Saturday, 16 June 2012 13:24

አንድ እና ተመሳሳይ

Written by  ኤፍሬም ስዩም
Rate this item
(0 votes)


አንድ የሆነ ሠነፍ የት እንዳለ ስለማያውቅ በደረሰበት መመላለስ አይችልም፡፡ ተመሳሳዮች በሚጓዙበት ፈንጠር - ፈንጠር - ብሎ - ይሮጣል እንጂ… “ልክ መድረኩ እንደሠፋው…ዳንስ..እንደማይችል - ተራ- ዘፋኝ”…መፈናጠርና መደነቅ …የማስመሰልና…የመቻል…ልዩነቶች ናቸውና፡፡

-1-

እኔ

አንድና ተመሣሣይ ፍፁም አንድ አይደለም፡፡ …

ብዙ የሚለያይ ነገር ያላቸው ብዙ አንድ አይነቶች አሉ፤ ነገር ግን ተመሳሳይ ናቸው እንጂ አንድ ሆነው አያውቁም፡፡

የማሕበረሰቡ ችግር መመሳሰልን መውደድ ነው፡፡

አንድ፡፡

አንድ መሆን የሚሻ ሠው በመመሣሠል ላይ ያመፀ መሆን አለበት፡፡ አንድ ከዕልፍ መነጠል … ከመንጋ  መገለል  … ከብዙው መውጣት፡፡ ግር አለማለት፣ የራስን ጣዕም የራሥን መጠን…የራስን …ሥፍራ- በራሥ - ለራሥ መገንባት - ነው፡፡ አንድ - መሆን - ብዙ - ኮረት ከመሆን - ይልቅ …መጠነኛ - ተራራ መሆንን…የመሥራት እውነት ነው፡፡

አንድና - ተመሳሳይ

አንድ መሆን በእኔነት ላይ ሲመሠረት፣ ተመሳሳይ - ደግሞ በማንነት ላይ ይቦካል፡፡ ዓለትና ዱቄት ግን - በብዙ ነገራቸው ልዩ መሆናቸውን መስበክ አንባቢውን ሠነፍ (አላዋቂ) ከማለት የዘለለ ስድብ አይደለምና…ዐለቱን - ለመልካም መሠረት …ዱቄቱን ደግሞ ለተራበ አንጀት ትተናቸዋል፡፡

ተመሳሳይ….

ተመሳሳይ በባሕልና በቅርስ፣ በታሪክና በእምነት፣ በተራራና በሸለቆ …በሸንተረርና በወንዝ…በሐገርና በጐሳ…በእኛነትና በማንነት - መሐል ሲሽሎኮሎክ ይኖራል፡፡ መኖር ከተባለ…

አንድ……….

አንድ - በመንፈስና በልብ በእኔነትና በመንፈሳዊነት ሜዳ ላይ - ራሱን ይፈጥራል፡፡ የራሱን ምንነትም በምሥራቅ በኩል ይፈጥራል (ይሠራል - አላልኩም)….

ተመሣሣይ……

ተመሣይ - ለባሕሉ ተቆርቋሪ - ለቅርሱ ጠበቃ ነው፡፡

ታሪኩንና ባሕሉን ግን እንክርዳዱን ከስንዴ ለይቶ አያውቅም፡፡ ሁሉም ነገር ባህሉ ነው

ተመሳሳይ በሸንተረርና በወንዝ ይመካል ይመፃደቃል፡ ስህተቱ ግን በርሱ ሐገር የሚገኙት በሌላ ዓለማት የሉም አልነበሩም …አይኖሩም ማለቱ ነው፡፡

ተመሳሳይ - ሐይማኖተኛ እንጂ መንፈሳዊ አይደለም…ለተመሳሳይ --መንፈሳዊነት…ብዙ ሆነው እየጨመሩ …የሚያጨበጭቡት ጩኸት እንጂ በሕይወት የሚተረጐም …የአምላክ (አምላካዊ) ሕይወት አይደለም…ሲዘምር በአጨበጨበበት መዳፍ …ከሰው ኪስና ከሰው እኔነት - ለተንኮልና ለሌብነት ጣልቃ ይገባል….

….ተመሳሳይ ማንነት እንጂ እኔነት የለውም፡፡ መጠሪያ ሥሙም …. እኛ እና የፓርቲና የሃይማኖት ተቋም ሥሙ ብቻ ነው፡፡ ተመሣሣይ ስለ ምንም ነገሮች ያለው ፍቅር የሚመሠረተው በስሜተኝነት ጎጆ ላይ እንጂ በአመክንዮ ሕንፃ ላይ አይደለምና አስቀድሞ እኔነቱን ቀጥሎም የኛ የሚላት ሐገሩን ያጠፋል …. ራሡን የማያውቅ ወንዘኛ ነውና፡፡

***

-2-

“የኮላ ኮላ ጠርሙስ ከመሆን ያድነን”

አሜን!!

