Tuesday, 01 October 2019 10:39

ከመሄጃው መድረሻው ይቀድማል

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


           እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በፈጠርከን መስፈርት መለኪያ አውጣልን፡፡
አንድዬ፡— ምን እያልክ ነው?
ምስኪን ሀበሻ፡— ወይ ሳትገጥምልን የቀረ ነገር ካለ አስተካክልልን፡፡
አንድዬ፡— አንተ ሰውዬ፣ በጠዋቱ አረቄ ጠጥተህ አናትህ ላይ ወጣ እንዴ!     
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ስንት ነገር አናታችን ላይ ወጥቶ፣ መች ለአረቄ የሚሆን ቦታ ተረፈንና! አንድዬ ግን ልጠይቅህ፡፡ እውነት ሁላችንንም ጥንቅቅ አድርገህ ነው የፈጠርከን?
አንድዬ፡— ጥንቅቅ አድርገህ ማለት ምን ማለት ነው? ሴራ ፖለቲካችሁን ልታመጣብኝ ነው! ዳር ዳሩን ከምትዞር፣ ለምን አንደኛውን፣ “ስትፈጥረን አዳልተሀል” ብለህ፣ በእናንተው ችሎት አታቆመኝም! መቼም ዘንድሮ በፈጣሪነት ላይም፣ “የባለቤትነት ጥያቄ” የምትሉትን ነገር ሳታመጡብኝ አትቀሩም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይህን ያህል ታዝበኸናል ማለት ነው?
አንድዬ፡— ትዝብት! ትዝብት ነው ያልከኝ? የምትታዘበው እኮ “ትዝብት ላይ ወድቄያለሁ፣” ብሎ ነገና ከነገ ወዲያ ለሚስተካከል ሰው ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እሱስ ላይ ልክ ነህ፡፡ እንደውም በአንዳንዶቻችን ላይ የሚታዩ ባሕሪያት፣ ከሰው ልጅነት እየዘለሉ ነበር፡፡
አንድዬ፡— ስማኝ ምስኪኑ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አቤት አንድዬ…
አንድዬ፡— ዓመቱን ሙሉ ስትነዘንዘኝ ከርመህ ሲደክምህ በዚህኛው አዲስ ዓመት ቀለል ይልልኛል ብዬ ነበር፡፡ ድምጹን አጥፍቶ ወደ ኑሮው ይገባ ይሆን እንዴ ብዬም ነበር እንጅ:: እንደውም ከመጥፋትህ የተነሳ ናፍቀኸኝ፣ እኔ ወዳንተ የምመጣ መስሎኝ ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ እያሾፍከብን ነው፣ አይደል!
አንድዬ፡— እኔ ምን አሾፍብሀለሁ! ራሳችሁ ላይ ማሾፍ ከጀመራችሁኮ ሰነበታችሁ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ እውነቴን ነው የምልህ…ከመጥፋቴ የተነሳ እናፍቅሀለሁ?
አንድዬ፡— አባባሉን ማለቴ ነው፡፡ ጠፋህብኝ፣ ናፈቅከኝ ይባል የለ፡፡ እንጂማ፣ እኔን መነዝነዝ፣ ቋሚ ስራችሁ ሆኖ የለ! እንደውም እንዳያያዛችሁ ዘንድሮም፣  ፋታ ስትነሱኝ የምትከርሙ ነው የሚመስለኝ…
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ይሄን ያህልማ ተስፋ አትቁረጥብን…
አንድዬ፡— ምን ላድርግ! ሁኔታችሁን ሳያችሁ፣ እኔ የፈጠርኳችሁ እንኳ፣ ግራ እየገባኝ ነው::  “ዲያብሎስ ተሸክሟቸው ሄዷል” ያልኳቸውን እኩይ ባህሪያት፣ በብዙዎቻችሁ ላይ ስመለከት እያስፈራችሁኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አንተ እንዲህ ከተማረርክብን፣ ወዴት ልንዞር ነው! ማንስ መጽናኛ፣ ማንስ መከታ ሊሆነን ነው! ግራ አጋባኸኝ እኮ!
