Print this page
Saturday, 12 October 2019 12:04

ኤሊውድ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• በሁለተኛ ሙከራው ቪዬና ላይ ይሮጣል፤ ከባለፈው ሙከራ በ26 ሰከንዶች መፍጠን ይኖርበታል፡፡
          • 41 አሯሯጮች ተመድበዋል፤ ውሃና ኤነርጂ መጠጥ በብስክሌት ይቀርብለታል፤ ፊት ለፊት መንገዱን እያበራለት የሚሄድ መኪናም አለ፡፡
          • ‹‹…ጨረቃን እንደረገጠው የመጀመርያ ሰው መሆን ነው ››
          • በዓመት ከ300 ቀናት በላይ ልምምድ ያደርጋል፤ በሳምንት እስከ 200 ኪሎ ሜትር እየሮጠ
          • በሩጫ ዘመኑ 12 ማራቶኖችን ሮጦ 11 አሸንፏል፤ ከ5 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ አግኝቷል፡፡


           ኬንያዊው የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤትና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ኤሊውድ ኪፕቾጌ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በያዘው እቅድ  ሁለተኛውን ሙከራ በቪዬና ከተማ ላይ ሊሮጥ ነው፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ለሰው ልጅ ምንም አይነት እንቅፋት አይኖርም በማለት የተናገረው ኪፕቾጌ፤ የሰው ልጅ የላቀ ብቃትን በተግባር ለማስመስከር ዝግጁ ነኝ  ብሏል:: የኤሊውድ ኪፕቾጌን ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት ሙከራ የዓለም ሚዲያዎች በከፍተኛ ትኩረት እየዘገቡት ሲሆን፤ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ይህ ታሪካዊ የስፖርት ውድድር ለመታደም  ወደ ቪዬና ከተማ እንደሚያቀኑ ታውቋል፡፡ በማራቶን የሚሰራውን ታሪክ የኬንያ መንግስት ተወካይ በስፍራው ተገኝቶ መታደም እንደሚገባው የኬንያ ሚዲያዎች ባለፈው ሰሞናት በመዘገብ ተፅእኖ ሲፈጥሩ ነበር፡፡ ኪፕቾጌ ምንም እንኳን በህጋዊ የማራቶን ውድድር ላይ ባይሆንም በቪዬና ከተማ በተዘጋጀው ልዩ ሩጫው ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚሳካለት ከሆነ፤ ለአትሌቲክስ ስፖርት ከሚፈጥረው ክብርና ሞገስ ባሻገር ለሳይንቲስቶች፤ ለስፖርቱ ኤክስፐርቶች እና ባለሙያዎች፤ ለስፖርት መጠጥ እና ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ከፍተኛ ምስራች ይሆናልም ተብሏል፡፡
‹‹የማራቶን ሩጫ በበርሊንና በቪዬና ሁለት የተለያዩ ውድድሮች ናቸው፡፡ በበርሊን ማራቶን የምሮጠውና የሮጥኩትም የዓለም ሪከርድ ለማስመዝገብ ነው:: ቪዬና ላይ ግን አዲስ ታሪክ ለመስራት፤ ጨረቃን እንደረገጠው የመጀመርያ ሰው ለመሆን ነው›› የሚለው ኪፕቾጌ‹‹ በመናፈሻ ውስጥ አበቦች አሉ አረሞች አሉ፤ ቪዬና ላይ ስለአበቦቹ ነው የምናወራው፤ መላው ዓለምን የሚያስደስት ልዩ ብቃት ለማሳየት ተስፋ አድርገናል›› ሲልም ተናግሯል::
በዓመት ከ300 ቀናት በላይ በልምምድ እና በውድድር የሚያሳልፈው የ34 ዓመቱ ኤሊውድ ኪፕቾጌ፤ የማራቶን ዘመኑን በከፍተኛ ስኬታማነት እያሳለፈ  መሆኑ ልዩ ስብዕና እንዳጎናፀፈው የተለያዩ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች የመሰከሩለት ሲሆን ስፖርቱን ካቆመ በኋላ ለመላው የዓለም ትውልድ ተምሳሌት በሚሆን ተግባር ለመስራት ያለውን ፍላጎት ለዚሁ ዓለም አቀፋዊ ጀግንነቱ መረጃ አድርገው ይጠቅሳሉ፡፡ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት መደበኛ ልምምዱን ባለፈው የውድድር ዘመን