Saturday, 23 November 2019 12:00

የልፋትን ዋጋ ከፋይ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን፣ ግልገል ጢቾ ወረዳ፣ ኩንዴ ሮጌ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ ለሆኑት የ58 ዓመቷ ወ/ሮ ንጋቷ ብሩ፤ ኑሮ እንደ መርግ የከበደ፣ እንደ እሬት የመረረ ነበር፡፡ ከአርሶ አደር ባለቤታቸው የወለዷቸውን ሦስት ልጆች ለማሳደግና ኑሮን ለማሸነፍ ሌት ተቀን ቢባትሉም፣ ኑሮአቸው ከእጅ ወደ አፍ ሆኖ ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ይህንን ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ለመለወጥ የሚያስችልና የልፋታቸውን ያህል ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ ያገኙት ግን ከዛሬ 5 ዓመት በፊት ለቢራ ምርት ግብአት ፍለጋ ወደ አካባቢያቸው የመጣውን ሄይኒከን ኢትዮጵያን ባገኙ ጊዜ ነው፡፡
ድርጅቱ ለቢራ ምርት ወሳኝ ግብአት የሆነውን የገብስ ምርት ከውጪ ከማስገባት ይልቅ በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ገብስ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ የቢራ ገብስ ምርጥ ዘርንና የእርሻ ግብአቶችን ይዞ ወደ ሥፍራው ዘለቀ፡፡ በወቅቱ እንደ ወይዘሮ ንጋቷ ሁሉ የአካባቢው በርካታ አርሶ አደሮች ለዓመታት ብዙ ደክመው ጥቂት በሚያገኙበት የእርሻ ሥራ በእጅጉ ተማረው ነበር፡፡ ከወራት ድካም በኋላ በሚያገኙት ጥቂት ምርት ኑሮአቸውን ማሻሻል  ተስኗቸው ለውጥ የሌለው ህይወትን ሲገፉ የኖሩት እኒህ አርሶ አደሮች በባለሙያና በምርጥ ዘር ታግዘው የቢራ ገብስን ማምረት ጀመሩ፡፡ ከእነዚህ አርሶ አደሮች መካከልም 3 ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጉት ወ/ሮ ንጋቷ ብሩ አንዷ ነበሩ፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ኤክታር ተኩል  መሬት ላይ እያረሱ የሚያገኙት ከሃያ ኩንታል ያልበለጠ አመታዊ ምርት፣ የቢራ ገብስን ማምረት ከጀመሩ በኋላ በሶስትና በአራት እጥፍ አድጐ ገቢያቸው ከፍ ማለት ሲጀምር፣ ተስፋቸው በዚያው መጠን እየለመለመ ሄደ:: ልጆቻቸውን በስርዓት ማሳደግና ማስተማር ጀመሩ፡፡ ወ/ሮ ንጋቷ እንደሚሉት ላለፉት 40 እና 30 ዓመታት በእርሻ መሬታቸው ላይ እየለፉ ከሚያገኙት አመታዊ ገቢ ይልቅ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የቢራ ገብስን በማምረት የሚያገኙት ገቢ በእጅጉ ልቋል፡፡ በማሳቸው ላይ የሚያመርቱትን የቢራ ገብስ በኩንታል 1680 ብር ሂሳብ በአካባቢያቸው ለሚገኘውና ከአርሶ አደሮቹ ላይ የቢራ ገብሱን እየገዛ ለሄይኒከን ቢራ ፋብሪካ ለሚያቀርበው አርሶ አደር ሹሜ ለገሰ ይሸጣሉ፡፡
ወ/ሮ ንጋቷ ዓመታዊ ምርታቸውን ለማሳደግም የተለያዩ ስልጠናዎች በባለሙያዎች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምርጥ ዘር፣ ፀረ-አረም መድኃኒቶችና ማዳበሪያዎችንም ያገኛሉ፡፡ ለወደፊቱም አቅማቸው በፈቀደ መጠን ተግተው ለመስራትና የተሻሉ ምርቶችን በማምረት፣ ገቢያቸውን ለማሳደግ መነሳታቸውን ነግረውኛል  -  ሴት አርሶ አደሯ ወ/ሮ ንጋቷ ብሩ፡፡
በአርሲ ዞን ባሉ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን በስሩ አሰባስቦ የቢራ ገብስ እንዲያመርቱ በማድረግ፣ ምርታቸውን እየገዛ ለሄይኒከን ኢትዮጵያ የሚያቀርበው አቶ ሹሜ ለገሰም፤ የአካባቢው አርሶ አደሮችን በማበረታታት፣ የተሻለ ምርት አምርተው የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ለማድረግ ጠንክሮ ይሰራል፡፡
አቶ ሹሜ አሁን ከ380 በላይ አርሶ አደሮችን በስሩ ይዞ የቢራ ገብስን በስፋት እያመረቱ የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 17ሺ ኩንታል የሚጠጋ የቢራ ገብስን ለሄይንከን ኢትዮጵያ ያቀርባል:: በዚህም እሱም ሆነ በአካባቢው ያሉ የቢራ ገብስ አብቃይ አርሶአደሮች ህይወት በእጅጉ እንደተለወጠ ይናገራል፡፡ ይህ ሁኔታም ቀጣይነት የሚኖረው የተመረተውን የቢራ ገብስ በአግባቡ የሚረከብ ድርጅት ሲኖር መሆኑንና ለዚህም አይኒከን ኢትዮጵያ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ በእጅጉ የሚመሰገን እንደሆነ ገልጿል፡፡
የሄይኒከን ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሚስተር ዩጂን ባልዤሮ እንደሚናገሩትም፤ ኢትዮጵያ ጥራት ያለው የቢራ ገብስ ለማምረት ምቹ የአየር ጠባይና የተመቸ የአፈር አይነት ያላት አገር በመሆኗ የቢራ ገብስን በብዛትና በጥራት ለማምረት የሚያስችል አቅም ካላቸው አገራት መካከል ዋንኛዋ ናት፡፡
አርሶ አደሮቹም የቢራ ገብስን በብዛትና በጥራት በማምረት ህይወታቸውን በተሻለ ሁኔታ ለመቀየር የሚችሉበት ዕድል አላቸው:: ሄይኒከን ኢትዮጵያ፣ የቢራ ገብስ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ከሚኖሩ 300 ያህል አርሶ አደሮች ጋር አብሮ መስራት መጀመሩን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአርሶ አደሩን ቁጥር በመጨመር በአሁኑ ወቅት ለድርጅቱ የቢራ ገብስ የሚያቀርቡ አርሶ አደሮች ቁጥር ወደ 4000 ማደጉን ተናግረዋል፡፡ ይህን ቁጥር በማሳደግም ወደፊት 20ሺ ከሚደርሱ አርሶ አደሮች ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚፈልጉም ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡


Read 1804 times