Saturday, 19 October 2019 13:00

የመስከረም ትዝብቶች - ከእሬቻ እስከ ህዳሴ ግድብ

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(6 votes)

 ይህቺ ጽሁፍ መስከረም ከጠባ ወዲህ የከተብኳት የመጀመሪያ መጣጥፍ ናት፡፡ እናም በመስከረም ወር ልጽፍባቸው ያሰብኳቸውን በርከት ያሉ ጉዳዮች በአንድ ርእስ ጠቅለል አድርጌ ላቀርባቸው ወደድሁ፡፡ ለአንባቢ ይመች ዘንድ መልእክቶቹን በአጭር ርእስ ከፋፍዬ እንደሚከተለው አቀርባቸዋለሁ፡፡ ከውጭ ግንኙነታችን ልጀምር፡፡
ግብፅ በታሪኳ ጦርነት አሸንፋ አታውቅም!
የግብጽን ጉዳይ ያስቀደምኩት በውጫዊ ጉዳይ ብጀምር ይሻላል ብዬ በማሰብ ነው፡፡ በመስከረም ወር ትኩረት አድርጌ ከተከታተልኳቸውና በትዝብት መነጽሬ ካየኋቸው ጉዳዮች አንዱ የግብጽ ባለስልጣናት “ድንፋታ” ነው፡፡ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የህዳሴ ግድብን አስመልክተው ንግግር አድርገዋል:: አልሲሲ ከዚያ አስቀድመው “የ2011 የፀደይ አብዮት በግብጽ ባይቀሰቀስ ኖሮ የህዳሴ ግድብ አይጀመርም ነበር” ማለታቸውን ከማህበራዊ ሚዲያ የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ ብቻ ሳይሆኑ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚህ ሹኩሪ ለሀገራቸው ፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ “ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ የውሃ ሙሌቱን መቀጠሏ ተቀባይነት የለውም” ማለታቸውንም ሰምተናል፡፡
እነዚህን ንግግሮች፣ ፉከራ፣ ዛቻና ማስፈራሪያዎች በየማህበራዊ ሚዲያው ሲናፈስ አስተውለናል፡፡ አንዳንድ ግብጻውያን በጋዜጣና በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮች ሲወራጩ አይተናል፣ ሰምተናል፡፡ በበኩሌ የግብጻውያን መወራጨትም ሆነ የፕሬዝዳንቱ ንግግር አላስገረመኝም፣ አላስደነቀኝም፡፡ ምክንያቱም ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ ዛቻና ማስፈራራት ብቻ ሳይሆን ተደጋጋሚ የጦርነት ዘመቻ መክፈቷም ታሪክ የመዘገበው ሀቅ ነው፡፡ ዳሩ ግን አንዱም የግብጽ ዘመቻ የተሳካ አልነበረም፡፡
ታሪክ እንደሚነግረን፤ በአፄ ላሊበላና ከዚያም በፊት በነበሩ ዘመናት ግብፆች ግብርና ታክስ ብቻ ሳይሆን የእጅ መንሻ ጭምር ለኢትዮጵያ ነገስታት እየላኩ ዓባይን እንደልባቸው ይጠቀሙ ነበር፡፡ ግብርና ታክስ ጊዜውን ጠብቆ ያልተላከለት አፄ ላሊበላ “የዓባይን ወንዝ እዘጋለሁ” የሚል ማስጠንቀቂያ መላኩን ከታሪክ መጽሐፍት አንብበናል፡፡ ግብፆች የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት ጠንከር ሲልባቸው አስፈላጊውን ግብርና ታክስ እየላኩ፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግስት የደከመ ሲመስላቸው እየፎከሩ መኖርን ያውቁበታል፡፡
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት የደከመ ስለመሰላቸውና አንዳንድ “ሆድ-አደር ባንዳዎችን” በገንዘብ መግዛት ስለቻሉ ተመሳሳይ ዛቻና ፉከራ ማሰማታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ቁም ነገሩ ግብፆች ከፉከራ አልፈው ኢትዮጵያን አሸንፈው አያውቁም፡፡ ይህንን በተመለከተ አንድ የፌስቡክ ወዳጄ “ወንድሜ፥ [ግብጽን] አትሳሳቺ በላት። የውጪ ጠላት ሲመጣ የእኔ ክልል፣ የእከሌ ክልል ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ የለም። ይሄ ሕዝብ [አሁን] ሥራ ፈቶ እርስ በርሱ ሲነታረክ አይታ እንዳትሸወድ። ኮሽ ካለ ቀድሞ ለመሞት ሲሽቀዳደም ታገኘዋለች። በሉአላዊነቱ የሚደራደር ሕዝብ አይደለም። ለቁራሽ መሬት ሳይቀር ከዳር እስከዳር ሆ! ብሎ ተነስቶ፣ ለምንና እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ ውድ ሕይወቱን ሲገብር የኖረ ሕዝብ ነው። እንዲያውም ሳታውቀው ይሄንን የደበዘዘ አንድነታችንን መልሳ እንደ ብረት ታጠነክረዋለች፥ ትሞክር!” የሚል አስተያየት ጽፎልኝ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ያለው እውነት ይሄ ነው!
ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር ብቻ ሳይሆን ከእስራኤልም ከሌሎችም ጋር ጦርነት መቀስቀሷ ይታወቃል፡፡ ግን በታሪኳ አንድም ጦርነት አሸንፋ አታውቅም፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል እ.ኤ.አ ከ1874 እስከ 1876 ባሉት ዓመታት የተለያዩ ጦርነቶች ተካሂደዋል:: ግብፅ በእስማኤል ፓሻ እየተመራች፣ በኦቶማን ኢምፓየር ትተዳደር በነበረበት በዚያ ወቅት ግዛቷን ወደ አቢሲኒያ ምድር ለማስፋፋትና ጥቁር ዓባይን ለመቆጣጠር ፈለገች፡፡ ይህንንም ለማድረግ በርካታ መኮንኖችን ከአውሮፓና ከአሜሪካ በመመልመል ከፍተኛ ሠራዊት ገነባች፡፡
በኤርትራ ጉንደት በተባለ ሥፍራ በተደረገ ጦርነት፣ ከቱርክ ጋር የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው የመጡ ግብጻውያን፣ በጦርነቱ ሳይሆን በኢትዮጵያ ተራራ ላይ የገጠማቸውን ቀጭን መንገድ ሲያዩ፣ በድንጋጤ መዋጣቸውን ታዋቂው የታሪክ ጸሐፊ ሀጋይ ኤሪክ ተርኮታል:: የኢትዮጵያ ጦረኞች ካደፈጡበት በመውጣት ፈጣን ጥቃት ሲሰነዝሩባቸው የሚገቡበት ማጣታቸውን ይኸው ታሪክ ጸሀፊ ያብራራል:: ገዢ መሬት ይዞ ያልታሰበ ጥቃት በመሰንዘር ወታደራዊ የበላይነትን የያዘው የኢትዮጵያ ጦር እንቅስቃሴውን ሲቀጥል፣ የግብፅ ጦር ለወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ ሙሉ በሙሉ መውደሙና የዚህ ትልቅ ሽንፈት ዜና በግብፅ ሲሰማ ከፍ ያለ ፍርሃትና ንዴት መፍጠሩም በታሪክ ዘጋቢዎች ተከትቧል፡፡
የጉራዕን ጦርነት ታሪክ እንጨምር፡፡ የተጨናገፈውን ወረራ ተከትለው ግብፃውያኑ እንደገና ኢትዮጵያን ለመውረር ሞከሩ፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ 13,000 የሚጠጉ ወታደሮችን ይዘው ነበር፡፡ ረቲብ ፓሻ በተባለ በግብጹ መሪ ወንድ ልጅ የሚመራ ጦር በምፅዋ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ገባ፡፡ ጉራዕ ሸለቆ አቅራቢያ 2 ምሽጎችንም አንደኛውን በጉራዕ ሁለተኛውን ጥቂት አለፍ ብሎ በሚገኝ ተራራ ላይ ሰራ። በኢትዮጵያ በኩል በነበረው ምቹ ያልሆነ የጦር ሜዳ አቀማመጥ ምክንያት በአንድ ጊዜ 15,000 ወታደሮች ብቻ ነበሩ ለውጊያ የተሰለፉት፡፡ ሁለቱ ኃይሎች ተገናኙ፡፡ ረቲብ በጉራዕ ምሽግ ውስጥ ካሉት 7,700 ወታደሮች ውስጥ 5 ሺዎቹ ከኢትዮጵያውያን ጋር ውጊያ እንዲገጥሙ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ይህ የግብጽ ኃይል በራስ አሉላ በሚመራ የኢትዮጵያ ሰራዊት በፈጣን ሁኔታ ተከበበ፡፡ በተደረገበት ጥቃት ወዲያው ተበተነ:: ኢትዮጵያውያኑ ባገኙት ድል ሳይኩራሩ ኃይላቸውን ካጠናከሩ በኋላ ጉራዕ በመሸገው ኃይል ላይ ሁለተኛውን ጥቃት ሰነዘሩ፡፡ ግብፆች መከቱ፡፡ በሚቀጥለው ቀን የኢትዮጵያ ጦር ምሽጉን ደረመሰው፡፡ የግብፅ ጦር ብዙም ሳይቆይ ሸሸ።
በአፋር በኩል የነበረውን ጦርነት ላክልበት፡፡ በግብጽ በኩል በርከት ያሉ የውጭ ዜጎች በዚህ ጦርነት ተሳትፈዋል፡፡ አዶልፍ አረንድረፕና የስዊስ አሳሽ የነበረው ወርነር ሙዚንገር በዋናነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሙንዚገር የግብጽ ጦርን እየመራ ኢትዮጵያን ለመውጋት በታዳጁራ (ጂቡቲ) በኩል ወደ መሀል ሀገር ዘልቆ ለመግባት ጉዞ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ይህ የሙዚንገር ሠራዊት የአውሳው ሱልጣን በነበሩት በሙሐመድ ኢብን ሃንፍሬ ጦር ተሸነፈ፡፡ ሙዚንገርም በዚሁ ጦርነት ተገደለ፡፡
ይሄ ሁሉ የግብጽ መንፈራገጥ ዋነኛ ዓላማ ሱዳንንና ኢትዮጵያን ያጠቃለለ ትልቅ ግዛት ለመመስረት ነበር፡፡ ሱዳንን ለተወሰነ ጊዜ ለማንበርከክ ብትችልም ከኢትዮጵያ ጋር ግን ተደጋጋሚ ጦርነት አካሂዳ፣ በሁሉም ጦርነቶች ተሸንፋ የሀፍረት ማቅ ተከናንባለች፡፡ የሚገርመው ነገር ግብጽን ደጋግመው ያሸነፏት የኢትዮጵያ የጠረፍ ግዛት አስተዳዳሪዎች፤ ማለትም በሰሜን በኩል የትግራይና የመረብ ምላሽ (ኤርትራ) ገዢዎች፣ በምስራቅ በኩል የአፋር ሱልጣን እንጂ መላው የኢትዮጵያ ጦር አልነበረም፡፡
ግብፆች በሁለት ነገር ጎበዞች ናቸው፡፡ አንደኛ፤ የረቀቀና የተቀነባበረ የሀሰት አሊያም የተጋነነ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት ጎበዝ ናቸው:: በዚህ ረገድ እያንዳንዱ ግብጻዊ በትብብርና ባልተቋረጠ ሁኔታ ከመንግስት ጋር ይሰራል:: ምንም ዓይነት መሳሪያ ሳይኖራቸው ኒኩሌር አለን እያሉ ያስወራሉ፡፡ ከተፈጠረች የዓመታት እድሜ ባልነበራት እስራኤል እንክትክቱ የወጣውን የአየር ኃይል በማጋነን ሰማይ ላይ አውጥተው ይተርኩለታል፡፡ በእኛ በኩልስ?
