Saturday, 14 September 2019 10:29

ቀነኒሳና ማራቶን ልዕልቷ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 • ‹‹የዓለም ማራቶን ሪከርድን ከኬንያውያን የሚነጥቁት ኢትዮጵያውያን ናቸው›› - ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች
      • ‹‹ቀነኒሳ በማራቶን ዝግጅቱ፤ ስልጠና፤አመጋገቡ አኗኗሩ ላይ ስር ነቀል ለውጥ አድርጓል፡፡›› - NN Running Team
      • ‹‹ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባት ጨረቃን እንደመርገጥ ነው…›› - ኤሊውድ ኪፕቾጌ


         46ኛው የበርሊን ማራቶን ከ15  ቀናት በኋላ የሚካሄድ ሲሆን  በረጅም ርቀት የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ የሆነው አትሌት  ቀነኒሳ መወዳደሩ ትኩረት ስቧል፡፡ በወንዶች ምድብ ከቀነኒሳ ጋር ሌሎች አራት የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች መሳተፋቸውም የኬንያ ማራቶኒስቶች በአሸናፊነት እና በፈጣን ሰዓቶቻቸው የያዙትን የበላይነት እንደሚቀናቀን እየተገለፀ ነው፡፡
በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የወርቅ ደረጃ በተሰጠው 46ኛው በርሊን ማራቶን ላይ ከ107 አገራት ከ66 ሺ በላይ ተሳታፊዎች ሲኖሩት፤ በዋና ዋና ጎዳናዎች የሚመለከቱት ከ1 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡ በዋናው የአትሌቶች ውድድር ከሚጠበቁት ፈጣን ሰዓቶችና የሪከርድ ብቃቶች ባሻገር ከ16 በላይ ልዩ ክብረወሰኖች በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ GUINNESS RECORD ላይ ለማስመዝገብ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው ተዘግቧል፡፡  በበርሊን ማራቶን ለሚያሸንፉ አትሌቶች በሁለቱም ፆታዎች በነፍስ ወከፍ 230ሺ ዩሮ የገንዘብ ሽልማት ከቦነስ ጋር የሚታሰብ ሲሆን ለዓለም ሪከርድ የተዘጋጀው የቦነስ ሽልማት ደግሞ 50ሺ ዩሮ ነው፡፡የዘንድሮው ውድድር  በተለይ ትኩረት መሳብ የጀመረው ከሳምንታት በፊት አትሌት ቀነኒሳ በቀለ እንደሚወዳደር በማስታወቁ ነው:: ቀነኒሳ ያለፈውን 1 ዓመት በማራቶን የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በከፍተኛ ትኩረት ሲሰራ እንደነበር ታውቋል፡፡  የበርሊን ማራቶንን እንደሚሮጥ ቀነኒሳ ከመናገሩ በፊት በሚወጡ ዘገባዎች ስለሪከርድ እየተጠቀሰ አልነበረም፡፡ የበርሊን ማራቶን ዳይሬክተር  ማርክ ሚልዴ «በወንዶቹ በኩል የተሻለ ብቃት እንደሚመዘገብ ተስፋ እናደርጋለን። በዚህ ውድድር ላይ የዓለም ክብረወሰን ይሰበራል ብለን ባንጠብቅም ፈጣን ሰዓት እንደሚመዘገብ እንጠብቃለን» በማለትም ተናግረው ነበር።
