Saturday, 16 November 2019 11:58

“ሥራ የፈታ ህዝብ በየወሩ መንግስት ልለውጥ ይላል”

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(3 votes)

     በዚች መጣጥፍ በምርጫ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦችን ለማካፈል ወደድሁ:: ጽሁፌን የምጀምረው አንድ ወዳጄ ጋር በስልክ ያደረግኳትን ሃሳብ በማቅረብ ነው:: … ባለፈው ሰሞን ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚቃወሙ “ጩኸቶችን” ስሰማ፣ ለአንድ ወዳጄ ስልክ ደወልኩና፤ “ምንድነው ነገሩ?” አልኩት:: ወዳጄም፤ “ምን መሰለህ… ህዝብ ሥራ ሲፈታ፣ የሚሰራው ቢያጣ በየወሩ መንግስት ልቀይር ብሎ ማስቸገሩ የሚጠበቅ ነው” አለና ፈገግ አሰኘኝ፡፡ ይህቺን ሃሳብ እዚህ ላይ አንስቼ የጽሁፌ መንደርደሪያ ያደረግኳት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ መንግስት በህግ አግባብ ተመርጦ፣ ስልጣን የሚሰጠው አካል በመሆኑ፣ ባኮረፍንና በተከፋን ቁጥር “ና ውረድ!” የምንለው አለመሆኑን ለማስገንዘብ ነው፡፡
በማንኛውም የፖለቲካ ስርዓት ቁልፍ የሆነው ጥያቄ፤ የመንግስት የስልጣን ጥያቄ ነው፡፡በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመንግስት ስልጣን የሚመነጨው በህግ ሲሆን፤ ይኸውም በዜጎች ፈቃድና ስምምነት በተመሰረተ ምርጫ የሚገኝ ነው፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ መንግስትም ህዝብም መብትና ግዴታዎች አሏቸው፡፡ ከእነዚህ መብትና ግዴታዎች ውስጥ መንግስት በህግ ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ውጪ ስልጣን ላይ አይቀመጥም፤ ህዝብም በምርጫ ስልጣን ላይ ያወጣውን አካል ሊያወርደው የሚችለው ጊዜውን ጠብቆ በሚካሄድ ሌላ ምርጫ ነው የሚለው ይገኝበታል፡፡
ብዙዎቹ የንድፈ ሃሳብ እውቀቶች (በተለይም ፍልስፍናና ስነ-መንግስት) በምንጭነት የተቀዱት ከግሪክ ነው፡፡ በጥንታዊት ግሪክ “የከተማ መንግስት” (city states) ነበሩ፡፡ በመሆኑም፤ ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ ምርጫም ሆነ ስል ህዝብ ውሳኔ ስናወራ፤ መነሻችን አቴንስ፣ ስፓርታ፣ ማራቶን፣… በመሳሰሉት ከተሞች የነበሩ “የከተማ መንግስታት” ናቸው፡፡
በእነዚህ ቀደምት የግሪክ የከተማ መንግስታት የነበረው የህዝብ ቁጥር አነስተኛ ነበር፡፡ በመሆኑም በዚያ ወቅት መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በየእለቱ ህግ የሚያወጡትም ሆኑ ውሳኔ የሚያሳልፉት አገረ-ገዢዎች (ንጉሶች) አልነበሩም፡፡ ያኔ የህዝብ ምክር ቤት (ፓርላማም) አልነበረም:: በመሆኑም መላው የከተማው ነዋሪ ይሰበሰብና በቀረበለት አጀንዳ ላይ ተወያይቶ ህግ ያወጣል፣ ውሳኔም ያሳልፋል፡፡
