Saturday, 02 November 2019 13:13

አዲሱ “አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ” በትግራይ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

      ‹‹ኢትዮጵያዊነት ለድርድር አይቀርብም››

• ግጭት የሚቀሰቅሱ አክቲቪስቶችና ሚዲያዎች አድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው
• ኢህአዴግ ካልቻለ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም አለበት
• ከህወሓት የተለየ ሃሳብ የሚያራምድ “አሲምባ” በሚል ይፈረጃል
• የምንታገለው ለኢሮብ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለትግራይም ነው


         ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሠረታቸውን በትግራይ ያደረጉ የብሔር ፓርቲዎች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ከሰሞኑ “አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዲፓ)” የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት በትግራይ ተመስርቷል፡፡ ይሄ ደግሞ በክልሉ የሚፎካከሩትን ፓርቲዎች ቁጥር ወደ አምስት ያሳድጋቸዋል፡፡ ለመሆኑ የፓርቲው ዓላማና ግብ ምንድን ነው? ከሌሎቹ የህወሐት ተፎካካሪዎችስ በምን ይለያል? ለክልሉ ሕዝብ ምን ትሩፋት ይዞ መጥቷል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፣ የፓርቲውን አመራር አባል አቶ ዶሪ አስገዶምን በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-


        የአሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዴት ተመሰረተ?
ከዚህ በፊት አብዛኞቻችን የህወኃት አባላት ነበርን፡፡ ከህወኃት ጋር ሆነን በትግራይም ይሁን በኢትዮጵያ ያሉ መጠነ ሰፊ ችግሮችን በውስጥ ሆነን እየታገልን፣ ማስተካከል እንችላለን፣ በሚል ዓላማ ለብዙ አመታት ተጉዘናል፡፡ ነገር ግን በህወኃት ውስጥ ለችግሮች መፍትሔ የሚሰጥና ነገሮችን የሚያስተካክል አካሄድን አላገኘንም:: ህዝቡ በተለያየ መልኩ በሠላማዊ ሠልፎች፣ በስብሰባዎቻችና በመድረኮች ላይ የሚያነሳቸው ችግሮቹ መፍትሔ እንዲያገኝለት ቢጠይቅም፣ ህወኃት ግን ምላሽ መስጠት አልቻለም፡፡ በዚህም እኛ የህወኃት አባል የነበርን የተወሰንን ሰዎች በፓርቲው ላይ እምነት ስላጣን፣ የራሣችንን ትግል ለማካሄድ ነው ፓርቲውን የመሰረት ነው፡፡
ድርጅታችሁ ለምን ‹‹አሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ›› ተባለ?
አሲምባ በሀገራችን ከሚታወቁ ተራራዎች አንዱ ነው፡፡ ተራራ ብቻ ሳይሆን ብዙ ታሪክም ያሳለፈ ነው፡፡ በጣሊያን ጊዜ አባቶቻችን እንደ ምሽግ ተጠቅመው ተዋድቀውበታል፡፡ የኢህአፓ ታጋዮች ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ባንዲራቸውን የተከሉት አሲምባ ላይ ነው፡፡ ኢህአፓዎች በኢሮብ ማህበረሰብ ዘንድ “አሲምባዎች” በሚል ነበር የሚታወቁት፡፡ ስያሜውን ያገኙት ከተራራው ጋር በነበራቸው ግንኙነት ነው፡፡
ብዙ ሰው ‹‹ለምን ፓርቲያችሁን አሲምባ አላችሁት?›› ይለናል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አሲምባ የሚለውን ስም ራሱ ይፀየፉታል፡፡ ለምን ትፀየፉታላችሁ ስንላቸው፣ በወቅቱ አሲምባ የነበሩ ታጋዮች ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ፈፃሚዎች ነበሩ ይሉናል፡፡ ኢ-ሠብአዊ ድርጊቱን ትተን በጐ ተሞክሮዎችን ብቻ መውሰድ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡ አሲምባ ላይ የነበረው ኢህአፓ፤ አያሌ ምሁራን ለህዝብ የታገሉበት ጥሩ ታሪክ አላቸው፡፡ ያንን ታሪካቸውንና ልምዳቸውን እንወስዳለን፡፡ ለምሣሌ የኢህአፓ ዋና ፀሐፊ የነበሩት ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ፣ ትውልዳቸው እዚያው አካባቢ ነው፡፡ እሣቸው ለአላማቸው ጽናት እንዴት እንደሞቱ በሚገባ ይታወቃል፡፡ ብዙ ጀብድ የፈፀሙ ምሁርም ታጋይም ናቸው:: እንደነዚህ አይነት ለአላማቸው የፀኑ፣ ለህዝብ ነፃነት የታገሉ በርካቶች አሉ፡፡ የአሲምባ ታጋዮች እርስ በእርሳቸው ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው:: ዛሬም በህይወት ያሉ አሉ፡፡ የእነሱን የትግል አላማ፣ ጽናትና የእርስ በእርስ ፍቅር፤ እንዲሁም ህዝባዊነት እያላችሁ እንወርሳለን፡፡ በእነሱ የጽናት ልክ እንታገላለን፡፡
ከህወሓት ጋር እያላችሁ ሊፈቱ ያልቻሉት ችግሮች ምንድን ናቸው?
