Print this page
Saturday, 26 October 2019 12:22

የሁለት ጽንፍ መሀከለኛ አስተርጓሚ

Written by  ሃዊ
Rate this item
(0 votes)

 መገናኛ ድልድዩ ስር ሃይማኖታዊ መዝሙር እያዜሙ የሚያጨበጭቡ አይነ ስውራን ይገጥሙኛል፡፡ ብዙውን ጊዜ በቁጥር ከአንድ በላይ ሆነው በማዜም ነው ምፅዋት የሚጠይቁት፡፡  በቀደም እነሱ እያዜሙ ሌላ ማስታወቂያ ነጋሪ፣ ሌላ ሙዚቃ ከፊት፡፡ ዘፋኙን እርግጠኛ ባልሆንም የሙዚቃው ቃና አለማዊ ነው፡፡ የአይነ ስውራኑ የጭብጨባ ሪትምና የአለማዊው ሙዚቃ ከበሮ ድለቃ አንድ ላይ ድንገት ተገጣጠሙ፡፡ ከአይነ ስውራኑ ዜማ ይልቅ ጭብጨባቸው ከድልድዩ ኮንክሪት ጋር እየተላጋ ድምፁ ይጎላል፡፡ የሁለት አለም ዜመኞች መሆናቸው ለቅፅበት ተረሳና፣ አይነ ስውራኑ በጭብጨባ አለማዊውን ሙዚቃ የሚያጅቡ መሰሉ፡፡ ወይንም የአለማዊውን ‹‹የአስረሽ ምችው›› የማስታወቂያ ድለቃ፣ በሃይማኖታዊው ጭብጨባ መሀል እየገባ ወይንም እስክስታ እየወረደ ያለ መሰለኝ፡፡
ቅፅበቷ ወዲያው ታረመና አጨብጫቢዎቹ የሰመረውን የሁለት አለም ትርታ መዘመራቸውን ገታ በማድረግ አሳለፉን። የማስታወቂያ ድለቃውም ብቻውን ቀረ፡፡ አንዱ ሌላውን የሚደግፍ ያስመሰለው ቅፅበት ሲያልፍ፣ ሁለቱም አለም ብቻቸውን ቀሩ:: ብቻቸውን ሲቀሩ፣ ወደ መደነቋቆር አመሩ:: በእርግጥ፣ ሁለቱም ዓለማት በዚያ ድልድይ ስር ያገጣጠማቸው ገንዘብ የመስራት ፍላጎት ነው፡፡ የእለት ወይንም የአመት ቀለባቸውን፡፡ ግን ቀለባቸውን ለማግኘት የሚጥሩት ከሁለት የዕምነት አቅጣጫ ነው፡፡ አንደኛው አቅጣጫ፣ ለምድር የሚሆነውን ቀለብ የሚሰፍርለት ‹‹ሰማይ›› መሆኑን በዜማው ይገልጻል፡፡ ሰማይን አምኖ፣ የምድር ምዕመናን አማኝነቱን ተንተርሶ እንዲመፀወተው የሚጠብቅ ነው፡፡ ሌላኛው አለም ደግሞ ምድርን መስሎ፣ ለምድራዊ አገልግሎት የሚውል የፀጉርና የቆዳ ቅባት ለመሸጥ ነው የሚያጯጩኸው። ለቅፅበት በአንድ መስመር የመጡ ቢመስሉም፣ ዘላቂ አንድነት ግን አይኖራቸውም፡፡ ዘላቂነታቸው ተቃርኗቸው ነው፡፡ መበጣበጣቸው!
