
የገጽ ብዛት፡- 328-2
የታተመበት ዓመት፡-፳፻፲ ዓ.ም

ምክንያተ ጽሕፈት
ጥቅምት 29 ቀን 2012 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ሥነ መለኮት ኮሌጅ/ዩኒቨርስቲ አዳራሽ፣ “ጦማረ መዋቲ” የተሰኘ መጽሐፍ ተመርቆ ነበር፡፡ በእርግጥ መጽሐፉ ከታተመ ቀደም ያለ ቢኾንም “ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር!” ያሰኘዋል እንጂ መመረቁ ማለፊያ ነው፡፡ በዕለቱም የመጽሐፉን ዳሰሳ እንዲሰሩ የተጋበዙ ሰዎች፤ አንዳንዶቹ በጊዜ እጥረት፣ አንዳንዶቹም በቋንቋ እጥረት በደንብ እንዳላነበቡት ተናግረዋል፡፡ ደግነቱ የፊተኞቹ ከባድ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሲናገሩ፣ ተከታዮቹ ደግሞ ቋንቋውን ባለማወቃቸው ተቆጭተው፣ ቋንቋ ማወቅ ያለውን ጥቅም ለማሰረዳት ሞከረዋል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህኞቹ ይህን ትልቅ ኃላፊነት ወስደው መቅረባቸው “አፈ ተማሪ” ቢያሰኛቸውም፣ ያሳዩት ትሕትና ለቋንቋው ያላቸው ቀናዒነት ግን “ልበ ተማሪ” ያስብላቸዋል፡፡
ደራሲውም በመድረኩ ቀርቦ መጽሐፉን ለማዘጋጀት ያነሳሳውን ምክንያት፣ ምን ያህል ጊዜ እንደወሰደበትና ለማሳተም ያየውን ውጣ-ውረድ በቃለ ትሕትና አብራርቷል፡፡ በነገራችን ጎን (ከደራሲው የሰማኹት ነው፤ በነገራችን ላይ ለማለት) ደራሲው ጥሩ የአማርኛና የግእዝ ሥነ ጽሑፍ ክህሎት እንዳለው ተረድቻለኹ፤ሊቃውንቱም መስከረውለታል:: በዚህም ላይ ጥሩ ደብተራ (ቅኔ፣አቋቋምና ድጓ አዋቂ) እና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ እንደኾነ ተነግሮለታል፡፡ የቅኔ ችሎታውን በተመለከተ በድርሰቱ ውስጥ ያሉትን ቅኔዎች ማየት ይቻላል:: ከምንም በላይ ደግሞ ሀገሪቱ የተቸገረችበትን ትሕትናን ከሥነ ምግባር ጋር አጣምሮ የያዘ መኾኑ ተመስክሮለታል፡፡ “ሰይፍ ዘክልኤ አፉሁ::” (ሁለት ስለት ያለው ሰይፍ) ይሏል ይሄ ነው እንግዲህ! እኔም እንደነዚህ ያሉ መልካም ሰዎችን ያብዛልን እያልኹ፣ መጽሐፉን ከብዙው በጥቂቱ ፣ከረጅሙ ባጭሩ እንደሚከተለው ዐይቸዋለኹና እነሆ፡-
የመጽሐፉ ይዘት
መጽሐፉ መዘክር (ማስታወሻ)፣ ስባሔ (ምስጋና) እና በአማርኛ የተጻፈ መግቢያ ያለው ሲኾን፣ በ28 ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው፡፡ የተሰጠው ርእስም የመጨረሻ ምዕራፍ የኾነው ‹‹ጦማረ መዋቲ›› (የሟቹ ደብዳቤ) ሲኾን፤ የመጽሐፉን ሀሳብ ተሸክሞ የመጓዝ ጉልበት አለው፡፡ ከመጽሐፉ ርእስ ስር ያለው፣ እናት ልጇን አቅፋ ስትደባብስ የሚያሳየው ሥዕልም ገላጭና ልብ-ወለዱ፣ አንዳች ልብ የሚሰብር ታሪከ እንዳለው ጠቋሚ ነው፡፡ የተጻፈበት መጠነ ፊደልም (font) እጅግም ተልቆ ወረቀት የማይበላ፣ እጅግም ረቆ ከዐይን የማያጣላ ነው:: ከጀርባው በመጋቤ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ የተሰጠ አጭር ማብራሪያ (blurb) ያለው ሲኾን፣ የደራሲው ምሥለ ገጽም (photo) ከግራ ጠርዝ ላይ ጉብ ብሎ ይታያል፡፡ የተጻፈበት ቋንቋም በርእሱ እንደተገለጠው ልሳነ ግእዝ ነው፡፡ አንዳንዶች እንዳሉትም፣ የመጀመሪያው በግእዝ ቋንቋ የተጻፈ ልብ-ወለድ ያሰኘዋል፡፡ በእርግጥም ገድላቱን፣ ድርሳናቱንና ተአምራቱን የቅዱሳን፣ የመላእክና የጻድቃን እንዲሁም የፈጣሪና የእናቱ ሥራዎች ናቸው ብለን ካላመንን በስተቀር በግእዝ የተጻፈ ልብ-ወለድ በእኔ ንባብ አላጋጠመኝም፡፡ መጽሐፉ፤ ከረጅም ልብ-ወለድ ዘውግ (genre) የሚመደብ ነው፡፡
መቼት
ክዋኔውን በ1970ዎቹ እና 80ዎቹ መግቢያ ላይ አድርጎ፣ የማይጨው ጦርነትንም (1928) በምልሰት (flashback) ያሳያል፡፡ ለዚህም ማሳያ ይኾን ዘንድ፡- “ወርኃ ግንቦት ውእቱ ወርኁ፣ ዕለታኒ ዐሠርቱ ወተስዐቱ ዕለት ይእቲ፡፡= ወሩም ግንቦት፣ ዕለቱም 19 ቀን ነበር፡፡”ይልና (ገጽ 80) እዚህ ላይ ዓመተ ምሕረቱን ባይገልጽም፣ በመጨረሻ “ለሊሁ (አእምሮ) የአምር ከመ ቀሲስ ባሕረ አብ ሞተ በ፹ወ፫ቱ[፲፻፹ወ፫ቱ]ዓመተ ምሕረት፡፡”
“አእምሮቄስ ባሕረ አብ በ1983 ዓ.ም መሞቱን ያውቅ ስለነበር ደብዳቤው ከማን እንደተላከ ግራ ገባው፡፡” ይላል፡፡ (ገጽ327)
የጦርነቱን መልክ ሲገልጽም፡-
‹‹በምድረ ማይጨው ተከሥተ ዘኢተከሥተ እምቅድመዝ፡፡ ቀዲሙ ነበረ ይሰማዕ ድምጸ መድፍዕ እምርሑቅ እምአንጻረ መቐለ፡፡ አሜሃ አልጸቀ ዕለተ እብሬታ ለአድያመማይጨው ትትሐረስ በድምጸ ቅስት ወተቃትሎ፡፡….በአሜሃ ዕለት ለኵሉ ዘነፍስአልቦቱ ምጕያይ ወአልቦቱ ጸወን፡፡ አልቦበአት ኀበ ይሤውር ርእሶ ውሉደ አዳም እንተ ሀሎ ውስተ መርህብ፡፡ አልቦ ግበ ምድር ኀበ ይቀብር ርእሶ እስከ ሶበ የኃልፍ ዝ ኵሉ መዐተ ሰማይ፡፡ ወቦ ዘይረውጽ ኀበ ጽጐጕ:: ቦ ዘይጸወን ታሕተ ዕፀው ዘከመ ዕፀው ያድኅኑ እመንገኒቅ፡፡ አልቦ አብ ዘይመውት ለቤዛ ወልዱ፡፡ ወአልቦ እም ዘተሐቅፍ ነደ እሳት ውስተ ሕጽና በእንተ ውሉዳ፡፡ ዐርክ ኢይሰምዕ ገዐረ ፍቁሩ፡፡ ነገረ እስትንፋስ ኮነ ነገሩ፡፡ ኵሉ ዘነፍስ ይርዕድ ወይረውጽ ከመ ያውጽእ ነፍሶ እምዝንቱ ሞተ ግብት እምኃይለ ኲናት፡፡››
