Saturday, 23 November 2019 12:23

የፖለቲካ ሱናሜ በጦቢያ!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(6 votes)

    በዘርና በጥላቻ የተወጠሩት ልሂቃንና ጦሳቸው!
   
             ወዳጆቼ፤ ምንም ነገር ከመስመር ሲወጣ…ቅጥ አምባሩ ሲጠፋ…አይገመቴ ሲሆን (Unpredictable እንዲሉ!) ያኔ ፍሩልኝ፡፡ አዎ ፍሩልኝ!! እንደ ዘንድሮው ፖለቲካችን!! ለነገሩ የጦቢያ ፖለቲካ መቼም ቢሆን አምሮበትና ጤና ሆኖ አያውቅም፡፡ በ60ዎቹ አብዮት፣ አንድ ትውልድ እምሽክ አድርጎ የበላው እኮ የተፈጥሮ አደጋ አይደለም፡፡ ኋላቀር የመበላላት ፖለቲካችን ነው! ፈረንጆቹ “Politics is a dirty game” የሚሉት በትክክል በእኛ አገር ሰርቷል፡፡ በእርግጥም ፖለቲካችን ቆሻሻ ነው፡፡ በእርግጥም ፖለቲካችን አውሬ ነው፡፡ በእርግጥም ፖለቲካችን ስግብግብ ነው፡፡ ይሄን የምንለው - ከታሪክ አንብበን ወይም በወሬ ሰምተን አይደለም፡፡ ኖረን ያየነው … አሁንም እያየነው ያለ ነው፡፡ (Live በሉት!)
የመዘመንና የመሰልጠን ምልክት ያሳየበት ጊዜ እንኳን የለም፡፡ ሁሌም ወደ ኋላ ነው የሚሄደው፡፡ እንደ ዘንድሮ ግን የኋሊዮሽ ብዙ እርምጃዎች ተራምዶ አያውቅም፡፡ ወደ ጥንት ኋላ ቀርነት በእጅጉ ተጉዞ  ዘረኝነት ላይ ተንጠላጥሏል፡፡ የፖለቲካ ጨለማ ውስጥ ዱሎናል፡፡ ወዳጆቼ፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እስከ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጐች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉት (ለሞትና ለአካል ጉዳት ጭምር የተዳረጉትም!) በጐርፍ… በሱናሜ ወይም በመሬት መንቀጥቀጥ … አይደለም፡፡ በፖለቲካ ሱናሜ ነው! በቂምና በጥላቻ በምንፈትለውና በምንሸምነው ኋላቀር ፖለቲካችን ነው!! ዜጐች ከገዛ አገራቸው… በገዛ ወንድማቸው የሚፈናቀሉት… በሌላ አይደለም - በጥላቻ ፖለቲካ ነው - ለልሂቃኖቻችን ምስጋና ይግባቸውና!!  
እኔ የምለው… በየጊዜው በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ የሚጐርፈውን የጦር መሣሪያ ዓይነትና ብዛት ታዝባችሁልኛል? (ስናይፐር ሁሉ አልቀረም እኮ!  ያውም በባሌ ሳይሆን በቦሌ፤ በምድር ሳይሆን በአየር!) ይሄኔ ነው “ደፍረውናል!” ማለት ነው! እስካሁን በፖሊስ መያዙ በይፋ የተነገረን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ብዛት እኮ ግማሽ የጦቢያን ህዝብ በደንብ  ያስታጥቃል፡፡ (ኮንትሮባንዲስቶቹ ግን ሊያስታጥቁን ሳይሆን ሊያጨራርሱን እንደሆነ አልጠፋኝም!) የአገሬን ልሂቃን መች አጣኋቸው! ቆይ ግን እነዚህ የክላሺንኮቭና የጥይት ኮንትሮባንዲስቶች መቼ ነው መሳሪያ ማጋዝ የሚበቃቸው? 100 ሚሊዮን ሕዝብ ሊያስታጥቁ እንዳይሆን ብቻ!
