Saturday, 16 June 2012 09:34

የሰው ልጅነት ከሰውነት ጋር ሲንጠራራ ወግ

Written by  ኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(1 Vote)

አቶ ቀረመንዝ ያለሴት ረዥም አመታትን ኖሯል፡፡ ያለሴትን በደንብ አብራራው ካላችሁኝ ከሴት ጋር ሳያወራ፣ ሳይተኛ፣ ሳይስቅ፣ ሳይሰዳደብ፣ ሳይፋቀር…ምንም ሳያደርግ እላችኋለሁ፡፡ በረዥም የእድሜ ዘመን ውስጥ ወደ የትም ያልተጠጋጋ ተመሳሳይ ህይወትን መኖር የኑሮን ርዝመት ያሳጥረዋል፡፡ ይህ ከሆነ ዛሬ ላይ አቶ ቀረመንዝ አንድ አመቴ የሚሆን መሰለኝ ብሎ ቢናገር ምንም የሚያስገርም ነገር የለም፡፡ አጭር ስሜት እንደ ቃል ነው…መሸጋገሪያ መንገዶቹ የማይታዩ የሚሆኑ ንፋስ ውስጥ እንዳሉ የቃል ፍጥረቶች፡፡ ስለዚህ አቶ ቀረመንዝ ባህሩን ይወናጨፍ ብሏል…ተራራውም እስከ ምቾቱ ይወፍር…አየሮችም ተነስተው በፍቅር ይጨፍሩ ይላል፡፡ ከራሱ አስቀድሞ መብትን ከህይወቱ ጥጋት ስር ሆነው ለተከተሉት የውበት መገናኛዎቹ ይሰጣል፡፡ ሃሳብና ቃል ሲደመሩ ተግባር ይሆናሉ፡፡ አቶ ቀረመንዝ ሲያስብ ያወራል፣ ሲያወራ ይሆናል፡ዛሬ አቶ ቀረመንዝ በከፍተኛ ድምጽ በሚናጥበት፣ የሃሳብ ቅርሳ ቅርፆች ከሚፈጩበት፣ አልኮል መጠጦች ማደሪያቸውን ከሰው ሆድ ዕቃ ውስጥ ከሚያከማቹበት የሃያ ሁለት ሰፈር እንብርት ስር ካለ “እንትና” ከተባለ ሆቴል ውስጥ አንድ ቢራ ይዞ ተቀምጧል፡፡