‹‹ከዚህ በፊት ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ነገር በማይጨው ምድር ተከሰተ:: ለድሮው ይሰማ የነበረው የመድፍ ድምጽ በሩቁ ከወደ መቀሌ አቅጣጫ ነበር፡፡ የዚያን ቀን ግን በጦርነት ለመታረስ ማይጨው አውራጃ ተረኛዋ ኾነች፡፡ የዚያን ዕለት በአካባቢው የነበሩ ሕያዋን ፍጥረታት ኹሉ መግቢያም መሸሻም አልነበራቸውም፡፡ በየመስኩ ተሰማርቶ የነበረው አዳሜ ኹሉ ራሱን የሚደብቅበት ዋሻ አልነበረውም፡፡ ያ ኹሉ የሰማይ መቅሰፍት እስኪያልፍ ድረስ ራሱን የሚቀብርብትም ጉድጓድ አላገኘም፡፡ በደመ ነፍስ  ወደ ጫካው የሚሮጥም ነበር፡፡ ዛፎች ከጥይት ያድኑ ይመስል ከዛፍ ስር የሚደበቅም ነበር፡፡ በዚያች ዕለት አባት ለልጁ መድኅን የሚኾንበት፣ እናትም ስለ ልጇብላ የሚነድ እሳት ለመሸከም የሚያስችል ጥንካሬ አልነበራቸውም፡፡ ወዳጅም የወዳጁን ጩኸት ለመስማት ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ ግቢ ነፍስ፣ውጪ ነፍስ ኾነ፡፡ ሰውም ኹሉ እንስሳውም ኹሉ ነፍሱን ለማዳን እግሬ አውጪኝ ብሎ በየፊናው ይፈረጥጥ ነበር፡፡” ይለናል፡፡ (ገጽ 81)
ታሪካዊውን የማይጨው ጦርነት ደግሞ እንዲህ ይገልፀዋል፡-
‹‹ማዕዜ ተወለድከ እኁየ፡፡ ይቤሎ አሐዱ አረጋዊ ለካልኡ እንዘ ይቀርብ ኀበ  እሳት ወየሐሲ ከርሦ በየማነ እዴሁ፡፡ ቁር ውእቱ መካኑ፡፡››
‹‹ጓዴ መቼ ተወለድኽ?›› ብሎ ጠየቀው ሽማግሌው፤ አጠገቡ የተቀመጠውን ሰውዬ ሆዱን በቀኝ እጁ እያሞቀ ቦታው ብርድ ስለነበር፡፡
‹‹በዘመነ ፍዳ፤ በክፉው ቀን፡፡›› አለ፡፡
‹‹ዘመንነ ዘመነ ፍዳ ውእቱ በምልዑ፡፡ አልቦ በኀቤነ ዘኢኮነ ዘመነ ፍዳ፡፡ ይትርፍሰ በአይ ዘመነ ፍዳ ተወለድከውእቱ ተስእሎትየ፡፡››
‹‹አየ ወዳጄ! ክፉ ቀን´ማ ሁሉም ዘመናችን ክፉ ቀን ነው፡፡ በሕይወታችን የመከራ ጊዜ ያልኾነ አለ? በየትኛው ክፉ ቀን ነው የተወለድከው ነው ጥያቄዬ፡፡››
‹‹በዘመነ ኢጣልያ ውእቱዘተወለድኩ፡፡ እምየ ነገረተኒ፡፡ ዘከመ ወለደተኒ እምውስተ በአት በምክንያተ ጕየታ ህየ ለአድኅኖ ርእሳ እምኲናት፡፡
