Saturday, 23 November 2019 13:00

የብልጽግና ፓርቲ እየመጣልን አይደለም?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(2 votes)

 ሁለት ነገር ላስቀድም፡፡ የመጀመሪያው ኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶችን በአባልነት ያልተቀበለበትን ምክንያት በተመለከተ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ፤ አብዛኛው ሕዝባቸው አርብቶ አደር በመሆኑ ነው ማለታቸው ይጠቀሳል፡፡ እሳቸው አልበቃም ያሉት የአርብቶ አደር ሕዝብ፤ እንደ ዶክተር አብዱል መጅድ  ሁሴን አይነት ሰዎችን ማፍራቱን ደግሞ መካድ አይቻልም፡፡ የመገለላቸው ወይም የመገፋታቸው እውነተኛ ምክንያት ምን እንደሆነ የሕወሓት ሰዎች አንድ ቀን ይነግሩናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሁለተኛ ሕወሓቶች አዲስ የሚቋቋመው የብልጽግና ፓርቲ አካል እንደማይሆኑ አሳውቀዋል፡፡ ከሚያቀርቡት ምክንያት አንዱና ዋነኛው፤ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝሙን የሚያጠፋና አገርን ወደ አሃዳዊ አገዛዝ የሚገፋ ነው የሚል ነው:: የፓርቲው አገር አቀፍ መሆን ከፌደራል ሥርዓቱ ጋር የሚያገናኘው ነገር ያለመኖሩንና ሁለቱ የተለያዩ መሆናቸውን በመግለጽ አቶ መለስ የተናገሩትን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ደጋግሞ እያሰማ ነው፡፡ የአቶ መለስን ቃል እንደ ወንጌል ቃል ለሚያምነው ሕወሓት፤ በቂ መልስ ነው እላለሁ፡፡
የሚያብሰለስለው መሪነቱን መነጠቁ ከሆነ፣ መቀሌ ላይ ያሰባሰባቸውን ኅብረ ብሔራዊ ፌደራሊስቶችን አስተባብሮ አንድ ግንባር መመስረት፣ እሱን ይዞ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር መፎካከር ይችላል፤ ወይም ደግሞ ከውህደቱ ተነጥሎ ቆይቶ፣ ውህደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በግንባር ወይም በቅንጅት ለመሥራት መደራደር ይችላል፡፡ የአዲሱ ፓርቲ መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ 16 ንዑስ ቁጥር 11 ሠ “ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የሚያደርገው የውሕደት ወይም የቅንጅት ወይም በፕሬዚዳንቱ የተደረገ ስምምነት የውሳኔ ሃሳብ ያፀድቃል” በማለት የተከፈተው በር ለሌሎች ብቻ ሳይሆን ለእርሱ ጭምር መሆኑን ቢረዳ  ይበጃዋል፡፡     
የኢሕአዴግን መፍረስና ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እጁን ታጥቦ መውጣት ከሚፈልጉ ሰዎች አንዱ በመሆኔ፣ ኢሕአዴግ በብልጽግና ፓርቲ እንደሚተካ መወሰኑ  መልካም ነገር ነው፡፡ ነገሩ የምሥራች የሚሆነው ግን የጉልቻ መለዋወጥ እስካልሆነ ድረስ ብቻ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የአጋር ድርጅቶች ከፍተኛ አመራሮች በውሕደቱ ላይ ተስማምተዋል፡፡ የታችኛውን አካል ሰብስበው ጉባኤ አካሂደው ድርጅቶቻቸውን ማክሰም አለባቸው፡፡ ይሄን አስበውበት ይሆን?
ደርግ የአንድ ፓርቲ ሥርዓት ይከተል ነበር:: ስለዚህም በገጠር የገበሬ ማኅበር፣ በከተማ ቀበሌ፣ በመንግሥት መ/ቤቶችና ፋብሪካዎች የፓርቲው መሠረታዊ ድርጅቶች ተቋቁመው ነበር፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ባሉበት አካባቢ፣ ያለ አዛዥና ያለ ተቀናቃኝ የፈለጉትን የሚያስፈጽሙ ነበሩ፡፡ ይህ አሠራር በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች ተወርሶ ሲሠራበት መቆየቱ ድብቅ አይደለም፡፡
