Saturday, 14 December 2019 12:42

“ትግራይ በምንም ተአምር አይገነጠልም”

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 - መገንጠል ማነስን ነው የሚያመጣው፤ ትርፍ የለውም
             - በፓርቲ ደረጃ በውህደት፣ በአገር ደረጃ በአንድነት እናምናለን
             - የምንታገለው ለትግራይ ሙሉ ነጻነትና መብት ለማቀዳጀት ነው
             - ፓርቲያችን በሀገር አንድነት ላይ ጽኑ አቋም አለው


            ከተመሠረተ 25 ዓመታትን ያስቆጠረውና ከአገር ውጭ በስደት ላይ የነበረው “የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት)”፤ ሰሞኑን ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው፤ ስያሜውን ወደ “ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ትዴፓ)” የለወጠ ሲሆን በምርጫ ቦርድ እውቅና አግኝቶ፣በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ በዝግጅት ላይ መሆኑን ጠቁሟል፡፡ በትግራይ እንደ ልብ ተንቀሳቅሶ ደጋፊዎቹን ለመቀስቀስ የሚያስችል በቂ ነጻነት እንደሌለ ግን አልካድም፡፡ በዶ/ር አረጋዊ በርሄ የሚመራው አዲሱ ትዴፓ፤ የፖለቲካ ፕሮግራሙ ምን ይመስላል? ከአረና ጋር ጀምሮት የነበረው ውህደት ከሸፈ ወይስ ተሳካ? ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የመዋሃድ ዕቅድ አለው የሚባለው እውነት ነው ወይስ አሉባልታ? ህወሓት በሚመራው ትግራይ ያለው የፖለቲካ ድባብ ያሰራል ወይስ ያፍናል? ትዴፓ ስለ ትግራይ ፖለቲካና ስለ ህወሓት ምን ያስባል? ስለ መጪው ምርጫስ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የፓርቲውን ሊቀ መንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄን አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-


              የድርጅታችሁን ስም ወደ “ትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ” የቀየራችሁት ለምንድን ነው?
“የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትስስር”ን በ1987 ዓ.ም ነው በውጭ ሀገር እያለን፣ የመሠረትነው፡፡ በወቅቱ ትስስር ያልንበት ምክንያት ከሌሎች የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ሃይሎች ጋር ተቀናጅተን፣ ሀገር አቀፍ የሆነ ፓርቲ ለመመስረት የነበረንን አላማ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም በየወቅቱ በሚፈጠሩ ህብረቶች፣ ግንባሮች ትብብሮች ውስጥ  ስንሳተፍ ቆይተናል፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ስንገባ ህጋዊ የሆነ አካሄድ መከተል ነበረብን፡፡ ከምርጫ ቦርድም ህጋዊ እውቅና ማግኘት ስላለብን፣ ራሳችንን ወደ ፓርቲ ለወጥን፡፡ ይሄን ስንል ግን መጀመሪያ የተነሳንለትን ከሌሎች ጋር የመተባበርና እስከ ውህደትም የሚደርስ እቅዳችን ይቀየራል ማለት አይደለም፡፡ አሁን አዲስ በሰየምነው ፓርቲ፤ ከምርጫ ቦርድ እውቅና ለማግኘት አስፈላጊ ሰነዶችን በማሟላት አመልክተናል፡፡
አዲሱ የምርጫና የፓርቲዎች አዋጅ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልታችኋል?
እኛ በቀድሞውም በአሁኑም ነው የተዘጋጀነው፡፡ ክልላዊ ፓርቲ እንደመሆናችን፣ አዲሱ የሚለው 4ሺህ ፊርማ ማሰባሰብ ነው፤ እሱን ፈጽመናል፡፡ ስለዚህ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተናል፡፡ ምናልባት ከአንድ ሣምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ዕውቅና እናገኛለን፡፡
ፓርቲያችሁ በዋናነት አሳካዋለሁ የሚለው አላማ ምንድን ነው?