‹‹እናቴ እንደነገረችኝ ከኾነ በጣሊያን ጊዜ ነው፡፡ ራሷንም እኔንም ከጦርነቱ ለማዳን ሸሽታ ከሄደችበት ዋሻ መወለዴንም ጨምራ ነግራኛለች፡፡›› አለ ሰውየው ትኩር ብሎ እየተመለከተው፡፡›› እያለ ታሪኩ ይቀጥላል:: ሰው በቤተ ክርስቲያን ተሰብስቦ ጠላውን እየጨለጠ ሲያወራ፡፡ (ገጽ 73-74)
የመጽሐፉ ጭብጥ
እውነቱን ለመናገር መጽሐፉ ብዙ ነገሮችን አምቆ የያዘ ነው፡፡ አንድ በትምህርቱም ኾነ በሥነ ምግባሩ ምስጉን የኾነ፣ ቄስ ባሕረ አብ የተባለ ቀና/ጀግና (Protagonist) እና ግያዝ የተባለ ቄስ አይሉት ጨዋ (መሐይም) ክፉ/መጥፎ (Antagonist) ገጸባሕርያትን ፈጥሮ ደግነትን፣ ጉብዝናን፣ ክብርን፣ ተወዳጅነትን፣ ወዘተ… በቄሱ፤ ልግመኝነትን፣ ስንፍናን፣ ተንኮልን፣ ክፋትን፣ ምቀኝነትን፣ ቅናትን፣ ወዘተ. በመሐይሙ በኩል ያሳየናል፡፡ በሌሎቹም ገጸባሕርያት ባህልን፣ ከንቱ ልማድን፣ ፍቅርን፣ ጥላቻን፣ ችግርን፣ ኃዘንን፣ ማግኘት - ማጣትን፣ መራብ - መጠማትን፣ መበደል - መጨቆንን፣ መታረዝ-መራቆትን፣ ተስፋን፣ ተስፋ መቁረጥን፣ ስጋትን፣ ፍርሃትን፣ በጥቅሉ በሰው ልጅ ላይ የሚታዩትንም የማይታዩትንም ስሜቶች ይገልጣል፡፡ እነዚህ ገጸባሕርያት በኑሮ ውጣ-ውረድ ጦርነት ገጥመው፤ ግማሹ አሸናፊ ሲኾን፤ ግማሹ ተሸናፊ ይኾናል፡፡
የመጽሐፉ ታሪክም በነዚህ ገጸባሕርያት ተሸካሚነት ከላይ የተገለፁትን ባሕርያተሰብ ይዞ ይገሰግሳል፡፡ ጉዞውንም በምድረ ኤፍራታና በዙሪዋ አድርጎ፣ የአካባቢውን ባህል፣ከንቱ ልማድ፣ የአብነት ትምህርት ቤት፣ ጦርነት፣ ውትድርና፣ ግብርና፣ ወዘተ.ጥርት ባለ ቋንቋ ይገልጻል፡፡
ተቀድቶ/ተኮርጆ ነው ባያሰኘውም ከባህሉ መቀራረብ የተነሳ የታላቁ ደራሲ ክቡር ዶክተር ሃዲስ ዓለማየሁ ድርሰት ከኾነው “ፍቅር እስከ መቃብር” ጋርም የሚያመሳስሉት ኩነቶች ይታያሉ፡፡ ብዙ ከንቱ ልማዳዊ ድርጊቶችም ይህ መጽሐፍ ከተወለደበት አገር ጋር በእጅጉ ይመሳሰላሉ፡፡ ለምሳሌም፡- ሰው ሲሞት ተራራ ላይ ወጥቶ መጮኽ፣ የዛር መንፈስ ከቤተሰብ ወይም ከዘመድ ካንዱ ወደ አንዱ ይተላለፋል ተብሎ መታሰቡ፣ ድግስ ደግሦ በማብላት በሰዎች ዘንድ ክብርን ለማግኘት የሚደረገው ሩጫና የመሳሰሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በዚሁም ከንቱ ልማድን ለመተው ምን ያህል ከባድ እንደኾነና የትኛው ተትቶ የቱ መቀጠል እንዳለበት ሰዉ መቸገሩን “…ባህልኬ ወልማድ ክቡድ ውእቱ እምኵሉ ነገር፡፡ ምስለ ውሳጣዊ አእምሮትነ ወምስለ አፍአዊ ቁመተ አካልነ ውእቱ ዘየዓቢ ባህለ አበዊነ፡፡ ሠናይ ውእቱ ዝንቱ ኵሉ:: ወባህቱ ቦ አሐዱ ተጽናስ እምዝንቱ ነገር፡፡ ኢነአምር አይ ነገረ ባህል ይደልዎ የሕልፍ እምነ አሀዱ ትውልድ ኀበ ካልኡ፡፡ ምእረ ነዐቅብ ዘኢይደልዎ ይትዓቀብ፡፡ ወምእረ ናማስን ዘኢይደልዎ ይማስን፡፡ በእንተዝ ኵልነ ንመስል ዘሀሎነ ውስተ ፍኖት በተወላውሎ፡፡››