ሰሞኑን ከውድድሩ ጋር ተያይዘው የሚወጡት ዘገባዎች ግን  የዓለም ማራቶን ሪከርድን ከኬንያዊያን ማራቶኒስቶች የመንጠቅ እድል ያላቸው የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች መሆናቸው እየጠቀሱ ናቸው፡፡ ምናልባትም በዘንድሮው ውድድ ከቀነኒሳ ጋር ሌሎች ምርጥ የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች መኖራቸው ከኬንያ አትሌቶች ውጭ የሚሻሸልበት እድልን አምልክቶ ይሆናል፡፡ ከ1500 ሜትር ጀምሮ እስከ ማራቶን ድረስ 17 የሩጫ ዓመታትን ያሳለፈው ቀነኒሳ ባስመዘገባቸው ሪከርዶች፤ የሜዳልያዎች ስብስብ እና ተያያዥ የውጤት ታሪኮች የዓለማችን የምንግዜም ምርጥ አትሌት ሆኖ እንደሚጠቀስ ይታወቃል፡፡ ከማራቶን በፊት በሩጫ ዘመኑ ከ21 በላይ የዓለም ሻምፒዮናነት ክብሮችንና የወርቅ ሜዳልዎችን ሰብስቧል፡፡ በኦሎምፒክ፤ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና፤ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስና በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ ለዓለም ሻምፒዮናነት በመብቃት ብቸኛውና የመጀመርያው አትሌት ነው፡፡ በሩጫ ዘመኑም 6 የዓለም ሪከርዶችን በማስመዝገብ በተለይ ደግሞ በረጅም ርቀት 5ሺ ሜትርና 10ሺ ሜትር ውድድሮች የዓለም ሪከርዶችን ላለፉት 15 ዓመታት ተቆጣጥሮ በመቆየቱም የዓለማችን  የምንግዜም ምርጥ አትሌት መሆኑን አረጋግጦለታል፡፡  ከ3 ዓመታት በፊት በ43ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ (2፡03፡03) በሆነ ጊዜ እንዳሸነፈ የሚታወስ ሲሆን ይህ ሰዓት  በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ 4ኛ ላይ የሚገኝ  ነው። በርሊን ማራቶን ላይ ከ1998 እኤአ ጀምሮ በወንዶች 8 ጊዜ የዓለም ሪከርዶች የተመዘገቡ ሲሆን 5 ጊዜ በኬንያውያን ፖል ቴርጋት(2፡04፡55)  በ2003፤ ፓትሪክ ማኩ (2፡03፡38) በ2011፤ ዊልሰን ኪፕሳንግ (2፡03፡23) በ2013፤ ዴኒስ ኪሜቶ (2፡02፡57) በ2014  እና ኤልዊድ ኪፕቾጌ (2፡01፡39) በ2018 እኤአ ላይ ናቸው፡፡ ሁለት ክብረወሰኖች ደግሞ በኃይሌ ገብረስላሴ በ2007 እኤአ ላይ(2፡04፡26) እንዲሁም በ2008 እኤአ ላይ (2፡03፡59) የተመዘገቡ ሲሆን ብራዚላዊው ሮነልድ ደ ኮስታ በ1998 እኤአ (2፡06፡05)ያስመዘገቧቸው ናቸው፡፡
በ46ኛው የበርሊን ማራቶን ላይ ከአትሌት ቀነኒሳ ጋር የሚሳተፉት የኢትዮጵያ ማራቶኒስቶች ጉዬ አዶላ፣ ልዑል ገብረስላሴ፣ ሲሳይ ለማ እና ብርሃኑ ለገሰ ሲሆኑ፤ ባለፉት 10 ወራት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተካሄዱ ማራቶኖች ያሸነፉና 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃዎችን በአማካይ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡ ከ2 ዓመት በፊት የመጀመርያ ማራቶኑን በርሊን ላይ የሮጠው ጉዬ አዱላ  ሁለተኛ ደረጃ ነበር ያገኘው፡፡ የ24 ዓመቱ ብርሐኑ ለገሰ ደግሞ የቶኪዮ ማራቶንን  በ2፡04፣48 የሆነ ጊዜ በማስመዝገብ አሸንፎ ለኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን የተመረጠ ነው፡፡ ልዑል ገብረስላሴና ሲሳይ ለማ ደግሞ በዱባይ ማራቶን ምርጥ ሰዓታቸውን በውድድር ዘመኑ ያስመዘገቡ ወጣት ማራቶኒስቶች  ናቸው፡፡
