Saturday, 05 October 2019 00:00

በቅርብ ያለ አማች ወፍጮ ላይ ይቀመጣል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 ሁለት ታሪኮች አሉ፡፡ ተመሳሳይም የሚለያዩም፡፡ አንደኛው የቡልጋሪያውያን ጋቭሮቮዎች ታሪክ ነው፡፡ ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ነው፡፡
የቡልጋሪያው ታሪክ እንዲህ ነው፣
በስግብግነታቸው ይታወቃሉ ከሚባሉት ጋቭሮቮዎች አንደኛው ብዙ ብርቱካን ይዞ እየበላ ወደ ሠፈሩ ይመጣል፡፡ የመንደር ጓደኞቹም ዘመዶቹም ብርቱካን መብላቱን አይተዋል፡፡ ከእነሱም መካከል ብርቱካን ያላቸው አሉ፡፡ ሆኖም ሲበሉ ያያቸው ስለሌለ የራሳቸውን ብርቱካን ደብቀው ከእሱ ብርቱካን እንዲያካፍላቸው ጠየቁት፡፡ አጅሬም እንደነሱው ጋቭሮቮ ነውና፤
‹‹አልሰማችሁም እንዴ ጎበዝ? እዚያ ወዲያ እሩቅ ከሚታየው መንደር’ኮ ብርቱካን በነፃ እየታደለ ነው፡፡ እኔም ያመጣሁት ከዚያ ነው፡፡
የሰፈሩ ጋቭሮቮዎች ብርቱካን ይታደላል ወዳላቸው ቦታ ነቅለው መሮጥ ጀመሩ፡፡ በየመንገዱ ያገኙት ሕዝብም ሲጠይቃቸው ብርቱካን በነፃ እንደሚታደል ይናገራሉ፡፡ የሰማው ላልሰማው እየነገረ አገሩ በሙሉ ብርቱካን ወደሚገኝበት መንደር በሩጫ እየጎረፈ ሄደ፡፡
ይሄኔ ያ በመጀመሪያ በነፃ ይታደላል ብሎ የዋሸ ጋቭሮቮ ነገሩ አጠራጠረው፡፡ ሲያይ የሕዝቡ ቁጥር ይብስ እየጨመረ ሄደ፡፡ ስለዚህ፤
‹‹አሃ! ሄ ነገር እውነት ይሆን እንዴ?›› ብሎ ራሱን ጠይቆ፣ ወደዚያው በፍጥነት መሮጥ ጀመረ፡፡
***
የኢትዮጵያው ታሪክ ደግሞ እንዲህ ነው፡፡
በአንድ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረ አንድ ሌባ ንብረት ዘርፎ ይሰወራል፡፡ ንብረቱ የተዘረፈበት ለመንግሥት ያመለክታል፡፡ መንግሥት ለሕዝቡ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ‹‹የገባችሁበት ገብታችሁ ይሄን ሌባ ፈልጋችሁ አምጡ!›› ብሎ፡፡ ስለሆነም ሕዝቡ በሙሉ ሌባ ፍለጋ ተሰማራ፡፡ ሌባው ግን አልተገኘም፡፡ በመካከል አንድ በመልክም በቁመትም ልክ ያንን ሌባ የመሰለ ሰው ከባላገር ይመጣል፡፡ ሕዝቡ ሮጦ ይህን ሰው ይይዘዋል፡፡ ሰውየው ‹‹እባካችሁ በመልክ ሌባውን መስያችሁ ነው’ እንጂ እኔ ሌባ አይደለሁም፡፡ ምንም የሰረቅሁት ነገር የለም›› አለ፡፡ የሚያምነው ጠፋ፡፡ የማሪያም ጠላት አደረጉት፡፡ ጬኽቱ በዛበት፡፡ ‹‹ሌባው አንተ ራስህ ነህ! ዛሬ ቀን ብታምን ይሻልሃል! እኛን ለማታለል በጭራሽ አትችልም፡፡ ይልቅ ተናገር!›› እያሉ አፈጠጡበት፡፡ ያም ሰውዬ  በልቡ እንዲህ አሰበ፤
‹‹አሁን ይሄ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ይሳሳታል? በፍፁም አይሳሳትም፡፡… እኔ ራሴ መስረቄን ረስቼው ይሆናል እንጂ!›› በመጨረሻም ‹‹አዎ እኔ ነኝ›› ብሎ አመነና ወደ ወህኒ ወረደ፡፡
