Saturday, 09 November 2019 12:13

… ያልተዘመረለት ህዝብ …

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“ኑሮ እንዴት ነው?”
“ደህና…”
“ሥራስ?”
“ደህና…”
“ስማ፣ ሀገር ተተረማመሰች፣ አይደል?”
“ይቅርታ… የቀጠሮ ሰዓት ደርሶብኛል፡፡ ቻዎ!”
ማንም ማንንም የማያምንበት ዘመን አልፎ… ትንሽ ተንፈስ አልን ብለን ይቺንም፣ ያቺንም ስናወራ እንዳልከረምን  ነገሮች…“ይቅርታ… የቀጠሮ ሰዓት ደርሶብኛል” ወደሚል መለወጣቸው አይቀርም፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ የሚፈልጉ አሉና!  
የምር ግን…አለ አይደል… የሆነ ሰው መልካም ሥራ ሠርቶ ሳይታወቅለት ሲቀር “ያልተዘመረለት” የሚሉት ነገር አለ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ … ከዳር ዳር ሊዘመርለት ሲገባ፣ ያልተዘመረለት ማለት የእኛ ህዝብ ነው፡፡ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ለዘመናት የእኛ ህዝብ የቻለውንና፣ አሁንም ምናልባት ባልተለመደና በከፋ መልኩ እየቻለ ያለውን መከራ፣ የቻሉ ህዝቦች አሉ? በየሀገሩ በትንሽዬ ሰበብ የሚነሳውን ነውጥ እናየው የለ እንዴ!
ስሙኝማ…በተለይ ቦተሊካው አካባቢ ‘የታወቀ የሰፈር ጉልበተኛ’ የሚያደርጋቸው ‘ትልልቅ ሰዎች” (ቂ….ቂ…ቂ…) ስናይ ግራ ግብት ይለናል፡፡ እንዴት ነው ይሄ ሁሉ ሲንቴቲክ… “እንደ አጥቢያ ኮከብ፣ ሲነጋ ታየ…” በሉልኝ የሚል… የኢንተርኔትና የቴሌቪዥን መስኮት ‘ሂሮ’ ሊበዛ የቻለው?
እናላችሁ... በላይኛው የእውቀት ዙፋን ላይ የሰቀላችሁት ሰው… አስተሳሰቡ ተጨራምቶ፣ ተጨራምቶ ሰባት ሰው ላለበት እቁብ የማይመጥን ሲሆንባችሁ በእጅጉ ያሳዝናል:: እንዲሁ ነው እየሆነብን ያለው… በክብር ኤቨረስት ተራራ ላይ የሰቀልናቸው፣ ከስማቸው በፊት ያሉት ማእረጎች የጂብራልታር አለትን ያህል የገዘፉ ሰዎቻችን እያሳቀቁን ነው፡፡ እውቀት አእምሮን ማስፋት ሲገባው፣ እውቀት ከራስ አጥር ውጪ የማየት ችሎታን ማላበስ ሲገባው፣ እውቀት አርቲፊሻል ግንቦችን የማፍረሻ ዘዴዎችን መርምሮ አስተቃቃፊ ሀሳቦች የመፍጠር አቅም ማጐናፀፍ ሲገባው…በተቃራኒ ሲሆንብን፤ ማዕረግ ማማ ላይ ባወጣናቸው ሰዎች እናፍራለን፤ ለእኛ ሳይሆን ለእነሱ፡፡
ታዲያላችሁ… እንዳለመታደል እንበለውና፣ እንዳለመታደል ሆኖ አሁን፣ አሁን ይቺ መከራ ቻይ ህዝቧ ሊዘመርለት የሚገባት ሀገር፣ በአደባባይ የምታያቸው… በእውቀት በስለዋል ተብለው የሚታሰቡ ዜጎች አብዛኞቹ የያዙት የተተረተረውን መስፊያ መርፌና ክር ሳይሆን ደህናውን መተርተሪያ መቀስ ሆኖ ሲገኝ፣ ያልተሳቀቅን በምን ልንሳቀቅ ነው?
እናላችሁ… ይህ መከራ ሲሸከም የኖረና መከራ መሸከሙን የቀጠለ ህዝብ ያልተዘመረለት ለማን ሊዘመር ነው!  
