Saturday, 14 December 2019 12:17

የአራተኛ ክፍል ፓስቴ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)


             “እናንተ እኮ ኮትና ሱሪዋን ለማግኘት ተክለ ሰውነቱ ወደ እናንተ የሚቀራረብ የአክስት ልጅ ተፈልጎ ተገኝቶ ነው! እሱም ቢሆን እሁድ ማለዳ ሰው ሳያየው ተነስቶ ከሹሮ ሜዳ የሸመታት ነች፡፡ ደግሞ እኮ…ይህንን ያኔ ራሳችሁ ነግራችሁት፣ ትን እስኪለው ነበር የሳቀው፡፡ እናላችሁ…ምን ለማለት ነው፣ ብዙዎች ‘ቦተሊከኞቻችን’ ያለፈ ታሪክ ሲያነሱ፣ ከአራተኛ ክፍል ፓስቲ አልፈው መሄድ ሲያቅታቸው እያየን ነው… ለማለት ያህል ነው፡፡”
               
          እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እናላችሁ…እሷዬዋ ምንም ባልተቀላቀለበት እውነተኛ ስሜት፣ ወይም አፍናው የቆየችው የሆነ ‘ነገርዬ’ አምልጧት…
“አንተ፣ ዛሬ ልዑል መስለህ የለም እንዴ! ምን ተገኝቶ ነው እንዲህ ጉንጭ በጉንጭ የሆንከው?!”
ምን! ‘ልዑል መስለህ የለም ወይ! ይሄን ሰሞን እንደውም ሰውዬሽ በዓይኑ እንትን እያየኝ ነው፣ ጭራሽ ልዑል ትመስላለህ!’ 
“ልትዳር የምትሄድ ትመስላለህ እኮ!”
‘ልትዳር’ን ምን አመጣው! አሁን ይሄን የሰማ አባወራ፣ ስለ አየር በአየር አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳይል ጎግል ገብቶ ቢፈትሽ ይፈረድበታል! እናላችሁ ነገሩ…“ለፍቅር ብዬ ኩሼ ብንል፣ ለጠብ ብላ የአደባባይ ማስረጃ ይዛ ትዞራለች” አይነት ነው፡፡
የሆነ ሰብሰብ ብላችሁ እየተጫወታችሁ ነው፡፡ (በእርግጥ ሰብሰብ ማለቱ ያለ ቢሆንም  ‘መጫወት’ የምትለዋ ነገር ግን…አለ አይደል…እንደ ፈቺው ነው፡፡) 
እናላችሁ…ከመሀላችሁ አንደኛው ወደ እናንተ እያየ “አጅሬ…” ብሎ አመልካች ጣቱን ይወዘውዛል፡፡
ያው መቼም በ“አጅሬ…” የጀመረው ለብሽሽቅ ነው ብላችሁ ፈገግ ማለት ትጀምራላችሁ፡፡ ምን ያደርጋል … ፈገግታው ከእናንተ በኩል ብቻ ነው:: ሰውዬው ፊቱን ከስክሶ ሲኖትራክ የወደቀበት የይድረስ፣ ይድረስ ኮብልስቶን አስመስሎታል፡፡ እናማ… ከልባችሁ ባይሆንም በሆዳችሁ… “አይ ሰውየዋ ደከመች ማለት ነው፡፡ ገና በሶስተኛ ድራፍቷ.. ‘እልም አለ ባቡሩ’ ማለት ጀመረች፣” ትሉና ዝም ትሉታላችሁ፡፡ እሱዬው ይቀጥላል…
“አንድ ጊዜ ያደረግኸኝን ነገር የረሳሁ መሰለህ!” ይላል፡፡
ምን! የምን “ያደረግኸኝን” ምናምን ነው! አሀ…ልክ ነዋ! በልጅነታችሁ አብራችሁ ያደጋችሁ ቢሆንም እንኳን በስተኋላ ኑሮ አራርቋችሁ ከስንት አንዴ ብትገናኙ ነው እኮ!…እንኳን “ያደረግኸኝን…” ምናምን ለመባባል ማለት ነው:: ግን ደግሞ የሆነ ነገር ማለት አለባችሁ፡፡
“አንተን ደግሞ ምን አደረግሁህ!”