ፓርቲያችን ክልላዊ ይሁን እንጂ በመላ ኢትዮጵያ እሣቤ ነው የሚንቀሳቀሰው:: በኢትዮጵያ ጉዳይ ከሌሎች ጋር በጋራ ይሠራል:: ማንኛውም ሰው ፕሮግራማችንን አንብቦ ከተቀበለው አባል መሆን ይችላል፡፡ በዋናነት የኛ አላማ፤ የህዝባችን የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብቱ እንዲረጋገጥ መታገል ነው:: ይሄ ማለት ከመገንጠል በመለስ ማለት ነው:: እኛ መገንጠልን አንፈልግም፤ አንደግፍም:: አንቀጽ 39 አፍራሽ ነው ብለን ስለምናምን እንቃወመዋለን፡፡
መገንጠልን ለምን እንደምትቃወሙ ሊያብራሩልን ይችላሉ?
ምን ይጠቅማል? የተገነጠሉ ሀገራትን እኮ እያየን ነው፡፡ ኤርትራ ተገነጠለች፤ ምን ተጠቀመች? መገንጠል ማነስን ነው የሚያመጣው፤ ጥቅም የለውም፡፡ በፍልስፍናም ይሁን በፖለቲካ ተገማችነት ደረጃ፣ መገንጠል በፈለገው አግባብ ይሁን…ጥቅም አያስገኝም፡፡ የመገንጠል ስሜትን የሚቀሰቅሱ ጥያቄዎችን፣ ብሶቶችን… መፍታትና ምላሽ መስጠት ነው እንጂ ሀገር ከእነ ችግሩ ቢገነጠል፣ ያው ከእነ ችግሩ ነው የሚቀጥለው፡፡ በፓርቲ ደረጃ በውህደት እናምናለን፤ በሀገር ደረጃ ደግሞ በአንድነት እናምናለን፡፡ በሀገር አንድነት ላይ ጽኑ አቋም አለን፡፡
ከዚህ ቀደም ከአረና ጋር ልትዋሃዱ እንደነበር ገልፃችኋል፡፡ አሁን ደግሞ ከአዲሱ ገዢ ፓርቲ  “ብልጽግና” ጋር የመዋሃድ ፍላጐት እንዳላችሁ እየተነገረ ነው፡፡ እውነት ነው?
እኛ በአላማ ከሚስማሙን ጋር በሙሉ ለመተባበርና ለመዋሃድ ዝግጁ ነን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ስርአት አመጣለሁ ብሎ ቆርጦ የተነሳ ድርጅት ካለ፣ ለመዋሃድ ዝግጁ ነን፤ ወደ ኋላ አንልም፡፡ ከአረና ፓርቲ ጋር የጀመርነው ሂደት አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ትንሽ ወደ ኋላ የጐተተብን አረና ውስጥ ተፈጥሮ ከነበረው ችግር ጋር በተያያዘ ነው፡፡ በተለይ አፈንግጠው ወጥተው ሌላ ፓርቲ ወደ መመስረት የሄዱ አባላት ስለነበሩ ትንሽ ተጓቶብናል፡፡ ከአረና የወጡ ልጆች፣ አሁን የህወኃት ተለጣፊ ፓርቲ ነው የመሠረቱት፡፡ እነዚህ ልጆች በፈጠሩት ችግር ሂደታችን ተደናቅፎ ነበር፡፡ አሁን ግን እንደ አዲስ እየቀጠለ ነው፡፡ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ውህደት ሳንፈጽም አንቀርም፡፡ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ግን ገና ምንም የጀመርነው ነገር የለም፡፡ የቀረበልን ጥያቄም የለም፡፡ ድርጅቱንም ገና በማጥናት ላይ ነው ያለነው፡፡
ህወኃት ከ“ብልጽግና” ፓርቲ ጋር አልዋሃድም ማለቱን ተከትሎ፣ የትግራይ ህዝብ ውክልና እንዳያጣ በሚል ከእርስዎ ፓርቲ ጋር ንግግር መጀመሩን የሚጠቅሱ መረጃዎች ወጥተዋል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎችም ተሰራጭቷል::---