ብዙ ችግሮች ናቸው የነበሩት፡፡ ዋና ግን የድንበር ጉዳይ ነው፡፡ ህዝባችን በድንበር አካባቢ የሚኖር ህዝብ ከመሆኑ አንፃር፣ ብዙ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የኢኮኖሚ ህልውና ችግሮች ተጋርጠውበታል፡፡ በተለይ በኤርትራና በኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ያም ሆኖ ግን የአልጀርሱን ስምምነት ውሣኔ የኢሮብ ህዝብ ላለፉት 20 ዓመታት ሲቃወም ኖሯል፡፡ በተለይ ዛላምበሣ፣ ባድመ አካባቢ ያለው ህዝብ ይሄን ስምምነት ሲቃወም ነው የኖረው፡፡ በ1996 ዓ.ም የአልጀርሱ ውሣኔ ሲወሰን ህዝቡ ነበር ቀድሞ የተቃወመው:: የኢሮብ ህዝብ ጽኑ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አንድ አባት በወቅቱ እንደውም “አይደለም አንድ የኢሮብ ሰው ይቅርና ኢሮብ ምድር ላይ ያለ ድንጋይ ወደ ኤርትራ ምድር ከተንከባለለ እንመልሰዋለን” ብለው ነበር፡፡ ህዝቡ በዚህ ልክ ነው በኢትዮጵያዊነቱ ላይ ያለው ጽናት:: በታሪኩም የኤርትራ አካል ሆኖ አያውቅም፤ ፍላጐትም የለውም፡፡ በኤርትራ በኩል ያለው የድንበር ህዝብም ወደ ኢትዮጵያ መካለል እንደማይፈልግ ደጋግሞ በሠላማዊ ሠልፍ ጭምር ገልጿል፡፡
በኤርትራ በኩል ያለው የድንበር ህዝብ ኢሮብ አይደለም እንዴ?
ኢሮብ ብቻ አይደለም፤ ትግሪኛ ተናጋሪውም አለ፡፡ በነገራችን ላይ በኤርትራ በኩል ያሉ ኢሮቦችን፣ ሳሆ ነው የሚሏቸው፡፡ ከኛ ማህበረሰብ ጋር በጣም ይዋደዳሉ፡፡ ይጠያየቃሉ:: ወንድማማች ነን፡፡ ነገር ግን ኤርትራ ውስጥ አሁን ኢሮብ ተብለው አይጠሩም፤ ሳሆ ነው የሚባሉት፡፡ በቋንቋው ነው የተሰየሙት:: ኤርትራዊነታቸውን ይፈልጉታል፡፡ የኢሮብ ህዝብ ግን ለኢትዮጵያዊነቱ ጽኑ ነው፡፡ ወደ ኤርትራ የመሄድ ፍላጐት ፈጽሞ የለውም:: ይሄን በተደጋጋሚ በማሳሰብ፣ የአልጀርሱን ስምምነት ቢቃወምም እስከ ዛሬ ምላሽ አላገኘም፡፡ ህወኃት/ኢህአዴግ ምላሽ ለመስጠት አልፈቀደም፡፡
የአልጀርሱ ስምምነት የኢሮብን ህዝብ ለሁለት የሚከፍል ነው፡፡ የኢሮብ ህዝብ ለሁለት ተከፈለ ማለት ደግሞ እንዲጠፋ ተወስኖበታል ማለት ነው፡፡ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እኮ ለአናሣ ብሔሮች አንድነት ዋስትና ይሰጣሉ፡፡ ይሄም ህግ ይጣሳል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያ ጥያቄያችን ህዝባችን ለሁለት አይከፈል ነው፡፡ ለዚህም እንታገላለን፡፡ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ ሌላኛው ችግር፤ በትግራይና በአማራ ክልል መካከል ያለው የወሰን ችግር ነው፡፡ ህዝቡን እየከፋፈሉ ያሉት ህወኃት እና አዴፓ ናቸው፡፡ ህዝቡ ችግር የለበትም፤ ድንበሩንም ራሱ ያውቃል፤ ራሱ መወሰን ይችላል፡፡ ህዝቡን ወደ ጥርጣሬና ወደ ግጭት ማስገባት አስፈላጊ አይደለም፤ በሠላማዊ መንገድ መፈታት አለበት የሚል አቋም አለን:: ችግሩ እንዲፈታም እንታገላለን፡፡ የትግራይና የአማራ ህዝብ በታሪክ ተጣልቶ አያውቅም፤ የሚያጣሉት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ ይሄን እንዲያስተካክሉ ተደጋግሞ ተነግሯቸዋል፡፡ ነገር ግን አላስተካከሉም፡፡ ስለዚህ አንዱ መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል ብለን የምንታገልበት ጉዳይ ይህ አጀንዳ ነው፡፡
የኢሮብ ህዝብን ለሁለት ይከፍላል የተባለው የአልጀርሱ ውሣኔ ተግባራዊ ባልተደረገበት ሁኔታ ጉዳዩን በዚህ መጠን አጀንዳ ማድረግ አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች አሉ:: እናንተ ምን ትላላችሁ?
