Print this page
Saturday, 26 October 2019 12:35

ማራ

Written by  መኮንን ማንደፍሮ
Rate this item
(10 votes)

 መኝታ ቤቴ ውስጥ ነኝ፡፡ መስኮቱ እንደተከፈተ ነው፡፡ ከውጪ የሚገባው ቀዝቃዛ ነፋስ አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ ቅዝቃዜ ቢኖረውም፣ መስኮቱን ልዘጋው አልፈለግሁም:: ደረቴና ክንዴ እንደተራቆተ ነው፡፡ አብዝቼ በጠጣሁት መጠጥ ምክንያት የፈዘዙ ዐይኖቼን ከመኝታ አልጋዬ ፊት ለፊት ከቆመ የልብስ ቁምሳጥን ጋር አብሮ ከተሠራ የቁም መስታወት ላይ ተክዬ የተጐሳቆለ መልኬን አስተውላለሁ፡፡ ጠይም ፊቴ ወዙ ነጥፏል፣ አመዳይ ያጐሳቆለው ይመስላል፡፡ ጥርሴ መወየብ ጀምሯል፡፡ የጠጣሁት አልኮል መላ ሰውነቴን አግሎት ረጅም አንገቴ ዙሪያ ያለው የደም ሥሬ ተገታትሮ ይታያል፡፡ እየገፋሁት ያለው ከባድ ሐዘን ያጠላበት የብቸኝነት ሕይወቴ፣ ያለ እድሜዬ እጅግ ያስረጀኝ መስሎ ተሰማኝ፡፡
በዘወትራዊው ኑሮዬ በተለየ ጉጉት የምከውነው አንዳችም ነገር አልነበረም፡፡ ለእኔ ሁሉም ነገር ትርጉም አልባ ነው፣ በመኖር ውስጥ ያለን አይቀሬ ተፈጥሮአዊ ጉጉት ገድየዋለሁ፡፡ ቤቴ ከገባሁ ጀምሮ የከፈትኩት የማይሊስ ዴቪስ የጃዝ ሙዚቃ ለአምስተኛ ጊዜ እየተጫወተ ነው፡፡ ሙዚቃውን ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ስላዳመጥኩት ሰልችቶኛል፡፡ ወደ ሙዚቃ ማጫወቻው ሄጄ ሌላ የሙዚቃ ሲዲ ቀየርኩና ሲጋራ ለኩሼ፣ ወደ መስኮቱ በመሄድ፣ አሻግሬ ውጪውን መመልከት ጀመርኩ፡፡ ከየቤቱ የሚፈልቀው የኤሌክትሪክ መብራት ወርቃማውን የጀንበሯን ብርሃን ተክቷል፡፡ መኖሪያ ቤቴ የሚገኘው መንደራችንን ለሁለት ገምሶ ከሚያልፈው ጠባብ የአስፓልት መንገድ ዳር ነው፡፡ በጠባቡ የአስፓልት መንገድ ላይ ጥቂት መኪኖችና እግረኞች በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዛሉ፡፡ ከአስፓልቱ ማዶ ከሚገኘው ምግብ ቤት በረንዳ ላይ ሁለት ሰዎች ተቀምጠዋል:: ከእኔ ቤት ትይዩ ከሚገኘው የስዊዲን ዜጐች የሚኖሩበት ባለ አንድ ፎቅ ትልቅ መኖሪያ ቤት ግቢ ውስጥ ሁለት ወንድ ፈረንጅ ልጆችና አንዲት ጠይም ሴት ልጅ እየተጯጯሁ ኳስ ይጫወታሉ፡፡ ሴቷ ልጅ ከፈረንጆቹ ጋር መጫወቷን አቋርጣ ተነጥላ (ጨዋታው አሰልችቷት ሳይሆን አይቀርም) ወደ ግቢው ትልቅ የብረት በር አመራችና፣ የአጥሩን ግንብ ተደግፎ የቆመ አነስተኛ ብስክሌት ላይ ወጥታ ግቢው ውስጥ መጋለብ ጀመረች፡፡
ሲጋራዬን መስኮቱ ደፍ ላይ ተረኮስኩና መጋረጃውን ጋርጄ፣ ወደ አልጋዬ ሄጄ ጠርዙ ላይ ተቀመጥኩ፡፡ ፊት ለፊቴ ጠረጴዛው ላይ ቂጡ የደረሰ የጐርደን ጂን ጠርሙስ ተቀምጧል፡፡ ጠርሙሱን አንስቼ ጂኑን ብርጭቆ ላይ ቀድቼ ተጐነጨሁና፣ አልጋው ላይ በጀርባየ ተንጋልዬ፣ ፊት ለፊቴ ከተጐለተው የልብስ ቁምሳጥን ጐን፣ ግድግዳ ላይ የተሰቀለ ፎቶግራፍ ላይ አተኩሬ በሐሳብ መባዘኔን ቀጠልኩ፡፡ ፎቶግራፉ ውስጥ ከወገቤ በታች ያለው አካሌ በሐይቁ ተውጦ፣ ወርቃማውን ውሃ በእጆቼ እየጨለፍኩ፣ መስፍንን በጨዋታ መልክ ስረጭ ይታያል:: ይህን ፎቶግራፍ የተነሳነው ለጉብኝት ዝዋይ በሄድንበት ወቅት ነው፡፡ በትዝታ ወደ ኋላ ተጉዤ ብዙ ታሪክ ማንሳት መጣሉ አዳክሞኝ፣ የእንቅልፍ ሰመመን ከቦኝ ሳለ ነው ድንገት ከቅርብ ጓደኛዬ ፀደይ ጋር የነበረኝን ቀጠሮ ያስታወስኩት፡፡ ጠዋት ቢሮ ሳለሁ ነበር ከሰዓት በኋላ ልንገናኝ በስልክ የተቀጣጠርነው፡፡ የእኔና የእሷ ጓደኝነት የተጀመረው የኮሌጅ ተማሪዎች ሳለን ነበር፣ ህንፃ ሥራ ኮሌጅ ውስጥ፡፡ ቀጠሮውን በመዘንጋቴ እፍረት ተሰምቶኝ ደውዬ ይቅርታ ለመጠየቅ፣ ምድር ቤት ማብሰያ ክፍል ውስጥ የረሳሁትን የሞባይል ስልኬን ልወስድ ከመኝታ ቤቴ ወጥቼ ደረጃውን ወረድኩ፡፡
* * * *
 ማብሰያ ቤቱ በጥብስ ሥጋ ጠረን ተሞልቶ ነበር፡፡ የማብሰያ ምድጃው ላይ ሠርቼ ሳልበላው የተውኩት የሥጋ ጥብስ መጥበሻ ላይ ክፍቱን እንዳለ ይታያል፡፡ ስልኬን ከፍቼ ማንበብ ጀመርኩ፤ ፀደይ በተደጋጋሚ ደውላልኝ እንደነበር ያሳያል፡፡ መልሼ ለመደወል የነበረኝን ሐሳብ ሰረዝኩና የእቃ መደርደሪያውን ከፍቼ፣ ፊት ለፊት ያገኘሁትን ያልተከፈተ የጐርደን ጂን ጠርሙስ ይዤ፣ የፎቁን ደረጃ እየተጐተትኩ ወጣሁ፡፡
ወትሮ ራሴን ለማዝናናት (ብቻዬንም ቢሆን) ጎራ ወደምልባቸዉ የመዝናኛ ቦታዎች ከሄድኩ ቆየሁ፡፡ ከሥራ የሚተርፈኝን የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው እቤቴ ውስጥ ነው፡፡ በዙሪያዬ ከነበሩ ወዳጆቼ ከራቅኩና ብቸኝነትን ከተላመድኩ ሰነባብቻለሁ፡፡ መቸም የእንጀራ ጉዳይ ነውና ጠዋት ከቤቴ ወጥቼ ሥራ ውዬ እገባለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ስልክ ከመደወል በቀር በአካል ሄጄ እናቴን ከጠየቅኳት ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በሰዎች ዐይን ስመዘን እድል ሁሉን ሸልማኝ በተድላ የምቀማጠል ሴት ነኝ:: ሁሉ ሰው ከቋጥኝ የከበደ የየራሱ መከራ እንዳለው የሚረዱ ጥቂቶች ናቸው፡፡ በሕይወቴ ላይ የተፈጠረው ነገር ሁሉ በፈጣሪ እውቅና ነው ብዬ ስላመንኩና በዚህ ምክንያት በእሱ ላይ ቅሬታ ስለያዝኩ፣ አጥቢያዬ ወዳለ ቤተ ክርስቲያን (በእምነቴ የካቶሊክ አማኝ ነኝ) ሄጄ አላውቅም፡፡ ምኞቴ ለምን አልሰመረም ብሎ ከመለኮት ጋር መገዳደርን ምን ይሉታል? በአንድ እጅግ አፈቅረውና አምነው በነበረ ሰው በመከዳቴ ብቻ እስከ እዚህ ድረስ መመረር ነበረብኝ? ግን ደግሞ፣ የት በተላለፍኩት ጥፋቴ ነው ይህ ሁሉ በእኔ ላይ የሆነው? ብዬ ራሴን ስጠይቅ፣ በእግዜሩ ላይ ያለኝ ማጉረምረም ይበረታል፡፡ እግዜሩስ በእኔ ደስተኛ ሕይወት ምቀኝነት ካልያዘው በቀር ለምን የሰጠኝን ደስታ ነጠቀኝ? “መከራ ሁሉ የሚበረታው ለበጐ አላማ ነው” በሚለው የአፅናኝ ነኝ ባዮች አባባል ፈፅሞ አላምንም፡፡ እንዲህ አይነቱን እሳቤ በልቤ በማሳደሬ፣ ከፈለገ እግዜሩ ገሀነም ይስደደኝ፡፡ የማላውቀው ሰማያዊ ተድላ ምኔ ነውና፡፡
መስፍን ጥሎኝ ከመሄዱ በፊት ሦስት ዓመታትን አብረን በፍቅር ቆይተናል፡፡ ሕይወቴ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ነበረው፡፡ ትዝ ይለኛል… ውጭ አገር ለሁለት ዓመት ሥራ ተመድቤ ሄጄ ሳለ፣ ናፍቆቱ ቆይታዬን እጅግ አስቸጋሪና አታካች አድርጎት እንደነበር፡፡ እና የመስፍን ናፍቆት ሲበረታብኝ አንድ ዓመት እንደቆየሁ፣ ጓዜን ጠቅልዬ ወደ አገሬ ተመለስኩ፡፡ ከመስፍን ጋር አብረን ሳለን፣ ራሴን ዓለም ላይ ያለች እጅግ እድለኛ ሴት አድርጌ እቆጥር ነበር፣ እጅግ የሚወዳትና አብዝቶ የሚያስብላት አጋር ከጐኗ ያላት፡፡
* * *
ዛሬ ረጅም መንገድ የእግር ጉዞ አድርጌ ነው እቤቴ የገባሁት፤ ከለገሀር (መስሪያ ቤቴ የሚገኘው እዚያ ነው) እስከ መኖሪያ ቤቴ ቦሌ ድረስ፡፡ ቤቴ ገብቼ የይድረስ ይድረስ የሠራሁትን ራት ቀማምሼ፣ ብዙ ጊዜ ከምቀመጥበት ሶፋዬ ላይ ከተጎለትኩ ግማሽ ሰዓት ሆኖኛል፡፡ እቤት ስገባ የተቀበለኝ አምበስ (አባቴ ከመንገድ ላይ ገዝቶ ያሳደገው ውሻ ነው) ሲላፋኝ፣ የቆሸሸውን ነጭ ሸሚዜን አለወጥኩትም፡፡ ፊት ለፊቴ ካለው የመስታወት ጠረጴዛ ላይ ቀን ሥራ ቦታ ሳለሁ የደረሰኝ የላኪው አድራሻ ያልተፃፈበት ደብዳቤ ተቀምጧል፡፡ በደካማ የማወቅ ጉጉት አንስቼ፣ የታሸገበትን ፖስታ ቀድጄ ማንበብ ጀመርኩ:: መስፍን የላከው ደብዳቤ ነው፡፡ ደብዳቤው በእጅ የተፃፈ ነው፡፡ ለኤልሲ ብሎ ይጀምራል፣ ከተለያየን ከአንድ ዓመት በኋላ የላከው የመጀመሪያ ደብዳቤው ነው፡፡ መልእክቱን አንብቤ እንደ ጨረስኩ ወረቀቱን ጠረጴዛ ላይ ወረወርኩና ሲጋራ ለኮስኩ፡፡ ያነበብኩት ነገር እጅግ አበሳጭቶኛል፡፡ ደብዳቤው እኔ ላይ ባደረሰው በደል በእጅጉ እንደ ተፀፀተና ይቅርታ አድርጌለት ዳግም ግንኙነታችን እንዲታደስ እንደሚፈልግ የሚገልፅ ነው፡፡ ይሉኝታ ቢስነቱ አናደደኝ፡፡ ያኔ ሁለንተናዋን የሰጠችውን ሴት ገፍቶ ሲሄድ አንዳች ቅሬታን እንዳላሳየ፣ ዛሬ በብጣሽ ወረቀት በላከው የይቅርታ ሽንገላው ረግጦ የሄደውን ፍቅር ዳግም መሻቱ በእጅጉ አሳረረኝ፡፡ ይህን ያደረገው ምናልባት የዋህ ልቤን ስለሚያውቀው አንዳች ተስፋን አለምልሞ ሊሆን ይችላል፡፡ መስፍን እንዲህ ካሰበ ተታሏል፡፡ በምን አይነት ተአምር ልቤ ዳግመኛ የእሱን ቃል አምኖ ሊከፈት ይችላል? ሁሉ ነገር እንዳልነበር ሆኗል፤ ሁኔታዎች የለውጥ ስርአት ተገዢ ናቸውና፡፡ ብርሃን አልፎ ጨለማ እንደሚነግስ አውቄያለሁ:: በክህደት የተሰበረዉ ልቤ ደንድኗል፡፡ በእርግጥ በደልን መርሳት አስገራሚ ጉዳይ አይደለም፤ ነገር ግን የበደሉንን ሰዎች ይቅር ለማለትም ሆነ ላለማለት የጉዳታችን መጠን ይወስነዋል፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት ነው መስፍንን በአካል ያየሁት፤ መሥሪያ ቤቴ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ሆቴል ውስጥ ቀጥሮኝ የተገናኘን እለት፡፡ ያ ቀን የእኔና የእሱ የአብሮነት ሕይወት ያበቃበት እለት ነው፡፡ ሳገኘው ገፁ ላይ ያስተዋልኩት ቀዝቃዛነቱ እንግዳ ሆኖብኝ ግር ብሎኝ ነበር፡፡ ሁሌም ሳገኘው እንደማደርገው ሁሉ በናፍቆት አቅፌ ሠላም አልኩትና፣ ፊት ለፊቱ ወንበር ስቤ ተቀመጥኩ፡፡ ወትሮ የማላውቀው ዝምታው ምስጢር ሆኖብኛል፡፡ አስተናጋጇ አቅርባልኝ የሄደችውን ካፑቺኖ ጠጣሁና:-
“ሳምንቱ እንዴት አለፈ?” አልኩት፤ ወንበሬን ይበልጥ ወደ እሱ እያስጠጋሁ፡፡
“ሁሉም ነገር መልካም ነበር፡፡” አለና፤ ፊቱ ለፊቱ የቀረበውን ቡና ፉት አለ፡፡
“የእኔ ውድ፤ የሆንከው ነገር አለ?” አልኩት፤ አተኩሬ እያስተዋልኩት፡፡
“ዛሬ ላገኝሽ የቀጠርኩሽ አንድ ነገር ልነግርሽ ፈልጌ ነው”
“ይቻላል፤ ምንድን ነው ጉዳዩ?”
