Saturday, 30 November 2019 13:52

የታሪክ ቅርስና ውርስ ሲወሳ

Written by  በታደለ ገድሉ ጸጋየ (ዶ/ር)
Rate this item
(1 Vote)

     የመጽሐፉ ርዕስ፡- የታሪክ ቅርስና ውርስ
አበበ አረጋይ  (ራስ)
አሰናጅ፡-  አጥናፍ ሰገድ ይልማ
የገጽ ብዛት፡- 376
ዘመነ ኅትመት፡- 2011ዓ ም
ኅትመት፡- አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት  
የመጽሐፉ ዋጋ፡- 250 ብር፤20 ዶላር   
ቀደም ሲል ከአምስት ያላነሱ መጻሕፍትን ለንባብ ያበቁት ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ በቅርቡ «የታሪክ ቅርስና ውርስ አበበ አረጋይ (ራስ)» የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ለአንባቢያን እነሆ ብለዋል፡፡ መጽሐፉ በታዋቂው አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ የህይወትና የነጻነት ተጋድሎ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡
በ38 ምዕራፎች የተከፋፈለው መጽሐፉ፤ በአምስቱ አመት የመከራ ዘመን ፋሽስቷ ኢጣሊያ ሀገራችንን በግፍ በወረረች ወቅት በጦር ስማቸው አባ ገስጥ (ራስ አበበ)፣ በየጦሩ ግንባር ከፋሺስቶች ጋር ፊት ለፊትና በደፈጣ ጭምር በመዋጋት፣ ለኢትዮጵያ ነጻነት መመለስ ስለ ከፈሉት መስዋዕትነትና ስላስመዘገቡት የድል ውጤት፤ ከነጻነት በኋላም በሀገሪቱ ስለ ነበራቸው ወሳኝ የፖለቲካ ሥልጣን (የአገር መከላከያ ሚኒስትር) በዝርዝር ይተርካል፡፡ ከኢጣሊያ ጦርነት በፊት ስለነበረው ያገራችን ታሪክ  ጭምር የሚያስገነዝበው መጽሐፉ፤ ስለ እንግሊዝ ተንኮለኛነት፤ ስለ ጦርነቱ ዋዜማና የክተት ጥሪ፤ ስለ አነጋጋሪው የንጉሡ ስደት፤ ራስ አበበ  ዱር ቤቴ ብለው  ስለፈጸሙት የዐርበኝነት ተጋድሎ፤ ስለ አስካላ አቦ ጦርነት (ጅሩ ደነባ አካባቢ የሚገኝ ቦታ)፤ በወቅቱ  በ1928 ዓ ም የጠላት ምሽግ የሆነቺውን አዲስ አበባን ከትግል አጋሮቻቸው ከወንድማማቾቹ ከደጃዝማች አበራ ካሳና ከደጃዝማች አስፋወሰን ካሳ፤ደጃዝማች ኃለማርያም ማሞ፤ ከደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ፤ከራስ መስፍን ስለሺ፤ ከደጃዝማች ዘወቅዱ አባ ኮራን፤ ከደጃዝማች ፍቅረማርያም ናደው ጋር 40 ሺህ ያህል  ሠራዊት አሰልፈው ጠላትን ሲያስጨንቁ  ውለዋል፡፡
ወቅቱ ክረምት ሆኖ ኃይለኛ ዝናም ይጥል ስለነበር ዐርበኞቹ እንደ ልብ መረጃ ለመለዋወጥ እንዳልቻሉና ከታላላቅ አርበኞችም ውስጥ እንደነ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶን የመሳሰሉ በትግል ላይ ስለወደቁ የተጠበቀውን ያህል ውጤት እንዳልተመዘገበ፤ ግን ከበባው በኢጣሊያ የጦር መሪዎችና ተዋጊዎች ላይ ከፍተኛ መደናገጥን እንደፈጠረ ደራሲ አጥናፍ ሰገድ ጽፈዋል፤መረጃዎችን ዋቢ አድርገው:: ራስ አበበ በሳላይሽ ተራራ፣ በዋዩ ክፍል (ሰሜን ሸዋ) መድፍ ከታጠቀው፤አውሮፕላን ከአሰለፈው፤50 ሺህ እግረኛ ጦር ከነበረው ከጀኔራል ትራኪያኒ ሠራዊት ጋር ስላደረጉት ጦርነትና የባንዳው ፊታውራሪ መሸሻ  ሠራዊት እንዴት እንደተደመሰሰ፤ ደጃዝማች አበራ ካሳ ከዐርበኝነት ወደ ጠላት አማኝነት እንዴት እንደገቡ፤ በ1929 ዓ.