ይሄ መቼም ተራ የኮንትሮባንድ ንግድ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ወደ አገር ውስጥ እየገባ እንደ ሸቁጥ በችርቻሮ የሚሸጥ ዓይነትም አይደለም፡፡ (በገፍ ነዋ የሚገባው!) በገፍ የገባ … በገፍ ይታደላል ማለት ነው!  (አንድዬ ይሁነን!) በጥላቻ ፖለቲካ የምንጨራረሰው አንሶን---ክላሺንኮቭና ስናይፐር ስንጨምርበት ለወሬም የምንተርፍ አይመስለኝም፡፡ እናላችሁ…ፖሊስ ከዚህ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ጋር በተያያዘ የደረሰበት መረጃ ካለ…ቢያሳውቀን መልካም ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡
እስቲ አስቡት… የጦር መሳሪያ በገፍ አስገብተው የሚያስታጥቁና እርስ በርስ ሊያጫርሱን የወጠኑ ቡድኖች.. ፓርቲዎች… ታጋዮች… የከሰሩ ፖለቲከኞች ወዘተ እንዳሉ ብንሰማስ? (ባይኖሩማ ይሄ ሁሉ ነፍጥ ወደ ጦቢያ አይጎርፍም ነበር?!) ግዴለም እንወቃቸው… ሊጨርሱንና ሊያጨራርሱን ያቀዱትን ወገኖቻችንን! (ጠላት የለንም ብዬ እኮ ነው!)
እናላችሁ… ድሮ (በቀድሞው የኢህአዴግ ዘመን ማለቴ ነው!) እንዲህ በገፍ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ወደ አገር ውስጥ ሲገባ ሰምተን አናውቅም (ወይስ ኢህአዴግ ነፍሴ ሲደብቀን ኖሯል?) መቼም እንዳሁኑ የኮንትሮባንድ መሳሪያ ቢጐርፍማ ኖሮ፣ ውጤቱን እናየው ነበር፡፡ ለነገሩ ጦቢያ አሉኝ የምትላቸወ ነፍጥ ታጣቂ  ታጋዮች (የትላንቶቹ “አሸባሪዎች”!) ተጠራርተው አገር ቤት ከከተሙ በኋላ (አንዳንዶቹ ጦራቸውን ሳይፈቱ ነው!) ከዚህ ውጭ ምን እንጠብቅ ኖሯል?!  
ወዳጆቼ፤ እስቲ የሆድ የሆዳችንን እናውጋ (የሆድን ማውጋት እኮ ቀርቷል!) እናላችሁ… በኮንትሮባንድ ይገባል ከሚባለው ህገወጥ የጦር መሳሪያ እኩል፣ የጐን ስጋትና ውጋት የሆነብን ምን መሰላችሁ? የጦቢያ ልሂቃን (ድንቄም ልሂቃን!)  አክራሪ ብሔርተኛ አክቲቪስቶች! ፅንፈኛ ሚዲያዎች! አዎ-- እነሱ የሚረጩት የጥላቻ ቫይረስ ከነፍጥ በላይ እያጨራረሰን ነው፡፡ (አንድዬ ይታረቀን እንጂ!!)
ወዳጆቼ፤ በዚህ የፖለቲካ ሱናሜ ዘመን፤ አለመጨነቅና አለመስጋት አይቻልም፡፡ እናም ጭንቀትና ስጋት የወለደው አጭር ፕሮፖዛል ለማርቀቅ ተገድጃለሁ፡፡ “የፖለቲካ ቀይ መስመር” የሚል፡፡ ይሄ በዘርና በጥላቻ ተፈትሎ የተሸመነ፣ የደም ግብር የለመደ … ክፉ ፖለቲካችን… እርስ በርስ አባልቶን ከመተላለቃችን በፊት አንዳች መላ መዘየድ… አንዳች መፍትሔ ማፈላለግ ያባት ነው፡፡ (“መንግሥት የህግ የበላይነትን ያስከብር” የምንል ሰዎች… ከኃላፊነታችን እየሸሸን እንዳይሆን ስጋት አለኝ!!)