እግረ መንገድ…“አውሮፕላን ተሳፍሬ አውሮፓና አሜሪካ መሄድ እየተመኘሁ፣ አይደለም መሄድ በአሜሪካ ኤምባሲ በር እንኳን ያለፍኩት  ከስንት አንዴ ነው…” የምትሉ ወገኖች… ምን መሰላችሁ…‘ዘ ሩል ኦፍ ዘ ጌም’ (የጨዋታውን ህግ) አላወቃችሁትም:: “ኢንቪቴሽን ተልኮልኝ ነው፣” “በአጎቴ ልጅ ግራጁኤሽን ላይ ለመገኘት ነው” የሚለውን ተዉትና ምን አድርጉ መሰላችሁ…ፖለቲከኛ ሁኑ! አራት ኪሎ ማን ይግባ ማን ግዴለም… ብቻ ‘ተቃዋሚ ፓርቲ’ የሚል የዳቦ ስም የተሰጠው ቡድን ማቋቋም ነው፡፡ ከዚያማ የአውሮፕላን ትኬት ብሎ ነገር የለ፣ የሆቴል ወጪ ብሎ ነገር የለ… መምነሽነሽ ነው፡፡
የምር ግን መሬት የያዘ የሚባል አላማና ፕሮግራም ያላቸውን ‘ፓርቲዎች’ እንተዋቸውና…አለ አይደል… መቶ ሠላሳ ምናምን የደረሱት እንዴት ነው? የዛሬ ስንትና ስንት ዓመት ተመስርተው የረሳናቸው ፓርቲዎች ሁሉ… ይኸው ‘አፈር’ ይሁን ምን እየማሱ… “አለን” እያሉን አይደል እንዴ! እና ይህንን ሁሉ ለቻለው የእኛ ህዝብ ያልተዘመረ ለማን ይዘመራል!
ስሙኝማ…የእኛ የሚዲያ ሰዎች ነገርም ግራ ከማጋባትም እያለፈ ነው፡፡ እናላችሁ… በእርግጠኝነት እንደ አጀንዳ የተያዘ በሚመስል መልኩ እንድንተቃቀፍ ሳይሆን እንድንተናነቅ እየተሠሩ ያሉ የሚዲያ ሥራዎች ለመኖራቸው በተለይ አሁን፣ አሁን ይበልጡኑ ግልጽ እየሆነ ይመስላል፡፡ ችግሩ እየታወቀ ነገራችን…አለ አይደል... ‘አለባብሶ የማረስ’ መሰለ እንጂ!
ግን ደግሞ… በአብዛኞቹ ሚዲያዎች ምናልባትም ፉክክሩ እየጠነከረ ስለመጣ፣ … “ሰዋችን ደብለቅለቅ ያለ ነገር ሲሆን ነው የሚወደው፣” በሚል አይነት ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው’ አስተሳሰብ ጥፋቶች እየተፈጸሙ ነው፡፡ በተለይ ቃለ መጠይቆች ላይ የሚታዩ ጥፋቶች ሰዉን  እንዳያሸሹት ያሰጋል፡፡
እናላችሁ… የማንኛውም የሚዲያ ተቋም የቃለ መጠይቅ እንግዳ፣ ፖለቲካዊ አመለካከቱም ሆነ ሌላ አስተሳሰቡ ምንም ይሁኑ ምን ሊከበርለት ይገባል፡፡ የሚጠየቁት ጥያቄዎች የእንግዳውን ሀሳቦች ከመሞገት አልፈው ሰብእናውን በአሉታ የሚነኩ ሲሆኑ አስቸጋሪ ነው፡፡ መረጃና ማስረጃ ይዞ በግልጽ ከመሞገት ይልቅ በ“አሉ ተባለ” ማስረጃ የሌላቸው ‘ትረካዎች’… ጠያቂው የራሱን አመለካከት ለማግነን የሚያደርጋቸው ሙከራዎች፣ በጊዜ ብዛት ህብረተሰቡ በሚዲያው ላይ ያለውን እምነት ሙሉ ለሙሉ እንዳይሸረሽሩት የሚያሰጋ ነው፡፡ ጠያቂዎች እንግዳው የእነሱን፣ (‘የእነሱ ቡድን’ የሚያስብሉ ምልክቶችም አይጠፉም) አስተሳሰብ ስለማይከተል ወይም ፊት ለፊት ስለሚሞግት ብቻ ለማሳጣት፣ በሰዉ ዘንድ አሉታዊ መልክ ለመስጠት ሲሞክሩ ማየቱ፤ ዘመን ጥሎት ለሄደው ሚዲያችን አሳዛኝ ነው፡፡
