Print this page
Saturday, 21 September 2019 12:55

ኢትዮጵያዊው ፕሮፌሰር፤ ስለ ትምህርት… ቋንቋ … ጋዜጠኝነት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

   “የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ያሳስበኛል”

               ፕ/ር ዘነበ ክንፈ ይባላሉ፡፡ በሩሲያ የወዳጅነት ዩኒቨርሲቲ (Russian FriendShip University) የጋዜጠኝነት መምህር ናቸው፡፡ በተለያዩ አገራት እየተዘዋወሩም ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤክስፐርትነት ይሰራሉ፡፡ በሩሲያ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንትም ናቸው፡፡ ከጥቂት ሳምንት በፊት ለስራ ጉዳይ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ጊዜ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አግኝቷቸው በትምህርት፣ በቋንቋ፣ በጋዜጠኝነትና በአክቲቪስትነት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል፡፡ እነሆ፡-

                በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ማሻሻያ ይፋ ተደርጓል፡፡ እርስዎ የሚያስተምሩበት የሩሲያ የትምህርት ፖሊሲ ትንሽ ለየት ያለ ነው ይባላል፡፡ ስለ ትምህርት ፖሊሲያቸው በጥቂቱ ቢያጫውቱን?
አዎ፤ የትምህርት ሥርዓታቸው ከሕጻናት መዋያ ጀምሮ የተለየ ነው፡፡ እንደኛ አገር አይደለም:: መደበኛ ትምህርት እስከ 10ኛ ክፍል ነው፡፡ አንድ ሰው ከሕጻናት መዋያ ጀምሮ እስከ ዘጠነኛ ክፍል በመደበኛነት ይማራል። 10ኛ ክፍል ሲደርስ በዲፕሎማ ይመረቃል፡፡ የሚመረቀው ግን በአንድ ትምህርት ወይም በቀለም ትምህርት ብቻ አይደለም:: በአራት የሙያ መስኮች የመመረቅ ግዴታ አለበት፡፡ ከመሰረታዊ ትምህርት ጎን ለጎን አራት አይነት ሙያና ትምህርት መርጦ ይሰለጥናል፡፡ ከዚያም ይመረቃል:: ለምሳሌ የኔን ልጆች የትምህርት ሁኔታ ባስረዳ፤ የመጀመሪያ ልጄ ከመደበኛ የቀለም ትምህርት ጎን ለጎን፣ በሳክስፎን የሙዚቃ መሳሪያና በቅርጫት ኳስ ሰልጥና በዲፕሎማ ተመርቃለች፡፡ ሁለተኛዋ ልጄ ደግሞ በፒያኖ የሙዚቃ መሳሪያና በባህልና ቱሪዝም ሰልጥናለች፡፡ በነገራችን ላይ አሁን ይህቺ ልጄ 20 ዓመቷ ነው። በመንግስት ስራ ላይ ነች:: የባህል ማዕከል ዳይሬክተር ሆና በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡ ትንሹ ወንዱ ልጄ ደግሞ ሲላይን በሚባል የሙዚቃ መሳሪያ ተመርቋል፤ በበረዶ ላይ በሚደረግ የተኩስ ስፖርት፣ በዋናና በአትሌቲክስ አሰልጣኝነት ጨርሷል፡፡ አንድ ታዳጊ 10ኛ ክፍል ሲደርስ፣ በእነዚህ ሙያዎች በሰፊው ሰልጥኖ ነው የሚወጣው፡፡ በተለይ የሙዚቃ ስልጠና ፈጽሞ አይቀርም፤ ግዴታ ነው፡፡ የእጅ ስራ ጥበብ፣ ዎርክሾፕ ገብተው በሥርዓቱ ነው የሚሰለጥኑት፡፡ የሩሲያ የትምህርት ፖሊሲ ወጣቶችን በበርካታ መስኮች ብቁ አድርጎ የሚያወጣ ነው፡፡
በኛ አገር አዲስ ስለተዘጋጀው የትምህርት ፖሊሲ ምን አስተያየት አለዎት?
