Saturday, 30 November 2019 14:02

የኢሕአዴግ ውህደት 3 ቀዳሚ ምክንያቶች!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(7 votes)

 ውህደት ለምን? ኢህአዴግ ያዘጋጀው አዲስ መተዳደሪያ ደንብ፣ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶችን ይዘረዝራል፡፡
በአገራችን ያስመዘገብናቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን” አስጠብቆ ለማስፋት፡፡
ስህተቶችን ለማረም፡፡
የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፡፡
በእነዚህ ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች ውስጥ፣ “ለውጦች”፣ “ስህተቶች”፣ “የመጪው ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት” የሚሉ ሦስት ዋና ዋና ፍሬ ሃሳቦች ናቸው ቀዳሚ ትኩረት የተሰጣቸው፡፡ በዚያው የትኩረት መጠንም፣ በጥንቃቄ ተፈትሸው በግልጽ መብራራት ይኖርባቸዋል፡፡
ለምሳሌ፣ “የኢህአዴግ ስህተቶችን ለማረም” የሚል ጤናማ ሃሳብና፣ “ከሺ ዓመታት በፊት የተፈፀሙ ስህተቶችን ለማረም” የሚል የተሳከሩ ሃሳብ፣ ምን ያህል እንደሚራራቁ አስቡት:: በግልጽ ማብራራትና አጥርቶ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ለምን ቢባል፣ አንደኛ ነገር፣ ቀሽም የአስተሳሰብ ብዥታና ዝርክርክርነት በተስፋፋበት በዛሬው ዘመን፣ በተቻለ መጠን፣ ከእያንዳንዱ ቃል ጀምሮ፣ የእያንዳንዱን ፍሬ ሃሳብ ይዘት አጥርቶ ለመጨበጥ፣ ሃሳቦቹንም አገናዝቦ በድምር ለመረዳት ጥረት ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው፡፡
ሁለተኛ ነገር፤ ጉዳዮቹ የሻይ ሰዓትና የድራፍት ወሬዎች፣ እለታዊ መረጃዎች፣ ወይም የገጠመኝ ማስታወሻዎች አይደሉም፡፡
ለ30 ዓመታት በስልጣን ላይ የዘለቀ የአገሪቱ አውራ ፓርቲ፤ እንደ አዲስ ለመደራጀት ያዘጋጀው፣ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ የሰፈሩ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ለዚያውም፤ የቅድሚያ ቅድሚያ የተሰጣቸው ዋና ዋና ሃሳቦች ስለሆኑ፤ በዚያው ልክ ፓርቲው ግልጥልጥ ብርትርት አድርጐ ሃሳቦቹን ማቅረብ፣ ዜጐችም አጥርተው ጠንቅቀው መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ያተኮረባቸው ሃሳቦች፤ የአገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሕግና ስርዓት አቅጣጫን የሚያመላክቱ ናቸውና፡፡
በዘመናችን ከገነነው ዳፍንታም የአስተሳሰብ ብዥታና ግብስብስ የአስተሳሰብ ዝርክርክነት እንጀምር፡፡ ሁለት መልክ አለው፡፡
መያዣ መጨበጫ የሌላቸው እልፍ ቁርጥራጭ ሃሳቦችን እያግበሰበሱ ግራ መጋባትና መደናበር፣ ነጋ ጠባ እልፍ ሃሳቦችን  እየጣሉ እያነሱ መቅኖ ማጣትና መባከን፣ አንዱ የአስተሳሰብ በሽታ ነው - ግብስብስ የዝርክርክርነት መልክ ልንለው ነው፡፡ “የተበጣጠሰ ሃሳብ” ይሉታል - ጠ/ሚ ዐብይ፡፡