የአዲሱ ፓርቲ የመተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 15 በፊደል ሠ፤ “የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት በፌደራል አካላት፣ በውጭ አገራት፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎች የሚሠራ የፖለቲካ ድርጅት ሥራዎችን የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎችን ያደራጃል” በማለት የገለጸው ሃሳብ፤ ያን የቆየ ብልሹ አሠራር የሚያስቀጥል ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: ደርግ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥፋቱና ኢሕአዴግ በዚያው መቀጠሉ ሲታወስ የብልጽግና ፓርቲም በዚያው መንገድ ለመጓዝ መቋመጡን ያሳብቅበታል፡፡ “ወይ አለማፈር” ይሏል ይህንን ነው፡፡
ስለ ሥልጣን ገደብ በሚናገረው የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 44 ንኡስ ቁጥር 1፤ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የኃላፊነት ዘመንና ቆይታን የሚገድብ ዝርዝር መመሪያ የማዕከላዊ ኮሚቴ እንደሚያወጣ ያመለክታል፡፡ ለምን በደንቡ መወሰን አልተፈለገም ዋና ጥያቄ ነው፡፡ የመጀመሪያው መልስ አስገዳጅ እንዳይሆን ተፈልጓል፡፡ ሌላው ልምዱን ማስቀጠል ታስቧል ነው፡፡ አቶ መለስ ሞት ቀደማቸው እንጂ ከሃያ አራት ዓመት በላይ በኢሕአዴግ ሊቀ መንበርነት የቆዩት የሥልጣን ዘመንና ዙሩ ባለመገደቡ ነው፡፡
ከዚሁ አንቀጽ ጋር ተገናዝቦ መታየት ያለበት የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ አባላትና መደበኛ የስብሰባ ጊዜ ነው፡፡ መደበኛውን ጉባኤ በየአምስት ዓመቱ ለማድረግ ያሰበው የብልጽግና ፓርቲ፤ በየሁለት ዓመት ተኩል አስቸኳይ ጉባኤ እንደሚካሄድ ደንግጓል፡፡ ሁለት ዓመት ተኩል የጠበቃ ጉዳይ ምኑ ነው አስቸኳይ የማያደርገው?
ከሶስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ጀምሮ፣ በጠቅላላ ጉባኤው የሚገኙ አባላት 30% የሚሆኑት አዳዲስ ሰዎች እንደሚሆኑ ተመልክቷል፡፡ እነዚህ አዲስ ሰዎች እንዴት እንደሚመጡ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ምናልባት የላይኛው አካል ገምግሞ ወደ ታች የሚወረውራቸውና፣ ከታች ወደ ላይ የሚስባቸው እንደሚኖሩ መገመት አይከብድም:: ይኸ ደግሞ የበታች አካላትን ነፃነት የሚያሳጣ መሆኑ ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡
ፓርቲው በዚሁ የመተዳደሪያ ደንቡ ላይ አባላት በአስቸኳይ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እንዳለባቸው፣ ሆን ብለው ምልአተ ጉባኤ እንዳይሟላ ማድረግ እንደማይችሉ ደንግጓል:: በአንቀጽ 11 ንዑስ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ አባላት “በሀገራዊና አካባቢያዊ ምርጫ ወቅት የመራጭነት ካርድ ማውጣት” እንዳለባቸው አስቀምጧል፡፡ ይህ በእኔ እምነት የግለሰቡን መብት መጋፋት ነው፡፡
ፓርቲው በውስጠ ደንቡ ያላካተተው፣ በግልጽ አማርኛ፣ መከላከያ ያልሠራለት፣ በቤተ ዘመድ የሚሰባሰቡ የከፍተኛ አመራሮች ጉዳይን ነው፡፡ ነገሬን ልሰብስብ፡፡ ከመተዳደሪያ ደንቡ እንደተረዳሁት፤የብልጽግና ፓርቲ ከኢሕአዴግ ስህተቶች የተማረው ጥቂት ነው፡፡ አዲሱ ፓርቲ ለግለሰብ መብትና ነፃነት ዋጋ አይሰጥም፡፡ የመንግሥት ተቋማትን የፓርቲ ጉዳይ አስፈፃሚ ማድረግ ስህተት ሆኖ አይታየውም፡፡ ስለዚህም የተለወጠ የፓርቲ አስተሳሰብና አሠራር ለምንናፍቅ የእኔ ዓይነት ሰዎች፤ “የብልጽግና ፓርቲ እየመጣልን አይደለም” ብል ይቀለኛል፡፡ እየመጣብን ነው ለማለት አሁን ጊዜው ገና ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
***
ከአዘጋጁ፡- በጽሁፉ ውስጥ የተንጸባረቀው ሃሳብ ጸሃፊውን ብቻ የሚወክል መሆኑን እንገልጻለን፡፡

Read 10591 times