ሌሎቹ ነገርዬው ያልገባቸው ‘ስታንድ አፕ ኮሜዲ’ ነገር ያደርጉትና ያሟሙቃሉ፡፡ ልክ ነዋ… የድራፍት ዙሪያ “ጉድ ሰራኸኝ፣” ብሎ ነገር… አለ አይደል… “እንትናዬን ነጥቀኸኝ፣“ “ያቺን ኦዲተሯን አስኮብልለህብኝ፣” ምናምን ከመባባል አያልፍም ብለው ነዋ፡፡ (በእርግጥ ዘንድሮ “አስኮብልለህብኝ” የሚለው ተቀጥያ እመጫት ‘ትርጉም’ ሊያስከትል ይችላል፡፡) እናላችሁ… እሱዬው ይቀጥላል… 
“ድሮ አራተኛ ክፍል እያለን የሠራኸኝን የረሳሁ መሰለህ!” ሲል ግን ማለቂያ እንዳልነበረው የዛራ ለቅሶ አይነት ስሜት በአንድ ጊዜ ሁሉም ላይ ‘ጉብ’ ይላል፡፡ ስታንድ አፕ ኮሜዲ የለ፣ ‘ሲትዳውን’ ምናምን የለ (ቂ…ቂ…ቂ…) በአንድ ጊዜ ‘ሙዳቸው’ ገደል ይገባል፡፡
እናንተ ግን አሁንም ፈገግ የማለት ሙከራ ላይ ናችሁ…
“ደግሞ አራተኛ ክፍል ምን አደረግሁህ!” ትሉታላችሁ፡፡ ስታስኮርጁት የነበራችሁት እናንተ፣ ‘ሆምወርክ’ ስትሠሩለት የነበራችሁት እናንተ! ከትምህርት ቤት ሲፎርፍ “እናቱ ታመው…” “አክስቱ ሞተው…” እያላችሁ ‘ስታጨናብሩለት’ የነበራችሁት እናንተ! መቼም የፈለገው ቢመጣ እነኚህን ነገሮች ትንፍሽ አይልም፡፡
“እየተደበቀ ፓስቴ ይበላል ብለህ ተናግረህ … ለአባቴ ቀኑን ሙሉ ያስገረፍከኝን የፈለገ ቢሆን የምረሳ መሰለህ!”
ኸረ በህግ አምላክ! ኸረ የ‘አይ.ኪዋችን’ ነገር የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ አጄንዳ እንዳይሆን! አሀ…ልክ ነዋ! ሀገሪቷ ህግ ማስከበር ያቃታት ትመስላለች ቢባል ታዲያ እንዲህ ነው እንዴ! ጉድ እኮ ነው…በሀምሳ አምስተኛ ዓመቱ የአራተኛ ከፍልን ፓስቴ፣  የጦርነቱ የመጀመሪያ ጥይት የሚያደርግ ሰው፤ ምድራዊ ወንጀለኛ መቅጫ ምናምን ሊዳኘው ስለማይችል፣ የውሀ ምልክት ታይቶባታል ወደተባለችው ፕላኔት ይላክልንማ!
ወይ የአራተኛ ክፍል ፓስቴ!
ደግሞላችሁ… በሌላ ጊዜ ሌላው ሰው እንዲሁ አዝናችሁ ባላችሁበት፣ ወይም እየተዛዘናችሁ መስሏችሁ በነበረበት ሰዓት ‘የክስ ፋይሉን’ ይከፍታል፡፡
“ስማ…ያን ጊዜ ለሥራ ኢንተርቪው የተጠራን ጊዜ ትዝ ይልሀል?”
አሁን ገና ጨዋታ መጣ፡፡ አሁን ገና ድራፍቱን ከመደበኛ ብርጭቆ ወደ ጃምቦ የሚያሸጋግር ጨዋታ መጣ፡፡ ከዳር እዳር ፈግ ትላላችሁ፡፡
“በደንብ እንጂ! እሱን ጊዜ እንዴት እረሳለሁ!” ሁለታችሁም እንዴት ፈርታችሁ እንደነበር፣ አንደኛችሁ የአባታችሁ ስም ጠፍቷችሁ ስትንተባተቡ እንደነበር፣ ምን አለፋችሁ… ‘ትዝታ በፖስታ’ ነገር ብቅ ይላል፡፡ በተለይ የሆነች ለመሀረብነት የተዘጋጀች የምትመስል ጨርቅ … ቀሚስ ብላ የለበሰችውና ካላጣችው መቀመጫ ፊት ለፊታችሁ ላይ ጋለል ብላ የነበረችው-- የጠቅላላ አገልግሎት ሃላፊዋ እንዴት ትረሳለች:: ባሻ ወልዴ ችሎት ይመስክራ! ቂ…ቂ…ቂ… እንዴ… የዛን ጊዜ የዓይናችሁ ‘ስፒድ ሊሚት’ ቢመዘገብ ኖሮ፣ “ከድምጽ ሦስት እጅ የፈጠነ ባቡር…” ምናምን እያሉ ባልፎከሩ ነበር፡፡)
ከዛላችሁ… አጅሬው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ስማ…ግን ያን ጊዜ ታክሲ ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ እስኪደነግጥ … እንደዛ ከት ብለህ የሳቅህብኝ ትዝ ይልሀል?”
