Tuesday, 08 October 2019 09:29

ሾኬን በ‘ሾኬ’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

“እናላችሁ… አስቸጋሪ ነው፡፡ የምር ግን… በተለይ ይሄ ሊለቀን ያልቻለው የ‘ሀገር ልጅነት’ ሾኬን ማስቀረት ካልቻልን፣ በወንዝ ልጅነት መሳሳቡን ማቆም ካልቻልን፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን ማየት ካልቻልን… ፖለቲካውን እያመሰው ያለው ‘ሾኬ’ ማህበራዊ ኑሯችንንም ማተረማመሱ አይቀርም፡፡ --”
       
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ቶተነሀም ሰባት ቃመ አሉ! (“አሁን ይሄ ወሬ ሆነና ነው ወይ!” የምትሉ ወዳጆች…ከአንዱ ዓረፍተ ነገር ሠላሳ ለማውጣት አልሞክርም…ምንም እንኳን የዘመኑ ዋነኛ  ‘የአዋቂነት’ ምልክት ይኸው ቢመስልም!)  
የምር ግን… ግራ የሚገባ ነገር እኮ ነው፡፡ ምን እናድርግ!...ዘንድሮ እኮ አንድ ነገር ብለው…አለ አይደል…ከሆነ ነገር፣ ከሆነ ቡድን ጋር ተወስዶ መለጠፍ ‘የጋራ መግባባት የተደረሰበት’ የሚሉት አይነት እየመሰለ ነው፡፡ እናላችሁ… ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ ነገና ከነገ ወዲያ ደግሞ አይደለም የራሳችንን ሀሳብ መናገር፣ የሆነ ቡድን ውስጥ ‘ሳይደለደሉ’ የእግዜርን ኦክሲጅን መተንፈስም ሊያስቸግር ይችላል፡፡
እናላችሁ…ሁሉም ነገር ከዶሮዋ አስራ ሁለት ሳይሆን ሀያ ሁለት ብልት ለማውጣት በሚመስል አይነት እየተሰነጣጠቀችና እየተበለተች “ምን ብል ማን ቅር ይለዋል?” አይነት ጥያቄ ወዴት እንደገባ ግራ ገብቶናል፡፡ ቅር የሚለው ሁሉ ቅር ብሎት ስላላሳየን --- ከስኒው ማዕበል ለማስነሳት መሞከር እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ዓይነት የተወሰደ ነው የሚመስለው፡፡
“እንደምን አደርክ?” ያልነው ሰው...አለ አይደል…
“እንደምን አደርክ ሲለኝ ጎንበስ አለማለቱ፣ በእኔ ብቻ ሳይሆን በወገኖቼ ላይ የተደረገ መብት ረገጣ ነው፣” ብሎ አብዮት ስለመቀስቀስ ‘ስልጠና’ ለመውሰድ የአልባንያ ደርሶ መልስ ትኬት ፍለጋ በምናምን ባንክና በ‘ጎፈንድሚ’ “እኔን ያላችሁ እስቲ ልያችሁ” ሊል ይችላል:: (የሀገራችን ፖለቲካ ብዙ ጊዜ የኮሜዲው የመጨረሻው የታችኛው እርከን ላይ የቆመ የሚመስለን ጊዜ በዝቷል ለማለት ያህል ነው፡፡)
እናማ…ትናንት፣ ከትናንት ወዲያ የቅርብ ወዳጅ ከሚባሉ መሀልም ከፊሉ፣ ከዘመኑ ጋር ‘ዘምኖ’ ‘የነገር ብለታ ኤክስፐርት’ ሊሆንባችሁ ይችላል፡፡ ስሙኝማ…ሀሳብ አለን፡፡ የጓደኝነት የአዋጪ ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎች ያስፈልጉናል፡፡ የምር! አሀ…አብዛኛው ወዳጅ ‘ከደረጃ በታች’ እየሆነ ሰዉ ተቸገረ!
“እንትናን ጓደኛ ላደርጋት ስላሰብኩ የአዋጪነት ሥራ እንድትሠሩልኝ ነው፡፡”
ጥናቱ ይሠራና ውጤቱ ይነገራችኋል፡፡ “ባጠናነው መሰረት ልጅቷ ከምንም፣ ከማንም በላይ ገንዘብ ከመውደዷ በስተቀር ሌላ ምንም አይነት ችግር የለባትም፡፡ እንዴት ነው ነገሩ… ‘የችግሮች ሁሉ እናት’ አናቷ ላይ ተክምሮ…“ችግር የለባትም፣” ብሎ ነገር ምን የሚሉት ጨዋታ ነው! ከዚህ በላይ ምን ይምጣ! 
