Saturday, 23 November 2019 13:03

የትዕግስትን መጽሐፍ እያነበቡ ትዕግስት ማጣት?!

Written by  ሻሎም ደሳለኝ
Rate this item
(1 Vote)

  የመጽሐፍ ስጦታ ልስጥህ ሲሉኝ፤ ደርሶ እምቦሳ ያደርገኛል። “የባስሊቆስ እንባ” የተሰኘው የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ በስጦታ መልክ እጄ ሲገባ የተሰማኝ ስሜት የዚህ ማሳያ ነው። መጽሐፉ የትዕግስት ታፈረ ሞላ ነው። መጽሐፉን አንብቤ ለማድነቅ 220 ገፆቹን በሙሉ መጨረስ አላስፈለገኝም፡፡  አዬ . . ?! የትዕግስትን መጽሐፍ እያነበቡ፣ ትዕግስት ማጣት ምን የሚሉት ደዌ ነው?
ፈረንሳዊው ባለቅኔ አርተር ራምቦ ለወዳጁ በፃፈው ደብዳቤ ላይ በግርድፉ እንዲህ ይላል … “እውነት እልሃለው… የዓለሙ ነገር ፋታ ቢሰጣት እንደ ሴት ልጅ ግጥምን መፃፍ የሚችል ሰው የለም”።
የትዕግስት ታፈረን “የባስሊቆስ እንባ” የተሰኘውን ስብስብ አጫጭር ልቦለዶች ሳነብ አስቀድሞ ወደ አዕምሮዬ የመጣው የአርተር ራምቦ ንግግር ነው። እውነትም ኪነ-ጥበብ እንደ ቡና በሴት እጅ ትቆላለችና። በአገራችን የድርሰት ታሪክ ውስጥ እንደ ፊርማዬ አለሙ፣ መቅደስ ጀምበሩ፣ ዓለምፀሀይ ወዳጆና ስንዱ አበበ የመሳሰሉ ድንቅ ሴቶች መኖራቸው እንደ ነብሰጡር ሆድ ደረታችንን የሚያስነፋ ኩነት ነው። ይሄን ኩራት የሚያስቀጥሉ መሰል ፀሃፍት ሲገኙ ደሞ እልል በቅምጤ ያሰኛል።
“የባስሊቆስ እንባ” የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ ነውና የአጭር ልቦለድ ባህርያትንና ምንነትን አስቀድመን እንይ።
አጭር ልቦለድ፣ ልክ እንደ ረዥም ልቦለድና ስነ ግጥም ሁሉ እንዲህ ነው ተብሎ መደምደም ባይቻልም፣ በተለያዩ ምሁራን ግን ብያኔዎችና መስፈሪያዎች (parameters) ተሰጥቶት እናያለን። ለአብነት ያህል የአንቶን ቼኾቭን “የቼኾቭ ጠብመንጃ” የሚባለውን ብያኔ ብናይ፤ “በሁለተኛው ትዕይንት . . . ግድግዳ ላይ ሽጉጥ ከተሰቀለ፤ በመጨረሻው ትዕይንት ላይ መተኮስ አለበት” ይላል። ብዙ ተቀባይነት ያተረፈው የሀሪሾ ብያኔ በበኩሉ…“ አጭር ልቦለድ ከአስር ሺህ ቃላት በታች የሚይዝ፣ አንድ ዋነኛ ግብ ለማምጣት የተዋቀረና ድራማዊ ለውጥ የሚታይበት አጠር ያለ ትረካ ነው። አጭር ልቦለድ በአንድ ቅፅበት በአንድ ነጠላ ሁነት ውስጥ በሚያልፍ አንድ ገጸባህሪ ላይ ያተኩራል። እነዚህ እንኳን ተሟልተው ባይገኙ አጭር ልቦለድ አንድነትን በዋናነት ማሳየቱ አይቀርም። የተዋጣለት አጭር ልቦለድ በተወሰነ መቼት የተቀረፀና አንድ ሁነት ውስጥ ገብተው በህሊናዊ ወይም በአካላዊ ድርጊት የሚሳተፉ አንድ ወይም ጥቂት ገፀባህሪያትን ይይዛል። ግጭት ወይም የተፃራሪ ሀይላት ፍጭት የማንኛውም አጭር ልቦለድ እምብርት ነው።” ይለናል።  እንግዲህ ከቾኾቭ በተለይም ደሞ ከሀሪሾ ብይን የምንረዳው፤ በአጭር ልቦለድ ውስጥ ደራሲያን ገፀባህሪያቱን የቤተሰብ ምጣኔ እንደሚጠቀም ሰው ጥቂት፤ መቼቱን ደሞ ውስን አድርጎ መሳልና ከሰሜን ወደ ደቡብ፣ ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ሳያመላልስ፣ ሳያንገላታ የግጭቶቹን መዳረሻ አንድ ነጠላ ውጤት አድርጎ መሸመን ያለበት መሆኑን ነው።
“የባስሊቆስ እንባ” በተሰኘው ስብስብ ስራ ውስጥ “አንድ እንባ”፣ “እጇ ‘ማይፈታ”፣ “ጉንዳኖቹ”፣ “ፀሐይ”፣ “የሰይጣን መኪና”፣ “ክታቤ”፣ “አንዴና ዘላለም”፣ “እንጃኔ”፣ “እያሃ ያብባል ገና” እና “የባስሊቆስ እንባ” የተሰኙ አስር ድርሰቶች ቢኖሩም፣ ከጊዜና ከቀልብያ ክጀላ አንፃር “እጇ ማይፈታ” እና “አንዴና ዘላለምን” በአጭር በአጭሩ፣ ከላይ ከላይ ለማየት ሞክሬአለሁ። ከሁሉ አስቀድሜ ግን የመጽሐፉን ሽፋን በኔ ዐይን ላስመልክታችሁ።
የመጽሀፉ ሽፋን በጥቁር መደብ የተሸፈነ ሲሆን የውሃ ወይም የዕንባ ጠብታ በሚመስል ቅርፅ ውስጥ አንድ አዛውንት የስፌት መኪናቸው ላይ ተፈናጠውና አቀርቅረው ሲያበጃጁ ይታያል። ለክርክራችን ቃል፣ ለስሜታችን እንጉርጉሮ እንደማይቸግረን ሁሉ፤ ደስታችንን በነጭ፣ ሀዘናችንን በጥቁር የመመሰል ልማድ አለን። በመሆኑም ደራሲዋ ልክ እንደ ገፀባህሪዋ ቢኒ (ቢኒያም) ሁሉ እኛንም የማህሌትንና የእጇ ማይፈታን፣ የዮኒንና የመሴ ቀዌን ህመም በእያንዳንዱ መስመር ከተደራሲው ላይ አጋብታ፣ ዕንባችንን የመሀረም ሲሳይ ልታደርገው ይሁነኝ ብላ መነሳቷን ያሳብቃል። የመፅሐፉን ሽፋን በጥቁር መደብ ወስና ከላዩ በግድንግድ የእንባ ዘለላ ማጀቧም ምስጢሩ፤ አንድ እንባ ነው። ጥቁሯ መደብና አንዲቷ የዕንባ ዘለላ እንደ ጠቋሚ ቃል ሹክ የሚሉን፤ ወደ ውስጥ ስንዘልቅ የሚጠብቁን ፊደላት “ሀዘን ንክር፤ የክርታስ ላይ እዝን” ሆነው ነው። ደራሲዋን በድርሰቶቿ በኩል ለተመለከታት ጨለምተኝነት ይታይባት ይመስላል። ነገር ግን እንባውን በከበበው ሰማያዊ ከፈፍና እንባው መሀል ጉብ ብለው የተራቆተውን ምድር በአረንጓዴ ለምለም ቀይረው ሊያበጁ እንደሚጥሩት አዛውንት፤ ደራሲዋም ተስፋን በጭላንጭል እንካችሁ ስትል ማጤን ይቻላል። በዚህ ረገድም የመፅሀፉ ሽፋን የተዋጣለት ነው።
