Tuesday, 01 October 2019 10:21

ሁለገቡ የሚዲያ ባለሙያ ምስጋናው ታደሰ የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ ይፈልጋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(4 votes)

• በአገር ውስጥ ከፍተኛ ህክምና ለአንድ ወር ይቆያል፤ የውጭ ህክምና ሊያደርግም ይችላል

           ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ እና ሁለገብ የሚዲያ ባለሙያ ምስጋናው ታደሰ በእግሩ ላይ ያጋጠመውን ከፍተኛ ህመም ለመታከም የኢትዮጵያውያንን ድጋፍ እየጠየቀ ነው፡፡ ምስጋናው ታደሰ ለስፖርት አድማስ እንደተናገረው በሚቀጥለው አንድ ወር ለሚከታተለው ከፍተኛ ህክምና እንዲሁም በተጨማሪ የውጭ ህክምና ሊያደርግ ስለሚችል ወጭውን ለመሸፈን አፈጣኝ እርዳታዎች ያስፈልጉታል፡፡  
በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ እና ህትመት ሚዲያዎች ከ20 ዓመታት በላይ ያገለገለው ምስጋናው በእግሩ ላይ ላገጠመው ከፍተኛ ጉዳት እና ህመም መነሻው በመኖርያ ቤቱ በራፍ ላይ አዳልጦት ከወደቀና የደረጃ መወጣጫ ከመታው በኋላ ነው፡፡ በወቅቱ ለጉዳቱ ብዙም ትኩረት ሳይሰጠው በቸልታ ቢያልፈውም የቀጭ እግሩ ከጉልበቱ በታች በፍጥነት በማበጡ ከአንቅስቃሴ አግዶታል፡፡ ያለፈውን ሁለት ሳምንትም የሚወደውን ስራ አቋርጦ በመኖርያ ቤቱ የሚቆይ ሲሆን ከቅርብ ጓደኞቹ በሚያገኘው ርዳታ ከፍተኛውን ህክምና እየተከታተለ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ምስጋናው በህመሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረስ ሳቢያ እያንዳንዷን እንቅስቃሴም በሰዎች ድጋፍ ለማድረግ መገደዱንም ገልጿል፡፡
ሁለገቡ የሚዲያ ባለሙያ ምስጋናው ታደሰ በመላው የኢትዮጵያ ስፖርት ቤተሰቦች  የሚከበር ሲሆን በስፖርት ጋዜጠኝነት በህትመትና ብሮድካስት ሚዲያዎች ለብዙዎች ተምሳሌት ለመሆን የበቃ ነው፡፡ ምስጋናው የፀሃፊነትና የጋዜጠኝነቱን ሙያ የጀመረው በትውልድ ከተማው ሐረር ውስጥ አምስተኛ ክፍል ላይ የሚኒ ሚዲያ ስራዎችን በመስራት ነው፡፡ ገና የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ሳይጀምርም ለኢትዮጵያ ሬድዮ በደብዳቤ እና በስልክ የስፖርት ዘገባዎችን ያቀርብ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኝነት ከ20 ዓመታት በላይ ሲያገለግል በሙያ ፍቅር፤ ልዩ ተሰጥኦ እና ትጋት  ነው፡፡ በተለያዩ 10 የስፖርት ጋዜጦችና መፅሄቶቻቸው በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ስፖርት ከ10ሺ በላይ ዜናዎች፤ ልዩ ዘገባዎች፤ ቃለምልልሶች እና መጣጥፎች እና ልዩ ልዩ መረጃዎች ሲፅፍ ቆይቷል፡፡ በሪፖተርነትዐ ከፍተኛ ሪፖርተርነትና በአዘጋጅ እና በዋና አዘጋጅነት ከሰራባቸው ታዋቂ የስፖርት ሚዲያዎች መካከል ኢንተር ስፖርት፤ ስካይ ስፖርት፤ ሃትሪክ ስፖርት፤ ቶፕ ስፖርት ዋናዎቹ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከህትመት ሚዲያው ባሻገር ምስጋናው በስፖርት ጋዜጠኝነት በተለያዩ የራድዮ የኤፍኤም ሞገዶች በርካታ ተወዳጅ የስፖርት ፕሮግራሞች እና ሾዎችን ከሌሎች አጋሮቹ ጋር የፈጠረ፤ የሰራ እና ያስፋፋ ነው፡፡ ስኬታማ ከሆነባቸው የራድዮ ፕሮግራሞቹ መካከል ፕላኔት ስፖርት የሚጠቀስ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ላይ ከሰኞ እስከ አርብ ከ2 እስከ 3 ሰዓት ተኩል በሚተላለፈው ኢትዮስፖርት ላይ በአዘጋጅነት እየሰራ ቆይቷል፡፡