‹‹…ምን ታደርገዋለኽ! ባህልና ከንቱ ልማድ ከኹሉም ነገር ይከፋል፡፡ የአባቶቻችን ባህልና ልማድ ከውስጣዊ አስተሳሰባችንም፣ ከውጫዊ አካላችንም ጋር ነው አብሮ የሚያድገው:: ነገሩ ጥሩ ነበር፤ግና በዚህ ነገር ወስጥ አንድ ችግር ያለ ይመስለኛል፡፡ ችግሩ ምንድን ነው ብትል… የትኛው ባህል ልማድ ከአንዱ ትውልድ ወደ አንዱ ትውልድ መተላለፍ እንዳለበት አለማወቃችን ነው፡፡ ተጠብቆ መያዝና መቆየት ያለበት አይያዝም፤ አይጠበቅምም፡፡ መጥፋት መረሳት የሌለበትን እናጠፋለን፤ እንረሳለንም:: በተቃራኒው ግን እናደርጋለን፡፡ ስለዚህም ኹላችንም በማመንታት ጎዳና ላይ የቆምን ይመስለኛል፡፡›› …እያለ ይገልጻል፤ በገፀ ባህርያቱ አንደበት፡፡ (ገጽ 128)
ከመጽሐፉ ፋይዳዎች ጥቂቶቹ
መጽሐፉ ብዙ ፋይዳዎች አሉት፡፡ ብዝኃ ባህል ባላት አገራችን፣ በተለያዩ አካባቢዎች ምን ዓይነት ባህል እንዳለ እንማርበታለን፡፡ በተጨማሪም መጽሐፉ በምሳሌዎች፣ በጥቅሶች፣ በአባባሎች የበለፀገ ስለኾነ የቋንቋን ውበት እስከ እነ ለዛው ዐይተን በማድነቅና እስከ እነ ወለላው በመንሰፍሰፍ ጠጥተን፣ የቋንቋ ጥማታችንን እናረካበታለን፡፡ በዚህም ላይ ታሪክን ዘወር ብለን እንድናይ መጽሐፉ የማይጨውን፣ የደርግን ጦርነቶች ያስቃኘናል፡፡
የቋንቋ ውበት
መጽሐፉ በቋንቋ ውበቱም በአገላለጹም ማለፊያ ነው፡፡
‹‹ልምልምት ይእቲ ምድረ ኤፍራታ፡፡ውስቴታ ይመስል መካነ ርስቱ ለተክለ ሕምር፡፡አልቦ ሕጸተ ዝናም በኀቤሃ፡፡ በእንተ ዘኮነት ጎሩ ለደመና ሰማይ ውእቱ ዘኢይትሌለያ ጠለ በረከት፡፡ ይብልዋ ሰብእ እለ ይነብሩ እምብሔረ መርቄ፡፡ ሶበኒ ይጐነዲ ዝናመ ክረምት ምህላ ውእቱ መርኆሁ ለአንቀጸ ሰማይ በከመ ባህለ [ልማደ] ህዝቡ፡፡ ሶበ ትትኬለል ወርኅ እምገጸመሬት [ምድር] ይትመሀለል ህዝቡ እስመ ይትአመን ከመ ዘሐመት ወርኅ፡፡ሶበ ይትከሠት ሕማመ ብድብድይትመሀለል ህዝቡ[ከማሁ]:: ደመናትኒ እለ ይነብሩ እምዲበ ርእሱ ለደብረ ጽበት ኢይጸንዕ ልቦሙ ለዘይትመሀለሉ በታሕቴሆሙ በከመ ኢታጸንዕ እም በአንብዓ ውሉዳ፡፡››