ም የሸዋ ዐርበኛ እንዴት ያለ አውራ እንደቀረ፤ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ነውረኛነት ያለው ቃል ስለ መናገራቸው፤ መጽሐፉ ይተርካል፡፡
በተጨማሪም ባንዳው ደጃዝማች ተወንድ በላይ እንዴት እንደተማረከ፤ ከባንዳ ኪዳኔ መሸሻ ጋር ስለተደረገው ጦርነትና ስለ ኪዳኔ ሞት፤ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ከአበበ አረጋይ ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት፤ ስለ ደጃዝማች ለጥ ይበሉ ገብሬ፤ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በማርሻል ግራዚያኒ ላይ በተጣለው አደጋ ምክንያት በግፍና በጅምላ ስለተጨፈጨፉት የኢትዮጵያ ሰማዕታት የታሪክ ቅርሱ ይተርክልናል፡፡ እንደዚሁም፤ አባ ገስጥ በተጉለት፤ በመንዝና በሌሎች ቦታዎች  ዐርበኞች እንዲጠናከሩና የባንዶች ጦር እንዲዳከም በማሰብ ከትግል አጋሮቻቸው ከእነ ደጃዝማች አውራሪስ፤ ከእነ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፤ ፊታውራሪ ደስታ ሸዋርካብኽ፤ ከእነ ፊታውራሪ አየለ ኃይሌ፤ ፊታውራሪ ዘውዱ አባ ኮራን፤ ከልጅ ማነ ብርሃን አባ ኮራን፤ ከግራዝማች ዘውዱ አስፋው፤ ከቀኛዝማች አበበ አውራሪስ፤ ከባላምባራስ በሻኽኃይሌና ከሌሎች ጋር እየተማከሩ የተቀናጀ የተጋድሎ ስልት በመቀየስ ይታወቃሉ፡፡
በዚህም እንደነ ዓለሙ ኤጀርሳ ከመሳሰሉና ከሌሎች መሰል ባንዶች ጋር  በተደረገ  ጦርነት፤ ለኢጣሊያ ያደሩ ከሃዲዎች ሲደመሰሱና ዐርበኞች ድል ሲቀዳጁ ጸሃፊው ያስቃኙናል፡፡ በጥቅሉ ራስ አበበ፤ በሸዋ ያልተሰለፉባቸው ዐውደ ግንባሮች የሉም ለማለት ይቻላል፡ በዋነኛነትም፡ በሸንኮራ፤ በአሌልቱ፤ በቅምብቢት፡ በወበሪ፤ በግንባር፤ በጦስኝ፤ በቁልቋል በር፤ በከሰም፤ በደንሴና በቡርቃ ግንባር፤ በውግር፤ በሰሞሳ፤ መድፍ፡ በተማረከበት፡ በአሳግርት፤ በእንሳሮ.በእነዋሪ፡ በተከታታይ፤ በካቺሴ፤ በምራኔ፤ በሮቢ ወንዝ ጦርነት፤ በያያ ቀጨማ፤ በመንዝ ደንገዜ ገጦ ጦርነት፤ በየይል፤ በሣጋ በር፤ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ በተሠውበት በጎርፎ ሜዳ የጦር አውድማዎች ከኢጣሊያ ጦር ሠራዊትና ከባንዳው ተዋጊ ጋር ተጋድሎ አድርገዋል‹:: ከዚህ የተነሣም ባንዳው ደጃዝማች ጨቡድ ሊማረክና የኩምቢ ከምሲ ባንዳ ሠራዊት ሊደመሰስ ችሏል:: ከኢጣሊያ ጋር የተደረገው ጦርነት ጣሊያኖች ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ እንዴት እንደተሸጋገሩና ተጋድሎው በመኻል ሲዳከምና ጠላት ሲያይል፣ ዐርበኛው ጥቃትን እየመከተ እንዴት እንዳፈገፈገ አጥናፍ ሰገድ ይነግሩናል፡፡
