Print this page
Saturday, 26 October 2019 11:28

ሴቶች በተለያዩ የአቅም ማነስ ወይንም ማየል ምክንያት ጉዳት ይደርስባቸዋል

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(5 votes)

      ባለፈው እትም ለንባብ ያልነው ሴቶች በቅርብ ሰው ሲጎዱ በጤናቸውም ላይ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚለውን አንብባ እባካችሁ ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ እኔ አንድ ገጠመኝ አለኝ ያለችው            ወ/ሮ ሐረገወይን እሸቴ ከቦሌ ሀራምሳ ነች፡፡
‹‹….እኔ ትዳር ስይዝ ደመወዜ ብር 60 ነበረች:: ባለቤቴ ደግሞ በወር ብር  200 ያገኝ ስለነበር የእኔን ደመወዝ ይንቃታል፡፡ እናም እንደዚህ አለኝ:: ….ስሚ …የአንቺ ደመወዝ እኮ የጸጉርሽን ቅባት እንኩዋን አይችልም፡፡ ስለዚህ ስራውን ልቀቂና አርፈሽ ከቤትሽ ተቀመጭ አለኝ፡፡ …አኔም ምንም እንኩዋን ልጅነት ቢኖረኝ የእናቴን ኑሮ በደንብ አውቅ ስለነበር….አ..አ…ይ….መጀመሪያ የመጣማ ይጠናከራል…እያለ እያለ ያድጋል እንጂ…ቁልቁል አይወርድም፡፡ ስለዚህ እኔ አንተን ከማግኘቴ በፊት ስራዬን ነው ያገኘሁት:: ስለዚህ አይሆን ካልክ የአንተ ትዳር ይቀራል እንጂ ስራዬማ አይቀርም አልኩት፡፡ በዚህም የተነሳ እግሩን ሰንዝሮ በእርግጫ ሲመታኝ የአራት ወር እርጉዝ ስለነበርኩ አስወረደኝ፡፡ እኔም በዚህ ተቆጥቼ ወደ እናቴ ሄድኩ፡፡
እናቴም…አይ..ሂ…ሂ..እንግዲህ እሱ እንዳለሽ ሁኚ እንጂ እዴት ልትኖሩ ነው አለችኝ፡፡ ለምን? ብዬ ጠየቅሁዋት፡፡ እኔ መቼም አባትሽ እንዳለው ነው የኖርኩት ….ስትለኝ…አሀ…በቀን ለአስቤዛ አንድ ብር እየተሰጠሸ…..ልብስሽን በአመት አንድ ቀን እሱ መርጦ ያሰፋውን እየለበስሽ…የኩችናውን ስራ ከጠዋት እስከማታ ጭስ እየጠጣሽ ስለሰራሽ….ነው ወይንስ ለምኑ ነው አባቴ እንዳለው የኖርሽው….በዚህ ላይ በየጊዜው ከልጆች እኩል እየተደበደብሽ….ስላት እሱዋም ተቆጥታ….እንዴ ምን ትላለች ይቺ….በይ ዝም በይ…ታዲያ ባሌም ኤደል እንዴ ይምታኛ….እንድስተካከል…ጎበዝ እንድሆን…ስራ እንዳውቅ ለማድረግ…ልጆቼን በትክክል ለማሳደግ እንድችል…ነው እንጂ ለክፋት ነበር እንዴ የሚመታኝ? አለችኝ፡፡
እኔም መልሼ እናትና አባትሽ አልቀጡሽም? ባልሽ እኮ ወዶሽ ልጆ ወልዳችሁ በጋር እንድታ ሳድጉ…ለወግ ማእረግ እንድታበቁ ነው እንጂ…ከልጆቹ እኩል ሰልፈኛ ሆነሽ እንድትገረፊ ነው ያገባሽ? …እኔማ ባሌ እንዲህ አድርጎ እቀጣለሁ ቢል ቤተሰቦቼን እንዳዋረደ ነው የምቆጥረው እንጂ እኔን ጨዋ ትሁንልኝ ብሎ ነው የሚለውን አባባል አልቀበልም አልኩዋት፡፡