እርግጥ በማህበራዊ ሚዲያ ብዙ ነው የሚወራው፡፡ እኛ ለውህደቱ ውይይት ብንጀምር ደስታውንም አንችለውም፡፡ ግን ገና አልጀመርንም፡፡ ገና እያጠናን ነው ያለነው እንጂ መዋሃዱን አንፈልግም አላልንም፡፡ ብንዋሃድ ደስታውን አንችለውም፡፡ እኛ ከ“ብልጽግና” ፓርቲ ባለፈም ከሌሎች ጋር መዋሃድ እንፈልጋለን፡፡ ይሄ ፓርቲያችን ያስቀመጠው አቅጣጫ ነው፡፡
የእናንተ የፖለቲካ ፕሮግራም ማህበራዊ ዲሞክራሲን ማዕከል ያደረገ ነው፡፡ የ“ብልጽግና” ፓርቲም ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ነው የሚያራምደው፡፡ ከዚህ አንፃር…
በደንብ አላየነውም ፕሮግራሙን፡፡ ግን በፖለቲካ ፍልስፍናችን ብዙም የምንለያይ አይመስለኝም፡፡ በሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ በዲሞክራሲ፣ በሃሳብ ነፃነት ማስከበር፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ፤ ሁለታችንም ተመሳሳይ አቋም አለን፡፡ በጣም ብዙ መሠረታዊ የሆኑ የሚያቀራርቡ ነገሮች ስላሉን፣ ወደ መተባበር አሊያም ወደ ውህደት መሄድ የምንችል ይመስለኛል፡፡
በአንድ አመት ከ6 ወር ጊዜ ውስጥ በትግራይ ከአራት በላይ አዳዲስ ፓርቲዎች የተፈጠሩ ሲሆን በክልሉ ያሉትን የፓርቲዎች ቁጥር ወደ ሰባት አሳድገውታል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእነዚህ ፓርቲዎች መፈጠር ምን ይጠቁማል?
በአጭር ጊዜ ውስጥ የእነዚህ ፓርቲዎች መፈጠር ምክንያቱ፣ ለረጅም ዘመን የዘለቀው የአፈና ስርአት ነው፡፡ ሁሉም በየቤቱ ሲቆዝም ኖሮ፣ አሁን ትንሽ መንቀሳቀሻ ሜዳ ሲያገኝ ነው ብቅ ብቅ ያለው፡፡ ፓርቲዎቹም መምጣት የጀመሩት ለዚህ ነው፡፡ አሁን ለውጡ ከመጣ በኋላና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እየዳበረ ሲመጣ ነው፣ በአገር አቀፍ ደረጃም በርካታ ፓርቲዎች የተፈጠሩት፡፡ ይሄ የፓርቲዎች ብቅ ብቅ ማለት የሚጠላ አይደለም፡፡ በቀጣይ በሆነ አቅጣጫ መሰባሰባቸው አይቀርም፡፡ ዋናው ሃሳቦች ወደ የመድረኩ መውጣታቸው ነው፡፡ በትግራይ በርከት ያሉ ፓርቲዎች ለመፈጠራቸው ግን የህወኃትም እጅ አለበት፡፡ አንዳንዶቹ ራሱ ሆን ብሎ የፈለፈላቸው ናቸው፡፡ ከዚህ በፊትም እነ ኦህዴድንን… ብአዴንን ፈጥሯል:: አሁንም ያንን ስልት ተጠቅሞ ነው፣ እነዚህን ፓርቲዎች እየፈጠረ ያለው፡፡ አዳዲሶቹም የተለየ ሃሳብ ሲያንፀባርቁ አይታይም፡፡ ለየት ያለ አቋም ያለን እኛና አረና ነን፡፡ የህወኃትን ዱላም የምንቀምሰውም እኛ ነን፡፡ እነሱ ከህወኃት ጋር ተጣብቀው በምቾት ላይ ነው ያሉት፡፡ ይሄ ሁኔታ ግን ሃላፊ ነው፡፡ ህዝቡ ሲነቃና ሲነሳ ሁሉም ይለይለታል፡፡
ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ “የትግራይ ህዝብ በዚህ ሰአት በህልውናው ላይ የተጋረጠ አደጋ ስላለ እሱን በጋራ ሆነን መመከት አለብን” ሲሉ ይደመጣል፡፡ በእርግጥ የትግራይ ህዝብ በአሁኑ ወቅት የህልውና ስጋትና የተጋረጠበት አደጋ አለ?