አንድዬ፡— እንግዲያው እርምህን አውጣ… እኔንም በጣም ግራ አጋባታችሁኛል፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— ተስፋ አታስቆርጠን እንጂ አንድዬ… እንደውም አሁን የተረዳነው ነገርኮ፣ ብቸኛው የችግራችን መፍትሄ አንተ መሆንህን ነው፡፡
አንድዬ፡— አትሰማኝም እንዴ! ግራ አጋባችሁኝ እያልኩህ፣ ጭራሽ መፍትሄ ትለኛለህ! ረስታችሁኛል እኮ! ስማኝ…አጠገባችሁ ላለው ያልታመንክ፣ እንዴት ለእኔ ትታመነኛለህ! እርስ በእርስ መከባበር ያልቻላችሁ፣ እኔን እንዴት ታከብራላችሁ? አጠገባችሁ ላለው በጎ ተግባር ሳትፈጽሙ እንዴት ነው እኔ ፊት በበጎ ለመታየት የምትጠብቁት! “የማይመስል ነገር ለሚስትህ አትንገር፣” እያላችሁ ትተርቱ የለ…የማይመስል ነገር አትንገሩኛ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ አስፈራኸኝ አኮ፣ የማላውቅህ ነው የሆንክብኝ፡፡
አንድዬ፡— የምታውቀኝ ይመስልሀል እንጂ አታውቀኝም፡፡ ጠዋት “በሰላም አውለኝ” እያልክ ከቤት የምትወጣ፣ “እከሊትን በሰላም አታስድራት፣” እያልክ ጠጠር የምትበትን ሰውዬ፣ አውቅሃለሁ አትበለኝ፡፡ ታውቀኝ ነበር? መልስልኛ፣ ሁላችሁስ እውነት ታውቁኝ ነበር?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ቀን ከሌት በርህን እያንኳኳን፣ ነጋ ጠባ ስምህን እያነሳን ለምንድን ነው ይሄን ያህል የምትጠራጠረን፡፡
አንድዬ፡— ካልጠረጠርኩ ደግሞ፣ ነገ ራሳችሁ ካልመነጠርንህ ማለታችሁ አይቀርማ! ደግሞ በሬን አንኳኳችሁ እንጂ፣ ስሜን አነሳችሁ እንጂ መቼ ቃሌን ፈጸማችሁ! ሙሴ ይዞላችሁ የመጣቸውን ትእዛዛት ሁሉ አፈር ድሜ አግብታችሁ የለ እንዴ! አንተ ማነህና ነው ለእኛ ትእዛዛት የምትሰጠው ልትሉኝ እየዳዳችሁ አይደል እንዴ! ተው እንጂ አታናግረኝ!
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ ከአዲሱ ዓመት ጋር ተለወጥክብኝ እንዴ?
አንድዬ፡— ጎሽ! “ጎሽ የእኔ ጀግና” አይደል የምትባባሉት፣ ጎሽ የእኔ ጀግና ልበልህ እንጂ፡፡ ጭራሽ እኔኑ ተለወጥክብኝ አልከኝና አረፍከው!
ምስኪን ሀበሻ፡— ሀሳብ ቢገባኝ እኮ ነው አንድዬ:: አንተን ለማሳዘን ብዬ አይደለም፡፡
አንድዬ፡— ይኸው አሁን ደግሞ ኃይማኖቱን የፖለቲካ ሜዳ እያደረጋችሁት አይደለም እንዴ! በምኑም፣ በምናምኑም ስትናቆሩ ኖራችሁ ሲያልቅባችሁ፣ ምስኪኖችና ድሆች ከእኔ ጋር መገናኛ መንገዳቸውን ለመበጠስ፣ ኃይማኖት ላይ የክፋት መረባችሁን እየጣላችሁበት ነው፡፡ በፖለቲካ ተውሳክ ልታስመቱት፣ በግራና በቀኝ ትደነቋቁሉት ጀምራችኋል!