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… በፖለቲካውም፣ በምኑም፣ በምናምኑም ይህ የሾኬ ነገር እኮ ስንቱን ዘጭ እያደረገ መሰላችሁ! ፊት ለፊት አለመምጣቱ ነው ጉዳቱ፡፡ የሾኬ ፖለቲካ ፊት ለፊት አይመጣም:: እንደ ድመት አድብቶ ከኋላ ነው ወጣቶቹ ‘ጠረባ’ በሚሉት ድምጽ የለሽ መሳሪያ ዘጭ የሚያደርገው… በተለይ ፖለቲካው:: የሀሳብ ሙግት ብሎ ነገር እንደሁ እንደ ‘ጎጂ ባህል’ አይነት አጠገቡ የሚደርስ እየጠፋ ነው፡፡
“ወይ ወዳጅ ነህ፣ ወይ ጠላት ነህ፡፡ ሦስተኛ አማራጭ ብሎ ነገር የለም፣” አይነት የድሮው ዙፋን ችሎት፣ የመጨረሻ ፍርድ የመሰሉ ‘ሾኬ’ዎች ሲብስባቸው ማየት አሪፍ አይደለም፡፡
“ሀሳቦቻችንን ጠረዼዛ ላይ እናምጣና እንከራከርባቸው” ብሎ ነገር መብት እንደ መንካት ሊመስል ይችላል! አሀ…የሀሳብ ድርቅ አእምሯችንን ‘ካልሀሪ ዴዘርት’ ባስመሰለበት፣ የምን ወደ ጠረዼዛ፣ ወደ ወንበር ወደ አ… (ይቅርታ… የ‘አርትኦት’ ስህተት ነው!) ወደ ምናምን ማምጣት ነው! ስፓጌቲው በሌለበት የሹካ መአት ቢደረደር ምን ዋጋ አለው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ጊዜው ተለውጦ የዓለም ፖለቲካ ‘ስቴሪኦ’ በሆነበት ዘመን፤ አሁንም ሁሉንም ነገር በ‘ሞኖ’ የምናይ መአት ነን፡፡ ፖለቲካውም በተለያዩ ቀለሞች የተዥጎረጎረ…በምናውቃቸውም፣ በማናውቃቸውም ቀለሞች ተሞልቶ… እኛ ከጥቁርና ነጭ ምልከታ ያልወጣን መብዛታችን አሪፍ አይደለም፡፡
እናላችሁ… ይህ የሾኬ ስትራቴጂ እያንደባለለው ያለው መአት ነው፡፡
ጎበዝ ሠራተኛ ከሆነ፣ “እኔ ሥራዬን መሥራት ብቻ ነው እንጂ እናንተ ጣጣ፣ ፈንጣጣ ውስጥ መግባት አልፈልግም” ያለ ከየት እንደተወነጨፈ በማያውቀው ሾኬ ይንደባለላል፡፡
ጥሮ ግሮ በ‘ላቡ፣’ በ‘ወዙ፣’ (‘ሁለቱም ወገኖች’ አሁንም ይቆጡ እንደሁ ብዬ ነው፡፡ ቂ…ቂ…ቂ…) ሀብት ካፈራ፣ “እኔ በዋሻ መንገድ አልሄድም፣ ሰዉ በሚርመሰመስበት ግልጽ አደባባይ ነው የምሄደው፣” የሚል...አለ አይደል…‘ሰልፍ ሊያበላሽ’ ስለሚችል ከየት እንደተወነጨፈ በማያውቀው ሾኬ ‘አፈር ሊቅም፣’ ይችላል፡፡
የፖለቲካ ሾኬ ያንደባልላል፣
የገንዘብ ሾኬ ያንደባልላል፣
የ‘ሀገር ልጅነት’ ሾኬ ያንደባልላል፣
እናላችሁ… አስቸጋሪ ነው፡፡ የምር ግን… በተለይ ይሄ ሊለቀን ያልቻለው የ‘ሀገር ልጅነት’ ሾኬን ማስቀረት ካልቻልን፣ በወንዝ ልጅነት መሳሳቡን ማቆም ካልቻልን፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን ማየት ካልቻልን ፖለቲካውን እያመሰው ያለው ‘ሾኬ’ ማህበራዊ ኑሯችንንም ማተረማመሱ አይቀርም፡፡
ቀደም ባለ ጊዜ ሆነ የተባለ ነው፡፡ ሰውየው በሰላሳ ሺ ብር የሆነች ሚጢጢ ፊያት ይገዛል:: ቤቱ ወስዶም ያቆማታል፡፡ በማግስቱ አዲሱ ባለመኪና ሞተሩን ያሞቅና ከግቢ ለመውጣት የኋላ ማርሽ ለማስገባት ሲሞክር እምቢ ይለዋል:: ደጋግሞ ቢሞክርም አልሆነም፡፡ ከእነ ጭራሹ እንደማይሠራም ያረጋግጣል፡፡ ያሻሻጡት ደላሎች ዘንድ ይሄድናም…
“እንዴት የኋላ ማርሹ የማይሠራ መኪና ትሸጡልኛላችሁ!” ሲል ያፈጣል፡፡ ምን ብለው ቢመልሱለት ጥሩ ነው…
“ምን! በሰላሳ ሺህ ብር ገዝተህ ደግሞ የኋላ ማርሽ ትፈልጋለህ!”