በተለይም ዐርበኛ የነበሩት ባለቤታቸው ክብርት እመቤት ቆንጂት አብነት፣ ከእነ አራስ ልጃቸው (አየለወርቅ አበበ) ጋር በካቢ ጦርነት መማረካቸው ከትግሉና ከዐርበኝነት መንገዳቸው ሊያሸሻቸው አልቻለም፡፡ ይልቁንም አይደለም እርሳቸው ወላጅ እናታቸው ክብርት አስካለ ጎበና ዳጨ «ልጄ የተቀበለውን መከራ እኔም እቀበላለሁ» በማለት ከጦሩ ጋር አብረው ይጓዙ ነበር፡፡ ጉዞው እንደተጀመረ በጸና ስለታመሙና በበቅሎ ለመሄድ ስላልቻሉ በቃሬዛ ጭምር ይጓዙ ነበር፡፡
አስቀድሞ ታምሞ የነበረው ልጃቸው ዳንኤል አበበም እንዲሁ በቃሬዛ  ይሄድ ነበር፡፡ በዚህም የራስ አበበ ቤተሰቦች ጭምር ለሀገራችን ነጻነት ከፍተኛ መሥዋዕትነት እንደከፈሉ ከታሪኩ እንረዳለን፡፡ ራስ አበበ በድንገት ከጠፉ በኋላ እንደገና ተመልሰው ሲመጡ፣ ካገር አገር ሲሳደድ የነበረው ዐርበኛ ሁሉ፤ ሞራል ገዝቶና ተበረታትቶ በጭቃ ሚካኤል፤ በሰቻት ክብ፤ በዳንሴ፤ በሾላ ገበያ በቆቦ ዐራዳ በፍቅሬ ግንብ በደነባ፤ በመንዲዳ፤ በወበሪ፤ በሳክላ፤ በዙሪያምሁይ፤ በሳሲት ባደረገው ውጊያ  ከፍተኛ ድል ለመቀዳጀት ተችሏል:: ትግሉም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዐርበኞች ማኅበር፣ መጀመሪያ በሰሜን ሸዋ መንዝ ጥቅምት 23 ቀን 1831 ዓ ም ተመሥርቶና ተጉለት አንቀላፊኝ በተባለ ቀበሌ፣  ታኅሣሥ 29 ቀን 1931 ዓ.ም ደንቡ ተሻሽሎ የሥራ መሪ አካላት ሲሠየሙ፤ ራስ አበበ አረጋይ የማኅበሩ የክብር ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ይተርክልናል፤ ውብ በሆነ አገላለጽ፡፡
መጽሐፉ መልአከ ፀሐይ ኢያሱ እንዴት እንደነገሡ፤ ራስ አበበ አርበኞችን ሲያስታርቁና የእርቅና የሰላም ድርድር ሲያደርጉ፤ ስለ ወሌንሶ ናጎንቤሳ ጦርነት፤ ስለ ዜና አብሳሪው የደጃዝማች ከበደ ተሰማ ደብዳቤ፤ ስለ ደብዳቤ ግንኙነት፤ የኢጣሊያ ጀኔራሎች ራስን ለማጥመድ ስላደረጉት ጥረት፤ የጂሩ ዐርበኞች በግፍ ስለ መገደላቸው ስናነብ --- የአምስት ዓመቱ የመከራ ዘመን ምን ያህል አሠቃቂ እንደነበር ያስታውሰናል፡፡ የዐርበኞች የሥልጣን ሽሚያም አግራሞትን ያጭራል፡፡ ኣባ ገስጥ ቆራጥ፣ ጀግናና የውሳኔ ሰው እንደነበሩ መጽሐፉ ይገልጻል፡፡ ናዚ ዐርበኞችን ለመደምሰስ 200 ሺህ ሠራዊት አሰልፎ ስለ መጠባበቁ፤ አባ ገስጥ በድል ዋዜማና መንግሥት፣ ከጄኔራል ካኒንግሃም ጋር ስለመገናኘታቸው ጸሃፊው ይነግረናል:: ንጉሡ በድል አድራጊነት አዲስ አበባ እንደ ገቡ፤ስለ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ፤ ከዐርበኛ ቆንጂት አብነት ስላገኙት መረጃ እናነባለን፡፡ በመጨረሻም፤ ይህንን በታሪክ የታጨቀ ድንቅ መጽሐፍ ታነቡ ዘንድ እጠቁማለሁ፡፡
የአዘጋጁ ማስታወሻ፡- ደራሲና ጋዜጠኛ አጥናፍ ሰገድ ይልማ፣ ቀደም ሲል የበደል ካሳ (ልብ ወለድ)፤ የእንስሳት አመፅና ድርድር (ፖለቲካዊ አሽሙር)፤ የሕይወቴ ምሥጢር (ግለ-ታሪክ)፤ የልጅ ኢያሱ አነሣሥና አወዳደቅ (ግለ ታሪክ)፤ አገር የፈታ ሽፍታ (ልብወለድ)፤ ሌላ የፖለቲካ አሽሙር፤ የተሰኙ ሥራዎችን ለአንባቢያን ማድረሳቸው ይታወቃል፡፡



Read 2435 times