ጋዜጠኛ ምስጋናው በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከፍተኛ ልምድ ያለው፤ የኢትዮጵያን አትሌቲክስ እና ታላላቅ እና አዳዲስ አትሌቶች የሩጫ ዘመን የሚያውቅ፤ ሪከርዶች፤ ሰዓቶች፤ የላቁ ውጤቶች፤ ውጣውረዶች በቃሉ የሚያውቅ እና በማንኛውም አጋጣሚ ይህን የካበተ እውቀትና ልምዱን የሚያካፍል ነው፡ ፡፡በኢትዮጵያ ስፖርት በተለይ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ያሉ አስተዳደራዊ ሁኔታዎችን ከስር ከስር የሚከታተል፤ እያንዳንዱን ሂደት የሚያውቅ፤ ምስጥራዊ መረጃዎችን ፈልፍሎ የሚያገኝና የሚተነትንም ምርጥ ባለሙያ ነው፡፡
በወቅታዊ የስፖርት ሁነቶች ላይ ንቁ ክትትል የሚያደርግ፤ ሽፋን የሚሰጥ፤ ለስፖርት ቤተሰቡ በተለያየ መንገድ የሚያደርስ፤ ትኩስ ወሬዎችን አድኖ የሚያገኘው ምስጋናው ታደሰ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ እንደባለውለታ መታየትና መከበር ያለበት ምስጉን ኢትዮጵያዊ መሆኑ አፈጣኝ ትብብር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ምስጋናው ታደሰ አሁን የሚከታተለው ከፍትኛ ህክምና የቅርብ ክትትል እና ልዩ ትኩረት የሚያስፈልገው ሲሆን ሃኪሞቹ በሰጡት ምክር የሚወስዳቸው መድሃኒቶች ፈዋሽ እንደመሆናቸው መርዛማነትም ስለሚኖራቸው ያለቸልታ በጥንቃቄ ሊጠቀማቸው ይገባል፡፡ እያገኘ ያለውን ህክምና ማቋረጥ እና የሚወስደውን መድሃኒት ማጉዋደል ጉዳቱን ወደ ሰውነቱ ሊያሰራጨው እንደሚችል እና ቀኝ እግሩን እስከመቆረጥ ሊያደርሰው እንደሚችል ሃኪሞቹ አሳስበውታል፡፡ ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰ ለስፖርት አድማስ በሰጠው አስተያየት፤ አስፈላጊውን ህክምና በአስቸኳይ አግኝቶ ወደ ስፖርት ሚዲያው መመለስ እንደሚፈልግ የተናገረ ሲሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ድጋፍ እንዲሰጠው በትህትና ጠይቋል፡፡
ጋዜጠኛ ምስጋናው ታደሰን ለመደገፍ በብስራት ሬድዮ መስራች እና ባለቤት በጋዜጠኛ መሰለ መንግስቱ፤ በቅርብ ወዳጁ ሰለሞን ተክለ ሚካኤል እንዲሁም በኢትዮ ስፖርት የሙያ ባልደረባው ታደለ አሰፋ የሚመራ ኮሚቴ የተዋቀረ ሲሆን ምስጋናውን መርዳት እና መደገፍ የሚፈልግ አካል ካለ በሚከተሉት የባንክ ቁጥሮች መጠቀም እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1000268456639
አዋሽ ባንክ 01320148371700
በሌላ በኩል የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የስፖርት ክፍል ባልደረባ ሳምሶን ከተማ አማካኝነት  ለጋዜጠኛ ምስጋናው እንድረስለት በሚል www.gofundme.com ላይ Fundraiser by Samson Ketema በሚል እንቅስቃሴም እየተካሄደ ነው፡፡ በድረገፁ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር እስከ 20ሺ ዶላር ለማሰባሰብ ዘመቻ እንደተጀመረም ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 9780 times