በእኛ በኩል ይህንን የግብጽ ፕሮፓጋንዳ በመልሶ ማጥቃት መመከት ሲገባን፣ የእነሱን የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደ ደህና ነገር እየተቀባበልን እናሰራጭላቸዋለን፡፡ የተማርነው ሳንቀር የግብፆችን ባዶ ፕሮፓጋንዳ አንጠልጥለን “ግብፆች እኮ እንዲህ ዓይነት ጦር አላቸው፣ እንዲህ ዓይነት መሣሪያ አላቸው፣ ኒኩሌር ታጥቀዋል፣ የአየር ኃይላቸው አይቻልም፣…” እያልን ፈርተን ህዝባችንን እናስፈራራላቸዋለን፡፡
ሁለተኛው የግብፆች ጉብዝና፣ የእጅ አዙር ጦርነት ለመዋጋት የሚያደርጉት ጥረት ነው:: ማለትም ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን እንድንዋጋ በማድረግ ማእከላዊ መንግስትን ለማዳከም የሚያደርጉት ጥረት፡፡ እኛ እርስ በርስ ስንባላ ዓባይን እንደ ልብ መጠቀም፡፡ ይህንን በተመለከተ ጀብሀንና ሻዕቢያን አስታጥቃ ከኛ ጋር በማዋጋት ያለ ባህር በር አስቀርታናለች:: ዛሬም ተመሳሳይ ነገሮችን ትሞክር ይሆናል፡፡ ግን የሚሳካ አይደለም፡፡ ግብጻውያን አንድ ነገር መረዳት አለባቸው፡፡ የፈለገውን ያህል ገንዘብ ቢያፈሱ፤ ያሻቸውን ያህልም ተጽእኖ ቢያሳድሩ አንድ ቀን እጃችን ላይ መውደቃቸውና እየተለማመጡ መኖር አይቀርላቸውም፡፡ እናም የህዳሴው ግድብ መጠናቀቁ አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበው፣ ከመሰሪ ስራቸውና ከከንቱ ፕሮፓጋንዳቸው ተቆጥበው፣ ሁለቱን ሀገሮችና ህዝቦች የሚያስተሳስሩ የጋራ ፕሮጄክቶችን መንደፍና በጋራ ለመስራት ትኩረት ማድረግ ለሁላችንም የሚጠቅም መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባቸዋል።
በመጨረሻም አንድ ነገር አስረግጬ ማለት ወደድኩ፡፡ ይኸውም፡- በ2011 የፀደይ አብዮት በግብጽ ባይቀሰቀስ ኖሮ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ “ፕሬዝዳንት” ሊሆኑ አይችሉም ነበር፡፡ የህዳሴ ግድብ ግን የፀደይ አብዮት በግብጽ ተቀሰቀሰም አልተቀሰቀሰ መጀመሩ የሚያጠራጥር አልነበረም፡፡
እሬቻን በደስታና በቅሬታ አሳለፍነው
በመስከረም ወር ከነበሩት ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ውስጥ “እሬቻ” ተጠቃሽ ነው፡፡ አንዳንድ የኦሮሚያ አክቲቪስቶችና ኦዴፓ እንደሚሉት፤ እሬቻ በአዲስ አበባ (ሆራ ፊንፊኔ) ይከበር ነበር:: “የነፍጠኛው ስርዓት” በወሰደው እርምጃ ተከለከለ፡፡ እነሆ ከ150 ዓመታት በኋላ ዘንድሮ እንደገና ተከበረ፡፡ በበዓሉ ዋዜማ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሲስተጋባ የነበረው “እሬቻ የሰላም፣ የፍቅርና የመቻቻል የምስጋና በዓል ነው” የሚል መልእክት ነበር፡፡
እሬቻ ባህል ነው፣ ሃይማኖት ነው፣ አምልኮ ነው፣ ፖለቲካ ነው… በሚለው ላይ በበኩሌ የጠራ ግንዛቤ ለመጨበጥ አልቻልኩም፡፡ አንዳንዱ “እሬቻ የዋቄ ፈታ ሃይማኖት የአምልኮ ስርዓት ነው” ሲል፤ ሌላው “የለም ዩኔስኮ የመዘገበው የሀገር ሀብት የሆነ የባህል ቅርስ ነው” ይላል፡፡ ይሄ ሁሉ ያልጠራ ነገር ባለበት ሁኔታ የበዓሉ እለት ደረሰ፡፡ ታዳሚዎች ከየአካባቢው መጥተው አዲስ አበባ ከተሙ፡፡ የአዲስ አበባ ህዝብ ስራውን ዘግቶ በፍቅር ተቀበላቸው፡፡ በበዓሉ እለት የክብር እንግዳ የነበሩት የኦሮሚያ ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ንግግር አደረጉ፡፡ ከዚያ ሁሉ ንግግራቸው “ነፍጠኞች በሰበሩን ስፍራ ሰበርናቸው” የምትለዋ ዐረፍተ ነገር የብዙዎችን ቀልብ ሳበች፡፡ ቀልብ መሳብ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶችን አስቆጣች፡፡ በመገናኛ ብዙሃን ሲስተጋባ የነበረው “እሬቻ የሰላም፣ የፍቅርና የመቻቻል የምስጋና በዓል ነው” የሚለው መልእክት መና ቀረ፡፡ እናም እሬቻን በደስታና በቅሬታ አሳለፍነው!