የምር እኮ…በቂ ባልሆነ ምክንያት እንግዳው ሀሳቡን እያስረዳ ባለበት፣ ከአንዴም አምስቴ ጣልቃ እየተገባበት፣ የጀመረውን ሀሳብ እንዳይጨርስ ማደናቀፍ፣ ችግሩ በእንግዳው በኩል አለመሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አቀራረቦች ለሚዲያዎቹም ስም ቢሆን ደግ አይደለም፡፡
እናላችሁ… ይህ መከራ ሲሸከም የኖረና መከራ መሸከሙን የቀጠለ ህዝብ ያልተዘመረለት ለማን ሊዘመር ነው!  
አንድ አሪፍ የሆነች ‘የፈረንጅ አፍ’ አለች…‘ሬዚግኔሽን’ የምትል፡፡ በገዛ ፈቃድ ሥራ መልቀቅ! እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል …ከዓመት በፊት የተጣለባቸውን ሀላፊነት በብቃት የማይወጡ ‘ቦሶች’… ‘ሬዚግኔሽን’ እያስገቡ ለራሳቸው ቀይ ካርድ ይሰጣሉ አይነት… ‘ብሬኪንግ ኒውስ’ ነገር ሰምተን አልነበር እንዴ! (የእኛ ባለስልጣናት በራሳቸው ተነሳሽነት “ይህ ሀላፊነት ከአቅሜ በላይ ነው” ብለው ሥራ ሊለቁ! “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር” የሚባለው በዚህ ጊዜ ነው፡፡) ታዲያላችሁ… መአት የፊርማ ስነስርአቶች ስናይ ከርመን አልነበር እንዴ!  “እና ቢፈረምስ ምን ይጠበስልህ!” የሚሉ የሚኖሩትን ያህል… “እና ያ ሁሉ ፊርማ ምን በላው!” የሚሉ እንዳሉም መገመት አያዳግትም፡፡
እናማ…እንጠይቃለን… ሁሉም አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሥራ ሠርተው ነው? ሰዉ ሁሉ በሚያገኛቸው አገልግሎቶች ተደስቶ ነው? ስንት ዘመን ሚዩዚየም ማድመቂያ ሊሆን ይገባው በነበረ ቢሮክራሲ እስትንፋስ አጥሯት የኖረች ሀገር፣ ተቋማቶቿ ሁሉ የጠላትን ዓይን በሚያቀላ ብቃት ላይ ተገኝተው ነው? የተራቆተው የሰዋችን የምግብ ጠረዼዛ፣ ሳህን ማስቀመጫ ትርፍ ስፍራ እየጠበበው ነው?
ስሙኝማ…ስለ አገልግሎት አሰጣጥ ካነሳን አይቀር…ሀሳብ አለን…መሥሪያ ቤቶች ‘ሲክ ሊቭ’ ምናምን እየተባለ ፈቃድ እንደሚሰጡት ሁሉ… የመብራት ሂሳብ መክፈያ የግማሽ ቀን ፈቃድ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ (የእንትን ሰፈሩ ወዳጄ…ያለፈውን ጭማሪ ምኑ ከምኑ ተይዞ እንደሚሟላ ግራ በተጋባንበት ወቅት በታህሳስም ገና ይጨመራል ተብሏል፡፡ ድንገት ‘ካልሰማህ’ ብዬ ነው!)
እናላችሁ… ይህ መከራ ሲሸከም የኖረና መከራ መሸከሙን የቀጠለ ህዝብ… ያልተዘመረለት ለማን ሊዘመር ነው!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2672 times