Saturday, 23 June 2012 07:19

የአውሮፓ ዋንጫው የምንግዜም ምርጥ ሆኗል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

የ14ኛው አውሮፓ ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ከትናንት በስቲያ ሲጀመር በመክፈቻው ጨዋታ ፖርቱጋል በክርስትያኖ ሮናልዶ ግብ 1ለ0 ቼክን በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለች የመጀመርያዋ አገር ሆነች፡፡ትናንት ምሽት ደግሞ ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት እየተሰጣት የቆየችው ጀርመንና ግሪክ ተጫውተዋል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫው ከትናንቱ ሁለተኛ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በፊት በተደረጉ 25 ግጥሚያዎች 61 ጎሎች ከመረብ ያረፉ ሲሆን እያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ እስከ 45ሺ የስታድዬም ተመልካች እያገኘ ነው፡፡ ዛሬ እና ነገ ደግሞ የሩብ ፍፃሜው ወሳኝ ፍልሚያዎች የሚቀጥሉ ሲሆን ስፔን ከፈረንሳይ እንዲሁም እንግሊዝ ከጣሊያን ይገናኙባቸዋል፡፡

የስፔንና የፈረንሳይ ግጥሚያ ቡድኖቹ በምድብ ማጣርያው በተለይ በአማካይ መስመር በነበራቸው ጠንካራ ብቃት ወደ ግማሽ ፍፃሜ ለመግባት ከባድ ትንቅንቅ ውስጥ የሚገቡበት ሲሆን ነገ በሚደረገው የእንግሊዝና የጣሊያን ጨዋታ ላይ ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች በጠንካራ የተከላካይ መስመራቸው በምድብ ማጣርያው ያሳዩትን አቋም የሚያስመሰክሩበት ይሆናል፡፡እስከ አውሮፓ ዋንጫው ሩብ ፍፃሜ በሁሉም ውድደሮች ባደረገቻቸው 17 ጨዋታዎች 16ቱን አሸንፋ በ1 አቻ የወጣችው ስፔን በዛሬው ጨዋታ  የምታገኛትን ፈረንሳይ አሸንፋ አታውቅም፡፡ ስፔንና ፈረንሳይ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ስፔን በ5 ጨዋታዎች ተሸንፋ በአንዱ ብቻ አቻ ተለያይታለች፡፡ በሌላ በኩል ነገ በሩብ ፍፃሜ የሚገናኙት እንግሊዝና ጣሊያን በተገናኙባቸው ጨዋታዎች ተመጣጣኝ ፉክክር ይዘው ቆይተዋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች በ25 ጨዋታዎች ተገናኝተው 8 ጊዜ ጣሊያን ስትረታ እንግሊዝ 7 አሸንፋ በ10 ግጥሚያዎች አቻ ተለያይተዋል፡፡

ፖርቱጋል በግማሽ ፍፃሜው ከስፔንና ፈረንሳይ አሸናፊ ጋር ረቡእ የምትገናኝ ሲሆን የፊታችን ሃሙስ ደግሞ በሩብ ፍፃሜው ትናንት ከተጫወቱት ጀርመንና ግሪክ ያሸነፈው ከነገው የእንግሊዝ እና የጣሊያን አሸናፊ ጋር የሚገናኝ ይሆናል፡፡

14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በገቢው መጠናከር፤ በቲቪ ተመልካች መብዛት፤ ከሜዳ ውጭ በታዩበት አወዛጋቢ አጀንዳዎች አነጋጋሪነት እንዲሁም በምድብ ማጣርያው ቡድኖች ባሳዩት ድንቅ የጨዋታ ታክቲክ እና ጥንካሬ የምንግዜም ምርጡ ሊሆን መቃረቡን የተለያዩ መረጃዎች በማውሳት ላይ ናቸው፡፡ በምድብ ማጣርያው ላይ በተደረጉ  24 ጨዋታዎች በአማካይ 2.5 የጎል መጠን መመዝገቡ ለውድድሩ ድምቀት አስተዋፅኦ ማድረጉን ያወሱ መረጃዎች በጥሎ ማለፉ በሚደረጉት ቀሪ ሰባት ጨዋታዎች ይሄው ሁኔታ ከቀጠለ በአንድ ጨዋታ በአማካይ የሚገቡ ጎሎች ተመን በ2000 እኤአ ላይ ላይ በ11ኛው የአውሮፓ ዋንጫ  ላይ በአማካይ 2.74 ተመዝግቦ የተያዘው ክብረወስንን እንደሚያሻሽልም ገምተዋል፡፡

የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ከውድድሩ ጋር በተያያዘ የብሄራዊ ቡድን ደጋፊዎች በሜዳ ውስጥና ከሜዳ ውጭ በፈጠሯቸው ብጥብጦች እና የዘረኝነት ተግባራት እንዲሁም ተጨዋቾች በፈፀሟቸው ጥፋቶች እስከ 505ሺ ዶላር በቅጣት ያስከፈለበት ሆኖ ልዩ ገፅታን ተላብሷል፡፡ የገንዘብ ቅጣቶቹ በስምንት የተለያዩ ጥፋቶች በአምስት አገራት ፌደሬሽኖች እና በአንድ ተጨዋች ላይ በተላለፉ ውሳኔዎች ገቢ የተደረጉ ናቸው፡፡ ኒኮላስ ቤንድትነር ግብ ካገባ በኋላ ቁምጣውን አውልቆ የለበሰውን የውስጥ ሱሪ በማስተዋወቁ የተጣለበት የ100ሺ ዶላር ቅጣት በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ሲሆን በሁለት የተለያዩ ጥፋቶች የ150ሺ ዶላር ቅጣት የተወሰነበት የሩስያ ፌደሬሽንም ጎን ለጎን የሚነሳ ነው፡፡

የአውሮፓ ዋንጫው በተለይ በሰሜን አሜሪካ ባገኘው የቲቪ ተመልካች ከ4 ዓመታት በፊት ከነበረው ብዛት በ82 በመቶ በማደግ አዲስ ሪኮርድ ያስመዘገበም ሆኗል፡፡ የምድብ ማጣርያውን አንድ ጨዋታ በአማካይ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ተመልካች በሰሜን አሜሪካ እንዳገኙ ሲታወቅ ይሄው ብዛት በእጥፍ እንደጨመረ ተነግሯል፡፡

ባለፈ ታሪክ በመመርኮዝ ለአውሮፓ ዋንጫው አሸናፊነት ወይም ታላቅ ውድቀት እነማን እንደሚበቁ የተለያዩ ግምቶችም ሲሰንዘሩ ቆይቷል፡፡ ጣሊያን በ1982 እና በ2006 እኤአ ላይ ያሸነፈቻቸው ሁለት ዓለም ዋንጫዎች በአገሪቱ እግር ኳስ የጨወታ ቅየራ ቅሌቶች ባጋጠሙበት ሁኔታ መሆኑን በማስታወስ ዘንድሮም ተመሳሳይ የቅሌት ድራማ በአገሪቱ መፈጠሩ ለዋንጫ አሸናፊነቷ ፍንጭ ይሰጣል ተብሏል፡፡ በትልቅ ዓለም አቀፍ ውድድር ዋንጫ ካገኘች ከ46 ዓመታት በላይ ያለፋት እንግሊዝ በባለፈው ታሪኳ መነሻነት የተተነበየላት ግን ውድቀቷ ነው፡፡ በዩሮ 96 ለግማሽ ፍፃሜ የደረሰችው እንግሊዝ ዘንድሮም ቢሆን ለግማሽ ፍፃሜው ከበቃች በአሳዛኝ ሁኔታ መሰናበቷ አይቀርም ተብሏል፡፡ በዓለም እግር ኳስ ታሪክ በ3 ትልልቅ ውድድሮች በማከታተል ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ ብሄራዊ ቡድን  በታሪክ አለማጋጠሙ ደግሞ ለስፔን የሻምፒዮናነት ማስጠበቅ እድል እንቅፋት ሆኖ የተነሳ ምክንያት ነው፡፡ በ2008 እኤአ የ13ኛው የአውሮፓ ዋንጫን ካሸነፈች በኋላ ከ2 ዓመት በኋላ የዓለም ዋንጫ ድልን የደገመችው ስፔን በ14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሻምፒዮናነቷን በማስጠበቅ ሃትሪክ ለመስራት የሚኖራት እድል ምናልባትም በሩብ ፍፃሜ ሊገታ እንደሚችል ተወርቷል፡፡

ለዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ፍፃሜ ከተጠበቁ ጨዋታዎች ስፔንና ጀርመን የሚገናኙበት ሁኔታ ከፍተኛ ግምት እንዳገኘ ሲታወቅ ፖርቱጋል ከጀርመን፤ እንግሊዝ ከፈረንሳይ በከፍተኛ ደረጃ የተጠበቁ የዋንጫ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ በአውሮፓ ዋንጫው ዋዜማ ኢኤ ስፖርትስ  በኮምፒውተር በተቀናበሩ አሃዛዊ ስሌቶች የዋንጫው ጨዋታ በጀርመንና ሆላንድ መካከል ተደርጎ ጀርመን 2ለ1 ሆላንድን ታሸንፋለች ብሎ መተንበዩ የሚታወስ ሲሆን የዚሁ ተቋም ትንበያ ሆላንድ ከሩብ ፍፃሜው ከተሰናበተች በኋላ የተሰጠው ክብደት መቀነሱ ይታወቃል፡፡