በዚህ ዓይነቱ አሰራር ህዝቡ ራሱ ይሳተፍ ስለነበር አሰራራቸው “ቀጥተኛ ዴሞክራሲ” (Direct democracy) ይባል ነበር፡፡ በዚህ በእኛ ዘመን ስራ ላይ እየዋለ ያለው “የውክልና ዴሞክራሲ” (Representative democracy) ነው፡፡ በዚህ ዘመን በ“ቀጥተኛ ዴሞክራሲ” መርህ መሰረት፤ ህዝብ በየቀኑ እየተሰበሰበ ህግ ያውጣ፣ ውሳኔ ያሳልፍ ቢባል ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል:: በዚህ ምክንያት በህዝብ ተመርጠው ስልጣን የተሰጣቸው የህዝብ ምክር ቤቶች አባላት በህዝብ ስም ህግ ያወጣሉ፣ ውሳኔ ያሳልፋሉ:: የእለት ተእለት ስራውን ደግሞ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ያስፈጽማሉ፡፡ በርግጥ በዚህም ወቅት ቢሆን ህዝብ በቀጥታ የሚሳተፍባቸው ምርጫዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ በፕሬዝዳንታዊ የመንግስት ቅርጽ ሁሉም ዜጋ በሚሰጠው ድምፅ ፕሬዝዳንቱን ይመርጣል፡፡ በትልልቅ ሀገራዊ ጉዳዮችም ላይ ህዝበ ውሳኔ (ሪፈረንደም) ሊካሄድ ይችላል፡፡
ምርጫ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የሚገለጽበት አግባብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ማካሄድ እጅግ የተወሳሰበና ከፍተኛ ድካም የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ ምርጫ ለማካሄድ የመራጩን ህዝብ ቁጥር፣ አሰፋፈር፣ የአየር ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ፣ እድሜ፣ ፆታና ባህል ጭምር ማወቅን ይጠይቃል:: ከዚህ በተጨማሪ ምርጫ ከፍተኛ ወጪን ይጠይቃል፡፡ ከጊዜ አኳያ አንድን ሀገራዊ ምርጫ ለማስፈጸም በትንሹ እስከ አንድ ዓመት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በነዚህና በሌሎችም ምክንያቶች የተነሳ ምርጫ በየወሩ ቀርቶ በየዓመቱና በየሁለት ዓመቱ ሊካሄድ አይችልም፡፡
በምርጫ ወቅት ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በሚያደርጉት ቅስቀሳ የህዝብ ስሜት ከመለኪያ በላይ የሚወጣበት ሁኔታም ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት በምርጫ ወቅት የተለያዩ ግጭቶች መከሰታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ እናም በየጊዜው ምርጫ እናካሂድ ብንል፣ በየጊዜው የህዝብን ስሜት በመቀስቀስ ግጭት መፍጠር፣ ሀብትና የሥራ ጊዜን ማባከን ከመሆን የዘለለ ትርጉምም ፋይዳም አይኖረውም ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል አንድ የተመረጠ የመንግስት አካል፣ በምርጫ ወቅት ለህዝብ የገባውን ቃል በተመረጠ ማግስት ሊያስፈጽም ወይም ስራ ላይ ሊያውል የማይችል መሆኑም ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውንም ዓይነት ተግባር ለማከናወን በቂ ጊዜ ያስፈልጋልና! ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተመረጡ ማግስት ለዘመናት የተጠራቀመውን የሀገራችንን ችግል ማስወገድ ቀርቶ ችግሩን ለይተው ለማወቅ ያልቻሉት በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህንን ካላደረጉ ብሎ ምክንያታዊ ያልሆነ ትችት መሰንዘር ግን ጋብቻ በፈጸሙ ማግስት ሙሽሪት ልጅ እንድትሰጥ ከመጠበቅ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡
በርካታ ሀገራት ሀገራዊ ምርጫ ከአራት ዓመት ባነሰ ጊዜ እንዳይካሄድ በህገ መንግስታቸው የደነገጉበት ዋነኛ ምክንያት፣ መንግስትን መምረጥም ሆነ ህዝብን ማስተዳደር በየወሩ የምንፈጽመው ተራ “ጨዋታ” ባለመሆኑ ነው፡፡


Read 2771 times