ምስኪን ሀበሻ፡— እኔ በበኩሌ አንድዬ እንዲህ እንዲሆን አስቤ ሳይሆን
አንድዬ፡— ሺ የሰበብ ዓይነት ለመፍጠርማ ማንም አይቀድማችሁ ይልቅ፣ የመጣውን ነፋስ እየተከተላችሁ አብራችሁ መንፈስና አቧራ መፍጠር ስታቆሙ፣ ያኔ ነው እውነተኛ የመንፈስ ጥንካሬ፣ ያኔ ነው እውነተኛ የእምነት ጥንካሬ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ፣ ፖለቲከኞች ነን የሚሉ ናቸው እኮ በእምነት ሊከፋፍሉን የሚሞክሩት፡፡
አንድዬ፡— እኮ፣ በእምነት ልትከፋፍሉን አትሞክሩ፣ ጥጋችሁን ያዙ ማለት ያለባችሁ እናንተ አይደላችሁም እንዴ! የፖለቲካ ነቀርሳችሁን በእምነቶች ላይ ስትበትኑ ዝም ብለን አናይም ማለት ያለባችሁ እናንተ አይደላችሁም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡— እሱማ ልክ ነው፡፡ ግን ደግሞ አንድዬ እምነቶች ውስጥም ያሉ አንዳንዶች አንደኛውን እምነት  ከሌላኛው ለማበላለጥ እየሞከሩ…
አንድዬ፡— ግዴለም ባትነግረኝም አውቀዋለሁ፡፡ ደግሞ ስማኝ…እየሰማኸኝ ነው ምስኪኑ ሀበሻ?
ምስኪን ሀበሻ፡— አንድዬ በደንብ እየሰማሁህ ነው፡፡
አንድዬ፡— የምትፈልጉት እኔ ቤት መድረስ እስከሆነ ድረስ፣ ከዚህኛው ቤት ውጡ ከዛኛው ለውጥ የለውም፡፡  እኔ ዘንድ እስካደረሳችሁ ድረስ በየትኛውም መንገድ ብትመጡ፣ በየትኛው ግዴለኝም፡፡ በጎ ተግባር ስትፈጽሙ እስከኖራችሁ ድረስ፣ ወገኖቻችሁ ላይ ክፉ እስካልሠራችሁ ድረስ…ትእዛዞቼን እስከፈጸማችሁ ድረስ የመጣችሁበት መንገድ፣ የትኛውም ቢሆን ቀና መንገድ ነው፡፡ ለእኔ ዋናው ጉዳይ በምስራቅ መጣችሁ በምእራብ፣ በሰሜን መጣችሁ በደቡብ ሳይሆን፣ እኔ ማወቅ የምፈልገው ምን ስትፈጽሙ እንደኖራችሁ ነው:: ገባህ?
ምስኪን ሀበሻ፡— በደንብ ነው የገባኝ አንድዬ፣ በደንብ ነው የገባኝ፡፡
እዚህ ላይ ነው እኮ የአንተ እርዳታ የሚያስፈልገን::
አንድዬ፡— ራሳችሁን በራሳችሁ መርዳቱ አይቀድምም?
ምስኪን ሀበሻ፡— እንዴት ሆኖ አንድዬ፣ እንዴት ሆኖ!
አንድዬ፡— እንዴት እንደሆነማ እነግርሀለሁ:: ውስጣችሁን አጥሩ፡፡ ውስጣችሁን የበከሉትን የጥላቻ፣ የበቀል፣ የማን አለብኝነት፣ የምቀኝነት…ክፋቶችን ጥርግ አድርጋችሁ አውጡ:: አእምሯችሁ በጎ በጎውን አልቀበል ያለው በእነዚህ ስለተጣበበ ነው፡፡ መጀመሪያ ራሳችሁን ስታጠሩ እኔም አለሁላችሁ እላችኋለሁ:: መድረሻው ላይ ከተስማማችሁ መንገዱም ይቀልላችኋል፡፡ በል ደህና ሁን፣ ሰላም ግባ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡— አሜን አንድዬ አሜን!
በድጋሚ… እንኳን ለብርሀነ መስቀሉ አደረሳችሁ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2645 times