እኔም ከቅፅበቷ ተነስቼ ዛሬ የምፅፈውን አቅጣጫ አገኘሁ፡፡ በመሰረቱ ሁሉም ነገር ከአራቱ መሰረታዊ መደቦች አይወጣም:: አራቱ መሰረታዊ መደቦች፡- ጊዜ፣ ቦታ፣ ህልውናና ግንኙነት ናቸው ይላል - አማኑኤል ካንት፡፡ አራቱ መሰረታዊ ናቸው አልኩ እንጂ ዓይነቶቹ በአጠቃላይ ዘጠኝ ናቸው፡፡ እነዚህ መሰረታዊያን፣ በምድር ላይ አዕምሮ ነገራትን የሚረዳባቸው ወይንም የሚተረጉምባቸው መግባቢያዎች ናቸው፡፡
የአይነ ስውሮቹ ጭብጨባና የማስታወቂያው ድለቃ የሚግባባው ‹‹ሪትም›› ላይ ነው። ሁለቱ አለምኛ ከበሮውን ለተለያየ ግብ ቢገለገሉበትም፣ በጊዜ ምት የሚፈጠረው ሪትም ግን ሙዚቃም ሆነ መዝሙር ለመፍጠር ሁለቱም አንጻርን ይገለገሉበታል፡፡ ከጊዜ፣ ከቦታና ከአዕምሮ ውጭ መሆን አይችሉም:: በአለማዊ ሙዚቃና በመንፈሳዊ መዝሙር መሀል ያለው ንጽጽርም ከአራቱ የመደብ (ዓይነት) መሰረታዊያን አንዱ ነው፡፡ ሁለት ወይንም ከዛ በላይ የሆኑ ነገሮችን… በማነፃፀር ነው ልዩነታቸውን መገንዘብ የሚቻለው፡፡ ከማነፃፀር በኋላ ‹‹ይደመሩ›› ወይንም ‹‹ይጻረሩ›› እንደሆነ መለየት ይቻላል:: ‹‹ቅርብና እሩቅ›› የሚለው መመዘኛ የርቀት ማነፃፀሪያና ብያኔ መስጫ ነው፡፡ ‹‹ፈጣሪ ሁሉን ቻይ ነው›› ለማለት የሰው ችሎታ ውስንነት የማነፃፀሪያው አውታር ነው፡፡ አዕምሮ እንደዚያ ነው የሚሰራው፡፡ ጊዜ፣ ቦታ፣ ህልውናና ተዛማጅነት  (relations) ከምንም ነገር በፊት ቀዳሚ የሆኑት አዕምሮ የሚሰራው በእነዚህ መተርጎሚያዎች አማካኝነት በመሆኑ ምክንያት ነው፡፡ የአእምሮ ቋንቋ ይህ ሆኖ ሳለ፣ የሰው ልጅ ደግሞ እንደ ማህበረሰቡና እንዳለበት የባህል አውድ ቋንቋ ይፈጥራል፡፡ ለምሳሌ፣ የሳይንስ ቋንቋና ከሳይንስ ባህል ርቆ ራሱን ያደራጀ ማህበረሰብ ቋንቋ አንድ አይደሉም፡፡ ልብ በሉ፣ ሁሉም ግን ሰው እንደመሆናቸው በመሰረታዊያኑ አራቱ ‹‹ካታጎሪ›› ጥላ ስር የሚመላለሱ ናቸው።  አንድ ሰው ወደ ሀኪም ዘንድ ሄዶ ህመሙን ያስረዳል፤ ወይም ለማስረዳት ይሞክራል:: ‹‹ይሸቀሽቀኛል፣ የእሳት ፍሙን አምጥቶ ጭንቅላቴ ላይ ይነሰንስብኛል፣ ይቆፍረኛል፣ ቆይቶ ደግሞ እንደ በረዶ ይጋግረኛል፣ ይቆረጥመኛል፣ ሰማይና ምድሩን ደበላልቆ አዙሮ ይደፋኛል…›› ብሎ የበሽታውን ባህሪይ ለሀኪሙ ሊገልጽለት ይችላል፡፡ ሀኪሙ፣ የበሽተኛውን የገለጻ ቋንቋ ወደ ህክምናው የመፍትሄ ቋንቋ ለመተርጎም ወደ ምርመራ ይገባል፡፡ መሰረታዊ መነሻው የሰውየው አካል ነው፡፡ ጤነኛ ሰው፣ የልብ ምቱ፣ የሰውነት ሙቀቱና አተነፋፈሱ… ለሁሉም የሰው ልጅ አማካይ ልክ አለው፡፡ ከዚያ በመነሳት የሰውየውን ገለጻ ከተለያየ የበሽታ ምልክት አንጻር እየጠረጠረ ምርመራውን ያካሂዳል:: በመጨረሻም በሽታውን ያገኝለታል። መድሀኒቱንም ያዝለታል፡፡   