‹‹የኤፍራታ መሬት ለምለም ናት፡፡ ለአሽክት፣ ለስሚዛ/ሰንሰል፣ ለዶግና ለመሳሰሉት ተክሎች ለነሱ ርስተ-ጉልት የተሰጠች ትመስላለች፡፡ ‘እንደዚህ ሁልጊዜ ለምለም፣ አረንጓዴ የኾነችው እና እርጥበት/አንዛብ የማይለያት’ኮ ለሰማዩ ጎረቤት ስለኾነች ነው፡፡’ ይላሉ ከወደ ቆላው የሚመጡት ሰዎች፡፡ እንደ ህዝቡ ልማድ ዝናብ ሲዘገይ የሰማዩ በር መክፈጫ ቁልፍ ምህላ ነው፡፡ ጨረቃም ከመሬት ስትጠፋ ታማ ነው ተብሎ ስለሚታመን ምህላ ነው መድኃኒቷ:: ወረረሽኝ ሲከሠትም እንዲሁ፡፡ በጽበት ተራራ አናት ላይ የሚታዩት ደመናዎችም እናት በልጇ ለቅሶ እንደማትጨክን ኹሉ፣ እነሱም ምህላ በሚያደርጉት ላይ ጠለ በረከታቸውን ላለማርከፍከፍ ሆዳቸው አይጨክንም፡፡” እያለ የቋንቋን ውበት ያሳያል፡፡ በእርግጥ ውበቱ ለግእዝ ሰዎች ሊኾን ይችላል፡፡ (ገጽ 32)
እውነት ነው የቋንቋው ውበትና ምሥጢር ነፍስን ሰቅዞ ስለሚይዝ፣ አንዴ ማንበብ ከተጀመረ ተዉኝ ተዉኝ፣ ልቀቁኝ ልቀቁኝ አይልም፡፡ ከሥነ ጽሑፍ ዓላባውያን አንዱ የኾነውን ቃላት መረጣም (Diction) ያሟላል፡፡
መጽሐፉ ለእነማን?
ለታሪክ ተመራማሪዎችና ጸሐፊዎች፣ ለሥነልቡና ባለሙያዎች፣ ባህልን ቋንቋን  ለሚያጠኑ ሰዎች (Folklorists and philologists) እና በተለይም ደግሞ ለቅኔ መምህራንና ተማሪዎች ሙያቸውን ለማሳደግና ለማሻሻል እጅግ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለኹ፡፡
ምን አዲስ ነገር አመጣልን?
፨ በመጀመሪያ ልብ-ወለድን በዚህ መልኩ በግእዝ ቋንቋ መጻፉ፣ በሀገራችን የቅርብ ታሪክ፣ የበኩር ሥራ ወይም አዲስ ያደርገዋል፡፡ በእርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስም በሌሎችም ድርሳናት፣ ገድላትና ተአምራት ልብ-ወለድ መሰል ታሪኮች አሉ፡፡
፨ በሁለተኛ ደረጃ በተለምዶ ቋንቋው የቅዳሴ የውዳሴ፣ በጥቅሉ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውል ስለኾነ ቃላቱም ኾኑ ሀሳቦቹ የተመረጡ (Formal words) ናቸው፡፡ በዚህ መጽሐፍ ግን ከዕለት-ዕለት የምንጠቀምባቸው ቃላትም (Informal words)ኾኑ ሀሳቦች ስለተገለጹ ቋንቋውን አንድ ደረጃ ከፍ ያደርገዋል፤ ቃላቱም እንዳይረሱ ያደርጋል፡፡
የመጽሐፉ እንከኖች
በእርግጥ በእኔ በኩል እንጂ እንከኖች/ጉድለቶች የተባሉት፣ ደራሲው ለምን እንዲህ አላደረገም ተብሎ አይገደድም፤ አይወቀስምም:: እኔም እንደ አስተያየት ነው እንከን ብዬ የወሰድኋቸው እንጂ ደራሲ ጥቁሩን ነጭ፣ ነጩን ጥቁር፤ ብርሃኑን ጨለማ፣ ጨለማውን ብርሃን የማድረግ ጥበባዊ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡
። ሙሉው ታሪክ በግእዝ ስለተጻፈ የገጽ ቁጥሮቹም በዚያው ቁጥር/አኀዝ ቢኾኑ፤
። ቋንቋው ከተወሰኑ ምልክቶች በስተቀር ትእምርተ ጥቅስም ትእምርተ አንክሮም ስለማያውቅ፣ እነዚህን ትእምርቶች መጠቀም አሰፈላጊ አይደለም፡፡ ቋንቋው በራሱ የአነባበብ ስልት ራሱን ስለሚገልጽ ማለት ነው፡፡ ገጽ 120 ላይ የተገለጸው ቅኔ፣ ባለቤቱ ማን እንደ ኾነ የተገለጸው፣ በተለምዶ ባለቅኔው ስለሚታወቅ ቢጣራ፤
። በግእዙ አብረው የሚሄዱ የዘይቤ አገላለጾችን አለመጠቀም፤
ለምሳሌ፡- አማዑተ ከርሡ ውሕዘ ከመ ማይ እምብዝሐ ፍርሐት፡፡ ከዚህ ይልቅ አማዑተ ከርሡ መስወ ከመ ሥብሕ ዘቅድመ ገጸ እሳት እምብዝኃ ፍርሐቱ ቢል፤ (ገጽ 54) ።
 የአማርኛ አገላለጽን ተርጉሞ መግለጽ፤
። ለምሳሌ፡- “አንድ አሙሰ የቀራት” ለማለት አሐቲ ሐሙስ ይእቲ ዘተርፈታ…በዚህ ምትክ አሐቲ ይእቲ ቅርፀተ ዘመን ዘተርፈታ ቢኾን፤ (ገጽ 55)
። በእርግጥ ደራሲው ይሄን ይስተዋል ብዬ ሳይኾን፣ እስከ ዛሬ በግልጽ የሚታወቁትንና የዜማ ምልክት ጭምር የኾኑትን ሞክሼ ፊደላት ኾነ ብሎ ማዛባት፤ ለምሳሌ፡- ኃይሉ፣ ብዙኃን፣ ኃዘን፣ ጎሕ ወዘተ. የሚሉትን ሐይሉ፣ ብዙሐን፣ ሐዘን፣ ጎህ ወዘተ.
። በተለምዶ ክፉ/መጥፎ ገጸባሕርያት መጨረሻ ላይ የእጃቸውን ያገኛሉ፡፡ በዚህ መጸሐፍ ላይ ግን ግያዝ የተባለው ክፉና መሰሪ ገጸባሕርይ ምንም ሳይኾን መቅረቱ ቅር ያሰኛል፡፡
እንደ መውጫ
በጥቅሉ ይህ መጽሐፍ ካለው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ አንጻር ቢነበብና በምርቃቱ ቀን ከመድረኩ ላይ አንድ አባት እንደተናገሩትም፤ ተገዝቶ ከቤት ቢቀመጥ መልካም ነው፡፡ ሌላውና ዋነኛው ደግሞ ባለቤቱ ማን ነው? የሚለው ያጠያይቃል፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ቋንቋው የእኔ ነው ብላ የምታምንና እንዲያድግ እንዲበለጽግ የምትፈልግ ከኾነ፣ እንደነዚህ ያሉ ደራሲዎችን ማበረታት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በተጨማሪም ግእዝ ቋንቋ እንዲህ ነው፣ እንደዚያ ነው እያሉ በየመገናኛ ብዙኃኑ የሚለፍፉ ሰዎች ቋንቋውን መማር፤ እንደነዚህ ያሉ ደራሲዎችንም መድረኮችንም መደገፍ ይገባቸዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 2552 times

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.