በጣም የሚገርመውና የሚያናድደው ነገር፣ በሚያዚያ 2011 ዓ.ም “የትግራይ ቱሪዝም ካርታ” የሚል ወጥቷል፡፡ ይህ ካርታ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት፣ ወደ ኢትዮጵያ የተካለሉ መሬቶችን በሙሉ ካካተተ በኋላ ሌሎቹን ቆርጦ አውጥቷቸዋል፡፡
መሬቶቹ ወደ ኤርትራ ተካትተዋል ማለት ነው?
ካርታው ላይ የተካተቱት ወደ ኢትዮጵያ እንዲካለሉ የተወሰኑት ቦታዎች ብቻ ናቸው:: ሌሎቹ ተቆርጠው ቀርተዋል፡፡ የትግራይን የቱሪዝም ሁኔታ በማያሳየው ካርታ ላይ ለኤርትራ የተወሰኑ የተባሉ ቦታዎች የሉም፤ ተቆርጠው ቀርተዋል፡፡ ይህ ካርታ ሲወጣ ነው በዋናነት ትግላችንን ለማጠናከር የወሰንነው፡፡
በመጀመሪያ ይህ ለምን ሆነ ብላችሁ አልጠየቃችሁም?    
ጠይቀናል፤ ነገር ግን ‹‹አንድ ግለሰብ ነው ይሄን ያደረገው›› አሉን፡፡ እንዴት የቱሪዝም ቢሮ ወይም… የክልሉ መንግስት ያፀደቀው ካርታ፣ የግለሰብ ስህተት ነው ይባላል፡፡ ያው ካርታውም እስካሁን አልተስተካከለም፡፡ እኛም “ከእንግዲህ እናንተ እኛን አትወክሉም፣ የራሳችንን ትግል እናደርጋለን” ብለን ነው በዚያው ቅጽበት ወስነን ከእነሱ የተለየነው፡፡ ፓርቲውንም  ለመመስረት የወሰንነው ከዚህ ድርጊት በኋላ ነው፡፡ ህዝቡ ግን በፊትም ጀምሮ ውሣኔውን በመቃወም፣ ስጋቱን በሠላማዊ ሠልፍና በተለያየ መንገድ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ ይሄን ደግሞ የሚቃወሙት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢሮቦች ብቻ ሳይሆኑ በመላ አለም የሚገኙ የኢሮብ ተወላጆች ናቸው፡፡ እስከ ዓለማቀፍ ፍ/ቤትም ለመሄድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡
የኢሮብ ህዝብ በኤርትራ ወረራ ወቅትም የሀገሩን ድንበር ላለማስደፈር፣ ምንም ስልጠና ሳይወስድ፣ መሣሪያ ከመጋዘን አውጥቶ፣ የመከላከያ ሠራዊት በአካባቢው እስኪደርስ ድረስ ለሁለት ቀን በጽናት ተፋልሟል፡፡ በወቅቱ መስዋዕትነት የከፈሉ ልጆች “እጡቅ ሠንበት” በመባል ይታወቃሉ፤ ይዘከራሉ፡፡ በዘፈንም “አንድ ሰው ለአንድ ሺህ” ተብለው በአካባቢው ይወደሳሉ፡፡ ይሄ ሁሉ መስዋዕት የተከፈለው ታዲያ ለምንድን ነው? ችግሩ ካልተፈታ አካባቢው ሠላም አይሆንም፡፡
ፓርቲያችሁ የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ጉዳይ እንዴት መፈታት እንዳለበት አማራጭ ያቀርባል?
