Saturday, 05 October 2019 00:00

የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች አብሮ የመስራት ስምምነት እስከ ውህደት ሊዘልቅ ይችላል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

ሰሞኑን ኦዴፓን ጨምሮ በጋራ የመስራት ስምምነት የተፈራረሙት 7 የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ግንኙነታቸው ተዋህዶ አብሮ እስከ መስራት ሊዘልቅ እንደሚችል የኦፌኮ ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
በጋራ የመስራት ስምምነቱን የተፈራረሙት በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ)፣ በፕ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው ኦፌኮ፣ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግና በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)ን ጨምሮ ሌሎች ዋነኛ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲሆኑ ከስምምነት ፊርማው በፊት በኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ለሁለት ቀናት የዘለቀ  ምክክር ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
በምክክሩ ወቅትም የኦሮሞ ሕዝብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ተለይተው መቀመጣቸውንና በአፈታታቸውም  ጭምር የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ለአዲስ አድማስ ያስረዱት ፕ/ር መረራ፤ ምላሽ የሚሹ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው ተብለው ከተለዩ 15 ጉዳዮች መካከል ሰላምና መረጋጋት፣ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጥያቄ፣ የአፋን ኦሮሞ የፌደራል የሥራ ቋንቋ የመሆን ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የ7ቱ ፓርቲዎች ሊቃነ መናብርት በየጊዜው እየተገናኙ የሚመክሩበት ‹‹ጋዲሳ ሆገንሳ ኦሮሞ›› የኦሮሞ መሪዎች ጉባኤ መመስረቱን ጠቁመው፤ ይህን መድረክ የሚያስተባብርና አጀንዳዎችን የሚያሰናዳ 5 አባላት ያሉት ኮሚቴም መቋቋሙን  አስታውቀዋል፡፡  
የኦሮሞ ፓርቲዎች በአመዛኙ በቆሙለት ሕዝብ ጉዳይ ተቀራራቢ አቋም እንዳላቸው በምክክሩ መታየቱን የጠቆሙት ፕ/ር መረራ፤ በቀጣይ እርስ በእርስ ለመዋሃድም ሆነ በቅንጅትና በተለያዩ አግባቦች አብሮ ለመስራት እንደማይቸገሩ ግንዛቤ መገኘቱንና ግንኙነቱ ምናልባትም እስከ ውህደት ሊደርስ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡   
በፓርቲዎቹ መካከል አላስፈላጊ ውዝግቦችና አለመግባባቶች የሚፈቱበት የሥነ ምግባር ደንብ በኮሚቴው እንደሚዘጋጅና  ፓርቲዎቹ መሠረታዊ የሆኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች በሚፈቱበት ሁኔታ ላይ በትብብር አብረው እንደሚሰሩ የኦፌኮ ሊቀ መንበር ተናግረዋል:: ፓርቲዎቹ ባለፉት 6 ወራት ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርጉ እንደቆዩ የታወቀ ሲሆን ስምምነቱ ከበሰለ የውይይት ፍሬ በኋላ የመጣ በመሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ በቀላሉ የሚናድ አይሆንም ተብሏል፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄዎች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠራችን፣ ከመጠላለፍ ፖለቲካ በመውጣት፣ የኦሮሞ ሕዝብን የሚመጥን የሰለጠነ ፖለቲካ ለማካሄድ ተስማምተናል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይሄ ለኦሮሞ ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ዋጋ ያለው መሆኑን አስምረውበታል፡፡  
በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ኦዴፓን ወክለው የተገኙት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በበኩላቸው፤ ይህ ትብብር በኦሮሞ ፓርቲዎች ሳይገደብ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋርም መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡  ባሉን ሀሳቦች ላይ በሰለጠነ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት እርስ በእርስ እየተማማርን፣ የአገራችንን ፖለቲካ ማዘመን አለብን ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አዳዲስ ሀሳቦችን በማፍለቅ አገሪቱን ማሸጋገርና በአፍሪካ ቀንድ የራሳችንን ጉልህ ሚና መጫወት አለብን ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ ቀጣዩ ምርጫም ያለ ጥርጥር ግልጽ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ይሆናል ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ ሕዝቡም ለእንደዚህ አይነቱ ምርጫ እንዲዘጋጅ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ 

Read 5549 times