በልዩ ትጋት በመስራት መቆየቱን የገለፀው ኪፕቾጌ ለጥንካሬ እና ለፍጥነት የሰራቸው ልምምዶች እና የስልጠና መርሃግብሮች ለማንኛውም ማራቶን ከሚያደርገው ዝግጅት ጋር እንደሚመሳሰሉ  ተናግሯል፡፡ ከልምምድ ባሻገር ኪፕቾጌ ለቪዬና ሩጫው ባደረገው ዝግጅት ከሌሎች ማራቶኒስቶች የላቀ ብቃት አሳይቶበታል የተባለው በሳምንት ከ200 እስከ 220 ኪሜ እየሮጠ መሆኑ  ነው፡፡ በቪዬና ከተማ ለልዩው የማራቶን ሩጫው የሚሆነው ጎዳና በጣም ምቹ እና የተደላደለ መሆኑ፤ የወቅቱ የአየር ሁኔታ ተስማሚ እንደሆነ መተንበዩ እንዲሁም የምርጥ አሯሯጮች በውድድሩ ላይ መሳተፍ የኪፕቾጌን ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት ተስፋ ያለመልመዋል:: ውድድሩ በሚካሄድበት ወቅት የቪዬና ከተማ ላይ ሙቀቱ እስከ 12 ዲግሪ ሴልሽዬስ እንደሚሆን መተንበዩ ሙቀት በሩጫ ላይ የሚፈጥረውን ጫና እንደሚቀንሰው እየተገለፀም ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የሚነሳው የቪዬናውን ሩጫ ያዘጋጁት 41 አሯሯጮች መመደባቸው ነው:: አሯሯጮቹ ኪፕቾጌ ቋሚ የአሯሯጥ ፍጥነት እንዲኖረው እያንዳንዱን ዙር ሁለቴ የሚዞሩለትና ከፊቱ የሚመጣውን የንፋስ ግፊት ከ50 እስከ 70 በመቶ የሚቀንሱለት ሲሆን ከመካከላቸው 14 የሚሆኑት በቅርቡ በተካሄደው የዶሃው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳተፉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኢትዮጵያዊው የ5ሺ ሜትር የዓለም ምርጥ አትሌት ሰለሞን ባረጋ አንዱ ነው:: በሌላ በኩል በሩጫው ላይ ልዩ የኤነርጂ መጠጥ  እና የተፈጥሮ ውሃን ከየጠረጴዛው በማንሳት እንዳይንቀራፈፍ ተብሎ ልዩ አሰራር የተፈጠረ ሲሆን፤ በየ3.1 ማይሎች ርቀት አስፈላጊውን መጠጦች የሚያቀብለው ብስክሌት እንደሚኖርና ከፊት የሚመራው መኪና በመሮጫው ጎዳናው ላይ ብርሃን እያደረገለት እንዲሮጥ ተመድቦለታል:: ከናይኪ ኩባንያ የሚቀርቡለት ዘመናዊ የመሮጫ ጫማ፤ ልብሶች እና ሌሎች ትጥቆችም አስተዋፅኦ እንደሚኖራቸው ሲጠበቅ፤ የናይኪ Vaporfly የመሮጫ ጫማ ከ2ዓመታት በፊት ለዚሁ ዓላማ ከተመረተለት በኋላ ባስመዘገበው ውጤት ብቻ ሳይሆን የዓለም ማራቶን አምስት ፈጣን ሰዓቶች በእነዚሁ ትጥቆች መሳካታቸው በማስረጃነት ተጠቅሷል፡፡
ከ2 ዓመታት በፊት Breaking2 በሚባለው ፕሮጀክት ከናይኪ ጋር በመስራት በጣሊያኗ ከተማ ሞንዞ ላይ የማራቶን ርቀቱን 2 ሰዓት ከ025 ሰከንዶች በሆነ ጊዜ ለመግባት የቻለው ኤሊውድ ኪፕቾጌ በቪዬናው የማራቶን ሩጫ ላይ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚቀሩት 26 ሰከንዶች ማራገፍ ይኖርበታል፡፡ በተያያዘ በቪዬና ለሁለተኛ ጊዜ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የሚያደርገውን  ሙከራ አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ናቸው፡፡ ኪፕቾጌ  ‹‹ማራቶን ከ2 ሰዓት  በታች መግባት ጨረቃን እንደመርገጥ ነው›› በሚል አስተያየቱ ራሱን ማበረታታቱ የመጀመርያው ተጠቃሽ ሁኔታ ነው:: እንደስፖርት ሳይንቲስት ድረገፅ ጥናታዊ ትንታኔ የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት እስከ 2050 እኤአ መጠበቅ እንደሚጠይቅ የተገለፀ ሲሆን፤ ሜዲሲን ስፖርት ሳይንስ ኤንድ ኤክሰርሳይስ በተባለ ልዩ ህትመት ላይ ደግሞ ያለፉትን 50 ዓመታት የማራቶን ፈጣን ሰዓቶች እነ  ክብረወሰኖች በማስላት  የሰፈረው ጥናት እንደሚያመለክተው ደግሞ ይህ ውጤት ሊመዘገብ የሚችለው ምናልባትም በ2032 እኤአ ይሆናል፡፡ ከ2ዓመት በፊት በሞንዞ ትራክ ላይ ያስመዘገበውን ሰዓት እንዲሁም በቪዬናው ሩጫ የሚያስመዘግባቸው ሰዓቶች በትክክለኛ የማራቶን ውድድር በተለይም በበርሊን ወይንም በለንደን ማራቶኖች ላይ ማስመዝገብ እንደማይችል  በመጥቀስ የኪፕቾጌን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት ሩጫ በስፖርቱ ዓለም ያለውን ህጋዊ ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የከተቱም አሉ፡፡
