Monday, 09 September 2019 12:23

የአዲስ ሆም ዴፖ የብሥራተ ገብርኤል ቅርንጫፍ ማስፋፊያ ተመረቀ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በተለምዶ ብሥራተ ገብርኤል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያለው አዲስ ዴፖ የማስፋፊያ ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት ጀመረ፡፡  አዲስ ሆም ዴፖ ከትናንት በስቲያ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤና የሚድሮክ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰርና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ናቸው፡፡
አዲስ ሆም ዴፖ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆኑት የዘመናዊ ሕንፃ ኢንዱስትሪና የኮምቦልቻ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ምርቶችን በጅምላና በችርቻሮ እንዲሸጥ ታስቦ በ1995 ዓ.ም 15 ሠራተኞችን ይዞ የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን ሥራው ሲጀመር ዓመታዊ ሽያጩ 6.2  ሚሊዮን ብር እንደነበር ዶ/ር አረጋ ገልፀዋል፡፡
የሽያጭ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 7 ያሳደገው አዲስ ሆም ዴፖ፤ በአሁኑ ወቅት የሠራተኞቹ ቁጥር 167፣ ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑም ወደ 317 ሚሊዮን ብር ማደጉ ተጠቁሟል፡፡  ለገበያ የሚቀርቡ የምርት ዓይነቶች ስፋትና ጥራት የጨመረው ድርጅቱ፤ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ዕቃዎች፣ የሕንፃ መሳሪያዎች፣ የኤሌክትሪክ፣ የቤትና የቢሮ የፊኒሽንግ ቁሳቁሶች የኤሌክትሮኒክ፣ የወጥ ቤት ዕቃዎችን በማቅረብ ላይ ሲሆን፤ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ሽያጭም እንደሚከናውን ታውቋል፡፡
ቀድሞ ከነበሩበት ቦታ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ሎሊ (Loli የሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላ-ሙዲ ሴት ልጅ ስም) ሕንፃ የተዛወረው የብሥራተ ገብርኤል አዲስ ሆም ዴፖ፤ ከዋንዛ ፈርኒሽንግ፣ ከቪዥን አሉሚኒየም፣ ከብሉ ናይልና ከአዳጐ ሚድሮክ ግሩፕ ኩባንያዎች ምርቶችን ተረክቦ ያከፋፍላል ብለዋል - ዶ/ር አረጋ፡፡ ሕንፃውን ለማስፋፋትና የማዘመን ሥራውን ለማከናወን 11 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገ ሲሆን፤ ለተጨማሪ 18 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡  


Read 10992 times