Saturday, 21 September 2019 13:07

የደግ፣ ደግ ምንቸት ይግባ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

           እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…ክረምትና ‘ቅዝቃዜው’ አልለቅ አለንሳ! “ሞቅ ሊል ነው” ስንል ውርጩ ሾልኮ እየገባ፣ “ፀሀይ ልትወጣ ነው” ስንል ከፓሲፊክ ውቅያኖስ ይምጣ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ የማናውቀው ደመና ሰማይ ለሰማይ ተስቦ እየሸፈነን… ‘ቆፈንና ውርጭ’ የሚቀንሱበት ዘመን ይሁንልንማ!
እኔ የምለው …እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…እኛ ዘንድ ጀምሮ መጨረስ ይህን ያህል አስቸጋሪ የሆነው ለምንድነው! በመከራ የጀመርነው፣ በተለይ ደግሞ ‘በጎ’ የሚባል ነገር…አለ አይደል…  አይደለም መጨረስ ማጋመስ እያቃተንእኮ ነው፡፡ የሆነ ነገር አዙረው የጣሉብን ይመስል … ደግ ነገር ለምን እድሜ እንደማይኖረው ግርም አይላችሁም! 
መቼም ዘንድሮ ሬስቱራንትና የምግብ ቤት አይነት ቢዝነስ ውስጥ መግባት ሁላችንም በተራ የሚደርሰን ነው የሚመስለው…የፈለገ ያህል ‘ቺስታ’ ብንሆንም ማለት ነው፡፡ “የሀገሬ ሰው የፈለገ ቢቸግረው ለቤተሰቡ ሀያ አምስት ኪሎ ጤፍ መግዛት ይቸግረው እንደሁ እንጂ ሬስቱራንት አራትና አምስት ጓደኞቹን ምላስ ሰንበር መጋበዝ አያቅተውም” የሚል ፍልስፍና ያለ ነው የሚመስለው፡፡
(“ሰዋችን ፍራንኩን ከየት ነው የሚያመጣው!” የሚባለው እኮ ዝም ብሎ የምቁነት ነገር አይደለም:: የምር ግን…አለ አይደል…ፈረንካው እንደ ሉሲ ‘ተቆፍሮ የሚወጣበት’ ስፍራ ካለ የምታውቁ ንገሩንና ዶማችንን ይዘን እንሰለፍ፡፡ ልክ ነዋ…ይህንንም፣ ያንንም መቆፈር እንደሁ ‘ናሽናል ፓሺን’ የሆነ ነው የሚመስለው! እነእንትና…ሂስትሪ በዶማ ነው የሚቆፈረው በአንካሴ? ተመሳሳይ ቦታ ቆፍራችሁ፣ ያልተመሳሰሉ ነገሮች የማግኘታችሁ ዓለምን የሚያስከነዳ ‘ጥበብ’ ስለራቀን ነው፡፡)  
እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የአዳዲስ ምግብ ቤቶችን ብዛት አንድ መቶኛ የሚሆኑ ሚጢጢዬ ማማረቻ ፋብሪካዎች ቢቋቋሙ፣ራስምታታችን ባይጠፋም ይቀንስልን ነበር፡፡ እናላችሁ… የሆነ ቅርብ ጊዜ የተከፈተ ወይም የከረመ ምግብ ቤት ነገር ምን ብሎ ይለጥፋል… “ምግብ በአዲስ መልከ ጀምረናል”  ለነገሩ እኮ…ስንት ዘመን ደንበኛ ሆናችሁ የከረማችሁበት ቤት በድንገት ‘በአዲስ መልክ ስለመጀመር’ ሲያወራ…አለ አይደል…“ሰዎቹ እንዲሁ አሸር በአሸሩን ሲያበሉኝ ነው እንዴ የከረሙት!” ማለታችሁ አይቀርም፡፡ ለስንት ወዳጆቻችሁ እኮ… “የዛን ቤት ቋንጣ ፍርፍር ብትመገብ፣ እንትን ምግብ አሠራር ትምህርት ቤት በከፍተኛ ውጤት በዲፕሎማ ያስመረቅካትን ሚስትህን ፍቺ ትጠይቅ ነበር” አይነት ነገር ስትሉ ነው የከረማችሁት!