ኪፕቾጌ 42.195 ኪሜትር የሆነውን የማራቶን ርቀትን ከሁለት ሰዓት በታች ለመግባት ጥረት በሚያደርገው ጥረት ያለፉትን አምስት ዓመታት ከናይኪ ጋር ሲሰራ እንደቆየ ይታወቃል:: ከ2 ዓመታት በፊት በጣሊያን ሞንዛ ከተማ በሞተርስፖርት ትራክ ላይ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት የመጀመርያውን ሙከራ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን  በ30 ደጋፊ አሯሯጮች በመታገዝ 2፡00፡25 የሆነ ፈጣን ሰዓት አስመዝግቦ ነበር፡፡ ይህ   ሰዓት በመስኩ ለሚከናወነው ጥናት ምርምር አስተዋፅኦ ቢኖረውም ትክክለኛ የማራቶን ውድድር ሆኖ እንደ ዓለም ክብረወሰን እውቅና የማያገኝና በፈጣን ሰዓቶች የሰፈረለት አይደለም፡፡በሮም አድርጎት የነበረው በቪዬናም የሚያስመዝገብው ሰዓት ለዓለም የስፖርት ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ ለሰው ልጅ ከፍተኛ ተምሳሌት እና ጀግንነት ሆኖ የሚጠቀስ ታሪክ ቢሆንም እንደ ህጋዊ የዓለም ሪከርድ አይያዝለትም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ The INEOS 1:59 Challenge የሚለውን የኪፕቾጌ ሩጫ ስፖንሰር ያደረገው የእንግሊዛዊው ቱጃር ሰር ጂም ታርክሊፌ  የኬሚካል ኩባንያ ኢኖስ ሲሆን የኬንያው የቴሌኮም ኩባንያ ሳፍሪኮምም ልዩ የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንዳደረገለት ታውቋል፡፡ የኪፕቾጌ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት እቅድ በስፖርቱ ዓለም መነጋገርያ ከሆኑ ሁኔታዎች ዋንኛው ሲሆን በዚሁ ታሪካዊ ስኬት ላይ ሌሎች ታዋቂ የኬንያ እና የኢትዮጵያ አትሌቶች እየሰሩበትም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይ ግን ኤሊውድ ኪፕቾጌ በዓለም የማራቶን ታሪክ የምንግዜም ምርጥ የሚያስበለው ማማ ላይ እየወጣ ይገኛል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ በበርሊን ማራቶን የዓለም ማራቶን ሪከርድን 2፡01፡39 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ኪፕቾጌ በሩጫ ዘመኑ 12 የማራቶን ውድድሮችን በመሮጥ 11 ጊዜ ማሸነፉ፤ ባለፉት አራት ዓመታት  10 ማራቶኖችን አከታትሎ በአንደኛነት መጨረሱ፤ ያለፉትን አምስት ማራቶኖች ሲሮጥ በአማካይ ሰዓት 2፡02፡59 ማስመዝገቡና በትራክ ኤንድ ፊልድ የማራቶን ዓመታዊ ደረጃ በዓመቱ ምርጥ ሰዓት ደረጃ ላይ ላለፉት አምስት ዓመታት በአንደኛ ደረጃ መቀመጡ ይታወቃል፡፡ በ2014 እኤአ የቺካጎ ማራቶንን፤  በ2015፣ በ2016፣ በ2018 እና በ2019 እኤአ የለንደን ማራቶንን ለአራት ጊዜያት፤ በ2015፣ በ2017፣ በ2018 እኤአ የበርሊን ማራቶንን ለሶስት ጊዜያት ማሸነፉም ሌላው የላቀ ስኬት ነው:: የሃምበርግ፤ የለንደንና የበርሊን ማራቶኖች የቦታ ሪከርድ እንደያዘም ይታወቃል፡፡