በኤርትራ በኩል ያለ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት አይፈልግም፡፡ ይሄን በሠላማዊ ሠልፍም  አረጋግጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ያለውም ወደ ኤርትራ መከለል አይፈለግም:: ይሄንንም በሠላማዊ ሠልፍ አረጋግጧል:: ስለዚህ ህዝቡ ራሱ ወስኗል ማለት ነው፡፡ መሬቱን፣ ድንበሩን ደግሞ የሚያውቀው ህዝቡ ነው፡፡ ስለዚህ ውሣኔውን ለህዝብ መተው ይበጃል ብለን ነው የምናምነው፡፡ በሀገር ሽማግሌዎች ድንበሩን ማስመር ይቻላል:: ግን ህዝቡ ይወስናል፤ ችግሩንም በቀላሉ መፍታት ይቻላል፡፡ ህዝቡ’ኮ በአስተዳደር ነው ወደዚያም ወደዚህም መካለል የማይፈልገው እንጂ ውላቸው፣ ግንኙነታቸው በፍቅር የተሞላ ነው፡፡ በመሀከላቸው ፀብ  የለም፡፡ በጦርነቱ ከሁለቱም ወገን ለሞቱት እኮ በጋራ ነው ሀዘናቸውን የገለፁት፡፡ ህዝቡ አሁንም ቢሆን ችግር የለበትም፡፡ ችግሩ የፖለቲከኞች ስለሆነ መሠሪ ፖለቲካቸውን ሊያቆሙ ይገባል፡፡ እኔ አንድ ተስፋ ያለኝ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ ወቅት ‹‹የኢሮብ ህዝብ ለሁለት አይከፈልም›› ብለዋል:: ይሄ ጥሩ ነው፡፡ እኛ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን፡፡ ነገር ግን ችግሩ ሲቋጭ የህዝቡን ህልውና በማያስደፍር መልኩ መሆን አለበት፡፡
ለዚህ እኛም እገዛ እናደርጋለን፡፡ ምሁራኖቻችንም የአድቮኬሲ እንቅስቃሴ እየጀመሩ ነው፡፡
ፓርቲያችሁ በኢሮብና በትግራይ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ያየዋል?
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የፍትህ ችግር አለ፡፡ የመብት ችግር አለ፡፡ በተለይ ህዝቡ የፈለገውን የመፃፍ፣ የመናገር መብት የለውም፡፡ ከህወኃት አስተሳሰብ ውጪ ሃሳብ ያለው ሰው ካለ፣ “ይሄ አሲምባ ነው” በሚል ይፈረጃል፡፡  ምክንያቱም አሲምባዎች አይወደዱም፡፡ ኢሲምባ ተብሎ የተፈረጀ ሰው ብዙ ችግር ይደርስበታል::  የኢሮብ ተወላጅ ፖለቲከኞች፤ ይሄን ችግር ሲጋፈጡ ነው የኖሩት፡፡
የፓርቲያችሁ ዓላማና ግብ ምንድን ነው?
በዋናነት ለኢሮብ ህዝብ የሚታገል ቢሆንም፣ ለትግራይ ህዝብ ነፃነትም ይታገላል:: አደረጃጀቱም ክልላዊ ነው፡፡ ከተቋቋምን ጀምሮ የኢሮብ ህዝብ ያሉበትን ችግሮች በተለያዩ መንገዶች ይፋ እያደረግን ነው፡፡ በዚያው ልክ የትግራይ ህዝብ እየተጋፈጣቸው ያሉ ችግሮችንም እንዲሁ መታገያችን እያደረግን ነው፡፡ የድንበርን ጉዳይ ስናነሳም፣ በትግራይና በአማራ፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለውን ጭምር ስለሆነ የትግላችን አድማስ ሰፊ ነው፡፡ ለኢሮብ ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ህዝብም ነው የምንታገለው፡፡
የፖለቲካ ርዕዮተ አለማችሁ ምንድን ነው?
