Saturday, 12 October 2019 12:24

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(0 votes)


                               “በፍቅር ያልተማረ በችግር ይማራል”
                                   
           ‹‹ሲርብህ ብላ፣ ሲደክምህ አረፍ በል፡፡ የምትኖረው አንዴ ነው፡፡ በትክክል ካሰብክ አንዴ መኖር በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ካስመሰልክ ግን እሷም ገሃነም ትሆንሃለች›› ይላሉ ሊቃውንት፡፡
አንድ የድሮ ቀልድ ነበረች፡- ‹‹ሳይኖሩ መቆጠብ ሞትን ማፋጠን ነው›› በሚል መርህ፤ የአለም ኢኮኖሚስቶች ፎረም ስለ ቁጠባ ምንነት ለማጥናት ጥያቄ አዘጋጅቶ ‹ድሃ› አገሮችን  ያወዳደረበት መድረክ፡፡ አንደኛ ኢትዮጵያ፣ ሁለተኛ ቡልጋሪያ፣ ሶስተኛ አርሜኒያ በመውጣት አሸነፉ ተባለ፡፡ ጥያቄው፡- ‹‹አንድ ኪሎ ማርጋሪን በየቀኑ እየተበላ በስንት ቀን ያልቃል?›› የሚል ነበር፡፡
ሶስተኛ የወጣችው አገር ተወካይ የመለሰው ‹‹አንድ ኪሎ ማርጋሪን በየቀኑ እየበላሁ አንድ ወር ያቆየኛል›› በማለት ነበር፡፡ በምላጭ ውፍረት ልክ በስሱ እየቆረጠ ዳቦው ውስጥ በመጨመር እንደሚበላም በዝርዝር አስረዳ። ሁለተኛው ደግሞ የመጀመሪያው ሰው ከሚበላው ማርጋሪን ግማሹን ያህል አፍልቶ ዳቦው ላይ በስፕሬየር እየረጨ፣ ጠዋትና ማታ ቢበላ፤ ለአንድ ወር የሚበቃው መሆኑን ተናገረ፡፡ አንደኛ የወጣው ሰው ተራ ሲደርስ፣ አንድ ኪሎ ማርጋሪን ጠዋትና ማታ በልቶ፣ ከአንድ ወር በኋላ አንድ ኪሎ ማርጋሪን እንደሚተርፈው በመግለጽ ነበር ውድድሩን ያሸነፈው፡፡…
‹‹እንዴት?›› ብለው ሲጠይቁት፤ ‹‹ቴክኒኩን›› አስረዳቸው፡፡ ምንድነው ቴክኒኩ?
* * *
ወዳጄ፡- ብዙ በተማርክ፣ ብዙ በኖርክና ብዙ ባወቅህ መጠን በማታውቀው ዓለም እንደምትኖር ትረዳለህ፡፡ ሶቆራጦስ እንዳለው፤ ‹አለማወቅን ማወቅ በራሱ እንደማወቅ ፀጋ ሊቆጠር ይገባል፡፡ ቢያንስ ‹‹የኔ ልክ ነው፣ ያንተ ልክ አይደለም፡፡›› እያልክ ከወንድሞችህ ጋር አትላተምም፡፡ በንፅፅሮሽ ሕግ አንተ ‹ትክክል› የምትሆነው ሌላው ሲሳት ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በበኩሉ ‹እኔ ትክክል ነኝ› ካለ፣ አንተ ተሳስተሃል ማለቱ ነው፡፡ ነገር ግን ‹ሁሉም ልክ›፣ ‹ሁሉም ስህተት› የሚሆንባቸው አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ ችግሩ የመረዳት፣ የመመርመርና የመገንዘብ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ለዚህ ነው የሚጠናወትህ፡፡ ዕውነት ደግሞ ‹እውነት› ያልሆነ ነገር ተቃራኒ ነው፡፡