ጭብጨባ መጥፎ ነገር ነው፡፡ ፖለቲከኛ ጭብጨባ ከሰማ የመሪነት በትሩን ይወረውርና ስሜት ውስጥ ገብቶ ተገቢ ያልሆነ ድርጊትና አፍ እላፊ ንግግር በማድረግ ያላጨበጨቡለትን ወገኖች ያስቀይማል፡፡ ጫጫታው በርዶ፣ ጭብጨባው ቆሞ እሱም ወደ መደበኛ “እሱነቱ” ሲመለስ ደግሞ ፀፀት ላይ ይወድቃል:: በእሬቻ በዓል ላይ ላጨበጨቡለትም ላላጨበጨቡለትም ፕሬዝዳንት ለሆነው ለአቶ ሽመልስ ይህ ሁኔታ የገጠመው ይመስላል፡፡ አንድ የፖለቲካ መሪ ንግግር ወደሚያደርግበት መድረክ ከመውጣቱ በፊት በርካታ ሁኔታዎችን ማገናዘብና ቢችል ሁሉንም ለማስደሰት ባይችል ብዙሃኑ ሳይቀየም ወደ ቤቱ እንዲመለስ ለማድረግ መጣር ይጠበቅበታል ብዬ አስባለሁ፡፡
በዚህ ሁሉ ሁካታ ውስጥ ሆኜ የአቶ ሽመልስን ንግግር ያየሁት በሌላ አቅጣጫ ነው:: በዚህ ወቅት “የኦሮሞ ህዝብ” (በተለይም ብዙኃን ወጣቶች) በአክቲቪስቶች ቁጥጥር ስር መሆናቸው ይስተዋላል፡፡ አቶ ሽመልስ ይህንን “የአክቲቪስት ጀሌ” የሆነ ወጣት “አለሁልህ፣ ከጎንህ ነኝ፣ ከዘመናት በፊት ቅድመ አያቶችህን ያሸማቀቁ ነፍጠኞችን ሰብሬልሃለሁ…” በማለት ወደ ኦዴፓ ለማምጣት የፈለጉ ይመስለኛል:: አሳዛኙ ነገር የእርሳቸውን ስህተት አሰፍስፎ የሚጠባበቅ ሌላ ኃይል በወዲያኛው ጫፍ መኖሩን ልብ አለማለታቸው ነው፡፡ “ነፍጠኛ ተባልኩ” በማለት ጩኸት ያሰማውን ወገን አስቀይመውም ቢሆን መላውን የኦሮሞ ወጣት “ከአክቲቪስት ጀሌነት” ነፃ ማውጣት ችለው ከሆነ እሰየው ነው፡፡ ካለበለዚያ ትልቅ የፖለቲካ ኪሣራ ሆኖ ይታየኛል፡፡
ይህንን በዚሁ እንለፈውና ስለ እሬቻ አንድ ነገር ለማንሳት ወደድሁ፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች እሬቻን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ የመጡ ዜጎች ብዛት በሚሊዮን የሚቆጠር እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነዚያ የበዓሉ ታዳሚ ዜጎች አንዲት ኮሽታ ሳያሰሙ፣ የመጡበትን ዓላማ ፈጽመው ሳያደርሱ ወደየመጡበት መመለሳቸው ትልቅ አክብሮት ሊቸረው ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡ በዓሉን ሊያከብሩ የመጡትና ኮሽታ ሳያሰሙ የተመለሱት ብቻ ሳይሆኑ በበዓሉ ማክበሪያ አቅራቢያ የሚኖሩ፣ በዓል ለማክበር የመጡ እንግዶችን በስርዓት ተቀብለው፣ ያላቸውን አካፍለው፣ ሥራቸውን ዘግተው፣ ምቾታቸውን መስዋእት አድርገው ስልጡን ከተሜነታቸውን ያረጋገጡ አዲስ አበቤዎችም አክብሮት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አምናለሁ፡፡
ከእሬቻ ጋር ተያይዞ አቶ ሽመልስ ያደረጉትን ንግግር መሰረት አድርገው በማህበራዊ ሚዲያ የጽሁፍ መልእክት ሲለዋወጡ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደኣና አቶ አሰማኸኝ አስረስ (ሁለቱም የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው) የፈጸሙት ድርጊት አሳዛኝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: እነዚህ “ትልልቅ” ባለስልጣናት አንዱ ደጋፊ ሌላኛው ነቃፊ መሆናቸው አይደለም ችግሩ:: ከመሪ (Leader) በማይጠበቅ ሁኔታ እንደ ቀደምት የአራዳ ሴተኛ አዳሪዎች ማዶ ለማዶ ሆነው ነገር መወራወራቸውን ሳይ “እነዚህ ናቸው የእኔ መሪዎች?