እናቴም መልሳ …አሁን እኮ እሱ ያለሽን እሺ ብትዪ ኖሮ ጽንሱ አይጨናገፍም ነበር አለችኝ:: እኔም ….እኔ ከዚህ በሁዋላ የእሱን ባልነት አልፈልግም …በቃ እማራለሁ…ብዬ ወሰንኩ፡፡ ከዚያም ስራዬን እየሰራሁ…ትምህርቴን እየተማርኩ …የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንደጨረስኩ አብሮኝ የተማረ ሰው ለትዳር ጠየቀኝና አገባሁ፡፡ አመታት እየተቆጠሩ ሲመጡ …እኔም ትምህርቴን በማሳደጌ ምክንያት ለተለያዩ ኃላፊነቶች ታጨሁ፡፡ አሁን ደግሞ ያ ሴቶችን የመጨቆን ነገር በባልተቤቴ መልኩን ለውጦ መጣ፡፡
ዛሬማ አንቺ እኮ ባለስልጣን ነሽ፡፡ የትም ስትሄጂ እኔን አታስፈቅጂም፡፡
ምን ተደርጊ? አንቺ እኮ አይፈረደብሽም፡፡ ልጆችሽን የምታይበት ምን በቂ ጊዜ አለሽና ነው፡፡ እቤት እትገቢው ስልኩ ተከትሎ ይመጣል፡፡ ላብቶፑ ጠረጴዛ ላይ ተዘርግቶ እሱ ላይ ማፍጠጥ ነው ስራሽ፡፡ ምክንያቱም ለአለቆችሽ መልስ መስጠት ስላለብሽ ነው:: ባለቤትሽ ስለልጆቹ ጉዳይ ሊያናግርሽ ቢፈልግ እንኩዋን ጊዜ የለሽም፡፡
ቤተሰቦቼን የምትጠይቂበት ጊዜና ፕላን አታዘጋጂም፡፡
በሆነው ባልሆነው ለምትጠየቂው ነገር መልስሽ ሙግት ነው፡፡ በስብሰባ ስም ከማንም ጋር ትውይ ታመሽና ከእኔ ጋር ወሲብ ለመፈጸም ፈቃደኛ አይደለሽም፡፡ ደክሞኛል….እራሴን አሞኛል …ወዘተ ...ትያለሽ፡፡
የሚሰራው ምግብ አይጥምም፡፡ አንዳንዴ ይቃጠላል፡፡ ሰራተኞቹ የሚቆጣጠራቸው የለም፡፡ አንቺ በቤት ውስጥ የለሽም፡፡
ሌላም ሌላም ነገሮችን እያነሳ ጭቅጭቅ ብቻ ሆነ ኑሮአችን፡፡ አንዳንዴም ልማታ ብሎ ይነሳል፡፡ ልጆቼ የ14 እና 16 አመት እድሜ ስላላቸው…ተው…ተው …ብለው በገላጋይነት ከመሐል ይገባሉ፡፡
የእኔ የህይወት ልምድ ሁለት አይነት ነው:: የመጀመሪያው ገና በህጻንነቴ ማለትም በ18 አመት እድሜዬ የተመሰረተ ትዳር ሲሆን ከላይ በገለጽኩት መሰረት በመጥፎ ሁኔታ ተቋጨ፡፡ የሁዋ ለኛው ደግሞ እድሜዬም ከፍ ካለ በሁዋላ ከተማርኩም በሁዋላ የመሰረትኩት ኑሮና ሁለት ልጆችን ያፈራሁበት ቢሆንም አሁንም ኑሮዬን መቀጠል አልችል አልኩ:: ስለዚህ የነበረኝ አማራጭ ጭርሱንም አገር ጥሎ መሰደድ ሆነ፡፡
እኔ በሁድኩበት አገር በቅርብ የማውቃት የስራ ባልደረባዬ የሆነች የውጭ አገር ዜጋ ልክ እኔ የደረሰብኝን ችግር እያነሳች ስታማርር እና ለፍቺ ስትጋበዝ ስመለከት….በአለም ላይ ያሉ ወን ዶች ምን ነካቸው? ነበር ያልኩት፡፡ በእርግጥ በጣም ጥሩ የሆኑ ለቤተሰቦቻቸው አሳቢ … ልጆቻቸው በወጉ የሚያሳድጉ….ለሚስቶቻቸው ጥሩ ክብር የሚሰጡ ወንዶች የሉም ለማለት ፈልጌ አይደለም፡፡ ነገር ግን ኑሮዬን በድጋሚ ብበትነውም በስራ ምክንያት የታዘብኩት ነገር ብዙ ወንዶች ሚስቶቻቸውን በተለያዩ መንገዶች እንደሚጨቁኑአቸው እንዲሁም ዱላ ወይንም ድብድብ እንደሚያደርሱባቸው ነው፡፡
