Saturday, 12 October 2019 11:55

በሰንደቅ አላማ ቀን ከሪፐብሊኩ ሰንደቅ አላማ ውጪ መያዝ አይፈቀድም ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

  በሰንደቅ አላማ ቀን በሕግ ከፀደቀው የሪፐብሊኩ ሰንደቅ አላማ ውጪ ይዞ መገኘት በሕግ እንደሚያስቀጣ የተገለፀ ሲሆን ዜጎች በሕግ የፀደቀውን ሕጋዊ ሰንደቅ አላማ ብቻ መያዝ እንዳለባቸው ተጠቁሟል፡፡
ከነገ በስቲያ ሰኞ ለ12ኛ ጊዜ የሚከበረው ብሔራዊ የሰንደቅ አላማ ቀን፤ በሕዝብ የሚነሱትን የተለያዩ ጥያቄዎች ለውይይት በማቅረብ፣ በለውጡ ሂደት ላይ ተቀራራቢ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚያስችል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መግለጫ ያመለክታል፡፡
‹‹ሰንደቅ አላማችን የብዝሀነታችን ድምር ውጤትና የአንድነታችን ምሰሶ ነው›› በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የዘንድሮ የሰንደቅ አላማ ቀን፤ የአገሪቱ ዜጎች በልዩነት የሚያነሷቸው ጉዳዮች ላይ የተደራጀ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በሕግ የፀደቀውን የሪፐብሊኩን ሰንደቅ አላማ በማክበርና በእሱ ብቻ በመገልገል ላይ አቋም እንዲይዝ ለማድረግ ያስችላል ተብሏል፡፡
ሰንደቅ አላማው የሉአላዊነት መገለጫና ለሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ አንድነት ምልክት መሆኑ ላይ የጎላ ልዩነት ባይኖርም፣ በአርማው ላይ ግን በሚፈለገው ደረጃ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር አለመቻሉን ያመለከተው መግለጫው፤ እንዲህ አይነት ልዩነቶችም በሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ከሕዝብ ጋር በሚደረግ ውይይት እየተመለሱና መግባባት እየተፈጠረባቸው እንደሚሄድ ይጠቁማል፡፡
የዘንድሮው የሰንደቅ አላማ ቀን፣ በዜጎች መካከል መግባባትና አንድነት የሚፈጠርበትና የጋራ በሚያደርጉ አገራዊ እሴቶች ላይ ውይይትና መግባባቶች ለመፍጠር እንደሚያግዝም ተገልጿል፡፡

Read 1410 times