ከ2015 እኤአ ወዲህ የለንደንና የበርሊን ማራቶኖችን በማፈራረቅ እንደሮጠ፤ በ2016 በኦሎምፒክ ለመሮጥ በርሊንን ከዚያም በ2017 የዓለም ሻምፒዮናን ትቶ በናይኪ ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት ውድድር እንደተሳተፈ የሚያወሱ የአትሌቲክስ ባለሙያዎች ልዩ ዘገባዎች፤ የምንግዜም ምርጥ መሆኑን ለማስመስከር በፈታኞቹ የቦስተን፤ የኒውዮርክ እና የቶኪዮ ማራቶኖች እንዲሮጥ ይመክራሉ፡፡ በዓለማችን ታላላቅ የማራቶኖች ሊግ በ6ቱም ማሸነፍ እንደሚኖርበትም ያነሳሉ:: በአንድ የውድድር ዘመን የቶኪዮ፤ የለንደን፤ የበርሊንና፤ የኒውዮርክ ማራቶኖችን በማሸነፍ ስኬታማ የሆነው ሌላው ኬንያዊ ዊልሰን ኪፕሳንግ ብቻ ነው:: በማራቶን ታሪክ በብዙ ማራቶኖች አከታትሎ በማሸነፍ ከኤሊውድ ኪፕቾጌ ቀጥሎ የሚጠቀሰው 6 ማራቶኖችን አከታትሎ ያሸነፈው የኢትዮጵያው አበበ ቢቂላ ነው፡፡ አበበ በ1960 እኤአ ላይ የመጀመርያውን ማራቶን ያደረገ ሲሆን በሮም ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ የወርቅ ሜዳልያ ሲያሸንፍ የዓለም የማራቶን ሪከርድን አስመዝግቧል:: ከዚያ በኋላ ተጨማሪ 5 ማራቶኖችን በተከታታይ ማሸነፍ የቻለ ሲሆን፤ የመጨረሻ ማራቶን ውድድሩን በ1963 እኤአ ቦስተን ላይ አድርጎ በ5ኛ ደረጃ ጨርሷል:: ከኢትዮጵያ የማራቶን ሯጮች ብዙ ማራቶኖችን አከታትሎ በማሸነፍ የሚጠቀሰው ኃይሌ ገብረስላሴ ሲሆን  5 ማራቶኖች አከታትሎ በማሸነፉ ነው፡፡
ኤሊውድ ኪፕቾጌ በዓለም አትሌቲክስ ያለው ልምድ ከ18 ዓመታት በላይ ሲሆን በተለይ የማራቶን ምርጥ ሯጭ ከሆነ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በሽልማት እና በስፖንሰርሺፕ ከ5 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ መሰብሰቡን መረጃዎች አመልክተዋል:: ከማራቶን በፊት በረጅም ርቅት የአትሌቲክስ ውድድሮች ያን ያህል የገነነ ውጤት አላስመዘገበም:: በ5ሺ ሜትር 12፡46 እንዲሁም በ10ሺ ሜትር 26፡49 ምርጥ ሰዓቶቹ ናቸው፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በ5ሺ ሜትር በ2003 እኤአ የወርቅ ሜዳልያ እንዲሁም በኦሎምፒክ በ2004 እና በ2008 እኤአ የብርና የነሐስ ሜዳልያዎችን ነው ያገኘው፡፡
በነገራችን ላይ ከኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ ባሻገር ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ሊገባ እንደሚችል ስሙ የሚጠቀሰው ከሳምንታት በፊት በበርሊን ማራቶን ሲያሸንፍ 2፡01፡41 በሆነ ጊዜ  የዓለም ማራቶን ሁለተኛውን ፈጣን ሰዓት እና የኢትዮጵያ ሪከርድ ያስመዘገበው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡
በረጅም ርቀት በ5ሺ እና 10ሺ ሜትር፤ በአገር አቋራጭ እና በጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች 24 ጊዜ ተገናኝተው 15 ጊዜ ቀነኒሳ ሲያሸንፍ ኪፕቾጌ 9 ጊዜ ድል ቀንቶታል:: ቀነኒሳ ሶስት የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳልያዎች 16 የዓለም ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳልያዎች እና ሁለት የዓለም ሪከርዶች ሲያስመዘግብ፤ ኪፕቾጌ 1 የወርቅ ሜዳልያ በኦሎምፒክ፤ 1 የወርቅ ሜዳልያ በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም 1 የዓለም ሪከርድ በማራቶን ብቻ ነው ያስመዘገበው፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ አትሌቶች በኦሎምፒክ እና በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 5 ጊዜ ተገናኝተው በ4ቱ ያሸነፈው ቀነኒሳ ነው፡፡

Read 6393 times