አንድ ጥሩ መጽሐፍ አንብበህ ስትጨርስ ሌላ ለመጀመር ትቸኩላለህ፡፡ ያንን ስትጨርስ ደግሞ ሌላ… እንደገና ሌላ፡፡ ጥምህ አይቆርጥም:: ዲፕሽንዴ እንደዘፈነው ‹ፍለጋህ አይቆምም:: አንድ ቀን ግን መልሱን ታገኛለህ፡፡… ከተረት ውስጥም ቢሆን፡፡…
ሰውየው ከፊት ለፊቱ የቆመውን ድንጋይ ለብዙ ዘመናት ሲያይ ቆይቶ ‹‹ይኼ ነው የኔ አምላክ፣ የማይበገረው፣ የማይሸነፈው›› ሲል አሰበ አሉ፡፡ ዝናብ ዘነበ፣ መሬቱ በጎርፍ ሲጥለቀለቅ ፈራና ዛፍ ላይ ወጥቶ ተረፈ፡፡ ቁልቁል ሲመለከት ድንጋዩን ውሃ ውጦታል፡፡ ‹ውሃ ከድንጋይ ይበልጣል› ብሎ ሀሳቡን ቀየረ፡፡ ሃይለኛ ፀሐይ ወጣ፣ ውሃው ተነነ፡፡ ፀሐይ ከውሃ የበለጠ ጉልበት አለው በማለት ወደ ፀሐይ አደላ:: ዳመና መጣ፣ ፀሐይን ጋረደበት። ስለ ደመና ጉልበት አስቦ ሳይጨርስ ከች አለ፡፡ ደመናውን አባርሮ ዛፎቹን ገንድሶ ሄደ። ድንጋይ ግን እንደ ቆመ ነበር፡፡ ሰውየው ግራ ገባው፡፡ በውጭ የሚያየው ነገር… እየሄዱ መምጣት፣ እየመጡ መሄድ ሆነበት፡፡ አሸናፊና ተሸናፊ የሌለበት። ዓይኖቹን ጨፍኖ ወደ ውስጥ ተመለከተ፡፡ መልሶ ሲከፍታቸው ድንጋይ ተፈርክሷል፡፡ እስከ ዛሬ ተሳስቻለሁ፤ የሁሉም አሸናፊ ‹ቀን› ነው - አለ ሰውየው፡፡ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ ያ ቀን፣ እንደ ሌሎቹ አልተመለሰም፡፡ ቀን አይደገምም። አሁን በትክክል ማሰብ ጀመረ፡፡ ከፊቱ የተሰለፉትን ስምንት ቢሊዮን ሰዎችና ከሁዋላው እስከ አዳም ድረስ የተቆላለፉትን ነገደ አዳም ተመለከተ፡፡ ‹‹እኔም ይህንን ቦታ እለቃለሁ፣ የሚቀረው ትዝታ   (Memory) ብቻ ነው። ትዝታ የሚኖረው ደግሞ አእምሮ ስለማይሞት ነው፡፡ ስለዚህ የኔ አምላክ ‹አእምሮ› ነው›› በማለት ጮክ ብሎ ለሰልፈኞቹ ተናገረ፡፡ እነሱም አእምሮ ለተባለው ነገር በየቋንቋቸው ስም አወጡለት፡፡ አንዳንዶቹ ዩኒቨርሳል ማይንድ፣ የተፈጥሮ ሕግና ሥርዓት (Law and order of nature) እያሉ ሲጠሩት፤ አንዳንዶቹ ጐድ፣ ቡድሃ፣ አላህ፣ ህሊና እውነት፣ እግዜር ወዘተ አሉት፡፡ ልክ መሆንና አለመሆን፣ ትንሽነትና ትልቅነት የለም። ትንሽነትና ትልቅነት መልካም የመሆንና ያለ መሆን በትክክል የማሰብና ያለማሰብ ጉዳይ ነው፡፡ የመጠንና የመበላለጥ አይደለም፡፡   
ወዳጄ፡- የመጠን ጉዳይ ሲነሳ፣ የጆርታን ስዊፍት “ጎሊቨርስ ትራቭል እና የቮስተር “ማይክሮማ›› የተባሉ መጻሕፍት አሉኝ:: ጐሊቨር በጉዞው ላይ ሁለት ዓይነት ሰዎች አጋጥመውታል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ከጉንዳን ያነሱ ሲሆኑ ሁለተኛዎቹ ደግሞ እሱ ራሱ በንጽጽሮሽ ጉንዳን አክሎ የታየበት ናቸው፡፡ ታላቁ ቮስተርም ተመሳሳይ ነገር ይነግረናል፡-