አንድም የተጋረጠበት ስጋት የለም:: “ተከበሃል፣ ጦርነት እየተቀሰቀሰብህ ነው፣ ትጠፋለህ” እያሉ ነው ፕሮፓጋንዳ የሚነዙት:: ይሄ ግን ነጭ ውሸት ነው፡፡ አላማው ህዝቡን ከለላ አድርጐ ለመጠቀም ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ አላማ የለውም፤ ፕሮፓጋንዳው፡፡ ራሣቸውን በራሣቸው ነው ህወኃቶች ያሠሩት፡፡ ከዚያ እስር ቤት እንወጣለን ብለው ሲጠጉ ደግሞ ምሽጋቸውን የበለጠ ለማጠናከር “ጠላት በዚህ መጣብህ፣ በዚህ ሊመጣብህ ነው” እያሉ ህዝቡን ያወናብዱታል፡፡ ይሄ ግን ተጨባጭ አይደለም፡፡ ማን ነው በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት የከፈተው? በህወኃቶች ላይ ጦርነት ተከፍቶባቸው ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥም ተከፍቶባቸዋል፡፡ እኛም ከፍተንባቸዋል፡፡ ጠላታችን ናቸው የሚሏቸው ሁሉ ከፍተውባቸዋል፡፡ በህዝቡ ላይ ግን አንድም ጦርነተ የከፈተ የለም፤ ለመክፈት ያሰበም የለም:: ህዝብና ህዝብ ደግሞ ጦርነት አይፈልግም:: ህዝብ በባህሪው ሠላም፣ ፍትህ፣ ዲሞክራሲ ነው የሚፈልገው፡፡ እኛ እዚህ መሃል ሀገር ነው ያለነው፡፡ የትግራይ ሰዎች ነን፤ ግን ጦርነት የከፈተብን የለም፡፡ ስለዚህ ይሄ ነጭ ውሸት ማደናገሪያ ነው፡፡ ፓርቲዎቹም የማደናገር ስራ ነው የሚሠሩት፡፡
ለቀጣይ ምርጫ ዝግጅቱ ምን ይመስላል? በትግራይ በነፃነት መንቀሳቀስ ትችላላችሁ?  
እየተደበደብንም እየተገደልንም ቢሆን መንቀሳቀሳችን አይቀርም፡፡ ለትግል ነው የገባነው፤ስለዚህ እንታገላለን፡፡ ያ ህዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን ፖለቲካዊ መብቱ እስኪጠበቅ ድረስ እንታገላለን፡፡ ምርጫው የህዝቡ መሆን አለበት፡፡ ህዝቡን ነፃ ሊያደርጉት ይገባል፡፡ እኔን ብቻ ነው የምትመርጠው ብለው ካፈኑት፣ እነሱም ሆኑ ህዝቡ ሠላም አያገኝም:: እኛም ሠላም አናገኝም፡፡ ስለዚህ የመጣው ቢመጣ፣ እስከ መጨረሻው ድረስ እንታገላለን:: አሁንም ያለብን አፈና ጠንካራ ነው፡፡ እዚህ ለጉባኤ የመጡትም ሲመለሱ ብዙ ችግር እንደሚደርስባቸው እናውቃለን፤ ነገር ግን ትግላችንን በጽናት እንቀጥላለን፡፡ የትግራይ ህዝብ መብት እስኪከበር ድረስ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ ህዝቡ በራሱ ጉዳይ በነፃነት መራጭ እስኪሆን ድረስ ትግላችን ይቀጥላል፡፡
የምትታገሉት ለነፃነት ነው ማለት ይቻላል?
እየታገልን ያለነው ነፃነት ለማግኘት ነው:: የጠመንጃ ጦርነት ግን አንከፍትም፤ ሠላማዊ ትግል ነው የምናካሂደው፡፡ ነገር ግን በትግራይ የሚካሄደው ትግል የነፃነት ነው፡፡ የአቢአዲ፣ የሽራይ፣ የመበለት፣ የደብረሃሬማ፣ የመቐሌ… ህዝብ በየጊዜው እያመፀ ነው፤ ግን ተደብድቦ ይታፈናል፡፡ ስለዚህ ትግላችን የነፃነት ነው፤ ከአምባገነናዊ ስርአት ቀንበር ነፃ የመውጣት ትግል ነው የምናደርገው፡፡  በሀገር አቀፍ ደረጃ የነፃነት ትግሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ሄዷል:: ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ወደፊት ተራምዷል፡፡ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የሚያሸጋግረውን ሂደት ጀምሯል፡፡
ቀጣዩን ምርጫ ብታሸንፉ ዋና ዋና የምትፈጽሟቸው ተግባራት ምንድን ናቸው?