በሴቶች ምድብ ደግሞ የበርሊን ማራቶንን እንደሚያደምቁ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ከ2 ሰዓት ከ19 ደቂቃዎች በታች የገቡ የኬንያና የኢትዮጵያ  ማራቶኒስቶች ናቸው፡፡ በተለይ የኬንያ ማራቶኒስቶች የላቀ ግምት የወሰዱ ሲሆን፤ አምና በበበርሊን ማራቶን ያሸነፈችውና የቦታውን ሪከርድ የያዘችው ኬንያዊቷ ግላዲስ ቼሮኖ ዋንኛዋ ናት፡፡ ግላዲስ ዘንድሮ በበርሊን ማራቶን በሩጫ ዘመኗ ለአራተኛ ጊዜ በማሸነፍ፤ 3 ጊዜ በማሸነፍ ልዩ ውጤት  ካስመዘገበችው ኢትዮጵያዊቷ አበሩ ከበደ የተጋራችውን ክብረወሰን ለማሻሻል ታነጣጥራለች፡፡ በማራቶን የኦሎምፒክና የዓለም ሻምፒዮን የሆነችው ሌላዋ ኬንያዊት ቪቪያን ቼሮይትም የዓለም ሪከርድን ለመስበር ተስፋ ማድረጓን ዘገባዎች ጠቅሰዋል፡፡ በሴቶች ምድብ የኬንያዎቹ ማራቶኒስቶች ከፍተኛውን ግምት ቢወስዱም ኢትዮጵያዊቷ ማራቶኒስት ማሬ ዲባባና ሌሎች የቡድኗ አባላቶች ተፎካካሪነታቸው ይጠበቃል፡፡ ማሬ በ2015 እኤአ ላይ በቤጂንግ 15ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳልያ እንደወሰደችና በሪዮ 31ኛው ኦሎምፒያድ የነሐስ ሜዳልያ እንደተጎናፀፈች ይታወቃል፡፡
በበርሊን ማራቶን ታሪክ ማሸነፍ የቻሉት ኢትዮጵያውያን ለ4 ጊዜያት ኃይሌ ገብረስላሴ (በ2006፤ 2007፤ 2008፤ 2009 እኤአ) እንዲሁም ቀነኒሳ በቀለ አንድ ጊዜ (በ2017 እኤአ) ናቸው::  የበርሊንን ማራቶንን በሴቶች ምድብ ጌጤ ዋሚ (በ2006 እና በ2007 እኤአ)፤ ትርፊ ፀጋዬ (በ2014 እኤአ አፀደ ሃብታሙ (በ2009 እኤአ ) አበሩ ከበደ (በ2010 ፤ በ2012 እና በ2016 እኤአ) አሸንፈዋል፡፡
ቀነኒሳ የተሳተፈባቸው ማራቶኖች…
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የመጀመርያ ማራቶኑን የሮጠው ከ5 ዓመታት በፊት  በፓሪስ ማራቶን ሲሆን በ2፡05፡04 በሆነ ጊዜ የግሉን ፈጣን ሰዓትና የቦታውን ክብረወሰን  አስመዝግቦ ከማሸነፉም በላይ በመጀመርያ ማራቶናቸው ፈጣን ሰዓት ካስመዘገቡ አትሌቶች በ6ኛ ደረጃ ያስቀመጠው ነበር፡፡   ከፓሪስ ማራቶን ተሳትፎው በኋላ በ6 ወራት ውስጥ በቺካጎ ማራቶን ሲያደርግ በ2፡05፡51  በሆነ ጊዜ 4ኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በ2015 እኤአ መግቢያ ላይ ደግሞ በዱባይ ማራቶን አድርጎ በ30ኛው ኪሜ ላይ ውድድሩን በጉዳት ምክንያት አቋርጦ ወጣ፡፡  ከዚያም በለንደን ይሮጣል ተብሎ ቢጠበቅም የነበረበት ጉዳት በማገርሸቱ ተሳትፎውን ሰረዘው፡፡ በማራቶን ዘመኑ አስደናቂውን ውጤት ሊያስመዝግብ የበቃው በ2016 የበርሊን ማራቶን ሲሆን (2፡03፡03) በሆነ ጊዜ በማሸነፍ ዓለምን አስደነቀ፡፡ ይህ ውጤቱ በኢትዮጵያ ማራቶን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን