Saturday, 19 October 2019 14:19

ለክቡር ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ግልፅ ደብዳቤ፡-

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ቅድሚያ በዓለም እጅግ የተከበረውን የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፍዎ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ልገልጽ እወዳለሁ። የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ፤ እርስዎ በኢትዮጵያና በጎረቤት አገራት መካከል ሰላም ለማስፈን ባደረጉት ጥረት እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣና ያለ ቅድመ ሁኔታ ከኤርትራ መንግስት ጋራ በመገናኘት የእርቅ ተነሳሽነት ጠቅሶ፣ ለእነዚህ ስራዎችዎ እውቅና በመስጠት የዓመቱ የኖቤል የሰላም  የኖቤል ተሸላሚ መሆንዎን ይፋ አድርጓል፡፡
የአገራችን መሪ ለዚህ ከፍተኛ ሽልማትና እውቅና መብቃቱ ሁላችንንም ሊያስደስተን ሲገባ፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ወገኖችዎ ግን የደስታው ተቋዳሽ እንዳንሆን የሚያደርጉን፣ እርስዎንም በተሰጠዎት ዓለማቀፍ እውቅና ልክ እውቅና ከመስጠት የሚያግዱን ቅሬታዎች አሉ፡፡ ይህ የተሸለሙት ሽልማት እንደእነ ማህተመ ጋንዲ ያሉ ታላላቅ የዓለማችን ሰዎች ያገኙት ሽልማት ነው። እርስዎም  እንደነዚህ ታላላቅ ሰዎች ይሆኑ ዘንድ  ምኞታችን ነው። የእነኚህ ታላላቅ ሰዎች አንዱ መለያ ባህርይ ለሰብዓዊነት ያላቸው ከፍተኛ እይታና ከጊዜያዊ ነዋያዊና የስልጣን ጥቅም ይልቅ ዘላቂ የሆነ ለሰው ልጅ የሚበጅ እሳቤ ያላቸው መሆናቸው ነው። በዚህም ምክኒያት ከቂመኝነትና ከበቀልኝነት የፀዱ ናቸው።
ክቡርነትዎም በዚህ በተሰጠዎ ዓለማቀፍ እውቅና ደረጃ ራስዎን ከፍ አድርገው ሁላችንንም ኢትዮጵያውያንን የደስታው ተካፋይ ሊያደርጉ የሚችሉበት እድል አለ። አብዛኞቻችን የትግራይ ብሄር ተወላጆች፣ እርስዎ ወደ ስልጣን  ከመጡ ወዲህ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ብሄር ተወላጆች እስር ቤት በመግባታቸው፣ ለውጡ ለኛ ሳይሆን እኛ ላይ እንደመጣ እንድንቆጥረው ተገድደናል። በተለይም እንደ ቀድሞ የስራ ባልደረባዎ እንደእነ ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ያሉ ወጣት ምሁራን እንዲሁም ወታደራዊ መሪዎች እንዲሁም ነጋዴዎች በእርስዎ ትእዛዝ መታሰራቸው እጅግ አሳዝኖናል። በዚህም ሳቢያ  በመላው ዓለም የምንገኝ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ‘ወፍሪ ሓርነት’ በሚል መሪ ቃል፣ እስረኞቻችን እንዲፈቱ ትግል ለመጀመር በመዘጋጀት ላይ እንገኛለን። ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማትና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾችን ለማስተባበርም ስራው እየተጀመረ ነው። ከነዚህ ተግባራት አንዱ ራሱ የኖቤል ኮሚቴው ላይ ጫና ማሳደርንም ሊያጠቃልል ይችላል።  
የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ ሽልማቱን ሊሰጥዎት ከወሰነባቸው ምክኒያቶች አንዱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን መፍታትዎ እንደሆነ በመግለጫው ተጠቅሷል። ታዲያ እርስዎም ይህን ከፍተኛ የሰብእና መለኪያ የሆነ እውቅናና ሽልማት በሚመጥን መልኩ፣ ራስዎን ከጊዜያዊ እልህና በቀለኛነት በማፅዳት፣ ወደ ስልጣን ሲመጡ የገቡልንን የይቅርታና የፍቅር ቃል ወደ ተግባር ይለውጡ ዘንድ እማፀንዎታለሁ።
ዛሬ በፖለቲካ ለውጡ ምክኒያት እስር ቤት የሚገኙ የትግራይም ሆነ የሌላ ብሄር ተወላጅ ኢትዮጵያውያንን በምህረት ከእስር ቢለቅቁ፣ ለዚህ ሽልማት ያበቃዎትንና በመላ ኢትዮጵያውያን ላይ ተስፋ የጫሩበትን የይቅርታና የፍቅር ቃልዎን ተግባራዊ ማድረግዎን ያሳያል። የተሰጠዎት የሰላም የኖቤል ሽልማትም ሁላችንንም በእኩል ያስደስታል፡፡ እናም ክቡርነትዎ ከምንከፋፈልና ከምንሸናነፍ፣ በእርስዎ ይቅርታ አድራጊነት ሁላችንም እናሸንፍ። የትግራይንም ሆነ የሌሎች ብሔር የፖለቲከኛ እስረኞች ይፍቱ!
በመጨረሻም መልዕክቴን በደንብ በሚገልፁልኝ በቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) ስንኞች ሃሳቤን እቋጫለሁ።
ለለውጥ ያጎፈረው ዙፋን ላይ ሲወጣ
እንደ አምናው ባለቀን ያምናውን ከቀጣ
አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ መቼ መጣ
ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ ምህረት አስተምረን አንድ አድርገን መልሰህ  
በድጋሚ እንኳን ደስ ያለዎ!
መርስዔ ኪዳን
ከሜኔሶታ ሃገረ ኣሜሪካ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

Read 8361 times