እናማ… በአሁኑ ጊዜ ቢሆን ይህ ሰው ለዚህ የደላሎቹ አባል የሆነ የ“ምናምኒዝም” ትርጉም ሰጥቶት ሌላ የስታንድአፕ ኮሜዲ ሀሳብ ያዋጣ ነበር፡፡
መንገዱ ተነጥፎ አሪፍ የሚመስል የእግረኛ መረማመጃ ስታዩ… “እሰይ! አሁን ሳንደነቃቀፍ የምንሄድበት አገኘን ማለት ነው፣” ትላላችሁ:: ወር ከሳምንት ሲሆን አምስት የኔቶ ታንክ የሚነቀንቀው የማይመስለው ንጣፍ ሁሉ አንድ በአንድ መወዛወዝ ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም ዝም ብሎ መደናቀፍ ብቻ ይቀርና ወደ መንገዳገድ እንገባለን፡፡
“ይህን የገነባው ኮንትራክተር ወይ ሥራውን በተገቢው ጥንቃቄ አልተከታተለውም፣ ወይም ደግሞ ችሎታው የለውም ማለት ነው፣” አይነት ነገር አንላላን፡፡ ይቺ ነገር ለኮንትራክተሩ ሹክ ስትባል ግን ነገርዬው ጥራት ስለጎደለው ግንባታ መሆኑ ሊቀር ይችላል፡፡ አጅሬው ‘ማርኬት ቫለዩ’ው እንደ ዶላሩ ‘ብላክ ማርኬት’ አንድ ለ‘ፎርቲ ምናምን’ ገብቷል ብሎ የሚያስበውን የማንነት ካርዱን ሊመዝ ይችላል፡፡
“ችሎታ የለውም ያሉኝ በሙያዬ ሳይሆን በማንነቴ ነው፣” በሚል ፍራንሲስ ፉኩያማ የሚባል ሰው መኖሩን ቢያውቅ  “‘አይዴንቲቲ ኢትዮፕያን ስታይል’ የሚል መጽሐፍ ጻፍልን” የሚል ‘ምከረ ሀሳብ’ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ (የሀገራችን ፖለቲካ ኮሜዲያዊ ይዘት እነ ትሬቨር ኖሃን ሊያስቀና በሚችል ደረጃ እየተመነጠቀ ይመስላል ለማለት ያህል ነው፡፡ ምናልባት በዚህም ከአፍሪካ ምናምነኛ፣ ከዓለም ምናምነኛ ልንባባል እንችል ይሆናል!)
“ከምስራቅ አፍሪካ ምናምነኛ የሆነ ህንጻ፣” “ከአፍሪካ ምናምነኛ የሆነ ምናምን፣” ከማለት በፊት ዝም ብሎ በንድፉ መሰረት መገንባት፣ በእቅዱ መሰረት መሥራት መቅደም የለበትም እንዴ?! በቅጡ ባልዳበረ አቅም፣ በሌለ ጡንቻ ራስን እንደ ማጠንከር ፉክክርን ምን አመጣው! አፍሪካ ላይ መንጠልጠልን ምን አመጣው! ግንባታው ይለቅና፣ ሥራው ይሠራና፣ ያን ጊዜ የመሰለው “ከአፍሪካ ምናምነኛ” “ከዓለም ምናምነኛ፣” ይበል! የምር ግነ ምን ይገርመሀል አትሉኝም…እኛ ‘ከአፍሪካ ምናምነኛ’ ስለመሆን ስናወራ ሌሎች ሀገሮች “ቆይ ይደርሱብንና አልፈውን ይሂዱ፣” ብለው ተቀምጠው ይጠብቁናል እንዴ!
መጀመሪያ የጓዳችንን ማየት አይቀድምም! የምናነጥሰውም፣ ምን የምንለውም በብሔር መነጽር ሊታይ ምንም ባልቀረበት ብዙ ቤት ሥራ አለ እኮ!
እናማ…በምኑም፣ በምናምኑም እያመሰን ያለውን የሾኬ ስትራቴጂ፣ የሚያንደባልል ሾኬ ያምጣልን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!Read 2374 times