Saturday, 21 September 2019 12:41

የእሬቻ በዓል ዘንድሮ በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች ይከበራል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

- ከፀጥታና ደህንነት ሀይሉ ጋር በትብብር ለሚሰሩ 20ሺ ወጣቶች ስልጠና እየተሰጠ ነውበአገራችን የመጀመሪያው የገዳ ፌስቲቫል ሊከበር ነው
      - ለበዓሉ 4 ሺ ሜትር ርዝመት ያለው ጩኮ እየተሰራ ነው፡፡
          
         በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ክብርና ልዩ ቦታ የሚሰጠውና ፈጣሪን የማመስገኛ በዓል የሆነው የእሬቻ በዓል ዘንድሮ በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ ከተሞች ላይ እንደሚከበር የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። በዓሉን ዘንድሮ ለየት ባለ ሁኔታ ለማክበርና በዓሉን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት ሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ከማይዳስሱ የአገራችን ቅርሶች አንዱ አድርጎ ለማስመዝገብ እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል:: የዚህ በዓል አካል የሆነና በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ የገዳ ፌስቲቫልም ይካሄዳል ተብሏል:: በአሉን በሰላም ለማክበር እንዲቻል ከፀጥታና ደህንነት ጥበቃ ጋር በተያያዘ የፀጥታ ዘርፉን የሚያግዙ 20 ሺ ወጣቶች ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሆነና ልዩ ዩኒፎርም እንደተዘጋጀላቸው ተገልጿል፡፡
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለፀው በዘንድሮው የእሬቻ በዓል ከ6 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ የእሬቻ በዓል በዓሉን በሚያደምቁ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች የሚታጀብ ሲሆን የገዳ ፌስቲቫልም የዚሁ በዓል አካል ይሆናል ተብሏል፡፡ በአለማችን እጅግ ግዙፍ የሆነውንና የኦሮሞ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ጭኮ በተለየ መንገድ በመስራት በድንቃ ድንቅ መዝገብ ውስጥ ለማስፈር እየተሰራ እንደሆነ አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
4ሺ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል የተባለው የዚሁ ጭኮ ሥራ የኦዳ ካፌ ባለቤት በሆኑ ግለሰብ እየተሰራ ሲሆን ጭኮውን ለመስራት እስካሁን ከ3 ሺህ ሁለት መቶ ኪሎ በላይ ቅቤ ጥቅም ላይ መዋሉ ተገልጿል:: የጭኮ ሥራው ገና ያልተጠናቀቀ ሲሆን ስራው ሲጠናቀቅ ለጭኮው የወጣው የገብስና የቅቤ ፍጆታ እንደሚገለጽም የጭኮውን ሥራ በባለቤትነት እየሰሩ የሚገኙት የኦዳ ካፌ ባለቤት ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ጭኮውን በአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ውስጥ በግዙፍነቱ አቻ ያልተገኘለት ባህላዊ ምግብ አድርጎ ለማስመዝገብም እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በነገው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚካሄደውና ከ50 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው የእሬቻ የሩጫ ውድድር የሚጀመረው የበዓሉ አከባበር መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም በሆራ አርሰዲ ቢሾፍቱ በሚካሄድ የማጠቃላይ ፕሮግራም ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ከመስከረም 20 እስከ 30/2012 በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚካሄደው የገዳ ፌስቲቫል በእሬቻ ባህልና የገዳ ሥርዓት በአንድነት በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፍ ያለውን ፋይዳ የሚያሳዩ ጥናታዊ ጹሁፎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡
ከመስከረም 12 እስከ 22 በሚከናወነው ልዩ የባዛርና የካርኒቫል ፕሮግራሞች የኦሮሞን ባህልና ታሪክ የሚያጎሉ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡ መስከረም 22/2012 በኦሮሞ ምሁራን የሚቀርቡ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚስተናገዱበት ፎረም እንደሚካሄድና መስከረም 23/2012 የዋዜማ ፕሮግራም እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡  በአዲስ አበባ ከተማ መስከረም 24/2012 በሚካሄደው የሆራ ፍንፊኔ እሬቻ በዓል ላይ ቁጥራቸው ከ6 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎችና የአለማችን አገራት የሚሰባሰቡ ተሳታፊዎች ተካፋይ ይሆኑበታል ተብሏል፡፡ የበዓሉ ሥርዓት የሚጠናቀቀውም በማግስቱ መስከረም 25/2012 በቢሾፍቱ ኦራ አርሰዴ በሚከናወን የእሬቻ ሥርዓት እንደሚሆንም አዘጋጆቹ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
የእሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን በዓል ስለሆነ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆን አዘጋጆቹ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Read 1980 times