Saturday, 21 September 2019 12:38

በኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ 976 ብር ደርሷል ተባለ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

 ባለፉት 3 ዓመታት በጤና ተቋማት ህክምና
         የሚያገኙ ዜጐች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል
                  
            በጤናው ዘርፍ ያሉትን ችግሮች ለማስተካከልና አገራዊ ዕቅድ ለሚመጡት ያግዛል የተባለው አገራዊው የጤና ወጪ ስሌት ጥናት ይፋ ሆነ፡፡ ጥናቱ አጠቃላየ የጤና ዘርፍ ወጪው በ2006 ከነበረው አጠቃላይ ወጪ በ3 ዓመት ብቻ በ23 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱን አመልክቷል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጀ በየሶስት ዓመቱ በሚሰራው በዚሁ የጤና ወጪ ስሌት ላይ እንደተገለፀው በ2006 ዓ.ም የነበረው አጠቃላይ የጤና ወጪ 49.5 ቢሊየን ብር ሲሆን በ2009 ዓ.ም ቁጥሩ አሻቅቦ 72 ቢሊየን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡ ለህክምና ከታካሚዎች ኪስ የሚወጣው ወጪ ከ33 በመቶ ወደ 31 በመቶ መቀነሱን ያመለከተው  ጥናቱ ከመንግስት የሚወጣው የጤና ወጪ ከ30 በመቶ ወደ 32 በመቶ አድጓል ተብሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ይፋ የተደረገው ይኸው ጥናት በ2009 ዓ.ም የታካሚዎች የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ 33.22 የአሜሪካ ዶላር ወይም 976 ብር መድረሱንም አመልክቷል፡፡
ከአጠቃላዩ የጤና በጀት 41 በመቶ የሚሆነው የሚውለው በመጀመሪያ ደረጃ የጤና አጠባበቅ ክፍል ሲሆን 29.4 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በሆስፒታሎች ደረጃ ወጪ የሚደረግ ነው ተብሏል፡፡

Read 824 times