ታምሞ ወደ ሀኪሙ ዘንድ የመጣው በሽተኛ፣ በቋንቋ ዘውግ በሽታውን ያስረዳበት መንገድ፣ ከሳይንስ ይልቅ ለጥበብ የሚቀርብ ነው። ማጋነኑ፣መመሰሉ፣ ተለዋዋጭ ዘይቤ መንተራሱ፣ ስሜታዊነቱ… ወደ ጥበባዊ ቋንቋ ይቀርባል፡፡ ሀኪሙ፣ የበሽተኛውን ጥበባዊ ገለጻ ትርጓሜ ለማምጣት፣ የሁለቱንም አለም ቋንቋ ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በሁለቱም ባህል ውስጥ ማለፍ አለበት፡፡ በሳይንሳዊ ባህል ባያድግበትም ተምሮታል፤ በጥበባዊ ባህሉ ደግሞ ተወልዶ አድጎበታል፡፡ መነሻ የሚያደርገው የሰውየውን ገለጻ ቢሆንም፣ ትክክለኛው የሞያ መነሻው ግን ምርመራው ነው፡፡ ከምርመራው ያገኘው የበሽታ ዐይነት ሳይንሳዊ ስም ቢኖረውም፣ ለበሽተኛው ለማስረዳት ሲል ግን ወደ ታማሚው ቋንቋ መለወጥ አለበት፡፡ በሽታው የተከሰተበት ምክንያት፣ ከሰውየው የኑሮ ዘይቤ ጋር የተሳሰረ ስለሆነ፣ ምን ሆኖ እንደ ታመመ ለመንገር ወደ ሰውየው አለም መመለስ አለበት፡፡  
ልክ እንደዚያው፣ የሁለቱ የድልድይ ስር ሙዚቀኞች አለምና ባህል የተለያየ ቢሆንም፣ የሙዚቃ ቋንቋ ግን ያግባባቸዋል፡፡ ሳይፈልጉት ለቅጽበትም ቢሆን አንድ ሙዚቃ እያጀቡ የተገኙ እንደመሰሉት፣ ቋንቋቸው ሙዚቃ እስከሆነ ድረስ ‹‹ሊደባለቁ አይገባም›› ይባል ይሆናል እንጂ ‹‹ፈጽሞ መደባለቅ አይችልም›› ማለት ጽንፈኝነት ነው፡፡ በእርግጥ ፅንሰ ሀሳቡ ሁለት ጫፍ ሆኖ የማይገጥም ሊሆን ይችላል:: ሙዚቃ ግን ከሀሳብ ባህል ውጭ የሆነ ቋንቋ ነው፡፡ ሀኪሙ የየትኛውንም አለም ሰው፣ ከሰውነቱ መሰረት ተነስቶ በመመርመር መፍትሄ ላይ መድረስ እንደሚችለው፣ ሙዚቃውም ሀሳብ ሳይለይ ዜማን የማድመቅ አቅም አለው:: አራቱ መሰረታዊ የካንት ካታጎሪዎች በመሰረቱ ሰውነትን ነው የሚገልፁት፡፡ መዚቃ አለም አቀፍ የሰው ልጅ ቋንቋ ቢሆንም… አተረጓጎሙ ግን ማህበረሰቡ እንዳለበት የፅንሰ ሀሳብ ማዕቀፍ የሚለያይ ነው፡፡ የሀሳብ ባህሉ የማይደግፈው ሙዚቃ፣ በባህሉ ውስጥ ለሚመላለስ አድማጭ አስቀያሚ ሆኖ ቢረብሸው አይደንቅም፡፡ የፈረንጅ የሮክ ሙዚቃ፣ ሙዚቃ ቢሆንም፣ የባህል ጽንሰ ሀሳብም ያዘለ ነው። ሙዚቃውን አድምጦ የሚረብሽ ከፅንሰ ሀሳቡ ወይንም ሙዚቃው ከታነፀበት የሀሳብ ባህል ጋር ያለውን ተቃርኖ ነው የሚገልጸው፡፡ ነገር ግን አንድ የሙዚቃ ቀማሪ፣ የሁለት አለማትን ድምጽ አጣምሮ የተዋሀደ ሙዚቃ ሊያፈልቅ ይችላል:: በሁለቱ ጥግ የቆሙ ውህዱን ባይወዱትም፣ አማካኝ ጆሮና በሀሳብ የእድገት ሂደት ላይ ለሚገኘው መሀከለኛው ባህል ግን የሚደመጥና የሚወደድ ግኝት ሊሆንበት  ይችላል። ማነፃፀርና ማጣመር የሚመጣው እንዲህ እያለ ነው፡፡ ንፅፅር ልዩነትን ለማወቅ ሲሆን፣ መነጣጠል ቢመስልም በሂደት ግን የተነጣጠለው ወደ አንድ ጥቅልነት ካልተደመረ እውቀትም፣ ውበትም፣ እውነትም አይሆንም፡፡