ኸረ በህግ አምላክ! ኸረ ፍሮይድ “ገና ተመራምሬ ያልጨረስኳቸው አእምሮዎች፣ ምስራቅ አፍሪካ አሉ ብሎ ፈንቅሎ እንዳይወጣ! ግን ደግሞ መናገር አለባችሁ…
“አልገባኝም፣ ምንድነው የምታወራው?”
“ላለማመን ብለህ እንጂ አሁን ይሄ ጠፍቶህ ነው! አንተ ሙሉ ልብስ ለብሰህ በእኔ ጂንስ ጃኬት የሳቅኸውን ረስተህ ነው!”
ጉድ ባይ ‘የኡላንባቶር’ ቅጠል፡፡ (የሰውና የቦታ ስሞች ላይ እንደ ጊዜው ለመሆን ነው፡፡)
“እና፣ የዛሬ አስራ ሰባት ዓመት የሆነውን ምን ልሁን ብለህ ነው የምታነሳው! ያኔ ተቃለድን፣ ተሳሳቅን…አለቀ፡፡ የተረሳ ነገር…”
“አንተ እርሳው እንጂ እኔ አልረሳሁትም፡፡”
እናንተ እኮ ኮትና ሱሪዋን ለማግኘት ተክለ ሰውነቱ ወደ እናንተ የሚቀራረብ የአክስት ልጅ ተፈልጎ ተገኝቶ ነው! እሱም ቢሆን እሁድ ማለዳ ሰው ሳያየው ተነስቶ ከሹሮ ሜዳ የሸመታት ነች:: ደግሞ እኮ…ይህንን ያኔ ራሳችሁ ነግራችሁት፣ ትን እስኪለው ነበር የሳቀው፡፡ እናላችሁ…ምን ለማለት ነው፣ ብዙዎች ‘ቦተሊከኞቻችን’ ያለፈ ታሪክ ሲያነሱ፣ ከአራተኛ ክፍል ፓስቲ አልፈው መሄድ ሲያቅታቸው እያየን ነው… ለማለት ያህል ነው፡፡
ወይ የአራተኛ ክፍል ፓስቴ!
ታዲያላችሁ… ማህበራዊ ዋስትናውን (‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ለመሆን ያህል!) ለማስከበር የሰነድ መአት ተሸክሞ በየፎቶኮፒው ቤት በሚዞርበት ሰዓት…አለ አይደል… “ዘጠነኛ ክፍል ያቺን የቄራዋን ልጅ እኔ እፈልጋታለሁ እያልኩህ፣ በጎን ገብተህ የወሰድካትን የረሳሁ መሰለህ!” የሚል ሰው፣ በእኛ ወጪ በስደተኝነት ሊቀበለው ፈቃደኛ ወደሆነ አካባቢ ይሂድልንማ! ወይስ… በዚህ ሰዓት የቄራዋን የሚያነሳው  “እስዋ ብትኖር ኖሮ እንዲህ ሞተሩ ሁሉ ፉዞ ሆኖ ‘ሞደፊክ’ መለዋወጫ እንኳን የጠፋለት፣ ለአንደኛው የዓለም ጦርነት ትሬንታኳትሮ አልሆነም ነበር” ለማለት ነው! (ቂ…ቂ…ቂ…)
እናላችሁ… “እኔም አልጣላ፣ ሲጣሉም አላይ…” እንዳለው ሰውዬ፣ የዘንድሮ ነገር…አለ አይደል…በ“እኔም አልጣላ…” የሚሆን አልሆነም፡፡ የአራተኛ ክፍል ፓስቲ ባይኖርም፣ ‘ጠላትነት’ በእናንተ እንቅስቃሴ የሚመጣባችሁ ሳይሆን በራችሁን አንኳኩቶ ከች ሊል ይችላል፡፡
ይኸው ነው፡፡
ወይ የአራተኛ ክፍል ፓስቴ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2356 times