Saturday, 30 November 2019 12:03

እነ አቶ ልደቱ ምርጫ ቦርድን እንከሳለን አሉ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  ኢዴፓን በሃይል ተነጥቀናል ያሉት እነ አቶ ልደቱ አያሌው ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ምላሽ የማይሰጣቸው ከሆነ ምርጫ ቦርድን በህግ ለመጠየቅ መዘጋጀቸውን አስታውቀዋል፡፡
ከአንድ ወር በፊት የብሔራዊ ም/ቤት ስብሰባ አድርገው አዳዲስ አመራሮች መርጠው ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን ህልውና እንዲያረጋግጥላቸው ጠይቀው የነበረ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት ፕሬዚዳንቱ አቶ አዳነ ታደሠ ቦርዱ ምንም አይነት ምላሽ ሊሰጣቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ለምናቀርበው ጥያቄም ቦርዱም ዝምታን መርጧል ብለዋል፡፡
“አሁንም ኢዴፓ በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ ጉልህ ሚና እንዳይጫወት ስውር ደባ እየፈፀመበት ነው የሚሉት አቶ አዳነ በፓርቲው ጉዳይ ቦርዱ ለመወሰን ለምን እንደተቸገረ አልገባንም ብለዋል፡፡ ችግሩ የተፈጠረው እንዴት ነው? ችግሩ ያለው ማን ጋር ነው? የሚሉትን ለይቶ ለማወቅ ሲባል አምስቱም የምርጫ ቦርድ አባላት በጋራ እንዲያነጋግሯቸው ህዳር 17/2012 በደብዳቤ መጠየቁንም አቶ አዳነ አስረድተዋል፡፡
አምስቱም የቦርዱ አባላት ባሉበት ነው በኢዴፓ ጉዳይ ከእንግዲህ መወያየት የምንፈልገው ያሉት አቶ አዳነ ለዚህ ጥያቄያችን ምላሽ የማይሰጠን ከሆነ በቀጥታ ቦርዱ ላይ በፍ/ቤት ክስ እንመሠርታለን ብለዋል፡፡
“በዋናነነት በኢዜማ የተወሰዱ ጽ/ቤቶቻችን እንዲመለሱ፣ ማህተማችን እንዲመለስ የቦርዱ ውሣኔ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ አዳነ ቦርዱ በተደጋጋሚ ኢዴፓ አልፈረሰም የሚል መግለጫ መስጠቱንና ካልፈረሰ ለባለቤቶቹ መመለስ እንደሚገባው አስረድተዋል፡፡
ይህን አቤቱታቸውንም በተመሳሳይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በደብዳቤ ማቅረባቸውንም አቶ አዳነ ተናግረዋል፡፡  

Read 10549 times