በሁለቱ መደባለቅና ፅንፉን ለመቀነስና መካከሉን ለማብዛት ይጠቅማል፡፡ ሁሉም ባህል በራሱ መስታወት ትይዩ ቆሞ ራሱን ሲመለከት፣ መገለጫዎቹ ንፁህና ውድ መሆናቸውን ያስባል:: እንዳይከለሱም ይታገላል፡፡ ነገር ግን እውቀት እየጨመረ፣ በመረጃ ግንኙነት በዳበረ አለም ውስጥ የትኛውም አይነት ባህል በሂደት መከለሱ የማይቀር ነገር ነው፡፡
ለመከላለስም አምሳያቸው የተቀራረበ ሀሳብና ባህል ያላቸው ቢሆኑ አደጋው ይቀንሳል። የመንፈሳዊ ዜማን… ከሮክ ጋር መደባለቁ የሁለቱንም ጎን የሚያሳድግ ላይሆን ይችላል፡፡ ማበጣበጥ ይሆናል፡፡ ሙዚቃው ብቻ ተዋህዶ፣ አድማጭ ግን ጆሮ የማይሰጠው ሊሆን ይችላል፡፡ ስሌቱ ምርጥ የሆነ፣ የአድማጭን ስሜት ግን የሚያርቅ ፈጠራ ቢሆን ግንጥል ጌጥ ነው፡፡ ምናልባት ድልድይ ስር የጭብጨባውና የሞንታርቦው ቅላፄ ለቅፅበት የተዋሀደ ሲመስል፣ አድማጩ የደነገጠው ለዚያ ሊሆን ይችላል፡፡
በመለኮታዊ አመለካከት ውጭ ሆነ በሳይንሳዊ እውቀት ባህል ውስጥ ረቂቅ ሚስጥር ይኖራሉ፡፡ ሚስጥሮቹን ወደ ሕዝብ እስከሚሰለቸው ደረጃ አውርዶ ተርጎሞ፣ ለሁሉም ባህል በሚገባ ቋንቋ ማቅረብ ግን ማንም ሊረዳቸው በማይችል ከፍታ ርቀው ከመረሳት ይታደጋቸዋል፡፡ ጥልቀታቸው የሚለካው በሰው አዕምሮ ስለሆነ፣ አዕምሮ ያለውና ለመጠቀም የፈቀደ እንዲቋደሳቸው መፍቀድ ብልህነት ነው፡፡
የእኛ አገር የትኛው ዘመን ላይ እንዳለ እኔ አላውቅም፡፡ የመረጃ ዘመን ግን ፈለግንም አልፈለግንም፣ ከጠቅላላው አለም አስተሳሰብ ጋር ሁሉም ስልጣኔ ከመሸገበት የየራሱ የንፅፅር አለመመሳሰል አውጥቶ፣ በአለም ሜዳ ላይ እንዲነጋገር፣ እርስ በርሱ እንዲለካካ አድርጎታል:: አንዱ አጥፊ ብሎ የሸሸው ባህል፣ ሌላው አዲስ ጀማሪ ሆኖ እንደ ብርቅ ነገር ተነክሮበታል:: ጠቃሚ ሀሳብን ከመጥፎው ጋር በቁሳቁስና በቴክኖሎጂ መልክ እየተለዋወጠ ይገኛል። ተጎጂ የሚሆነው ተቀባዩ እንደሆነ ግልጽ ነው። በተለይ የተቀበለውን ነገር የሚተረጉመው በተሳሳተ መንገድ ከሆነ፣ ችግሩ የበለጠ ይሆናል፡፡ የባህል ግጭቱ ከባህር ማዶ ባህል ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ወይም ከላይ ወደ ታች ሳይሆን፣ ጎን ለጎንም ጭምር ነው። የሃይማኖት ባህልም እንደ ድሮው ከሳይንስ ባህል ጋር ብቻ አይደለም ባላንጣነት ያለው። በአንድ እምነት ስር ያሉ የተለያዩ ወይም በአጠቃላይ በፈጣሪ የሚያምኑ ሃይማኖቶች እርስ በርስ ካላቸው ትልቁ ተመሳሳይነት ይልቅ ጥቂቱ ልዩነት ላይ አትኩረው የጥላቻ ባህልን ለማዳበር እየለፉ ነው፡፡
ትልልቅ የሀሳብ ጽንፎች ብቻ ሳይሆን ትንንሽ አላስፈላጊ ተቃርኖዎችም ተፈጥረዋል። ርዕዮተ አለም የሌላቸው ወይም የማያስፈልጋቸው ጥፋቶችን ልክ ሀኪሙ የበሽተኛውን ባህላዊ/ ጥበባዊ ቋንቋ ወደ ሳይንስ እንደለወጠው፣ ሁሉም በራሱ ውስጥ ሌላውን ማየት የሚያስችል መተርጎሚያ ካልተበጀ፣ ጥግ ከመፈለግ ባህል በኋላ ጥግን የማስከበሪያ ባህል ወደ ተግባር መቀየሩ አይቀርም፡፡  


Read 1624 times