Saturday, 26 October 2019 12:09

ማን ምን አለ?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 * ‹‹…እኛ አገር ኢትዮጵያዊነት የምትባል በጣም ድንቅ መርከብ አለች፡፡ ጠንካራ፡፡ ብርቱ:: ውብ የሆነች፡፡ ይህች መርከብ እየተንሳፈፈች ባለበት፣ የዛሬ ዓመት ከበረዶ ግግር ጋር ልትጋጭ ብላ፣ ልትሰጥም ብላ፣ በአስደናቂ የእግዚአብሔር ምህረትና ቸርነት እንደምንም ብላ አምልጣ አልፋለች፡፡ ከዚያም ያንን የበረዶ ግግር ካለፈች በኋላ ዓመቱን በሙሉ አንድ ጊዜ የብሔርተኝነት ግግር በፊቷ ሲቆም፣ ሌላ ጊዜ የመፈናቀል የበረዶ ግግር በፊቷ ሲቆም፤ አንዴ ወደ ቀኝ እያለች፣ እንደገና ወደ ግራ እያለች፣ ደሞ እየታጠፈች… ብዙ የበረዶ ግግሮችን አልፋ ዛሬ እዚህ ደርሳለች፡፡ ነገር ግን ዛሬም እቺ ኢትዮጵያዊነት መርከብ ከፊቷ የበረዶ ግግር አለ፡፡ ዛሬም ማለፍ ያለባት የበረዶ ግግሮች አሉ፡፡… ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያን ሊያድን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው!››
     ዶ/ር ወዳጄነህ መሃረነ (‹‹አንዳፍታ›› ዩቲዩብ)
* ‹‹…የተባለውን በሙሉ ሰምቻለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ስምና ክብር የሚገባው ለእኔ ነው ብዬ በፍጹም አላምንም፡፡ ክብሩን ሁሉ እግዚአብሔር ይውሰድ…››
     ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ (የሰላም ሚ/ር ለሰላም የኖቤል ሽልማት  ዕውቅና ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ የተናገሩት)
* ‹‹…ታሪክ፣ እምነትና ጎሳ ቢኖር፣ የሚያመሳስላቸው ነገር ምርጥ ምሽጎች መሆናቸው ነው፡፡…››
    ፈላስፋና ፀሐፊ መሃመድ አሊ (ኢቲቪ መዝናኛ)
* ‹‹…ዶ/ር ዐቢይ ለዘመናት የሄድንበትን የመበቃቀል ስህተት፣ በአዲስ መንፈስ በይቅርታ እንሻገር ሲል፣ እንደ ማንኛውም ዜጋ እኔም ደስ ብሎኝ ይሄን ሀሳብ ተቀብያለሁ፡፡ ይሄ እንግዲህ የሆነው ኢትዮጵያ የሄደችበትን የመከራ ዘመን በማሰብ አንድ ቦታ ላይ እንዘጋዋለን የሚል (እንደ አንድ ዜጋ) እምነት ስለነበረኝ ነው፡፡ አሁን ያሉትን ሁኔታዎች ስንመለከት፣ በብሔር-ተኮር ፖለቲካ ጎራ ያሉ ሀይሎች ጫፍ እየወጡ፣ ኢትዮጵያዊ የሚለውን የዜግነት ሀሳብ እየገፉ፣ ዜጎች እንደ ልባቸው እንደ ዜጋ የሚኖሩበትን እያፈረሱ… የመገፋፋትና የማፈናቀል… ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሄ ሊታረም የሚችልበትን መንገድ… እንደ አንድ ዜጋ በግሌ ሞክሬአለሁ፡፡ ሊሰሙኝ የሚችሉ ባለሥልጣናትን ‹‹ምን እያደረጋችሁ ነው›› ብዬ ጮሄአለሁ፡፡ አዝናለሁ፤ ይሄን ስናገር ግን… ተስፋ ሰጪ አይደለም፡፡ ያሰብነው ጋ እየሄድን አይደለም፡፡ ለውጡ ሃዲዱን ስቷል ብዬ ነው የማምነው…››
   አርቲስትና አክቲቪስት ታማኝ በየነ (ለአማርኛው ቢቢሲ ከሰጠው ቃለ ምልልስ)

Read 2510 times