እኛ የመረጥነው ሶሻል ዲሞክራሲን ነው:: ሶሻል ዲሞክራሲ አሁን ካለው የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አብሮ ይሄዳል፡፡ ከዚያ ባሻገር የፌደራሊዝም ስርዓተ - መንግስት ነው የምንከተለው፡፡
ለኛ ሀገር ከፌደራሊዝም የተሻለ አማራጭ አለ ብለን አናስብም፡፡ አሁን ባለው የፌደራሊዝም አፈፃፀም ላይ ያሉ ችግሮች ግን መፈታት አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ አሁን ያለው ችግር የተፈጠረው ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ በመሠራቱ ነው፡፡ ይሄ መስተካከል አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ ህገ መንግስቱም ቢሆን የተወሰኑ ማሻሻያዎች እንደሚያስፈልጉት እናምናለን:: በኢኮኖሚ በኩል ደግሞ አሁን መሬት፤ የህዝብና የመንግስት ነው ይባላል:: በተግባር ግን መሬት የህዝብ አይደለም፡፡ እኛ መሬት በተለይ የመኖሪያ ቦታ ለዜጐች በነፃ ወይም በተመጣጣኝ ዋጋ መሰጠት አለበት የሚል አቋም ነው ያለን:: ዜጐች በገዛ ሀገራቸው ቤት ከሌላቸው ዜግነታቸው ታዲያ ምኑ ላይ ነው? ከዚህ አንጻር ማንኛውም ዜጋ በነፃ ወይም በርካሽ ዋጋ የቤት መስሪያ ቦታ ማግኘት እንዳለበት በፕሮግራማችን ተቀምጧል፡፡
በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ምን ትላላችሁ?
ኢትዮጵያዊነት ለድርድር አይቀርብም:: የኢሮብ ህዝብ ኢትዮጵያዊነትን ፈጽሞ ለድርድር አያቀርብም፡፡ አንዳንዴ የሚገርመው፣ በትግራይ ውስጥ “እንገነጠላለን” ብለው የሚጽፉ አክቲቪስቶች አሉ፡፡ ይሄን አጥብቀን ነው የምንቃወመው፡፡ እኛ ሁሉ ነገራችን ኢትዮጵያ ነች፡፡ የራሷ ፊደል ያላት፣ ለባዕድ ሃይል ያልተገዛች ሀገር ናት፡፡ ለዚህች ሀገር ልዕልና  እንታገላለን፡፡
በአሁኑ ወቅት የለውጥ ሂደት ላይ የምትገኝ ሀገር ናት፡፡ ፓርቲያችሁ የለውጥ ሂደቱን እንዴት ይገመግመዋል?
አሁን የተጀመረው ለውጥ ብዙ ጥሩ ነገሮችን ያመጣ ነው፡፡ ለምሣሌ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው እርቅ ትልቅ ድል ነው:: ግን ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ገና ይቀራል፡፡ ይሄ በትጋት መሠራት አለበት፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት በኩል
ጥሩ ተሰርቷል፡፡ ይሄ የለውጡ ሂደት ትልቁ ስኬት ነው፡፡ ነፃነት እየተሰማን ነው፡፡ ምናልባት አሁን ችግር እየሆነ ያለው የግጭቶች መበራከት ነው:: እርግጥ ግጭቶች አሁን የተጀመሩ አይደሉም:: ለእነዚህ ግጭቶች ዋና መንስኤ የሆነው ደግሞ ኢህአዴግ ሀገሪቷን በትክክል መምራት አለመቻሉ ነው፡፡ በተለይ በአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች መካከል ያለው አለመግባባት ብዙ አደጋ አድርሷል፡፡ እነዚህ ድርጅቶች ሳይስማሙ ህዝብን አንድ አድርገው መምራት አይችሉም:: በዋናነት ግጭት እየፈጠረ ያለው ይሄ የኢህአዴግ ድርጅቶች አለመስማማትም ነው፡፡ ይሄን ችግር ተመካክረው መፍታት አለባቸው:: ይሄን ማድረግ የማይችሉ ከሆነ ግን ለሀገር ህልውና ሲባል የሽግግር መንግስት መቋቋም አለበት፡፡ ምክንያቱም ከስልጣን ይልቅ ሀገር ትቀድማለችና፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ ፖለቲካኞች አሉ፡፡ ኢህአዴግ ብቻውን መምራት ካልቻለ፤ ሀገር ለማዳን ሲባል፣ ወደ ሽግግር መንግስትም ማምራት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሚዲያዎችም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መረጃ ለህዝቡ በትክክል ማድረስ ይገባቸዋል፡፡ የብሔር ግጭት የሚቀሰቅሱ ሚዲያዎች፤ ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው፡፡ አክቲቪስቶችም ግጭት ከመቀስቀስ መታቀብ አለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን ከሀገር ስለማይበልጡ፣ ለህግ መቅረብ አለባቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ትልቅ ሚና መጫወት ይገባቸዋል፡፡   


Read 4278 times