አንድ ሰው “እጇ ማይፈታ”ን አንብቦ ልክ እንደ ክርስቶስ “ከናንተ መካከል ሀጥያት የሌለባት ይህቺን ሴት ይውገራት” ይል ይሆን እንጂ ድንጋይ የጨበጠበትን እጅ አንከርፎ የሚቆም አይኖርም። ቢኖር እንኳን ክፉ ልቡ የማታ የማታ እንደ ፈርኦን የገዛ የዕንባው ባህር ውስጥ ያሰጥመው ይመስለኛል። ታሪኩ በምልሰት ዘዴ የቀረበ ነው። የዛሬን በትላንት መስታዎት ያስቃኛል።
“ያኔ ሁላችንም ልጅ ነበርን ‘ንብ ጉንጫችንን ቢነድፍልን እንወፍራለን’ የምንል የዋሆች። ‘እኔ ዶሮ ልሁንልሽ አንቺ የዶሮዋ ባለቤት ሁኚና እንጫወት’ ብለው ታላላቆቻችን ቆሏቸውን ጨርሰው ቆሎ እንድንበትንላቸው ሲያነግሱን በደስታ የምንነግስ ሁላችንም ልጆች ነበርን” ብሎ የሚጀምረው ታሪክ ወደ ኋላ ይመልሰናል። ከልጅነት ዘመን አንቢያንን ይቀላቅላል።
የአጭር ልቦለድ ባህርያት የሚባሉት ነጠላ ውጤት፣ ጥድፊያና ቁጥብነት ይስተዋልበታል። ታሪኩ መስመሩንና መዳረሻውን ሳይስት፣ በውስን ገፀባህሪያት ካሰበበት ሲዘልቅ እናገኛለን። እጇ ‘ማይፈታ የተባለችው ሴት በልጅነቷ ለወንድሟ መኪና መስሪያ ብላ የሽቦ ስርቆት ውላለች። የእህቷን ምኞት ለማሟላት ካልጠና የልጅነት ጅስሟ ደም ገብራለች። ይሄን ሁሉ ውለታ ብትውልም ግን ለልፋቷ የእርግማን ምስ፣ ለቁስለቷ የኩርኩም መልስ ተበረከተላት። ይሄ ሁሉ እንኳ አልተሰማትም ምክንያቱም ትላለች። “ምክንያቱም . . . ወንድሜ በሽቦ መኪና መስራት በጣም ያስደስተው ነበር። እህቴ ደግሞ በጭቃ ቤት መስራት፤ እኔስ? መኪናውም ቤቱም ያምረኛል። ግን ጊዜ የለኝም።ከእኔ ፍላጎት ይልቅ ወንድሜና እህቴ የሚፈልጉትን ሲያገኙ እደሰት ነበር። . . . የእኔ ሀሳብ  የእህቴ ቤት ጣሪያ አልባ አለመሆኑ ብቻ ነው።” እንዴት ያለ ቅድስና ነው ጃል!
የዚህ ድርሰት ተምሳሌታዊነት ድንቅና ረቂቅ ነው። ይህቺን ሴት የማይመስል ማን አለ? ፍቅር ለማመን እንጂ ለማሰብ እድል አይሰጥም። በእህትና በወንድም ፍቅር ታውረው ስንቶች ባልጠና አካላቸው የመከራን ቀንበር ለመሸከም ቆረጡ?! ስንቶች የልጅነት ህልማቸውንና የልጅነት እድሜአቸውን ገበሩ?! ስንቶች እኮ ስንቶች?!!! . . .