ወዳጆቼ፤ህግ ማስከበር የመንግስት ሥራ መሆኑን እኛም… (ተራ ተርታ ዜጎች!) መንግስትም… አክቲቪስቶችም---ፅንፈኛ ብሔርተኞችም (ልሂቃንም)… ጠንቅቀን እናውቃለን፡፡ ግን ደግሞ ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ መዘንጋት የለብንም፡፡ ቀውስ… ረብሻ… ሁከት… ግድያ… መፈናቀል… ስጋት… ፍርሃት… ሽብር የነገሰበት ዘመን ላይ ነን፡፡ የጥላቻ ቫይረስ እየተዘራብን ነው፡፡ እኛም ከሥር ከሥሩ ፍሬውን እያጨድን ነው፡፡  ዘረኝነትን… ጥላቻን… ጠባብነትን… ቂምና በቀልን የዘራ ፍቅርና በረከት አያጭድም፡፡ ዕድሜ ለጽንፈኛ ልሂቃኖቻችን! ዕድሜ ለፅንፈኛ አክቲቪስቶቻችን! ዕድሜ ለዘረኛ ፖለቲከኞቻችን! ከአንደበታቸው የጥላቻና የክፍፍል እሳት እየተፉ…አነደዱን፡፡ ተቃጥለን ከማለቃችን በፊት ግን አንድ መላ መዘየድ አለብን፡፡ ከእልቂት ለመትረፍ! ከጥላቻ እልቂት!
 አትታዘቡኝና… አንዳንዴ ምን አስባለሁ መሰላችሁ? ለተወሰነ ጊዜ ከፖለቲካ የመታቀብ አዋጅ ቢታወጅ እላለሁ፡፡ ለ6 ወር ወይም ለዓመት… ከፖለቲካ ብንታቀብ! አገራዊ “የፖለቲካ ፆም” ቢታወጅ! (ትንሽ እፎይ እንድንል እኮ ነው!) ነፃነቱንማ በደንብ አየነው! ተንፈላሰስንበት፡፡
የለውጡን ሃይል ክሰሰው ብትሉኝ -- ምን እንደምል ታውቃላችሁ? “ሳታለማምደን የነፃነት ባህር ውስጥ ዘፍቀህ ልንሰምጥ ነው!” በነገራችን  ላይ የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መንግስት የሚከሰሰው በሌላ ሳይሆን ምድራዊ ባልሆነ ትዕግስቱና ገደብ የለሽ ነፃነቱ ነው፡፡ (ከአፈና ወደ ነፃነት ተዘሎ ይገባል እንዴ?!) ለካስ ትዕግስትና ነፃነትም ያንገሸግሻል!
ወዳጆቼ፤ ቅጥ አምባሩን ያጣውና በጥላቻ የጨቀየው ፖለቲካችን እርስ በርስ አጫርሶንና አገር አሳጥቶን ሰው አገር ከመሰደዳችን በፊት (የስደት አገርም ላይገኝ ይችላል!) ወደ ህሊናችን መመለስ ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ (እንደዘገየን ግን ልብ በሉ!) በእርስ በርስ ጦርነት አገር አልባ ሆነው… በስደት አገራችን የመጡትንና በአዲስ አበባ አውራ ጐዳናዎች የሚለምኑትን የሶርያ ተወላጆች--- በዓይናችን በብሌኑ እያየን እንኳን ከጥፋት አልተመለስንም፡፡ - በጥላቻ ጨለማ ውስጥ እየዳከርን ነው!! (እናሳዝናለን!)