በ2010 እኤአ ተደርጎ በነበረው 19ኛው ዓለም ዋንጫ በትንበያው 70 በመቶ ስኬታማ የነበረው ካስትሮል ኤጅ የተባለው ተቋም በሰራው ስሌት ለዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ ድል ግንባር ቀደም ተቀናቃኞች ያደረገው በብዙዎች ግምት ያገኙትን ጀርመንና ስፔን ነው፡፡ ባለፉት የአውሮፓ ዋንጫዎች የነበሩ ውጤቶችን በማስላት በካስትሮል ኤጅ የተሰራው ትንበያ የዋንጫውን ድል 54 በመቶ እድል የሰጠው ለጀርመን ሆኗል፡፡

በአውሮፓ ዋንጫው በትንበያ ከተሳተፉ እንስሳት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው የፖላንዷ ዝሆን ሲታ ከዩክሬኖቹ አሳማ እና ሽኮኮ የተሻለ ትክክለኛነት ሳይኖራት ቀርቷል፡፡ ዝሆኗ በመክፈቻው ጨዋታ ፖላንድ ግሪክን እንደምታሸንፍ ገምታ ፖላንድ በመሸነፏ ሳይሳካላት የቀረ ሲሆን ከዚያ በኋላ በሌሎች የምድብ ጨዋታዎች ያደረገችው ትንበያ በአመዛኙ ሊሳካላት ባለመቻሉ ከትንበያው ቁማር ትኩረት እያጣች መጥታለች፡፡ ዩክሬን ያቀረበቻቸው የውጤት ትንበያ የሚሰሩ እንስሳት ግን ከዝሆኗ ተሽለዋል፡፡ ፍሬድ የተባለው ሽኮኮ ከ10 ጨዋታ ስድስቱን በትክክል በመገመት እንዲሁም ፋንቲክ የተባለው  አሳማ ከ10 አምስቱን በትክክል በመገመት ተሳክቶላቸዋል፡፡ በአወራራጅና አቋማሪ ድርጅቶች ሩብ ፍፃሜው ሲጀመር ለዋንጫው ከፍተኛ ግምትን ለጀርመንና ስፔን ሲሰጡ ፖርቹጋል፤ እንግሊዝ፤ጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ ቼክ ሪፖብሊክና ግሪክ እንደቅደምተከተላቸው ለሻምፒዮናነት ተጠብቀዋል፡፡

የአውሮፓ ዋንጫው የምድብ ማጣርያ እጅግ አስደናቂና ከፍተኛ ደረጃ ያሳየ ፉክክር በብሄራዊ ቡድኖቹ መካከል ታይቶበታል፡፡ ከምድብ ማጣርያው በመሰናበት ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ሆላንድ የሞት ምድብ ሰለባ ሆና ተጠቃሽ ብትሆንም ዴንማርክና ክሮሽያ በምርጥ ተፎካካሪነት  መውደቃቸው ያነጋገረ ነበር፡፡ የጎል ስፖርት ድረገፅ ባጠናቀረው ሀተታ ከ24 የአውሮፓ ሊጎች የተውጣጡ 368 ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን ያሳተፈው የአውሮፓ ዋንጫው ላይ የምድብ ማጣርያው ሲያበቃ  የስፔኑ ላሊጋ ላይ የሚጫወቱ 21 ተጨዋቾች በየቡድናቸው ባሳዩት ብቃት የሊጉን ተፅዕኖ በአንደኛ ደረጃ ያስቀመጠ ሆኗል፡፡ የፖርቱጋል ፕሪሚዬራ ሊጋ ተጨዋቾች አስተዋፅኦ  በ2ኛ ደረጃ ሲቀመጥ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ፤ የጣሊያኑ ሴሪኤ  የዩክሬን ፕሪሚዬር ሊግ፤ የሩስያ ፕሪሚዬር ሊግ፤ የፈረንሳይ ሊግ 1 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጨዋቾች እስከ ስምንት ያለው ደረጃ አግኝተዋል፡፡

 

 

New layer...
New layer...
Read 2816 times Last modified on Saturday, 23 June 2012 10:45