ተመሣሣይ ነገሮችን ግራና ቀኝ ልብ ሥለማይላቸው እንጂ ራሡን የሚመሠረትው ከመመሣሠል በተነጠሉ ግለሠቦች (እኔነቶች) ላይ ነው፡፡ ተመሣሣይ ስለ ዕገሌ ያወራል … ይሠብካል … ይሠበካል፤ ዕገሌ ከተመሣሥሎ ራሡን የለየ መሆኑን ልብ አይልም …

ተመሣሣይ የተመረጠውን ይመርጣል እንጂ የሆነ ምርጫ የለውም፡፡ ወደ የትኛውም የነፋስ አቅጣጫ ያዘነብላል እንጂ የራሡ የሆነ ምርጫ የለውም፡፡ ወደ የትኛውም የነፋስ አቅጣጫ ያዘነብላል፡፡

ከየትም እንኳ ቢነፍሥ ማዘንበል መጽናት ማጋደል እንጂ መቆም አይችልም፡፡ ምክንያቱም ራሡ በራሡ የሆነ የራሡ እኔነት ስለሌለው በቅርንጫፎች ላይ እንደተንጠለጠሉ ቅጠሎች እንጂ ግንድ እና ቅርንጫፍ አይደለምና …

(አንዳንዶች ይሕችን ዓለም ዳግም ፈጥረዋታል) …

አንድ የሆኑ አንጆች የዚህ ዓለም ታላላቅ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው፡፡ የዚህ ዓለም ውበትም ሆኑ የዚህ ዓለም ክፋት በብዙዎች (በተመሣሣዮች) አልተሠራም፡ ተመሣሣይ የጉልበት እንጂ የመፍጠር ዓቅም የለውም፡ “ከሺሕ ወንዶች አንድ፣… ካገር ሙሉ ሴቶች ግን ምንም እንዲል … “አንዱ” ተመሣሣይ ንድፍ ማውጣት አይችልም… እርሡ ራሡ መንፈሱ… የሆነ የአንድ ሠው ሐሳበ ንድፍ ስለሆነ፡፡

***

-3-

አንድ የሆነ ሰነፍ....

አንድ ነው ግን ሠነፍ ነው - ምክንያቱም አንድ መሆኑን የመሠረተው ከተመሳሳይ ጠጠሮች ውስጥ አንዱን ሆኖ ስለሆነ፡፡ አንድ የሆነ ሠነፍ እኔነቱን የሚሠራው በረቂቅ ብልጥነት አልያም የተመሳሳይን መፈክር በማንነት ኮረብታ ላይ ቆሞ በመጮህ ነው፡፡ የእነርሱን መፈክር ስላስተጋባ… የብዙዎችን ለብቻው ስለ ጮኸ… አንድ ይመስላል እንጂ ፍፁም አንድ አይደለም፡፡ አንድ የሆነ ሠነፍ የት እንዳለ ስለማያውቅ በደረሰበት መመላለስ አይችልም፡፡ ተመሳሳዮች በሚጓዙበት ፈንጠር - ፈንጠር - ብሎ - ይሮጣል እንጂ… “ልክ መድረኩ እንደሠፋው…ዳንስ..እንደማይችል - ተራ- ዘፋኝ”…መፈናጠርና መደነቅ …የማስመሰልና…የመቻል…ልዩነቶች ናቸውና፡፡ አንድ - የሆነ - ሠነፍ - ስሕተቶችን - ያባብሳል እንጂ መንቀፍ አይችልም፡፡ እርሱ የተመሳስሎ ውጤት ስለሆነ በማንነት እንጂ በእኔነት ….የተለካ አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ አንድነቱን በእኛና በየኛ የመፈክር - ጭቃ - ላይ - ስለመሠረተ ---የእኔነትን - የሐሳብ ንጽሕና ይፀየፋል፡ ኮረብታው ከተራራው የሚገኝበት ጊዜ አለ…ሕንፃውን የሠሩት …አዕባን ግን ከተራራው ትከሻ የተከፈሉ ናቸው፡፡ ሠነፍ አንድ ክፋይ ኮረት ነውና..ጥበብን እና …እውቀትን ..በሕዝቦች …ልክ…ይሠፋል፡፡ ተመሳሳዮችም የተሠፋላቸው …በልካቸው መሆኑን እንጂ…ጨርቃቸው …ከቅርፊትም ይሁን ከቃጫ ግድ አይሰጣቸውም …ማንነታቸውም ጥራት ላይ ሳይሆን…ብዛት…ላይ ....ታትሟልና…በእኔነት..ተራራ…ላይ…የቆመ…ምርጥ የሆኑ …አንዶች ግን ለገላ --- የማይሻክረውን …አስተውለው ያበጁታል..ያለብሱትማል…መናኛ …የሆነውን…ግን..ከሕሊናቸው አውጥተው ይጥሉታል…

***

-4-

አንድ

አንድ - የሆነ ምርጥ የሙዚቃን ---ቃል ---አይከተልም፡ በሕዝብ ሐሳዊ ዲስኩርም የዕዝኑ መስኮቶች ሊከፈቱ አይችልም…የድለላና የሽንገላ …ስብከትም …የእኔነቱ ልክ አይደለምና…በሀርና ሐረግ፣ በእኛና በማንነታችን…በወንዝና በጐሣ …ሸለቆ አይሽሎከሎክም፡፡ አንድ… በነገሮች (በሐሳቦች) መሃል - ከተነገሩት - ምርጥ - ሃሳቦች ይልቅ…ያልተነገሩና ያልተባሉትን…ዝም የተባሉትን ልብ ይላል፡፡ በወሬ መካከል ያልተወራውን ያዳምጣል፡፡ አንድ - በጆሮው ግንድ አይሰማም፡፡ በቅጽ ከንፈሮቹም አያወራም…በፀጥታው ሥፍራ - ፀጥታውን ያያል…ዜማ የሌለው ሙዚቃም ለራሱ ይፈጥራል…አንድ የሆነ “ምርጥ” በጫጫታ መሃል እንደሚገኝ “ክቡር ቤተ - መቅደስ” ነው፡፡

ለምሣሌ

ፒያሳ እንደሚገኘው ቅዱስ - ጊዮርጊስ - ቤተ - ክርስቲያን….

 

 

Read 2880 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 14:07