ለአንባቢዎች እንዲተላለፍ የምፈልገው ነገር አለ::
አንድ ወንድ ለትዳር የሚያጫትን ሴት አይቶ ገምቶ ጥሩ በመሆንዋ አምኖ ሲሆን ምናልባት ከተጋቡ በሁዋላ አንዳንድ ሊታረሙ የሚችሉ ነገሮች ቢኖሩ በእርጋታ መነጋገር እንጂ ጉልበት አለኝ ብሎ ዘሎ ልማታ ማለት የለበትም፡፡ በእሱም በኩል ቢሆን ምናልባት ሚስትየው አይታ ወደ ብታገባው ወይንም ቤተሰብ የቤተሰብን ጥሩ ታሪክ በማጥናት ትዳር ቢመሰርቱም አንድ የጎደለ ነገር ቢኖር ወይም መታረም ይገባዋል የሚባል ነገር ቢያጋጥም በእርጋታ ሚስቱ የምትነግረውን አስተያየት ተቀብሎ ማረም እንጂ አንዲ ምናገባሽማ…እኔን የመናገር አቅም የለሽም…ወዘተ ማለት አይጠበቅበትም፡፡
ወ/ሮ ሐረገወይን እሸቴ ከቦሌ ሀራምሳ (እድሜ 67)
ሴቶች በቅርባቸው ባለ ወንድ ወይንም በሌላም ሊጠቁ…ሊደበደቡ…ወሲባዊ ጉዳት ሊደርስ ባቸው…የአካልና የስነአእምሮ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ሲባል ምክንያቶቹ በርካታ ናቸው፡፡ በዋነኛነት የሚጠቀሱት ግን ትምህርት ….የስራ እድል….. የመሳሰሉት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ሴቶች የስራ እድል ካገኙ በደረጃቸው ሀብታቸው የሚገነባ ከሆነ እንዲሁም የትምህርት እድል ካላቸው በወንዶች የሚደርስባቸው ጉዳት ይቀንሳል፡፡
ወንዶች የተወሰነ አቅም ያላቸው ቢሆኑና ሴቶቹም ያንን አቅም መጠቀም የሚችሉ ከሆኑ ብዙ ጊዜ ጉዳት ሲደርስ አይታይም እና በተመሳሳይ ሁኔታ አንዲት ሴት የተወሰነ የአቅም መጠን ቢኖራት ወንዶቹ በዝቅተኛ ደረጃ እንደሚገመቱና ዋናውን የህይወታቸው ድርሻ ሴትዋ እንደም ትመራው በማሰብ ጉዳት ወደማድረስ ያዘነብላሉ፡፡ ምክንያቱም በጋብቻው ጥገኛ ወደመሆን አዝማሚያ ስለሚያዘነብሉ ነው፡፡
ባጠቃላይም በኢኮኖሚው እኩልነት የሌለ ሲሆን ወንዶች በሴቶች ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እየጨመረ ይሄዳል፡፡
በአለም ላይ በርካታ ወንዶች ሴቶች በትምህርት ወይንም በሚሰሩት ስራ አለዚያም በሚኖራቸው የሀብት ክምችት እንዲበልጡዋቸው አይፈልጉም:: ብዙ ወንዶች የበላይ ሆነው ሴቶች የበታች ሆነው ኑሮአቸውን መምራት ሲሹ ይታያል፡፡ አንዳንዶች ሴቶች ይሁን ብለው ሲቀበሉ ብዙዎች ደግሞ ለምን? ብለው ይከራከራሉ፡፡ ባጠቃላይ ግን ተሳስቦ እና ተመካክሮ መኖር እንጂ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች በሚመስል ስሜት ኑሮን መግፋት ለትዳር አጋሮቹ፤ ለልጆቻቸው፤ ለቤተሰቦቻቸው፤ብሎም ለማህበረሰቡ የሚጠቅም አለመሆኑን Archive or public health (2018) ያስረዳል፡፡

Read 11185 times