Print this page
Saturday, 23 November 2019 12:30

የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል…?

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)

    የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአገሪቱ ላይ የሚታየው ፖለቲካዊ ቀውስና አለመረጋጋት እንዲሰክንና ሰላም መረጋጋትና አንድነት በአገሪቱ ላይ እንዲሰፍን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት… በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ምሁራንን እየጋበዘ፣ በየወሩ ውይይት ለማድረግ ዕቅድ የነደፈ ሲሆን የመጀመሪያውን ውይይትም ‹‹የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል?›› በሚል ርዕስ ባለፈው ረቡዕ ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ፒያሳ በሚገኘው ግራንድ ኤሊያና ሆቴል ለግማሽ ቀን አካሂዷል፡፡
የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ካሣው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ስነ ልቦና ፕሮፌሰር ሀብታሙ ወንድማገኝ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ፕሮፌሰር ጥሩ ሰው ተፈራና ዶ/ር ጠና ነጋዎ ‹‹የአገር ግንባታ ከየት ይጀምራል?›› በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለውይይቱ መነሻ የሚሆን ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
አባቶች ዘመን ያፈራው ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ጊዜ የነበራቸውን አዕምሯዊ መረዳትና አካላዊ ብቃት ተጠቅመው፣ አገር አቁመውና ጠብቀው የማቆየታቸው ምስጢር ወደ አሁኑ ትውልድ እንዴት ይሻገር፣ የአሁኑ ትውልድስ ለረጅም ጊዜ በውጣ ውረድ ውስጥ ተሰርታ የቆየችን አገር አንድነቷንና ሰላሟን ጠብቆ ለማስቀጠል ምን ያህል አቅሙ፣ ችሎታው፣ ፍላጎቱና ጥረቱ አለው? አገሬን መገንባት እችላለሁ ካለስ ከየት ነው መጀመር ያለበት?... በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል በውይይቱ፡፡ በውይይቱ ላይ ከተነሱ ሃሳቦችና አስተያየቶች ጥቂቶቹን ከዚህ በታች አቅርበናል፡፡


                       “ወላጁን የማያከብር አስተማሪዎቹን አያከብርም”
                         የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት፣ ተ ቀዳሚ ሙፍቲ ኡመር እድሪስ

          እኔ ባደጉበት አካባቢና ቤተሰብ ውስጥ  ታላቅ እህትና ታላቅ ወንድም፣ እንደ እናትና አባት ይከበሩ ነበር፡፡ ወላጆች ሲመገቡ ልጆች ቆመው የሚያበሉ ሲሆን፤ ለዚህም የወላጆች ትልቁ ምስጋናና ስጦታ፣ ጉርሻ ነበር፡፡ በልጅነቴ አባትና እናትም ሆነ እንግዳ ሲመጣ፣ ከመቀመጫችን ብድግ ብለን ነበር የምንቀበለው፡፡
ወላጁን የማያከብር ልጅ አስተማሪዎቹን አያከብርም፤ አስተማሪዎቹን የማያከብር ልጅ መሪዎቹንም አገሩንም አያከብርም፡፡ ስለዚህ ወላጅ ከስር መሰረቱ ልጆቹን ገርቶ፣ አሰልጥኖና ጥሩ መስመር አስይዞ ለት/ቤት ማስረከብ አለበት:: ይህንን የቤት ሥራ ቤተሰብ በአትኩሮት ንኦት መስራት ይገባዋል፤ ይህ ካልሆነ ጥሩ ትውልድም ሆነ አገር ልንገነባ አንችልም፡፡
________________________

                  “ህፃናት ግብረገብነት መማር አለባቸው”
                       በምሥራቅ ሀረርጌ ሀገረ ስብከት የመጡ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት አባት


           መምህራን ከቤተሰብ የተረከቡትን ልጅ ሥነ ሥርዓት በተሞላበት መልኩ ማስተማር አለባቸው፡፡ ሱሪውን ዝቅ አድርጎ የሚሄድ አስተማሪ፣ ለተማሪዎቹ እንዴት ያለ ስነ ምግባር ያስተምራል? ቤተሰብም ሆኑ መምህራን ትውልድን ለመገንባት ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ መንግስትም ግብረ ገብነትን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት ይገባዋል፡፡
ሕጻናት ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ግብረገብነትን መማር አለባቸው፡፡ ቀደም ሲል ይህ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ለዚህ ሁሉ ችግርና ቀውስ አንጋለጥም ነበር፡፡ ከዚህ በኋላም አንድም ሰው እንዲሞት፣ እንዲቆስል፣ ንብረት እንዲወድምም ሆነ መንገድ እንዲዘጋ አንፈልግም፡፡ ወጣቶች ከክፉ ድርጊት ታቀቡ፣ ወላጆች ልጆቻችሁን ምከሩ፤ መንግስትም የሕግ የበላይነትን አስከብር፡፡

