Saturday, 30 November 2019 12:08

የፖለቲካ ሃይሎች አገር የማዳን ውይይት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

  “የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳስቦኛል”

          የአፍሪካ ሕብረት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ ብሔርና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ የጥቃት አዝማሚያዎች መታየታቸው በአገሪቱ ዜጎች ሕልውና ላይ ስጋትና አደጋ መደቀኑን በማመልከት መንግሥት አስፈላጊ የእርምት እርምጃዎች እንዲወስድ አሳሰበ፡፡
ኮሚሽኑ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ይዞታ በገመገመበት ሪፖርቱ፤ በአገሪቱ ባለፉት ጥቂት ወራት የተከሰቱት ፖለቲካዊና ማህበራዊ መነሻ ያላቸው ግጭቶችና ጥቃቶች አሳሳቢ ናቸው ብሏል፡፡
በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ዜጎች አስፈላጊውን መንግሥታዊ ጥበቃና የደህንነት ዋስትና ማጣታቸው በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን ኮሚሽኑ አስገንዝቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግጭትና ጥቃትን መነሻ ባደረገ መፈናቀል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች (በምዕራብ ጉጂ፣ ጅግጅጋ፣ ቅማንት፣ በአማራ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ከ1 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊው ሰብዓዊ እርዳታ በአግባቡ እንዲቀርብ መረጋጋት መፈጠር እንዳለበት ያሳሰበው ኮሚሽኑ፤ ሁሉም ባለድርሻዎች ለዚህ እንዲረባረቡ ጠይቋል፡፡
የአገሪቱን የፖለቲካና ማህበራዊ መሰረት እያናጋና ወደ ስጋት እየከተተ ያለው የማህበራዊ ሚዲያን በመጠቀም የሚነዙ የጥላቻ ንግግሮችና የሃሰት ዘገባዎች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ብሄርና ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን እየተሰጣቸው መምጣቱ አሳሳቢ ነው ብሏል።
ሃይማኖትንና ብሔርን በመለየት ሰዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈፀም፣ መደብደብና ንብረታቸውን መቀማት እንዲሁም በእምነት ተቋማት ላይ ጥቃት መፈፀም ለአገሪቱ እጅግ አደገኛ ልምምድ መሆኑን የጠቆመው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ ድርጊቶቹ በመንግሥት በኩል በይፋ ሊወገዙና ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብርና እንዲያስከብር፣ የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ የውጭ አካላት ተጣርተው ተገቢው ፍትህ እንዲሰጥ፣ በብሔራቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት በሚደርስባቸው ጥቃት ስጋት ውስጥ የገቡ ዜጎች የደህንነት ዋስትና እንዲከበር እንዲሁም አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ተጎጂዎች በተገቢው እንዲካሱና  በመንግሥት ድጋፍ እንዲቋቋሙ ኮሚሽኑ ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎችና አክስቲቪስቶች መንግሥት በዚህ ረገድ የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ የጠየቀው የአፍሪካ ህብረት፤ ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በአገሪቱ ላይ የተደቀነውን ስጋት ለመቀልበስ የሚረዳ የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት እንዲጀምሩም ጥሪ አቅርቧል፡፡


Read 10180 times