Saturday, 23 June 2012 07:38

ዳሸን ቢራ በደብረ ብርሃን ከተማ አዲስ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

የዛሬ ሳምንት በደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ፊት ላይ ከወትሮው የተለየ የደስታ ስሜት ይነበብ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ኩባንያ ሸሪኩ ከሆነው ዱዌት ግሩፕ ጋር በመሆን በከተማዋ የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጡ ነበር፡፡የመሠረት ድንጋዩን ያስቀመጡት የዕለቱ የክብር እንግዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትርና የ”ጥረት” ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በረከት ስምኦን ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር የመሠረት ድንጋዩን ካኖሩ በኋላ ንግግር አድርገው ነበር፡፡

ይህ ፋብሪካ በደብረብርሃን ከተማ እንዲቋቋም የተደረገው በአጋጣሚ አይደለም፡ በአማራ ክልል ሰፋፊ ኢንቨስትመንቶችን የሚያካሂደው “ጥረት”፤ በክልላችን በሁሉም አካባቢ የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ የክልላችን መንግሥት አቅጣጫም በዞኖች መካከል የተመጣጠነ የኢንዱስትሪ ስምሪትና የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ አካባቢው ደጋማና ገብስ አምራች በመሆኑ ወደፊት የቢራ ገብስ ፋብሪካ ሊገነባ ይችላል፡፡ ስለዚህ፣ የሕዝብ ተጠቃሚነት እንዲኖርና በአካባቢው ለውጥ መፍጠር ስለተፈለገ፣ በታሪካዊቷ የደብረ ብርሃን ከተማ ይህን የመሰለ ዘመናዊ ፋብሪካ እንዲቋቋም ተደርጓል” ሲሉ የከተማ ነዋሪዎች ደስታና ጭብጨባ የተለየ ነበር፡፡

ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር በአማራ ክልል በኢንቨስትመንት ዘርፍ በእርሻ፣ በማኒፋክቸሪንግና በአገልግሎት (በትራንስፖርትና በንግድ) የሚንቀሳቀሰው ጥረት ኮርፖሬት፤ ከሚመራቸው ድርጅቶች አንዱ መሆኑን አቶ ታደለ ካሣ የ”ጥረት” ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገልጸዋል፡፡

አቶ ታደሰ በአገራችን የቢራ ገበያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው የአገራችን መካከለኛ መደብ እየጨመረ ሲሄድ የቢራ ተጠቃሚውም ቁጥር በዚያው መጠን ይጨምራል ብለዋል፡፡ ተወዳጅና ተመራጭ የሆነውን ዳሸን ቢራችንን ይበልጥ ማስፋት እንዳለብን አምነን፣ ከዓመት በፊት እንቅስቃሴ ጀመርን ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ሜታ ቢራ ፋብሪካን ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በመሆን ለመግዛት ተወዳድረው እንዳልተሳካላቸው ተናግረዋል፡፡ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮችን በመፈለግ መቀመጫው እንግሊዝ ከሆነው ዱዌት አሴት ማኔጅመንት ግሩፕ ጋር ለአንድ ዓመት ውይይት ሲያደርጉ ቆይተው፣ በአብዛኛው በመስማማታቸው ዱዌት ግሩፕ በ90 ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ድርሻ ገዝቶ ዳሽን ቢራ ደግሞ እስካሁን ያለውን ፋብሪካ በአክሲዮንነት ይዞ፣ በአጠቃላይ በ180 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ዳሸን ኃ.የተ.የግ.ማ ፈርሶ፣ ዳሸን አክሲዮን ማኅበር ባለፈው ሳምንት መቋቋሙንና እንዲያድግ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚሰራው ፋብሪካ ከ45-50 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል እንደሚፈጅ ተገልጿል፡፡በዚሁ መሠረት የጐንደሩ ዳሸን ፋብሪካ ከ1.2 - 1.5 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር የማምረት አቅም እንዲኖረው ይደረጋል፡ በደብረ ብርሃን የሚገነባው ፋብሪካ ደግሞ ከ1-3 ሚሊዮን ሄክቶሊትር ቢራ የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን የድርጅቱን አጠቃላይ የማምረት አቅም 4.2 ሚሊዮን ሄክቶ ሊትር የሚያደርስ በመሆኑ የአገሪቱን የቢራ አቅርቦት ድርሻ ከ30-40 በመቶ መሸፈን ያስችለዋል ብለዋል፡ አቶ ደምሴ በኢትዮጵያ የዱዌት ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የዳሸን ቢራ አ.ማ የቦርድ አባል ሲሆኑ ከዳሽን ቢራ አ.ማ ጋር በሽርክና በመሥራታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ ድርጅታቸው በኢንቨስትመንት የሚያንቀሳቅሰውና የሚመራው ገንዘብ የተሰበሰበ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደምሴ፤ ዓላማውም የጡረተኞቹን ካፒታል ማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዜግነት እንግሊዛዊ በትውልድ ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ የጠቀሱት አቶ ደምሴ፤ በደብረ ብርሃን ብቻ ሳይሆን በመላ አገሪቱ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ማቀዳቸውን በዱዌት በኩል ደግሞ በዓመት ቢያንስ እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው እንዲሁም እውነተኛና ትክክለኛ ሸሪክ ካገኙ ካፒታሉ ከዚህም ሊበልጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ዱዌት ግሩፕ በኒውዮርክ፣ በኒውዴልሂ፣ በዱባይ፣ በቶኪዮና አሁን ደግሞ በአዲስ አበባ ኢንቨስት እያደረገ ሲሆን 3 ቢሊዮን ዶላር ካፒታል እንደሚያስተዳድር ታውቋል፡፡ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ በ325.12 ሚ. ብርና በ8.5 ሄክታር መሬት ላይ በ1992 ዓ.ም በጐንደር ከተማ አባ ሳሙኤል የተመሠረተ ሲሆን በወቅቱ የማምረት አቅሙ 300ሺህ ሄክቶ ሊትር እንደነበር የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ አቶ መክብብ ዓለሙ ገልጸዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ በ94.2 ሚ.ብር በተደረገለት ማስፋፊያ በአሁኑ ወቅት 769ሺ ሄክቶ ሊትር ቢራ እያመረተ መሆኑን አቶ መክብብ ተናግረዋል፡፡

 

 

 

Read 18162 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 11:05