ዋናው ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማስከበር ነው፡፡ ሀሳብን በነፃነት መግለጽን ማረጋገጥ ነው:: ይሄ አሁን በህወኃት ታግዷል፡፡ ይሄን ነጻነት ካረጋገጥን በኋላ ማህበራዊ ዴሞክራሲን መሰረት ያደረገ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ ፕሮግራሞች አሉን፤ እነሱን እንተገብራለን:: በአጭሩ በኑሮ ለተጎዳው ሕዝብ ትኩረት ሰጥተን፣ ብልጽግናና እድገትን ለማምጣት እንሰራለን፡፡ የግል ባለሀብቶች ላይ እገዳ ሳናደርግ፣ እነሱ ሊሸፍኑ የማይችሉት ዘርፍ ላይ መንግስት ራሱ እየገባ፣ የሕዝብ ተጠቃሚነትን በሚያመጡ የኢኮኖሚ ሴክተሮች ላይ እንሰራለን፡። በማህበራዊ ጉዳዮች ደግሞ በትምህርት፣ በኑሮ፣ በድርቅ፣ በጤና… የተጎዳው ሕዝብ እንዲያገግም እናደርጋለን፡። የትግራይ ሕዝብ በእድገት ደረጃ ኋላ እንዲቀረ ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በቅርቡ በወጣ መረጃ እንኳ 29 ከመቶ የትግራይ ሕዝብ ከድህነት ወለል በታች ነው የሚኖረው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ 22 በመቶ ያህሉ ነው ከድህነት ወለል በታች ያለው::
ህወኃት በቅርቡ “የፌደራል ስርአቱን ማዳን” በሚል በመቀሌ ጉባኤ አካሂዷል፡፡ የፌደራል ስርአቱ የተጋረጠበት አደጋ ምንድን ነው? አሃዳዊነት ተመልሶ እየመጣ ነው የሚል ውንጀላም ይሰማል --
ምንም የተጋረጠበት አደጋ የለም፡፡ አሁን ካሉት የፖለቲካ ድርጅቶች አሃዳዊነትን የሚያራምድ ማን ነው? ይሄን አካሄድ ለይተው ይንገሩን። ከየት እንደፈጠሩት እኔ አይገባኝም:: እውነቱን እንናገር ከተባለ ደግሞ አሃዳዊ የነበሩት እነሱ ናቸው፡፡ አንድ ፓርቲ፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት እያሉ፣ ማዕከላዊነትን ያጠብቁ የነበሩት እነሱ ናቸው:: ከላይ የሚንቆረቆረውን ብቻ እየጫኑ የኖሩ አሃዳውያን እነሱ ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ አሃዳዊ ሆኖም እኮ ዴሞክራት መሆን ይቻላል:: እንደ ትልቅ የፖለቲካ ነውር ለምን ይታያል? ደግነቱ አሃዳዊነትን ላመጣ ነው የምታገለው ብሎ በፕሮግራሙ ቀርፆ የሚንቀሳቀስ የፖለቲካ ድርጅት የለም፡፡ ስለዚህ “የፌደራል ስርአቱን እናድን፤ አሃዳዊነት ሊመጣ ነው” የሚለው ነገር ሰውን ለማወናበድና ለማሸማቀቅ የመጣ ፈጠራ ነው፡፡ ይሄ ፈጠራቸው ቀስ በቀስ እየተጋለጠ ይሄዳል፡፡
ትግራይን የመገንጠል፣ “ዲፋክቶ ስቴት” የመመስረት ሃሳብ በትግራይ ልሂቃን ዘንድ ይንሸራሸራል፡፡ የሚሳካ ሃሳብ ይመስልዎታል?
ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ትግራይ በምንም ተአምር አይገነጠልም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ቅንጣት ታህል በመገንጠል አያምንም፡፡ የኢትዮጵያ እምብርት እኮ የትግራይ ሕዝብ ነው:: የኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ሁሉ ነገር የሚጀምረው ከትግራይ ነው፡፡ ታዲያ ከዚህ ወዴት ነው የሚገነጠለው? ስለዚህ ትግራይ በምንም ተአምር አይገነጠልም፤ የሚታሰብም አይደለም፡፡ ሕወኃት ይሄን ጠንቅቆ ሊረዳ ይገባዋል፡፡

Read 12898 times