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ገፋፍቶኛል፡፡ እነዚህ ወንድሞች የታላቅ ህዝብ “መሪዎች” ሳይሆኑ ትልቁን ስዕል ማየት የማይችሉ የመንደር “ውሪዎች” ሆነው ነው የታዩኝ፡፡ በበኩሌ እነዚህ “ጓዶች” የኢትዮጵያን ህዝብ ስልጣን ለመሸከም የደነደነ ትከሻ የሌላቸው፣ ሆደ ሰፊነት የራቃቸው፣ የመሪነት ብቃት የጎደላቸው ሆነው ነው ያገኘኋቸው:: እንደኔ እንደኔ ሁለቱም ከያዙት ስልጣን ሊወርዱና ዘረኝነትንና ጠባብነትን ሊታከሙ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዤ አንዲት ነጥብ ጠቅሼ ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትም ይሁኑ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች አሊያም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ካደረጉት ንግግር ውስጥ አንዲትን ቃል መዝዞ በማውጣት ተናጋሪውን ለማሳጣት ላይ ታች በማለት ጊዜና ጉልበትን ማባከን አግባብነቱ አይታየኝም፡፡ በሌላ በኩል፤ አንድ ሰው “ነፍጠኛ” ብሎ ሲናገር “ይሄ ነገር እኔን ነው” ብሎ መነሳት፣ ሌላው ሰው “የቀን ጅብ” ሲል “የቀን ጅብ ያለው እኔን ነው” ብሎ መደንበር፣ አንዷ በጻፈቺው ግጥም “መንጋ” ስትል “እኔ ነኝ መንጋው!?” ብሎ ጫጫታ መፍጠር፣ ወዘተ. ተገቢ አይደለም፡፡
የዶ/ር ዐቢይ የኖቤል ሽልማት
የመስከረም ወር በመገባደድ ላይ እያለ ከሰማናቸው ሀገራዊ ጉልህ ጉዳዮች ውስጥ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ተሸላሚ መሆን ተጠቃሽ ነው፡፡ በበኩሌ ዶ/ር ዐቢይ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው ሽልማቱን ራሴ ያገኘሁት ያህል አስደስቶኛል፡፡ አንዳንዶች “ዶ/ር ዐቢይ ለምን ተሸለሙ” ሳይሆን ለሽልማት የሚያበቃ፣ በቁጥር በዛ ያለ የሰላም ተልእኮ አልፈጸሙም ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡ እነዚህ ወገኖች ያልገባቸው ብዙ የሰላም ተልእኮን ማሳካት ሳይሆን አንዲት ትንሽ ነገር ለሽልማት ልታበቃ የምትችል መሆኑን አለመገንዘባቸው ነው፡፡
ባለፉት 26 ዓመታት በማረሚያ ቤት የነበሩት የህሊና እስረኞች ብቻ ሳይሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሰፊው፣ አጥር-አልባ እስር ቤት ውስጥ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ እናም ሞት የተፈረደበትን ጨምሮ 100 ሚሊዮን ህዝብን ከእስር ከመፍታት በላይ የሰላም የኖቤል ተሸላሚ የሚያደርግ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡
ዶ/ር ዐቢይ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው በይፋ ከተነገረ በኋላ ሁለት አስገራሚ ነገሮችን አስተውያለሁ፡፡ አንደኛው ያስገረመኝ ነገር “ይህ ሽልማት ለዶ/ር ዐቢይ አይገባቸውም” በሚል መንፈስ የተጀመረው ፊርማ የማሰባሰብ “የክፋት” ዘመቻ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይን በፖለቲካ መቀናቀን አንድ ነገር ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይን በምቀኝነት መንፈስ መቀናቀን ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ያለው ዘመቻ ከምቀኝት ውጪ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንዳችም ፋይዳ አያስገኝም:: ሁለተኛው የገረመኝ ነገር “ዶ/ር ዐቢይ ለኖቤል ሽልማት እጩ እንዲሆኑ የጠቆምኳቸው እኔ ነኝ፣ የለም እከሌ ነው” የሚለው ማህበራዊ ሚዲያውን ያጨናነቀ እሰጥ አገባ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ዘመቻ የሥራ ፈቶች ከንቱ ዘመቻ ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም ባይ ነኝ፡፡
‹‹ቄሮ የአባቱ እርሻ በአረም ተውጦ መንገድ በመዝጋት ላቡን ያፈሳል››
የመንገድ መዝጋት ዘመቻ ሰሞኑን ከሰማናቸውና የትዝብት ዓይናችን ካረፈባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ መግቢያ አቅራቢያ ባሉ ከተሞች አካባቢ መንገድ በመዘጋቱ የሀገሪቱ የትራንስፖርት ፍሰት እክል ገጥሞት እንደነበር ሰምተናል፡፡ ይህንን ማን አደረገ ሲባል “ቄሮ” የሚል መልስ እንሰማለን:: ይህንን ሃሳብ ሳወጣና ሳወርድ በነበርኩበት ወቅት አንድ የስራ ባልደረባዬ ወደ ቢሮዬ መጣ፡፡ ብዙ ነገር ስናነሳ ስንጥል ከቆየን በኋላ ስለ መንገድ መዘጋት የሰማሁትን ነገርኩት፡፡ ይህ የሥራ ባልደረባዬ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ሲሆን፤ እሱም ያየውንና የሰማውን ከገለጸልኝ በኋላ፤ “ቄሮ የአባቱ እርሻ በአረም ተውጦ፣ አዝመራው በወፍ እየተበላ እሱ መንገድ ለመዝጋት ከአቅሙ በላይ የሆነን ግንድ በማንከባለልና ድንጋይ በመሸከም ላቡን ያፈሳል:: ጊዜውንና ጉልበቱን ያባክናል፡፡ ይህ የሚገርም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ሊቆጣጠሩ ይገባል…” የሚል ትዝብቱን ነገረኝ፡፡
ይህ ለውጥ እንዲመጣ የህይወት ዋጋ የከፈሉት ወጣቶች ዓላማ በሀገራቸው ፍትህ እንዲረጋገጥና እኩል ተጠቃሚነት እውን እንዲሆን እንጂ ወንጀል እንዲስፋፋ አልነበረም:: እናም በወንጀል የተጠረጠሩ ሦስት፣ አራት፣ ወይም መቶ ሰዎች ስለታሰሩ ‹‹እነዚያ ሰዎች ካልተፈቱ ሞቼ እገኛለሁ›› በሚል መንፈስ መንገድ መዝጋትና መንግስትን ወጥሮ መያዝ የወንጀለኞች ተባባሪነትና ሽፍትነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ስም ሊሰጠው አይችልም:: የሚገርመው ነገር የክልል “ልዩ ኃይል” አባላት የዚህ ህገ ወጥ ድርጊት ተባባሪ ሆነው መታየታቸው ነው፡፡
ወንጀልን ይከላከላል የሚል እምነት የተጣለበት ቄሮ የሽፍታ ተባባሪ ሆኖ መገኘት ዜጎችን ሁሉ ሊያሳስብ የሚገባው ስጋት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ድርጊት በመንግስት ውስጥ መንግስት (A state within a state) የተፈጠረ መሆኑን የሚያመላክት አደገኛ አዝማሚያ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3412 times