***
በቡልጋሪያም ሆነ በኢትዮጵያ ወይም በሌላ አገር ሕዝብ ሕዝብ ነው፡፡ የቡድን ስሜት የቡድን ስሜት ነው፡፡ አንድ አቅጣጫ ይዞ ያንኑ ቦይ ተከትሎ መፍሰስ ከጀመረ ማቆሚያ የለውም፡፡ አንድም በመጭበርበር ወንዝ ፈጥሮ፣ ወንዝ ሆኖ ሊጎርፍ ይችላል፡፡ አንድም ትእዛዝ አክብሮ፣ በታዛዥነት እየፈሰሰ ግለሰቦችን እየተጫነ፣ አንዴ መውረድ ወደ ጀመረበት አሸንዳ በጀማ ይጓዛል፡፡ ላቁምህ፣ ልገድብህ ቢሉት በጄ አይልም፡፡ የመንገኝነት ስሜት (Herd Instinct) በበጎም በክፉም ሊነዳ የሚችል ብርቱ ስሜት ነው፡፡ ልዩ ጥንቃቄ የሚፈልግ አደገኛ ቡድናዊ ደመ-ነብስ ነው፡፡ በተለይ እንደ እኛ አገር ባህላዊ ህብሩ፣ ኢኮኖሚያዊ ትግግዙ፣ ጎሳዊ ትስስሩና አገራዊ አንድነቱ ቋጠሮው በጠበቀበትና ውስብስብ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ የእያንዳንዱ ቀልጣፋ ግለሰብ ወይም ደፋር ቡድን ፍላጎት የብዙሃኑን ፍላጎት የሚቃኝና የሚመራበት ሁኔታ ሃይል ነው፡፡ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ድርጅቶች፣ ፓርቲዎችና ማህበራት አዋሹን ሕዝብ ወዳፈተታቸው አቅጣጫ ለመውሰድ በማባባልም፣ በመደጎምም፣ በማታለልም፣ በማዘዝም፣ በማስፈራራትም ቦይ ለመቅደድ መጣጣራቸው አይቀርምና የመንገኝነት ጉዳይ አጠያያቂና አደገኛም ሊሆን ይችላል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ሁሉም የሕዝቡን ችግርና ብሶት መሰረት ያደረገ ቋንቋ አንግቦ ይነሳል፡፡ አንደበተ - ቀናው፣ ዲስኩር የሚዋጣለት በቀላሉ ይደመጣል፡፡ የእኛ ሕብረተሰብ የተራኪና አድማጭ ሕብረተሰብ  (Story-teller society) ነው፡፡ ደህና ተናጋሪ ካገኘ አዳምጦ ወደማመን እንጂ መርምሮ ወደ መረዳትና ተንትኖ ወደ መቃወም ገና ሙሉ በሙሉ የተሸጋገረ አይደለም፡፡ በግሉ አስቦ፣ በግሉ መርምሮ፣ በግሉ ለራሱ የሚቆም ጥቂቱ ነው። መብቱን ለማስከበር የሚራመደው ገና ጎረቤትና ጎረቤት ተያይቶ፣ እነ እገሌ ምን አሉ? ተባብሎ ነው፡፡ ስለዚህም የነቃ ይቀድመዋል፡፡ ጮሌ እንዳሻው ይነዳዋል፡፡ አንደበተ ቀና ያሳምነዋል፡፡ አስገራሚው ነገር ግን የዞረ ለትም ያው ነው፡፡ ሲገለበጥም እንደዚያው ነው፡፡ የዚያኑ ያህል ደመ-መራራ ነው፡፡ የተከተለውን ሊያባርረው፣ የካበውን ሊንደው፣ ያከበረውን ሊንቀው ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ በማህበረሰቡ ዘንድ የመንገኝነት ስሜት መሪ ሚና መጫወቱን አለመዘንጋት ነው፡፡
ይህን የመንገኝነት ስሜት የሚመራ ሁሉ የተቀደሰ ዓላማ አለው ለማለትም አይቻልም፡፡
‹‹ሆድ ዕቃው የተቀደደበት እያለ ልበሱ የተቀደደበት ያለቅሳል›› ይሏልና፡፡ ስለዚህም እውነተኛውን ከሀሳዊው፣ ዋናውን ከትርፉ፣ ኦርጅናሌውን ከአስመሳዩ፣ ምርቱን ከግርዱ ለይቶ፣ አይቶ መጓዝ የሚያስፈልግበት ሰዓት ነው፡፡ ኤሪክ ሆፈር የተባለው ፀሐፊ ‹‹አብዛኞቹ የቅዱስ ሰው ምርጥ ሀሳቦች ከሀጢያተኝነት ልምዱ ያገኛቸው ናቸው›› ያለውን አለመዘንጋት ነው፡፡ የወቅቱ መዞሪያ - ኩርባ  (Turning point) መቼና የት እንደሆን የማያይ ቡድን ወይም ፓርቲ እንደ አቴቴ ሸረሪት ድር ራሱን በራሱ ተብትቦ፣ ራሱን በራሱ ውጦ ለባላንጣው ሲሳይ የሚሆን ነው፡፡ ትንሽ መንገድም ቢሆን