ከሁለት ወራት በፊት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስቴር ፕ/ር ሂሩት ወ/ማርያም ወደ ሞስኮ በመጡ ወቅት ተገናኝተን ነበር፡፡ በውይይታችን ወቅት ሁለት ትምህርትን የሚመለከት የሚኒስቴር መስሪያ ቤት መኖሩ መልካም መሆኑን ተነጋግረናል:: በነገራችን ላይ የሩሲያም ተመሳሳይ አወቃቀር ነው ያለው፡፡ መደበኛ ትምህርት የሚመለከተው ሚኒስቴር አለ፣ በሌላ በኩል የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የሚከታተል ሌላ ሚኒስትር መ/ቤት አለ:: በውይይታችን የተረዳሁት፤ አዲሱ የትምህርት ሥርዓት፣ ወደ ድሮው 12ኛ ክፍል ወደሚባለው እንደሚመለስ ነው፡፡ እኔ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ:: ተገቢነት አለው፡፡ ምክንያቱም የትምህርት ነገር እየወደቀ መምጣቱን ከጥናቶች ተረድቻለሁ፡፡ በነገራችን ላይ በአለማቀፍ ደረጃ የትምህርት ጥራት በሁሉም አገራት በእጅጉ እየወደቀ ነው። ሁሉም አገራት በአስቸጋሪ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ እያለፉ ነው፡፡ የኛም ከዚህ አንጻር ነው መታየት ያለበት፡፡ ሉላዊነትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው፡፡ አሁን አንድ አስተማሪ ክፍል ውስጥ ቆሞ የሚያስተምርበት ዘመን እያለፈበት ነው። ዛሬ አንድ የ1ኛ ክፍል ተማሪ የራሱን ኮምፒውተር ይከፍታል። ራሱን ከኮምፒውተር ጋር ያለማምዳል:: ከልጅነቱ ጀምሮ ከኢንተርኔት ጋር ይዛመዳል፡፡ ይህ ልጅ ዘጠነኛና 10ኛ ክፍል ሲደርስ ክፍል ውስጥ ቁጭ ብሎ መማሩ ትርጉም ያጣበታል፡፡ ስለዚህ የተሰላቸ የትምህርት ክትትል ነው የሚኖረው፡፡ ለዚህ መፍትሄው አስተማሪው ከዘመኑና ከቴክኖሎጂው እኩል እንዲራመድ ማድረግ ነው። በዚህ ረገድ የአገሪቱ የትምህርት ፖሊሲ አቅጣጫ በግልጽ መቀመጥ አለበት፡፡ ዛሬ የአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎችና ፕሮፌሰሮች በኢንተርኔት፣ በማራኪ አቀራረብ የነፃ ትምህርት መልቀቅ ጀምረዋል፡፡ በርካቶች ያንን ያገኛሉ፡፡ ያነባሉ፡፡ ራሳቸውን በራሳቸው ለማሰልጠን ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ዛሬ በአመዛኙ በአለም ላይ ያለው እውነታ ይሄ ነው፡፡ ከዚህ እውነት ጋር መሰናሰል ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ሲስተማችን መቀየር አለበት፡፡ ሌላው ልጆች ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ጉዳዮች እየበረከቱ መጥተዋል፡፡ ‹‹እገሌ ሚሊየነር የሆነው ትምህርቱን ከ10ኛ ክፍል አቋርጦ በጀመረው ቢዝነስ ነው›› የሚሉና የመሳሰሉ መረጃዎች፣ በሰፊው በዲጅታል አለሙ እየተሰራጩ ነው፡፡ ስለዚህም ልጆች አፍቃሪ እውቀት ሳይሆን አፍቃሪ ንዋይ እንዲሆኑ የሚያደርግ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ ነው:: በዚህ ምክንያት የሚቀጥለው ትውልድ ገንዘብን ከእውቀት እንዲያስቀድም እየሆነ ነው፡፡
ይህን ጉዳይ እንዴት ማስተካከል ይቻላል?
ዘመኑን የዋጀ የትምህርት ስልት በመከተል ነው:: እውቀትን ማዕከል ያደረገ የትምህርት አሰጣጥ ያስፈልጋል፡፡ ይሄን እንዴት እናድርግ የሚል ጥናትም ያስፈልጋል፡፡ ምሁራን በዚህ በኩል ከፍተኛ ሃላፊነት አለባቸው፡፡
በአዲሱ የትምህርት ፖሊሲ የመምህራን የብቃትና ድልድል ሁኔታም ተካትቷል፡፡ ይሄን እንዴት ይገመግሙታል?