ለማንኛውም ጭንቀት የወለደውን ፕሮፖዛሌን እነሆ፡- መንግስት በፍጥነት ካልተጠቀመበት ግን ጊዜ ያልፍበታል፡፡  

 የፖለቲካ ቀይ መስመሮች
(ጭንቀትና ብሶት የወለዳቸው)
*በማንኛውም የአገሪቱ ክፍል ለተቃውሞም ሆነ ለድጋፍ መውጣት መብት መሆኑ በህገመንግስቱ ተደንግጓል፡፡ ይሄ መብት በዘላቂነት ተጠብቆ እንዲዘልቅና ገደብ እንዳይጣልበት ለትግበራ የሚያመች መመሪያ ወይም ደንብ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዚህም መሰረት፤በሰላማዊ ሰልፍ ላይ ማንኛውም ተሳታፊ፣ ከሞባይል በቀር ምንም ዓይነት መሳሪያ፡- ዱላ፣ገጀራ፣ፌሮ፣ አካፋና ሌሎች የቁፋሮ መሣሪያዎችን ይዞ መውጣት አይፈቀድም፡፡ (ባህልን እንደ ሰበብ ማቅረብ ተቀባይነት የለውም) ለነገሩ ሰላማዊ ሰልፍ ከምዕራብ አገራት ከኮረጅናቸው ሃሳብን በሰላም የመግለጫ ሥልጡን መንገዶች አንዱ ነው፡፡
*ፖለቲከኞች፣ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ አክቲቪስቶች፣ ልሂቃን፣ ጋዜጠኞች ወዘተ- ከ20 ዓመት በላይ ወደ ኋላ በመጓዝ፣ በሌሉ መንግስታት፣ ሥርዓት፣ ነገስታት ወዘተ-- ላይ ማስረጃ ያለውም ሆነ የሌለው ክስና ወንጀል ማቅረብ ሆነ መተረክ በጥብቅ የተከለከለ ነው፡፡ ተከሳሹ በህይወት በሌለበት ሁኔታ ክስ መቅረቡ ምን ይፈይዳል? በአንድ ዘመን፣በአንድ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የተፈጸመን ግፍና በደል ለማጋለጥና ጥፋቱ እንዳይደገም በማስተማርያነት ለመጠቀም ከሆነም፣ ይሄ መሆን ያለበት በታሪክ ክፍለ ጊዜ፣የጥናትና ምርምር ሥራዎች በሚቀርብበት አዳራሽ እንጂ በፖለቲከኞች የምርጫ ቅስቀሳና  ፕሮፓጋንዳ ላይ ፈጽሞ መሆን የለበትም፡፡ (ታሪክን መጻፍም ሆነ መተረክ የፖለቲከኞች ሳይሆን የታሪክ ባለሙያዎች ነው፡፡)
*አንድን ወይም ሌላን የህብረተሰብ ክፍል በጅምላ የሚፈርጅ ስያሜ መጠቀም፣ ቁጣን ቁጭትንና ጥላቻን የሚቀሰቅስ የበደልና ጭቆና ታሪክ በማስታወስ ለግጭት ማነሳሳት ፈጽሞ የተከለከለ ቀይ መስመር ነው፡፡ የሚቀንሰው፣ የሚጎዳው፣ የሚያጠፋው እንጂ የሚጨምረው፣ የሚደምረው፣ የሚያለመው ምንም ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ፡- ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብና መሰል አሉታዊ ትርጉም ያላቸው ስያሜዎችን መጠቀም በህግ የተከለከለ ነው፡፡   
ወዳጆቼ፤ የፖለቲካ ቀይ መስመሮች በሚል የተቀመጡት ክልከላዎች ወይም ገደቦች፤ የጦቢያን አክቲቪስቶች፣ ጽንፈኛ ፖለቲከኞች፣አክራሪ ልሂቃን ወዘተ-- ሊያስቆጣ እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ ቢቆጡም ግን አይፈረድባቸውም፡፡ ፍረጃ፣ ጥላቻ፣ ክስና ወንጀል ብቻ የለመዱ ሰዎች ይሄንን ብቸኛ ሱሳቸውን ሲነጥቋቸው መቆጣት ብቻ ሳይሆን ኤሌክትሪክ ሁሉ ሊጨብጡ ይችላሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች የጥላቻ ፖለቲካ ሰለባ ከሚሆኑ እነዚህ ጥቂት የፖለቲካ ተዋናዮች ቢቆጡና ቢያኮርፉ ይመረጣል፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ቀይ መስመር ወደሚመለከተው ክፍል የሚመራው የህዝብ ድምጸ ውሳኔ ከተደረገ በኋላ መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡    

Read 4157 times