የኢትዮጵያ የማራቶን ሪከርድ ሆኖ ለ8 ዓመታት የቆየውን የኃይሌን ሰዓት በ56 ሰከንዶችን አሻሽሎ አዲስ የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርዱ ሆኖ የተመዘገበ፤ በተጨማሪም በወቅቱ  በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ሁለተኛ የሆነ ነበር፡፡ ከ3 ዓመታት በኋላ በ2019 የለንደን ማራቶን ሁለተኛ ደረጃ ያገኘው ሌላው የኢትዮጵያ ማራቶኒስት ሞሰነት ገረመው (2፡02፡55) በሆነ ጊዜ የኢትዮጵያን ማራቶን ሪከርድን የተረከበው ሲሆን እና በማራቶን ምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ያለውንም ደረጃ ወስዶበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በማራቶን የምንግዜም ፈጣን ሰዓቶች ደረጃ ላይ ከሞሰነት ገረመው የኢትዮጵያ ማራቶን ሪከርድ ቀጥሎ ዴኒስ ኪመቶ ያስመዘገበው (2፡02፡57) ሲሆን የቀነኒሳ (2፡03፡03)  4ኛ ላይ የሚገኝ ነው።  ከዚያም በ2017 እኤአ ላይ  አምስተኛውን ማራቶን ለመሮጥ የዱባይ ማራቶንን ቢመርጥም በተሟላ አቋም ለውድድሩ መድረስ ሳይችል ቀርቷል:: በለንደን ማራቶን ባገኘው 3ኛ ደረጃ በሪዮ ዲጄነሮ በተካሄደው 31ኛው ኦሎምፒያድ በማራቶን ቡድን ሳይካተት መቅረቱ አነጋጋሪ ነበር፡፡  በ2017 የለንደን ማራቶንን  ተሳትፎውም በሁለተኛ ደረጃ ሲጨርስ (2፡05፡57)  የሆነ ጊዜ አስመዝግቦ ሲሆን አስቀድሞ ከነበረው ፈጣን ሰዓት የወረደ በመሆኑ በቋሙ ላይ ጥርጣሬዎች መፈጠራቸው አልቀረም፡፡ በ2018 እኤአ ላይ ቀነኒሳ 6ኛ ማራቶኑን ከኬንያዊው ኤልውድ ኪፕቾጌ እኩል ለክብረወሰን ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት በለንደን ማራቶን ላይ ቢሰለፍም፤ (2፡08፡53) በሆነ ጊዜ በ6ኛ ደረጃ  ጨርሶ  ያልተጠበቀውን ውጤት አስመዘገበ:: ከ46ኛው የበርሊን ማራቶን በፊት የተወዳደረበት ማራቶኑ የ2018 አምስተርዳም ማራቶን ሲሆን ባገረሸበት ጉዳት ውድድሩን ለማቋረጥ የተገደደው የማራቶን ርቀቱ 1 ኪሜትር ሲቀረው ነበር፡፡
ቀነኒሳ ከ46ኛው የበርሊን ማራቶን በፊት…
አትሌት ቀነኒሳ በቀለ  ወደ ማራቶን ፊቱን ካዞረ 10 ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን በ9 ማራቶኖች ተሳትፎ ያሸነፈው ሁለት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት የዓለም ማራቶን ሪከርድ የያዘው ኪፕቾጌ ከተሳተፈባቸው 10 የማራቶን ውድድሮች ሁሉንም ማሸነፍ ችሏል፡፡