በሚያግባባቸው አቋም አብረው ሊሄዱ የሚችሉ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ቡድኖች ሲነጋ በቀኝ ጎናቸው ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ለመንቃት በርትቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ዳተኝነትን ማስወገድና የቤት ሥራን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹ሰነፍ ይፀድቃል ወይ ቢለው፣ ገለባ ይበቅላል ወይ? አለው›› እንዳለው ገለባ ሆኖ ላለመቅረት ማለት ነው፡፡
ዛሬም የሦስት ምክሮች ዘመን ነው - ስለዚህ ባንድ በኩል ‹‹ዝግጅት! ዝግጅት! አሁንም ዝግጅት!›› ማለት ተገቢ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹ፅናት! ፅናት! አሁን ፅናት!›› ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ምክር አዲስ እንዲወለድ የሚጠቅመውን ያህል ነባሩ በቀላሉ እንዳይፈረካከስ ይጠቅማልና የጠንካራ ድርጅት መሰረት ነው፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችን የመበታተን ሥጋት እንደ አገር ችግር ማየት ተገቢ ነው፡፡ አንዲት ነብሰጡር ሴት ጎረቤቷ በምትወልድበት ቀን ልውለድ ብትል እንደማይሆንላት ሁሉ፣ የፖለቲካ ድርጅቶችም የራሳቸውን ዕድሜና ብቃት የማፍሪያና የማዘርዘሪያ ከዚያም ለፍሬ መብቂያ ጊዜ አይተው ብቻ ነው መነሳት ያለባቸው። ሌላው ከሚቀድመን ተብሎ ሳይጠነክሩ የሚሰራ ሥራ የብልህ መንገድ አይደለም፡፡ የማያስተማምን ውህደት በሰም የተጣበቀ ጥርስ መሆኑን መርሳትም አይገባም፡፡ ‹‹ዛሬ የትላንትና ተማሪ ነው›› እንዳለው ቶማስ ፉለር፣ ትላንትናን ማሰብ የተማሪውን አስተማሪ እንደማወቅ ይሆናል፡፡ ማሰብ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ነው፡፡ ‹‹ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል›› እንዲሉ የሞተ ነገር ላይ መነታረክ ያልሞተውን ነገር እንዳናይ ያደርገናል፡፡ ሳያስቡ መጓዝ መፈክርን ያስነጥቃል፡፡ ሳያስቡ መጓዝ የተገኘን እድል በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፡፡ ባገኙት እድል ክፉኛ አለመፈንደቅ ብልህነት ነው፡፡ በደረሰ ጊዜያዊ ሽንፈትና ችግርም የመጨረሻ የመንፈስና የአካል መፈረካከስ ድረስ መውረድም ደካማነት ነው - የሚደኸይ ጉረሮ ሁሌ ጣፋጭ ነገር ይመኛል እንዲል መጽሐፍ፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሽኩቻ፣ ከመሰነጣጠቅ፣ ለበያቸው ሲሳይ ከመሆን መቼ ይሆን የሚወጡት? የሚለው ጥያቄ ዛሬም አለ፡፡ ዛሬም ከመከፋፈል፣ ዛሬም ከመጠላለፍ እንዳይወጡ የሚያደርጋቸው የመርገምት አዙሪት ያው እንደተለመደው የት/ቤት፣ የአፈር ፈጭ አብሮ - አደግንት፣ የመጠፋፋትና የአውቅሁሽ ናቅሁሽ ፖለቲካ ይሆን? በቅርብ ያለ አማች ወፍጮ ላይ ይቀመጣል!   

Read 7905 times