ታዲያላችሁ… አሁን ስለ ምግብ ‘መታደስ’ ሲወራ የሆነ ቆንጠጥ የሚያደርግ ነገር አለ፡፡ (ማነው ፖለቲካ ብቻ ነው ‘የሚታደሰው’ ያለው!) ቢሆንም ግን የለመዱትን ቶሎ መላቀቅ አስቸጋሪ ነውና (ቀሺም ፖለቲካም ቢሆን…) ትሄዱና…አለ አይደል… አሁን ወደ ‘ሄር ክላስ’ የተጠጋችውን ቦዘና ሹሮ ታዛላችሁ፡፡ አንዴ ትቀምሱና “በእርግጥም ለውጥ አለ” ትላላችሁ:: (ስሙኝማ…ይቺ አባባል የፖለቲካችን ‘አጄንዳ’ ሆና አረፈችው እንዴ! ‘አጄንዳዎች’ እየበዙብን ስለሆነ ነው፡፡)
እናማ…ምን አለፋችሁ አይደለም የእኛዎቹ፣ አስራ ሁለቱ ዓለም ላይ ያለ የቅምም ዘር በሙሉ የገባበት ነው የሚመስለው፡፡ “እንዲህም ማጣፈጥ ይቻላል!” ዘፈናችንም “በአስራ ሁለት ቅመም የተሠራች ዶሮ” ከሚለው “በሀምሳ ስድስት ቅመም የተሠራች ሹሮ” ‘ሊለወጥ’…ወይም ‘ፖለቲካሊ ኮሬክት’ ለመሆን ያህል… ‘ሊገለበጥ’ ይችላል፡፡ (ዘንድሮ ፖለቲካ የነካካንም፣ ፖለቲካ የነካካን የሚመስለንም ለምንገለባበጥበት ፍጥነት እውቅና ለመስጠት ያህል ነው፡፡ የእንቁጣጣሽ እንኩሮም በዛ ፍጥነት አይገለባበጥማ! እንትና… ‘ካልጠፋ ቃል እንኩሮ የሚለውን ለምን ተጠቀመ?’ የሚል ፓነልዲስከሽን አዘጋጅ አሉ! ቂ…ቂ…ቂ…) 
ታዲያላችሁ፣ ለአንድ ለሁለት ሳምንት ሹሮ በጣእም ከፍታዋ ላይ ትቆያለች፡፡ ሶስተኛው ሳምንት ላይ ልክ በሆነ የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማእቀብ፣ የሀምሳ ስድስት ቅመም ጣዕም ጠፍቶ ይሄ… “ብሉት ግዴለም”፣ “አትብሉት አደገኛ ነው” እያልን የምንከራከርበት ዘይት፣ ‘የጣእሞች ሁሉ እናት’ ሆኖ ቁጭ ይልላችኋል፡፡ በአምስተኛው ሳምንት ደግሞ እሱ ይጠፋና “‘አይስ ሹሮ’ ይቀርብላችኋል፡፡ አሀ…“ያውም በሸክላ ድስት ትክትክ ስትል ያረፈደች ያበደች ሹሮ” የተባለችው እንዴት ነው እስከ ሚጢጢዋ የእግር ጣት የሚሰማ የሰሜን ዋልታ ንዝረት የሚለቅብን! እናላችሁ…አይደለም የጀመርነውን መጨረስ፣ ማጋመስ እንኳን እያቃተን ሁሉ ነገር ‘ጠቅሞ ላይጠቅም’ አይነት ሆኖ ይቀራል፡፡
የሆነ መሥሪያ ቤት አዲስ ባለስልጣን ይሾምላችኋል፡፡ “በዚህ የእቁብ ጸሀፊውም፣ የእድር ዳኛውም ‘ዘውድ ጫኑልኝ’ በሚልበት ዘመን እንዲህም አይነት ባለስልጣን አለ?” የሚያሰኝ አይነት በመላእክነት ተፈጥሮ፣ ግን ክንፉ ተረስቶ ወደምድር የተላከ ይመስላል፡፡ እሱ እንደዛ ግንባሩ ጉልበቱን ሊገጭ እስኪመስል አጎንበሶ ሰላም ለሚለው የእኛ የደም ዝውውር ‘ሲስተም ፌይለር’ ይገጥመዋል፡፡ በምድራዊ ‘የበላይ አካል’ ባለስልጣን ተሹሞ የተመደበ ሳይሆን ዘጠና ዘጠኝ ከመቶአችን ከማንገባበት የሰማይ ቤት ተቀብቶ የተላከ ይመስል፣ ሰው ከሰው ሳይለይ “ልነጠፍላችሁ” ለማለት ምንም አይቀረውም፡፡