አዲስ የተዘጋጀው የመተዳደሪያ ደንብ፣ እንዲህ አይነት ዝርክርክነት ውስጥ ላለመግባት ጥንቃቄ የተደረገበት ይመስላል፡፡
የፓርቲውን መሰረታዊ ሃሳቦች ለመግለጽ፣ 1፣2፣ 3፣ …ብሎ ዓላማዎችን፣ መርሆችን እና እሴቶችን ይዘረዝራል፡፡ ሃሳቦቹን እጥር ምጥን አድርጐ ለማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ ሃሳቦቹን እርስበርስ ለማገናዘብም ሞክሯል፡፡
ይሄ፣ ከተበጣጠሰ የሃሳብ ዝርክርክነት ለማምለጥ ይረዳል፡፡
ሌላኛው የአስተሳሰብ በሽታ ደግሞ፤ “ሾላ በድፍን” የሚባለው አይነት ነው (Floating abstractions እንዲሉ)፡፡ የዳፍንት ብዥታ፣ እንደ ‹‹ኖርማል›› ሲቆጠር ማለት ነው፡፡
እንደሌላው ዓለም ሁሉ፤ የዘመናችን የአስተሳሰብ ብዥታና ዝርክርክነት በኢትዮጵያም እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ የሃሳብን፣ የግብን እና፣ የድርጊትን ምንነት የማይገልፁ፣ ተገቢነታቸውን የማይዳኙ፣ ፋይዳቸውን የማይመዝኑ መፈክሮች፣ ቀስ በቀስ የቱን ያህል እንደበረከቱና እንደገነኑ ተመልከቱ፡፡
“የህዝብ ጥያቄ” የሚል ሌጣ መፈክር፣ ቀዳሚ ምሳሌ ነው፡፡ የጠያቂዎቹ ማንነት አለመታወቁ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ የጥያቄው ምንነትና የሃሳቡ ይዘትም አይገለጽም፡፡ አስር ሰዎች የሚያራግቡት የውሸትና የአሉባልታ ወሬ፣ የተንኮልና የጥላቻ ቅስቀሳ ሊሆን ይችላል:: ብሽሽቅና ጭፍን ውንጀላን፣ ዝርፊያንና ውድመትን፣ ማፈናቀልንና ግድያን ለማቀጣጠል የሚራገብ ሃሳብ ቢሆንም እንኳ፣ አጥርቶ ለማየትም ሆነ ለማሳየት ከመሞከር ይልቅ፣ በብዥታና በደፈናው “የሕዝብ ጥያቄ” ተብሎ ይሰየማል፡፡
ወይም ደግሞ፣ እውነትን፣ የሰው ንብረትንና ሕይወትን ለማክበር የሚጠቅም ጥሩ ሃሳብም ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄኛውም፤ ተጣርቶ ሳይታይና ሳይመዘን፣ በብዥታና በደፈናው፣ “የሕዝብ ጥያቄ” ተብሎ ይጠራል፡፡
የክፋትና የቅንነት፣ የጥፋትና የበረከት ሃሳቦች፣ እውነትና ሐሰት እኩል እንዲስተናገዱና እንዲራገቡ የሚያደርግ እንዲህ አይነት ዳፍንት አስተሳሰብ መያዝ፤ ክፋትን፣ ጥፋትንና ሃሰትን እንደመጋበዝ ይቆጠራል፡፡
ከ“ሕዝብ ጥያቄ” ጐን ለጐን፣ “ብዝሃነት” የሚል መፈክርም፣ ሌላ የብዥታ አስተሳሰብ ኮከብ ምሳሌ ነው፡፡ “የሃሳብ ብዝሃነት” በራሱ እንደ መልካም ውጤትና እንደ ግብ ይዘመርለታል፡፡
“ብዙ የእውቀት መስኮች”፣ “ብዙ ትክክለኛ ሃሳቦች” ማለት አይደለም - የሃሳብ ብዝሃነት ማለት፡፡ የተስተካከለም ሆነ የተሳሳተ ሃሳብ፣ ያለ ልዩነት በደፈናው እንድንቀበል፣ ሳናገናዝብ፣ ሳንዳኝና ሳንመዝን፣ ጥሩና መጥፎ ሃሳቦችን በእኩልነት እንድናስተናግድ የሚጋብዝ መፈክር ነው - “የሃሳብ ብዝሃነት”፡፡
“የባሕል ብዝሃነት” የሚለው መፈክርም፣ - መልካም የስራ ባህልንና መጥፎ የሚስኪንነት ባህልን፣ እኩል እንድናስተናግድና እንድናከብር የሚያስገድድ የብዥታ አስተሳሰብ ዳፍንት መፈክር ነው፡፡