በቀኝ እጁ ይዞ በግብታዊነት ሲጫወትበት የነበረውን የቡና ማንኪያ ስኒ ማስቀመጫው ላይ አኑሮ አተኩሮ አየኝና፡-
“ግንኙነታችን እንዲቆም ወስኛለሁ፤ ይህን ነው ልነግርሽ የፈለግኩት”
በሰማሁት ዱብ እዳ እጅግ ደነገጥኩ፡፡ ሰውነቴን አላበው፤ አጥወለወለኝ፡፡ ብዙ ጊዜ መንፈሴን የሚያውክ ነገር ሲገጥመኝ እንዲህ ነው የምሆነው፡፡ ንግግሩ በግድየለሽነት የሰነዘረው ይሁን እንጂ ልቤ ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን የሐዘን ኃይል አይረዳውም፡፡
“ምን ነው? ምን ተፈጠረ? ደግሞስ ምን በደልኩህ?” አልኩት፤ ግራ ገብቶኝ ዐይን ዐይኑን እያየሁ፡፡
“አንቺን የምወቅስበት ምንም ምክንያት የለኝም፡፡ በቃ… ይህ የደረስኩበት ውሳኔዬ ነው::” አለና ገፁን እንዳኮሳተረ በዝምታ ውጪ ጎዳናው ላይ ተከለ፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ወደ መፀዳጃ ቤት ሄድኩና አለቀስኩ፡፡ ስመለስ መስፍን አልነበረም፡፡ ይበልጥ መንፈሴ ተረበሸ:: ከእሱ ውጪ የሚኖረኝ መፃኢ ሕይወቴ አስፈራኝ፡፡ ባሳለፍነው ሕይወት ውስጥ በመሐላችን ቅራኔን ሊፈጥር የሚችል አንዳችም ምክንያት አልነበረም፡፡ ከሆቴሉ ወጣሁና መንፈሴን ያረጋጋዋል ብዬ ወዳሰብኩት ከከተማ ዳር ወዳለ ስፍራ መኪናዬን ነዳሁ፡፡
ለረጅም ቀናት በታላቅ ድብርት ተከብቤ ስለሰነበትኩ ሳምንት ቆይቼ ነበር ሥራ የገባሁት:: የተጠራቀሙ ሥራዎች ስሰራ ውዬ፣ አመሻሽ ላይ ወደ ቤቴ እየተመለስኩ ሳለ ድንገት መንገዴ ላይ መስፍንን አየሁት፡፡ ከአንዲት ቀይ ወፍራም ሴት ጋር ተቃቅፎ ወደ አንድ ቡና ቤት ሲገባ:: እጅግ ደነገጥኩ፡፡ እንደዚያ እጅግ አፈቅረው የነበረ ሰው በቀላሉ በሌላ ሴት ይተካኛል ብዬ ፈፅሞ አልገመትኩም ነበር፡፡ አሁን ዘግይቶም ቢሆን ሲገባኝ፣ ታላቁ ስህተቴ ይህ እንደሚሆን አለመጠርጠሬ ነው፡፡
ኋላ ላይ ቆይቼ ሳጣራ ከመስፍን ጋር አብራ ያየኋት ሴት የሥራ ባልደረባው መሆኗን ደረስኩበት፡፡ እንቆቅልሽ የሆነብኝ ከእዚች ሴት ጋር መቼ ግንኙነት ጀመረ የሚለው ነው - ፋይዳ ባይኖረውም፡፡ ምናልባት ለሥራ ጉዳይ ውጭ አገር በነበርኩበት ወቅት ሊሆን ይችላል፡፡
* * *
አንድ ቀን ከሥራ እንደተመለስኩ መስፍን ለላከልኝ ደብዳቤ ምላሽ ጻፍኩለት፡፡
‹‹እባክህ! እባክህ! ተወኝ!››
(ማራ የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ትርጉሙም መራራ ማለት ነው፡፡ ጸሐፊው ቃሉን የተጠቀመበት አውድ በሰው ልጅ ላይ በሚደርስ ከባድ መከራ የተነሳ የሚፈጠርን ሐዘን ያጠላበት የኑሮ ሁኔታ ለመግለፅ ነው፡፡)

Read 2874 times