ሳይረስ ከምትባለው ትልቋ ኮከብ ነዋሪዎች አንደኛው ለጉብኝት ወደ ምድር ያቀናል:: ሰውየው ቁመቱ 500,000 ጫማ ነው፡፡ እግረ መንገዱን ስተርን በምትባለው ፕላኔት ላይ የሚኖር፣ የሱን ሩብ ያህል ቁመት ያለው ጓደኛ ያፈራና ይዞት ይመጣል፡፡ ጓደኛሞቹ ሜዲትራኒያን ባህርን ሲያቋርጡ፣ የባህሩ ጥልቀት የሳይረሳዊው ሰው ከቁርጭምጭምቱ በታች ነበር፡፡ በጨዋታቸው መሀል ግዙፉ ሰው ሳተርናዊውን፡-
‹‹ስንት የስሜት ህዋሳት አሏችሁ?›› በማለት ጠየቀው፡፡
ሳተርናዊውም፤ ‹አለን› የሚያሰኝ አይደለም:: ሰባ ሁለት ብቻ ነው›› አለው
‹‹መካከለኛ ዕድሜያችሁስ?››
‹‹ምን ዕድሜ ይባላል? ብልጭ ድርግም ነው፣ እንደተወለድን እንሞታለን ማለት ይቀላል፣ ለመማር እንኳ አልታደልንም፡፡ መካከለኛው ዕድሜያችን 15,000 ዓመት ነው›› …. ጓደኛሞቹ እየተጨዋወቱ ውቅያኖሱ መሃል ሲደርሱ፣ ብዙ ሰዎችን የጫነች መርከብ እግራቸው ስር ስትንኮራኮር ተመለከቱ፡፡ ሳይረሳዊው ብድግ አድርጎ የግራ እጅ አውራ ጣቱ ላይ አስቀመጣት:: በተፈጠረው ነገር የመርከቢቱ ተጓዦች ደነገጡ:: ቀሳውስቱ ሰይጣን የሚያባርር ድግምታቸውን ሲያነበንቡ፣ ፈላስፋዎቹ የግራቪቲ ህግ እንዴት ሊሻር እንደሚችል ለማወቅ መጠየቅና መከራከር ያዙ፡፡ ሳይረሳዊው እንደ ደመና ከሸፈናቸው መንገደኞች ጋር ‹ሳሂብ› ሁኖ ከልቡ ያወራ ጀመር፡፡
‹‹ታላቁ አምላክ በአምሳሉ ለፈጠራቸው፣ ዕድለኛ የሆናችሁትን እናንተ የምድር ሰዎች ስላገኘሁዋችሁ ደስ ብሎኛል›› አላቸው…
‹‹አይሂሂ… ምኑን ዕድለኛ ሆንን? ምንስ ሰላም አለን? በየቦታው ጦርነት ነው፡፡ በዚህ ቅጽበት እንኳ ይሄኔ አንድ ቦታ፣ አንድ ሰው ሌላውን ይገድላል፣ ያፈናቅላል ወይም ሌላ ጉዳት እየፈፀመበት ነው፡፡ ወደን እንዳይመስልህ፤ በመርከብ ታጭቀን ከቦታ ቦታ የምንዘዋወረው›› አሉት፡፡
‹‹ይኼን መስማት ያሳዝናል፣ ራመድ ብዬ ልጨፈላልቃቸው እንዴ… እነዚህን አረሞች?›› በማለት ጠየቀ፤ ሳይንሳዊው ተቆጥቶ፡፡
‹‹ኧረ ምን በወጣህ? ጣጣቸውን ሲጨርሱ አደብ ይገዛሉ፡፡ በፍቅር ያልተማረ በችግር ይማራል›› አለው፤ ከፈላስፋዎቹ አንዱ፡፡ በዚሁ ተሰነባበቱና፣ እንግዶቹ በዝና የሚያውቋት ምድር እንደ ጠበቋት ባለመሆኗ እያዘኑ ጉዟቸውን ወደ ሌላ አቅጣጫ አደረጉ፡፡ እኛም እያመሰገንን ወደ ቀልዳችን ተመለስን፡፡  
* * *
ቅድም እንዳልነው፤ የኛን ተወካይ አንደኛ ለመውጣት ያስቻለው፣ ለአንድ ወር በየቀኑ የዳቦውን ክፋዮች እያነሳ ከፊት ለፊቱ ካስቀመጠው የቆርቆሮ ማርጋሪን እያሳየ ደረቁን ዳቦ ስለሚበላ፣ አንድ ኪሎ ማርጋሪን እንደሚተርፈው በማሰመኑ ነበር፡፡ በማስመሰል አንደኛ፣ በመኖር መጨረሻ ሆነን ተሸለምን!!
ታላቁ ማህተማ ጋንዲ፡- ‹‹ነገ እንደምትሞት እያሰብክ ኑር፣ ዘለዓለም እንደምትኖር ሆነህ ተማር›› ይለናል፡፡
ሰላም!!

Read 1287 times