ደግሞላችሁ…እኛም ለማመስገን የሚቀድመን ስለሌለ (‘ለመኮነን’ የመጣደፋችንን ያህል ባይሆንም!) አለ አይደል… “እንዴት አይነት የተባረከ ሰው ነው…” ምናምን አንባባላለን፡፡ ያ በአጠገቡ ስናልፍ እንኳን እንደ ስምንት መቶ ዋት የኤሌክትሪክ ሀይል የምንፈራው ‘የአለቃ በር’ ወልል ይላል:: የ‘ኤክሲኪዩቱቭ ሴክሬተሪ ወረቀተ ያልያዘ የመከልከልና የመፍቀድ ስልጣንም ይቋረጣል፡፡ “ገና በሳምንቱ ጉንጯ ስምንት ወር መኖ ያላገኘች ፍየል መሰለች እኮ!” ምናምን እንባባላለን፡፡ (ያውም ‘ተጨባጭ ሰበብ ተገኝቶ!) እናላችሁ… እሳቸው ቢሮ ሰተት ብሎ መግባት ነው፡፡ “እዚሕ የመጣሁት የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ለማስከበር እንጂ ቢሮዬን ቆልፌ ለመቀመጥ አይደለም” አይነት በ‘ፈረንጅ አፍ’ ስላልሆነ ብቻ ዓለም አቀፍ እውቅና የተነፈገው ዲስኩር ይደጋግማል፡፡ 
መቼም… አይደለም አርበሰፊው ባለስልጣን፣ አርባጠባቦቹ እኛ እንኳን ተቀምጠን ስንከርምበት የማይሞቅ ወንበር የለም፡፡ እናላችሁ… የዛ ክንፍ የለሽ መልአክ ያደረግነው ባለስልጣን ወንበሩ መሞቅ ሲጀምርና ሲደላደል ታሪኩ ከምዕራፍ አንድ እንደገና መጻፍ ይጀምራል፡፡ መኮሳተሩና ግንባር መከስከሱ የእሱ የተፈጥሮ ገጽታ ላይ የሆነ ሳይሆን…አለ አይደል… የሆነ ጭምብል ነገር ያደረገ ይመስላል:: “ይሄ ሰውዬ ያው የምናውቀው ባለስልጣን ነው ወይስ ሌላ አለቃ ላኩብን?” ለማለት ምንም አይቀረንም:: አይደለም አጎንብሶ ሰላም ሊላችሁ፣ ‘ቀና ማለቱን’ ከማብዛቱ የተነሳ ትከሻው ወደኋላ ሊንሸራተት ምንም አይቀረው፡፡  
ፈገግታውን፣ ሰላምታውን ምናምን እርሱት:: በአጠገቡ ስታልፉ ርቀታችሁን ካልጠበቃችሁ ግልምጫው…አለ አይደል…“ሰዉ ለካ በሞያሌ በኩል በእግሩ የሚያቀጥነው ወዶ አይደለም” የሚል ከሌላ ታሪክ ተቆርጦ ‘በኮምፒዩተር ስህተት’ የገባ የሚመስል መደምደሚያ ላይ ትደርሳላችሁ፡፡  ያ እንደ እንትን ሞል መግቢያ ወለል ብሎ የሰነበተው የቢሮው በር ክርችም ይላል… ልክ ወደሆነ የኑክሌር ምርምር ጣቢያ አይነት የተለወጠ ይመስል፡፡ እናላችሁ… እንዲህ እንጀምራለን፣ እንዲህ እናፈርሳለን፡፡
ደግሞላችሁ… በፖለቲካው ውስጥ አይታችሁልኝ እንደሁ የሆነ ‘ፖለቲከኛ’፣ በሉት ‘ምናምኒስት በሉት ደገምገም አድርጎ በሚሰጠው አስተያየት “ይሄማ ከልቡ ለሀገር እድገትና ለህዘብ ብልጽግና የሚያስብ ነው” ትላላችሁ፡፡ “ሀገራችን እኮ መከራዋን እየበላች ያለችው የእሱ አይነት ሰዎች  ስለሌሏት ነው” እንላለን:: “እንደው የእኛ ምቀኝነት ሆኖ እንጂ ምናለበት ደህና ሊሠራ የሚችልበት ወንበር ቢሰጡት!” ይባላል፡፡ 
እናላችሁ… አንድ ወር ሳይሞላው…የኦሎምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ጂምናስቲከኞችን በሚያስንቅ ቅልጥፍና ግልብጥብጥ ይልና የማናየው ቀንድና ጭራ ያበቀለ እስኪመስለን ልውጥውጥ ብሎ ቁጭ! “እኛ ዘንድ መቼም ደግ አይበረክት፣ የሆነ ነገር አዞሩበት እንዴ!” እንዳንል በፖለቲካችን እንደዛ አይነት ጥርጣሬዎች ስለሌሉ ነው፡፡ ሰውየው ‘ይዞርበት’ እንደሁ እንጂ ‘የሚዞርበት’ አይኖርማ! ቂ…ቂ…ቂ...
ደግ፣ ደጉን አስጀምሮ ያስጨርሰን፡፡ ክፉ፣ ክፉውን እዛው ይያዝልን!
የደግ፣ ደግ ምንቸት ይግባ፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 2796 times