በእኔ ግምገማ እዚህ ላይ አንድ ክፍተት አያለሁ:: እርግጥ ነው 1ኛ ደረጃ ማስተማር ያለባቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ነው ይላል፣ ሁለተኛ ደረጃ ሁለተኛ ዲግሪ ያለው ይላል፡፡ ይሄ ተገቢ ቢሆንም ዋነኛው ጥያቄ፤ አስተማሪው ራሱ ዲግሪውን ይመጥናል ወይ የሚለው ነው፡፡ ይሄ በደንብ መታየት አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ አስተማሪ በማንኛውም የትምህርት ብቃት ላይ ቢገኝም፣ በየአመቱ ራሱን ከዘመኑ ጋር እንዲያመጣጥን ማሰልጠን ያስፈልጋል:: አስተማሪዎቹ የንድፈ ሃሳብ ሳይሆን የተግባር እንዲሆኑ፣ ቤተ ሙከራ ሊሟላላቸው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል የቋንቋ ጉዳይ አለ፡፡ ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ ነው፡፡ እኛ አገር ያለው የቋንቋ አተያይ አስገራሚና ተገቢ ያልሆነ ነው:: እኔ ባለሁበት ዩኒቨርሲቲ እያንዳንዱ አስተማሪ ቢያንስ አራት አለማቀፍ ቋንቋ አጣርቶ ማወቅ አለበት፡፡ እኔ በመሰረቱ ሰባት ቋንቋ ነው የምችለው፡፡ ዩኒቨርሲቲው ራሱ ነው ከፍሎ ቋንቋ የሚያስተምረን:: ዘንድሮ ፈረንሳይኛ የተማረ በቀጣይ ስፓኒሽ እያለ ይቀጥላል፡፡ እኛ አገር ቋንቋ ላይ ያለው አተያይ አስቸጋሪ ነው፡፡ እኛ ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የሚመጡ የተለያዩ አገራት ዜጎችን በቋንቋቸው ለማስረዳት ነው የምንሞክረው፡፡ እኛ አገርም ቋንቋ ላይ ያለን አተያይ ተቀይሮ፣ አንድ መምህር የተለያዩ የአገር ውስጥ ቋንቋዎችን እንዲያውቅ መደረግ አለበት፡፡ በተለያየ ቋንቋ የማስረዳት ክህሎት መዳበር አለበት፡፡ በሌላ በኩል፤ የኛ አገር አስተማሪዎች በእነሱ ትምህርት ተማሪ ፈተና እንዲደፍን አይፈልጉም፡፡ እንደ ዝናም ይቆጠርላቸዋል፡፡ አሁን ባለሁበት አገር ግን ይሄ በተቃራኒው ነው፡፡ አንድ መምህር በርካታ ተማሪዎች ውጤታማ ካልሆኑለት ችግር አለበት ማለት ነው:: በሚገባ ይገመገማል፡፡ ችግሩን እንዲያስተካክል ይደረጋል፡፡
አዲሱ የትምህርት እቅድ ብዙ የሚያስተካክለው ነገር ይኖራል የሚል ግምገማ አለ፡፡ ነገር ግን አሁንም የልጆችን የሥራ ፈጣሪነት፣ የቴክኖሎጂ ዝንባሌ የሚያዳብር እንደ ‹‹የእጅ ሥራ›› አይነት ትምህርት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ አካባቢና ተፈጥሮ ሀብታችንን ያማከለ ሁነኛ ትምህርት መሰጠት አለበት፡፡ ቀድሞ ‹‹እርሻ›› የሚባል ትምህርት ነበር፡፡ የኛ አገር አብዛኛው የኢኮኖሚ ምንጩ ግብርና ነው እንላለን፤ ነገር ግን በዚህ መስክ ሁነኛ የትምህርት አይነት የለንም፡፡ ከብት እርባታ፣ ዶሮ እርባታ የመሳሰሉት ላይ ብዙ መስራት ያስፈልጋል፡፡
የጋዜጠኝነት መምህር እንደመሆንዎ በአሁን ወቅት ያለውን የጋዜጠኝነት፣ የአክቲቪስትነትና የጦማሪነት ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መምጣቱን ተከትሎ፣ በጋዜጠኝነት ላይ የመጡ አዳዲስ ባህሪያት በራሳቸው  አከራካሪ ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ ማን ነው? አክቲቪስት ማን ነው? ጦማሪ ማን ነው? የሚለው አሁንም ድረስ በአለማቀፍ ደረጃ አከራካሪ ነው፡፡ የተለያዩ አገራት እነዚህን ለመበየን ሕጎችን እስከማውጣትም ደርሰዋል። እኔ ያለሁበት ሩሲያም ጋዜጠኛ ማን ነው? የሚለውን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሕግ አለው:: እንግሊዝም እንዲሁ፡፡ ዛሬ አንድ ሰው ብቻውን ለሚሊዮኖች