ለወንድሟ ሽቦ እሰርቃለሁ ብላ መዳፏ በእሳት ተለበለበ። አልበቃትም። ለእህቷ ጣሪያ ፍለጋ ወጥታ ጉያዋ ተሸነታተረ።
“በእሳት የተቃጠለ እጄን ዘረጋሁና በደህናው እጄ አወጣሁት። እህቴ ጣሳውን ስታየው ጩኸቷን ለቀቀችው። ደነገጥኩ። ጣሳው ጉያዬን ደም ነክሮት ኖሯል። ፈፅሞ አልታወቀኝም ነበር“
ታዳ ህልሟ ተሳካና ወንድሟም የሽቦ መኪናውን፣ እህቷም የጭቃ ቤቷን በሳር ሳይሆን በቆርቆሮ ገነባች። የራሷን ቤት ለመስራት ያዘጋጀችው አፈር ፊቷ ተቆልሏል። ግድ አልሰጣትም። እሮጥ ብላ የወንድሟን እጅ አፈፍ አድርጋ አስነዳኝ አለችው። አመናጭቆ በአይኑ ቂጥ መለሳት። ደነገጠች። በሮጡለት መሰናከል፣ በቆሙለት መገፋት ዕጣ ፈንታዋ ሆነ። የወንድሟ ውብ የሽቦ መኪና ውስጥ የመዳፏ ላይ ደም ማረፉ ተዘነጋ። እንባ እንባ እያላት እህቷ ዘንድ አቃናች። እሷም ብቶን ግን በጄ አልል አለቻት። መልሷ “እሺ ከሺ” መብለጡን የተገነዘበ አልነበረም። ይሄን ግዜ ስድብ ቀናት “ገብጋባ እኔ ላንቺ ቆርቆሮ ሳመጣ ደም በደም አልሆንኩም? እኔ ላንቺ ብዬ መርፌ አልተወጋሁም? እኔ ላንቺ ብዬ ኩርኩም አልቀመስኩም?” አለቻት ። እህቷ ግን የማይገርፉት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል ሆኖባት አንቧረቀች። እናቷም እህትሽን አስለቅሰሻል ብላ ሌላ ኩርኩም አከለቻት። እንዲህ ነው እንግዲህ። ስንት ዘመን ተደፍተው፣  ሶፋና ቲቪ ቀይረው፣ እህትና ወንድም አስተምረው፣ እናት አባታቸውን ጡረው ሲያበቁ፤ ልረፍ ሲሉ የሚጠዘጥዛቸው የማያጡን፣ የሚገላምጣቸው የማይነጥፍባቸውን ምስኪናንን ሁሉ ነው ድርሰቱ የሚከስትልን። ሴት ለስሜቷ ቅርብ ናት። ለዚህም ነው የእጅ ላይ ፀጉር እስኪያስቆም ድርሰቶቿ የአንባቢን ቀልብ የሚሰርቁት።
ድርሰቱ ማብቂያው ላይ እንዲህ ይላል፡-
“ይህ ሁሉ ያኔ ልጆች እያለን ነበር” ጠባሳው ግን በነበር ብቻ አልተገታም “ ወንድሜ ሚስት ሊያገባ ስለሆነ አንዳች ቀዳዳውን እንድሸፍንለት ይፈልጋል። እህቴ አዲስ ሥራ በመጀመሯ - የእኔ ልብ ደሞ ልጅነታችንን ያስባል። ‘እጇ ማይፈታ’ ይላሉ ሰዎች፤ ግን ወድጄ አይደለም። እጄን ልፈታው ስል የጣቴና የብብቴ ጠባሳ አሁን ድረስ ሸምቅቀው ይይዙኛል። ልዘረጋ ሳስብ ይደድርብኛል። ይኼን ማንም ማየት አይችልም። የተበተብኩትን የሀዘን ክር መፍቻ ማንም መርፌ አልሰጠኝም። ዝም ብሎ ብቻ ‘እጇ የማይፈታ’ ይላል ሰው።” የሰው ልጅ ልክ እንደ ድሪቶ ጨርቅ ብዙ ቦታ የተጠቃቀመ ነው። ባንድ ጀንበር አይበቅልም። ከብዙ መልክ የተቀነበበ ማህበራዊ ድሪቶ ነው።
“አንዴና ዘላለም” የተባለው ድርሰት በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ከተካተቱ አጫጭር ልቦለዶች ውስጥ ሰቃዩ ይመስለኛል። ገፀባህሪያቱ ሁለት ናቸው። የግጭቱ ማጠንጠኛ ጊዜ እና  ምኞት ነው። የዘመን አንቀልባው ትዝታ ነው።  