______________________

                          “ብዙሃኑ ጥቂቶቹን ለምን ማሸነፍ አቃታቸው?”
                               የዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስም

            የዚህ አገር ትንሳኤም ሆነ ሞት በወጣቱ ትከሻና እጅ ላይ የተመሰረተ ነው ትላላችሁ፤ እንዲያ ከሆነ ወጣቱ ላይ ትኩረት አድርጎ ይሰራ የነበረው የወጣቶች ሚኒስቴር ለምን ፈረሰ? ቀውሱን የሚፈጥሩት ጥቂቶች ናቸው፤ ብዙሃኑ ጥቂቶቹን እንዴት ማሸነፍ አቃታቸው? የሚልም ነገር ይነሳል፡፡ እነዚህ ጥቂቶች በቁጥር ብቻ መለካት አለባቸው ወይ? ጥቂት ናቸው እያልን ራሳችንን ከምናጽናና እና ከምናታልል ከጥቂቶቹ ጀርባ ያለውን አቅም… ለምን አናጠናም? ብዙኃኑን ማንቀጥቀጥና አገር ማነቃነቅ የቻሉት ምን አቅም ሆኗቸው ነው… የሚለውን መፈተሽና ማወቅ የለብንም ወይ?! በዚህ አገር ላይ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት፣ የሌሎችን ስህተት ላለመድገም መጠንቀቅ ያስፈልጋል:: ባለፈው ስርዓት የተጠሉትን ነገሮች “ለውጥ አምጪ ነን” ባዮች ሲደግሙት ማየት በእጅጉ ያስከፋል - ያማልም፡፡ በዚህ ሁኔታ መቼም መረጋጋትንና ዘላቂ ሰላምን መፈለግ የዋህነት ነው፤ ይሄ ነገር በደንብ ሊታሰብበት ይገባልም፡፡

_____________________

                         ወጣቱን የሁሉም ነገር ተጠያቂ እናደርጋለን
                            ሃና ሀይሉ የወጣቶች የሕይወት ክህሎት አሰልጣኝ

          እኛም እንደ ማህበረሰብ ችግር አለብን፤ ነገር ግን ወጣት ቆሻሻ ሲያቃጥል፣ መንገድ ሲጠርግ ማድነቅና ማበረታታት ቀርቶ ዞር ብለን አናየውም፡፡ ቆሻሻ ከሚያቃጥለው ይልቅ ጎማና ንብረት ለሚያቃጥለው፣ መንገድ ከሚጠርገው ይልቅ መንገድ ለሚዘጋው፣ አካባቢ ከሚያለማው ይልቅ አካባቢና ንብረት ለሚያወድመው ትኩረት ሰጥተን በመንግስትም በሚዲያም እናወራለን፡፡ ታዲያ ጥሩ የሚሰራውን ሳናደንቅና ሳናበረታታ መልካም ትውልድ ከየት እናመጣለን? አንድ ወጣት ጥሩ ዜጋ የሚሆነው መድረሻውን ሲያውቅና ግብ ሲያስቀምጥ ነው፡፡
እኔ ዩኒቨርሲቲ በነበርኩበት ጊዜ… ብዙ ወደ ጥፋት የሚወስዱ፣ ክፉ ተግባር ያላቸው ተማሪዎች በዙሪያዬ ነበሩ፡፡ ነገር ግን አላማና ግቤን እንዲሁም መድረሻዬንም ስለማውቅ፣ ከክፉ ነገር ተጠብቄ፣ ጥሩውን መንገድ መርጬ እዚህ ደርሻለሁ፡፡

_________________________

                     ሕዝቡን እርስ በእርስ የሚያጋጨው ሌላ ምክንያት የለም
                       አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው

           ከምንም በላይ ለዚህች አገርና ትውልድ እርቅና ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሊኖሩባትና ከህልማቸው ሊገናኙባት የማይችሉባትን አገር ሰጥተን ከልጆቻችን ተጣልተናል፣ ከታሪካችን፣ ከትላንትና ከትላንት ወዲያ መሪዎቻችን፣ ከራሳችን ከምንም በላይ ደግሞ ከፈጣሪያችን ተጣልተናል፡፡›
ለዚህ ሁሉ ጠብ ዘርፈ ብዙ እርቅ ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ረገድ የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የሚመለከተው ሁሉ መስራት ይጠበቅበታል፡፡ በአገሪቱ ላይ ችግር እየፈጠሩ ያሉት በራሳቸው መተማመን ያቃታቸውና በስነ ልቦና ቀውስ ውስጥ የሚሰቃዩ ጽንፈኛ ብሔርተኞች እንጂ፡፡

Read 2228 times