በማራቶን ራሱ የሚፈልገውንና መላው የአትሌቲክስ ዓለም የሚጠብቅበትን ውጤት ለማስመዝገብ ያልቻለባቸው ዋንኛ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ያጋጠሙት የተለያዩ ጉዳቶች እንዲሁም ከአኗኗሩ ጋር በተያያዘ የተፈጠሩበት ጫናዎች ናቸው፡፡ በ2018 የአምስተርዳም ማራቶን ላይ ቀነኒሳ ሲሳተፍ ወደ መደበኛ አቋሙ ተመልሶ ፈጣን ሰዓት ሊያስመዘግብ ይችላል በሚል ግምት ቢሆንም ውድድሩን እየመራ ቆይቶ አጠቃላይ ርቀቱ ሊጠናቀቅ 1 ኪሎ ሜትር ሲቀረው አቋርጦ መውጣቱ ስርነቀል ለውጥ እንዲያደርግ አስገድዶታል፡፡ ከአምስተርዳም ማራቶን በኋላ  የግሉ አሰልጣኝ መርሻ አስራት፤ የማነጀሩ ጆስ ሄርማንስ ግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽንና የኤንኤን የሯጮች ቡድን NN Running Team  በማራቶን ዝግጅቱ እና ውጤታማነቱ ላይ በጋራ በመስራት ለውጥ ለማምጣት ተባብረዋል፡፡ ለማራቶን በሚያደርገው ልምምድ፤ ልዩ ዝግጅት እና በአኗኗር ሁኔታው ላይ ለውጥ እንደሚያስፈልግ በማመናቸው ነበር፡፡
አትሌት ቀነኒሳ የማራቶን ዘመኑን አስመልክቶ በቅርቡ በሰጠው አስተያያት‹‹ ዛሬ 20 ዓመቴ አይደለም፤ ለማራቶን የሚያስፈልግ ቁመና እና የአካል ብቃት እንዲኖረኝ በምስራው ልምምድ እና ዝግጅት ለውጥ እንደሚያስፈልገኝ አምኜበታለሁ፡፡ እውነቱን ለመናገር የሩጫ ዘመኔን ከማቆሜ በፊት  የላቀና ከፍተኛ ውጤት በማራቶን ማስመዝገብ አለብኝ፡፡ ስለዚህም ከማራቶን ቡድንና የተለያዩ ባለሙያ አጋሮቼ ጋር በመስራት ቀጥዬአለሁ፡፡ በማራቶን ያለኝን አቅም ለማስመስከር እፈልጋለሁ፡፡›› በማለት ተናግሯል፡፡ በዚህ መሰረት ያለፈውን አንድ ዓመት አትሌት ቀነኒሳ በልዩ ትኩረት በሆላንድ ኒጅመገንና በአገር ውስጥ እየተዘጋጀ ነበር:: ዋናው እቅዱ በ2020 እኤአ የቶኪዮ ኦሎምፒክ የማራቶን ቡድን ለመካተት መሆኑን ቢገልፅም፤ ይህን የዝግጅት ትኩረቱን በመታዘብ የዓለም አትሌቲክስ ባለሙያዎች የማራቶን ርቀትን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት አቅም እንዳለውና የዓለም  ሪከርድን ለመስበር እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲመሰክሩበት የቆዩበትን አጀንዳ መልሰው አራግበዋል፡፡
አትሌት ቀነኒሳ በማራቶን ወጥነት ያለው አቋም እንዳያሳይ መነሻ የነበረው በተለይ በ2010 እኤአ ላይ የገጠመው የጡንቻ መሰንጠቅ ነበር፡፡ ይህ ጉዳት መላ ተክለሰውነቱን ከማቃወሱም በላይ ከጉዳቱ ለማገገም በወሰደው ህክምና ውስጥ ያለፈባቸው ሂደቶች ተጨማሪ መዘዞች ሳይፈጥሩበት አልቀረም፡፡ ባለፉት 8 ዓመታት ውስጥ በማራቶን ማስመዝገብ የሚችለውን ውጤት እንዳያሳካ ከጡንቻ መሰንጠቁ በኋላ  በጉልበቱ፤ በቋንጃው፤ በጀርባው በጎድኑ እና በእጁ ላይ የሚያገረሹት ጉዳቶቹ እንቅፋት ሆነውበታል፡፡ ከትራክ እና የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች ዝግጅትና ተሳትፎው በተያያዘ የሚሰራባቸው የልምምድ ስርዓቶች፤ የሚከታተላቸው መርሃ ግብሮች፤ አመጋገቡ እና አኗኗሩ ከፈታኙ የማራቶን ውድድር ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም:: በማራቶን አስደናቂ ውጤት እንዳያስመዘግብ እና ወጥ አቋም እንዳያሳይ ያደረገውም ይሄው ነው፡፡‹‹ በማራቶን የምፈልገውንና የምችለውን ውጤት ማስመዝገብ ያልቻልኩበት ዋናው ምክንያት የተለያዩ ጉዳቶች  በመላው የሰውነት ክፍሌ ሲፈራረቁ መቆየታቸው ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ትንሽ ሞራል አሳጥቶኛል›› በሚል አስተያየት የሰጠውም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡
ከአምስተርዳም ማራቶን በኋላ ማኔጅ የሚያደርገው ግሎባል ስፖርት ኮምኒውኬሽንና ዋና አሰልጣኙ በማራቶን የሚፈልገውን ውጤት ለማሳካት አስቀድሞ በሚሰራቸው ልምምዶች እና በአኗኗሩ ላይ ስርነቀል ለውጥ እንዲያደርግ መክረውታል፡፡ ስለዚህም በሰውነቱ ላይ በተደጋጋሚ ከገጠሙት ጉዳቶች ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ብሎ የግሎባል ስፖርት ኮምኒኬሽን ዋና መስርያ ቤትና የኤንኤን ሯጮች ቡድን መቀመጫ ወደአደረጓት የሆላንዷ ኒጅመገን ከተማ አቅንቷል፡፡ የመጀመርያ ርምጃው ፒተር ኤመርስ ከተባለ ሆላንዳዊ ፊዝዮቴራፒስት ጋር መስራት ነው:: ይህ ዶክተር የቀነኒሳ ሙሉ ሰውነት በመመርመር በተለይ በጉልበቱ ላይ ያሉትን ችግሮች ከታዘበ በኋላ እንዲያገግም በተከተለው ሂደት  የምንግዜም ምርጥ አትሌት የማሟሟቂያ ስርዓትን  “warm up for the GOAT (Greatest of all Time)” የሚል ህክምናውን እስከመፍጠር አድርሶታል፡፡. በተጨማሪ በክብደት በመጨመር በአጠቃላይ ሰውነቱ ላይ የተፈጠረውን ጫና በሚቀንስ ተከታታይ ህክምና ውስጥም ማለፍ ነበረበት፡፡ ስለሆነም በክብደት መጨመር የሚፈጠርበትን የአቋም መናጋት ለማስተካከል ከሌላው ሆላንዳዊ የስፖርት ኑውትሪሽኒስት አርማንድ ቤትኖቬል ጋር እየሰራ ቆይቷል፡፡ ይህ የስነ ምግብ ባለሙያ ከኬንያዊው ኤሊውድ ኪፕቾጌ እና ከሌሎች የኤንኤን የሯጮች ቡድን አባላት ጋር የሚሰራ ሲሆን ለቀነኒሳ ልዩ የአመጋገብ ፕሮግራም በማውጣት እና በኒጅሜገን በነበረው ቆይታ በየቀኑ የሚመገባቸውን ምግቦች ፖውሊን ካላይሰን የተባለ ባለሙያ እንዲያዘጋጅለት አድርጓል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በአመጋገቡ ላይ ምክር ስለተሰጠው በዚያው መመርያ እየተጓዘ ከመቆየቱም በላይ የእለት እለት አመጋገቡን ለስነምግብ ባለሙያው በየቀኑ በማስታወሻዎች በማድረስ ንቁ ክትትል ማድረጉንም ቀጥሏል፡፡ NN Running Team  በድህረገፁ ላይ ‹‹ የቀነኒሳ መልሶ መታደስን›› አስመልክቶ በቀረበ ዘገባ እንደተጠቀሰው በሆላንድ ቆይታው ከጉዳቶቹ ካገገመ እና ክብደት ከቀነሰ በኋላ  በየልምምድ ፕሮግራሙ ጣልቃ በቀን ለሁለት ግዚያት የ90 ደቂቃ እንቅልፍ በመተኛት እረፍት ያደረገ ሲሆን፤ በየቀኑ ሲያደርግ የነበረውን ልምምድ በቀን ከ45 ኪሜትር ወደ 150 ኪሜት ማሳደግ ችሏል፤ በተጨማሪ ከቤተሰብ፤ ከተለያዩ ሃላፊነቶች ርቆ በመቆየት በማራቶን ዝግጅቱ ላይ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ አስችሎታል፡፡ ከሆላንድ ኒጅመገን ቆይታው በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ በልምምዱ ፤ በተክለሰውነቱ አጠቃላይ ማገገም፤ በአመጋገቡ ላይ የፈጠራቸውን ለውጦች በልዩ ትኩረት ሲያደርግ ቆይቶ ለበርሊን ማራቶን ዝግፍጁ መሆኑን ሊያረጋግጥ ችሏል፡፡
‹‹ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች መግባት ጨረቃን እንደመርገጥ ነው…››ኪፕቾጌ