መቼቱ ቲሩም ፒያሳ ነው። “ድሮ ድሮ እኔና ጓደኛዬን እዚህ ቤት ያጠመደ አያጣንም ነበር። አሁን አሁን ደግሞ ከአስቤዛ ብር ሲተርፈኝ የጥንት ጓደኛዬን እጠራትና ፒያሳ ቲሩም ኬክ እንበላለን።”  
የድርሰቱ አላማ ስለ ተራኪዋና ስለ ጓደኛዋ ፒያሳ መዋል፣ ቲሩም መታደም፣ ኬክ መብላትን መተረክ አይደለም። የፒያሳን ገፅታ፣ የካፌውን ስፋት፣ የኬኩን ጥፍጠት መተረክ አልተከጀለም። መቼቱ ቦሌ ሆነ ጉለሌ የሚያመጣው ለውጥ የለም።
የአጭር ልቦለድ አንዱ መገለጫ ጥድፊያ ነው። ወደ መዳረሻው የሚደረግ ጥድፊያ። ድርሰቱ አጭር ልቦለድ መሆኑ ቀርቶ ረዥም ልቦለድ ቢሆንና ደራሲውም አዳም ረታ ቢሆን ኖሮ፣ ከካፌው መገኛ ጀምሮ በካፌው ውስጥ ስለሚኖረው ድባብ፣ ስለ ኬኩ ጥፍጥና፣ ኬኩ ስለተቀመመበት የስንዴ ዱቄት፣ ስንዴው ስለተፈጨበት ወፍጮ ቤት ሁሉ ሳይቀር እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር በተረከልን ነበር።
‹‹ንዳል›› በተሰኘው ግጥሙ ውስጥ  ሰለሞን ዴሬሳ፤
“ነኝ እንዳልል
የት መሆኔን አየሁኝ” እንዲል፣ የድርሰቱ ቁም ነገር ማጠንጠኛም ይሄው ነው። ልክ እና ስህተት ከማን አንፃር ይዳኛል? ቅለት እና ክብደት እንዴት ይፈረጃል።
በዚህ ድርሰት ውስጥም የሚታየው ይሄው ሀሳብ ነው። ጓደኛዋ ለምን አላገባሽም ለምን አልወለድሽም?... እያለች የመሴ ቀዌን መሳሳት እየነቀሰች ስትዘረዝር፤ መሴ ቀዌ እንዲህ ስትል ትመልሳለች፡-
“አሁን የገባኝ ነገር ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? ትክክልና ስህተት የሚባል ነገር የለም። … … እየውልሽ… ጓደኛዬ ሕይወት ማለት ወጣትነት ውስጥ ያለ ህልም ነው። ተኖረም አልተኖረም እሱ ሕይወት ነው። ሰዎች የዋሆች ናቸው፤ ሕይወት ማለት ደህና ሥራ መያዝ ፣ ልጅ ወልዶ መሳምና ልጅ መዳር ይመስላቸዋል። ያልተወለደ ስንት ፅንስ በሆድ አለ? አደባባይ ያልወጣ ስንት ትዳር በውስጥ አለ? ያልተኳለ ስንት ታሪክ አለ?” እያለች ትሞግታለች።
ሌላው ‹‹የባስሊቆስ እንባ›› በተሰኘው ድርሰት ውስጥ የምናገኛቸው የድርሰቱ ውበት በዘዬ ቃላት መሞላት ነው። በልቦለድ ውስጥ የዘዬ ቃላት በተገቢው ቦታ መገኘት የድርሰትን ጥራት ይጨምራል። ሌላው ደሞ ሲምቦል ማበጀት ነው። ‹‹እንጃኔ›› የሚለው ድርሰት ውስጥ የምናገኛቸው ሲምቦሎች ሌላኛው የድርሰቱ ውበት ናቸው።
ከብዙ መዳፈር ጋር የትዕግስት ታፈረ ሞላን ‹‹የባስሊቆስ ዕንባ›› አጭር ልቦለዶች መድበል እንዲህ አየሁት። አንብባችሁት ከሆነ ሀሳብ እንድንካፈልበት ብዬ እንዲህ ምልከታዬን ለመነሻ ያህል አቀረብኩ።
 ቸር ያቆየን።

Read 1602 times