መረጃ ማሰራጨት የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ለዚህ የመገናኛ ብዙሃን (ማስሚዲያ) ፅንሰ ሀሳብን ማጎልበቱ ጠቃሚ ይሆናል። ማስሚዲያ  ሰፊ ትርጉም ያለው ነው፡፡ ማስ ሚዲያ በውስጡ የሰው ሃይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ሀሳብን አቀናጅቶ የያዘ ነው። መረጃን የማጥራትና የማቅረብ፣ ሁሉም አንድ አይነት አመለካከት የሚይዝበት ነው፡፡ ጋዜጠኛው ከሌላው መረጃ አቅራቢ የሚለየው በተቋም ስር ሆኖ በሃላፊነት ለሁሉም ማዳረስ መቻሉ ነው። የማህበረሰብን አተያይና አስተሳሰብ የመቅረጽ ሃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህ ነው ጋዜጠኛ ማስትሬት ያደርጋል የሚባለው:: ብዙ አገሮች በሕጋቸው ላይ በማህበራዊ ሚዲያ የሚጻፍ መልዕክት የሚያስተላልፉ ግሰለቦችን ጋዜጠኛ ብለው አይበይኗቸውም፡፡ ምክንያቱም ጋዜጠኛ ሲባል መረጃ ሰብሳቢ፣ የሰበሰበውን መረጃ የሚያገናዝብ፣ አገናዝቦም ተገቢ ነው ብሎ ያዘጋጀውን ማሰራጨት የሚችል ነው። መረጃን አጣርቶ ነው የሚያቀርበው። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያለው ግን መረጃን በመሰብሰብ፣ በመተንተን፣ በማገናዘብ ማስተር አላደረገምና ዝም ብሎ ነው መረጃ የሚለቀው፡፡ ስለዚህ የጋዜጠኝነት ሥራ ሰርቷል አይባልም፡፡ የማጣሪያ ወንፊት የለውም:: ለዚህ ነው ዛሬ በኛም አገር ሆነ በርካቶች በሚለቀቁ መረጃዎች እየተሳሰረ እየተተራመሰ ያለው፡፡ በሩሲያ ብሎገር (ጦማር) የሆነና በቀን ሶስት ሺህ ሰው የሱን ጽሁፍ የሚመለከት ከሆነ፣ ወዲያው የአገሪቱ ሕግ፤ ተጠያቂነት ያለው ጋዜጠኛ አድርጎ ይመዘግበዋል፡፡ ወዲያውኑ የአገሪቱ የሚዲያ ሕግ በሰውየው ላይ ይተገበራል፡፡ ጋዜጠኝነትን እንዲያጠና ይገደዳል፡፡ ግብር መክፈል የመሳሰሉ ሕጎች ይተገበርበታል፡፡ በኛ አገር ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያላቸው አሉ፡፡ ሩሲያ ቢሄዱ ከ3ሺህ በላይ የሚለው ሕግ ይተገበርባቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ በቻይና ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታይ ያላቸው ብሎገሮች ከጀርባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ይኖሩዋቸዋል፡፡ አንድ ብሎግ ዘገባዎች የሚያዘጋጅለት፣ የሚተነትንለት ሰው ከጀርባው አለ፡፡ እሱ ፊት ለፊት ስሙን ብቻ ነው የሚጠቀመው፡፡ ስፒግል የተሰኘውን የጀርመን የብሎግ መጽሔት ብንመለከት፤ የሚታወቁት ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከጀርባቸው ግን እስከ 2 መቶ የሚደርሱ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ይሄ አሰራር እኛም አገር መተግበር ቢችል መልካም ነው፡። በሚሊዮን የሚቆጠር ተከታይ ያለው ነገር ግን ያለ ምንም ተጠያቂነት ያገኘውን መረጃ የሚለቅ ሰው፣ በሕግ፣ ተጠያቂነት በሙያ እንዲሰራ ማድረግ ይቻላል፡፡ ያለ ሕግ ተጠያቂነትና የሃላፊነት ስሜት ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ መልዕክት ማሰራጨት በሕግ የሚገታበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡
በኛ ሚዲያዎች አንድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር፤ በዜናዎቻቸው ምንጭ አይጠቅሱም፡፡ ‹‹እገሌ በዚህ ቦታ እንዲህ አለ›› ከማለት ይልቅ ‹‹ይህ እንዲህ ተባለ›› የሚል ድፍን መረጃ ነው የሚሰጡት፡፡ ይሄ አይነቱ አካሄድ የሕግ ተጠያቂነት ሲመጣ አስቸጋሪ ነው። ሙያዊም አይደለም፡፡ በሌላ በኩል፤ ጋዜጠኛ በሕዝብና በባለሥልጣን መካከል ያለ ድልድይ ነው፡፡ የሕዝቡን መልዕክት ለመንግስት የሚያደርስ ነው፤ ጋዜጠኛ፡፡ በኛ አገር አንድ የምታዘበው ጉዳይ ደግሞ ጋዜጠኞች በአንድ ጉዳይ ላይ ስፔሻላይዝ አለማድረጋቸውን ነው፡፡ ለምሳሌ ስፖርት የሚዘግብ ጋዜጠኛ ምርምሩ በሙሉ ስለ ስፖርት መሆን አለበት፡፡ የፖለቲካ ጉዳይ የሚዘግብ ቢቻል ሁለተኛ ዲግሪውን ፖለቲካ ማጥናትና ስለ ፖለቲካ ምርምር የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ ስለ ኢኮኖሚ የሚዘግበውም ኢኮኖሚን መማርና መመርመር አለበት፡፡ እኔ የማስተምራቸው ጋዜጠኞች እንደዚህ በሁለት በኩል የተሳሉ እንዲሆኑ ነው የማደርገው፣ የምመክራቸውም፡፡ ጎበዝ ጋዜጠኛ፤ ራሱን ሁሉም ጋ ከመበተን ይልቅ በአንድ የመረጠው ጉዳይ ስፔሻላይዝ ለማድረግ ነው የሚጥረው፡፡
በሩሲያ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ዳያስፖራ ማህበር ፕሬዚዳንት ነዎት… በሩሲያ ያሉ ዳያስፖራዎች ስለ አገራቸው ምን ያስባሉ? በምን ደረጃ ላይስ ይገኛሉ?
እኔ ይሄ ዲያስፖራ የሚለውን ስም አልወደውም:: የኢትዮጵያ ተወላጆች ማህበረሰብ ብንለው ይሻላል:: በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ቀላል የሚባል ቁጥር እንደሌለው የተለያዩ መረጃዎችን ማየት ይቻላል፡፡
በውጭ ባለው ማህበረሰባቸው በእጅጉ ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት አንዷ የሆነችውን እስራኤልን ብንመለከት፣ አገር ውስጥ ካለው በውጪ ያለው ሕዝቧ ይበልጣል፡፡ ሊባኖስም እንደዚሁ፣ ህንድም ሰፊ ማህበረሰብ በውጪ አላት፣ ቻይናም በተመሳሳይ፡፡ እነዚህ አገራት ገቢያቸውም ከፍተኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያም በውጭ ያሉ ዜጎችን ማፈላለግና ወደ ገንዘብ መቀየር አለባት፡፡ ሕንድ 4 ቢሊዮን ዶላር ነው በ2019 ያስገባችው። በእርግጥ ኢትዮጵያም በዚህ በኩል የምትታማ አይደለችም፡፡ የበለጠ ማስፋት ግን ያስፈልጋል፡፡ በሩሲያ ያለን የኢትዮጵያ ማህበረሰብ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡልንን ጥሪ ተቀብለን፣ በርካታ ተሳትፎ እያደረግን ነው:: የዳያስፖራው ትረስት ፈንድ ተሳታፊም ነን። ይህ ትረስት ፈንድ ምን ላይ ይዋል በሚሉ ጉዳዮችም ላይ እየተወያየን ነው፡፡
ስለ አገርዎ ምን ያስባሉ?
በጣም እያደገ ነው፡፡ ነገር ግን በጣም የሚያሳስብ ነገር ያየሁት የሕዝብ ብዛት ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ከአገር ስወጣ ወደ 47 ቢሊዮን ነበር፤ አሁን 110 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
በዚያ ልክ ግን የአገሪቱ የምርት መጠን አላደገም። ይሄ አደገኛ ነገር ነው። በተለይ አዲስ አበባ ተጨናንቃለች፡፡ ሌሎች ከተሞች በአዲስ አበባ ልክ ማደግ አለባቸው፡፡ የሥራ ፈጠራ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ አገሪቱ እያደገች ነው፡፡ በዚያ ልክ ግን ከውጭ የተበደረችው እዳ አሳሳቢ ነው። እራሳችንን ለቅኝ ግዛት አሳልፈን እየሰጠን እንዳይሆን እሰጋለሁ። ለቀጣዩ ትውልድ የምናስረክበው ምንድነው? ባርነት ነው? ይሄ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡


Read 3054 times