ይህ  በእንዲህ እንዳለ ኬንያዊው የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት እና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ኤሊውድ ኪፕቾጌ ከሁለት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ  በቪዬና የማራቶን ርቀትን ከሁለት ሰዓት በታች ለመግባት ጥረት እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት በጣሊያን የሞንዛ የሞተርስፖርት ትራክ ላይ ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት ባደረገው ሙከራ  2፡00፡25 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበ ሲሆን ውድድሩ ለዓለም ክብረወሰን እውቅና የማያገኝ በመሆኑም ክብረወሰን ሆኖ አልሰፈረለትም፡፡ በወቅቱ ኪፕቾጌ ከ2 ሰዓት በታች የማራቶንን ርቀት ለመሸፈን ጥረት ያደረገው በ30 ደጋፊ አሯሯጮች በመታገዝ ነበር፡፡ በጥቅምት ወር ላይ በቪዬና ሙከራውን ሲቀጥል መደበኛ ልምምዱን በመስራት መሆኑን ለጥንካሬ እና ለፍጥነት የሚሰራቸው ሁሉ ለማንኛውም ማራቶን ከሚያደርገው ዝግጅት ጋር እንደሚመሳሰሉ  የተናገረ ሲሆን ከሌሎች ማራቶኒስቶች የላቀ ብቃት የተባለው በሳምንት ከ200 እስከ 220 ኪሜ እየሮጠ መሆኑ መገለፁ ነው፡፡ የዓለም ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኤልውድ ኪፕቾጌ ከ2 ወራት በኋላ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች ለመግባት በቪዬና ሲሮጥ ከሚመደቡት ከ15 በላይ አሯሯጮች ባሻገር በብስክሌት እና በመኪና የማሯሯጥ ድጋፍ ይደረግለታል ተብሏል፡፡
በሮም አድርጎት የነበረው ሙከራ ኦፊሴላዊ እውቅና እንዳልተሰጠው ሁሉ በቪዬናም የሚያስመዝገብው ሰዓት እንደ ህጋዊ ሪከርድ አይያዝለትም፡፡ ኤሊውድ ኪፕቾጌ በበርሊን ማራቶን ካሸነፈ ለአምስተኛ ተከታተሳይ ዓመት ሆኖ አዲስ ክብረወሰን ይመዘገብለታል፡፡ ከኃይሌ ገብረስላሴ ጋር እኩል 4 ጊዜ በማሸሐነፍ የውጤት ክብረወሰኑን አምና ተጋርቶት ነበር፡፡ ኪፕቾጌ ግን ‹‹ማራቶን ከ2 ሰዓት  በታች መግባት ጨረቃን እንደመርገጥ ነው›› በሚል አስተያየቱ መበረታታቱን ቀጥሏል፡፡ በ2018 እኤአ ላይ ኪፕቾጌ በበርሊን ማራቶን የዓለም ማራቶን ሪከርድን 2፡01፡39 በሆነ ጊዜ ያስመዘገበው ኪፕቾጌ የሃምበርግ፤ የለንደንና የበርሊን ማራቶኖች የቦታ ሪከርድ እንደያዘም ይታወቃል፡፡
The INEOS 1:59 Challenge በተባለው የኪፕቾጌ ማራቶንን ከ2 ሰዓት በታች የመግባት እቅድ የዓለም ክብረወሰን ሊመዘገብ የማይችል ሲሆን፤ ታላቅ የማራቶን ሯጮች በአሯሯጭነት ከመመደባቸውም በላይ ብስክሌት እና መኪናም እንደሚያሯሩጡት ተገልጿል፡፡ ኪፕቾጌ በሪዮ ኦሎምፒክ ያገኘውን የማራቶን የወርቅ ሜዳልያ በቶኪዮ 31ኛው ኦሎምፒያድ ማስመዝገብ ቢፈልግም ዋናው ትኩረቱ በቪዬና ማራቶን ከ2 ሰዓት በታች በመግባት እቅዱ ነው፡፡

Read 8445 times