“ህገመንግስት ይለወጥ፤ አይለወጥ” የሚለው ድፍን መፈክርም፣ ከእነዚሁ ተርታ የሚመደብ ነው፡፡ ምንና ምን ለምን እንደሚለወጥ ወይም እንደማይለወጥ፣ በምን አይነት ህጋዊና ስርዓታዊ መንገድ ሊለወጥ እና ላይለወጥ እንደሚችል፤ በዝርዝር ሃሳቦችን አጥርቶና ተንትኖ፣ በድምርም ሃሳቦቹን አገናዝቦና በቅጡ አቀናብሮ ለማቅረብ ወይም ለመረዳት መሞከር፣ እየተረሳ መጥቷል:: በብዥታና በደፈናው፤ “ይለወጥ፣ አይለወጥ” እያሉ መደናበር፣ በዘመናችን የገነነ የአስተሳሰብ በሽታ ነው፡፡
እንዲያውም፤ ከዚህም አልፎ፣ “ለውጥ” የሚለውን ቃል በቁንጽል በማራገብ፣ አንዳች መልዕክት ማስተላለፍ የሚቻል እስኪመስለን ድረስ፣ የብዙዎች አስተሳሰብ እየተደፈነ ነው:: ምን አይነት ለውጥ? በምን ያህል መጠንና ፍጥነት? በምን መንገድ? ብሎ ማሰብ፣ ማብራራት፣ መጠየቅና ማገናዘብ ከቀረ፤ በእርግጥም ተደፍኖብናል፡፡
“ለውጥ” የሚለው ቃል፣ በቂ የመግባቢያ ቃል እየመሰለ መጥቷላ፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሁለት ቅጽል መጨመር እንዴት አቀበት ይሆንብናል? ጠቃሚና ጐጂ ለውጥ፣ የመሻሻልና የመውረድ ለውጥ፣ የከፍታና የቁልቁለት ለውጥ፣ ጥሩ እና መጥፎ ለውጥ፣ መልካም እና ክፉ ለውጥ…እንዲህ ትንሽ ፈታ ቢል ይሻላል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ፣ የለውጡን አይነት አጥርቶ ማወቅ፣ ከዚያም መልካምና ክፉ ብሎ መዳኘት፣ መጠነኛና ከፍተኛ ብሎ መመዘን እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት አገላለጽ ይሆናል፡፡ በዳፍንት አስተሳሰብ ሳቢያ የሚፈጠረውን ብዥታ ለማስወገድ ይረዳል፡፡
“አላማችን የኢኮኖሚ ለውጥን መፍጠር ነው” ከማለት ይልቅ፣ ለውጡ የእድገት ይሁን፣… ወይም ከአበበ ንብረት ወርሶ ለከበደ የመስጠት የሶሻሊዝም ለውጥ ይሁን፣…የለውጡን ምንነት ለይቶ መናገር ያስፈልጋል፡፡
የእድገት ለውጥ ከሆነም፣ አይነቱ፣ መጠኑና ቆይታውንም ለማሳየት መሞከር ይገባል፡፡
ለምሳሌ፣ “ቀጣይነት ያለው ብልጽግናን የሚያረጋግጥ” የሚለውን አባባል፣ ከአዲሱ የኢህአዴግ መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ መጥቀስ ይቻላል - የወደፊት አላማውን ለማመላከት የሰነዱ መግቢያ ላይ የሰፈረ አባባል ነው፡፡ ዳፍንት ወይም ዝርክርክ አባባል አይደለም፡፡ እዚያው መግቢያ ውስጥ በቀዳሚነት ከሰፈረው ሌላ አባባል ጋር አነፃጽሩት፡፡
“በአገራችን ያስመዘገብናቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦችን አስጠብቆ ለማስፋት…”
የለውጥ መስኮች በፈርጅ መዘርዘራቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን በደፈናው፣ “ለውጦችን” ከማለት ይልቅ፣ “መልካም ለውጦችን” ወይም “እድገቶችን” በማለት የለውጦቹን ዓይነት ለይቶ ለማሳየት መሞከር ይቻል ነበር (እንደዚያ ለማለት ታስቦ እንደተፃፈ አያጠራጥርምና)፡፡
“ስህተቶችን ማረም” የሚለው አባባልም፤ እንዲሁ ለብዥታ እንዳይዳረግ፣ ትንሽ ማፍኪያ ያሰፈልገዋል፡፡ በኢህአዴግ ሊቀመንበር በጠ/ሚ ዐቢይ ንግግሮች እንደተገለፀው፣ እንዲሁም ምክትላቸው ም/ጠ/ሚ ደመቀ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው ከሆነ፤ ስህተቶቹ ይታወቃሉ፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን በቆየባቸው አመታት ውስጥ የያዛቸው የሃሳብ ስህተቶችንና የፈፀማቸው የተግባር ስህተቶችን ለማረም፣ የኢህአዴግና የአጋሮቹ ውህደት ያስፈልጋል ብለዋል - የድርጅቱ መሪዎች፡፡
ስለዚህ፣ በደፈናው “ስህተቶችን ለማረም” ከማለት ይልቅ “ስህተቶቻችንን ለማረም” ወይም “የፓርቲያችንን ስህተቶች ለማረም” በማለት ጉዳዩን ጠራ ማድረግ ይቻላል፡፡
የሺ ዓመት፣ የ500 ዓመት፣ የ100 ዓመት፣ ጥንት የነበረና ያልነበረ ታሪክን፣ እንደ እውነተኛና እንደ ወቅታዊ ጉዳይ እያስመሰሉ ለሚቃዡ የፖለቲካ ቁማርተኞች መንገድ ላለመክፈት ይረዳል፡፡ አለበለዚያ፣ “ከሺ ዓመታት በፊት የተሰራ ስህተትን ማረም” እያሉ የፖለቲካ ስካርን ለሚያባብሱ ክፉዎች ይመቻቸዋል፡፡
“የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት በዘላቂነት ለማረጋገጥ” የሚለው ሦስተኛው የውህደት ምክንያትስ ምን ማለት ነው?
የተበጣጠሰ ዝርክርክር አስተሳሰብ መጥፎ የመሆኑ ያህል፣ የቅጽበት የቅጽበቷ ላይ የመቅበዝበዝ፣ የዛሬና የዘንድሮ ምርጫ ላይ ብቻ የመንደፋደፍ ውል የለሽ አስተሳሰብም መጥፎ ነው፡፡
የዛሬ 50 ዓመት፣ “ለጊዜው ያዋጣል” በሚል ሰበብ የተጀመረው የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ቀስ በቀስ መዘዞቹ እየበዙ፣ ጠቅላላ አገሪቱን የትርምስና የጥፋት አፋፍ ላይ እንዳደረሳት አይተናል፡፡ “ለጊዜው ያዋጣል ወይ” ከማለትም በላይ “ያዛልቃል ወይ” ብሎ በረዥሙ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
“ለዛሬ ገንዘብ ማግኘት” የማለት ጉዳይ ሳይሆን፡ “በየጊዜው እየበለፀገ የሚሄድ ሕይወት” የሚል አላማ፤ የቅርቡንም የሩቁንም ጊዜ አዳምሮ የማቀናበር ጉዳይ፣ ለሰው ልጅ የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ ለራስም፣ ለልጅ ልጆችም፣ ይህንን መመኘትና እውን እንዲሆን መጣር፣ እጅግ ቅዱስ አላማ ነው፡፡
“የመጪው ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት በዘላቂነት ለማረጋገጥ” የሚለው አባባል፣ ይህንን ለመግለጽ ከሆነ መልካም ነው፡፡ በእርግጥ እዚህም ላይ፣ በጥንቃቄ ጉዳዩን ጠራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ፀረ ብልጽግና የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችም፣ ተመሳሳይ አባባል ይጠቀማሉ፡፡
“ብልጽግናን መቃወም፣ የኢንዱስትሪ እድገትን ማደናቀፍ”…”የመጪውን ትውልድ ፍላጐት በዘላቂነት ማረጋገጥ ነው” ይላሉ:: ለእንዲህ አይነት ፀረ ብልጽግና አስተሳሰብ፣ መንገድ ላለማመቻቸት ጉዳዩን ጠራ ማድረግ ይቻላል፡፡
አሁን ላለውና ለመጩው ትውልድ፣ በየጊዜው የሚበለጽግ ሕይወትን የሚያቀዳጅ ስልጣኔን ማስፋፋት ያስፈልጋልና፡፡  


Read 2215 times