የሚያየው ነገር ሁሉ ይጮሃል፣ የተቀመጠበት ወንበር ይጨፍራል፡፡ ዛሬ ገና ነው ከዚህ እንግዳ የድምጽ ጭፈራ ጋር የተዋወቀው፤ ያስተዋወቀው ፍርሃቱ ነው፤ ፍርሃቱ የሞቱን ቀን መገመቱ ነው፤ ግምቱ ቅርንጫፎች እንዲያወጣ የመከረው የማወቅ ስስቱ ነው፡፡ እድሜውን በየመጽሐፍቱ ላይ ሲያራግፍ የሴትነት ቅኔን መርምሮም ከእውቀቱ ቀላቅሎትም አያውቅም፡፡አቶ ቀረመንዝ መፈክር የለውም፡፡ መፈክር ስለሌለው የስሜቱን ንዳት የሚጠጋጋውን እየመረጠ በአንደበቱ ይንጋጋል፣ በእግሮቹ ይተባል፣ በአይኖቹ ይጥራል፡፡ የእንትና ሆቴል ልምምዱ ትኩረቱን ያውቀዋል፤ ትኩረቱ በአይን በመተርጐም አቅጣጫን ያማክራል፡፡ “እንትና” ሆቴል እርሻ ነው፤ የእጦት ህልውና በቸልተኝነት የዘራቸው ትርጉም ያጡ ሴቶች የበቀሉበት፡፡ የእርሻው አዝመራ የሚደርሰው በየቀኑ ነው፤ በየቀኑ ምሽት ላይ የፈኩ የሴት አዝዕርቶች ከመፍለቂያቸው ተንቧችረው ይወጣሉ፡፡ ማንም ቢገምት በማይደርስበት የጡዘት ፍጥነት ለራሳቸውም ለወንዱም ዝርያ ይደምቃሉ፡፡ ይሄ ሰብል በብዙ ወንዶች ሲታጨድ ከርሞ ዛሬየአቶቀረመንዝን ተራ እየጠበቀ ነው፡፡ ማጨጃው ገንዘብ ካለ፣ ከሴት ውስጥ መግባትም መውጣትም ቅንጣት የስሜት ጥረት ብቻ ናት፡፡ አንዷ ትመጣለች፤ ብዙ ትጨፍራለች፤ በመጨረሻ ተገላምጣ ትሄዳለች፡፡ አቶ ቀረመንዝ እንደተቀመጠ ነው፡፡ እስካሁን ትኩረቱን የሚስብ ነገር ሊያገኝ አልቻለም፡፡ በሙሉ ሴቶቹ ልጆች ናቸው፤ ምንም ነገር የረፈደባቸው የማይመስሉ የህይወት ላይ ስዕሎች፡፡ ፈገግታቸው ውስጥ እሱ የሚጠብቀው ያህል እንቅስቃሴ ሊታይባቸው አልቻለም፡፡ ገላቸውን እያየው አልናፍቅህ አለው፤ ቶሎ ተዳሶ ቶሎ የሚለመድ አይነት ተራ ቆዳ ለብሰው በብናኝ ጨርቅ አይኑ ስር ይርመሰመሳሉ፡፡ ሴተኛ አዳሪዎች ይዘት የላቸውም ብሎ አሰበ፤ ህይወታቸው እንደ ንፋስ ነው፡፡ ንፋስን የሚጠራው ግዑዝ አካል ብቻ ነው፡፡ የነዚህ ሴቶች ጉዞ ወደ አንድ ርቀት ነው…ገንዘብ፡፡ አቶ ቀረመንዝ ከዚህ በላይ የሆነች …ይዘት ያላት፣ ህግ ያላት፣ የሚናፈቅ ገላ ያላት፣ የሚንቀሳቀስ ፈገግታ  እያሳየች የምታወራ ነው የሚፈልገው፡፡ “እንትና” ሆቴል ይህችን የመሰለች ሴት አልዘራም፤ አቶ ቀረመንዝም ከነዚህ ሴቶች አንዳቸውንም አያጭድም፡፡ ሴቶቹ አይኖቹን ረበሿቸው፡፡ መጮህና መናገር ቢከብደው እያያቸው አኮረፋቸው …ሴቶቹን፡፡ ብዙ አኩርፏቸው ከተቀመጠበት ዳንሰኛ ወንበር ላይ ተነስቶ ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ሰዓቱ መሽቷል፤ የሰፈሩ ቀለም ግን እንደ ቀስተዳመና ነው…ምክንያት ፈልጐ እንደወጣ ቀስተደመና፣ መሬቱ ላይ ራሱ መብራት አለ፡፡ አቶ ቀረመንዝ ቀስተዳመናውን እየረገጠ አብሮት ምክንያትን ፍለጋ ወደፊት መሄድ ጀመረ፡፡ ዘሪሁን ህንፃ ጋር ሲደርስ አይኖቹ የብርሃን ጥሪ አጋጠማቸው፤ ጥሪው ከዓይኖቹ ከበስተግራ በኩል ይጮሃል፡፡ የብርሃኑ ባለቤት ቺቺንያ የተባለው መንደር ነው፡፡ ሙከራ አይከፋም በሚል የብርሃኑን ድምጽ ተከትሎ ወደ መንደሩ ራሱን አሰረገ፡፡ ቺቺንያ ከእንትና ሆቴል ይለያል፡፡ የእንትና እርሻ የታጠረ ወሰን አለው፤ የቺቺንያ መንደር ግድቡን ጠርምሰው በወጡ ሌላ የግል በቃይ አዝዕርቶች ተሽቆጥቁጧል፡፡ መሬቱ ሴት ናት፡፡ የቺቺንያ ሰማይ ሴት ናት፡፡ ሰማይዋ ታች ከምድር ያሉትን ልጆቿን የምትጠብቅ እናትን ትወክላለች፡፡ ለቺቺንያ ተብሎ የወከከ ብርሃን ከሰማይዋ ይላካል፡፡ አቶ ቀረመንዝ ጭንቅላት ውስጥ ቀጫጭን ሴታዊ እብደቶች ያለፈቃድ ይመላለሱበት ጀመር፡፡ የወሰነው ውሳኔ አስቀያሚነቱ እየደጋገመ ይሰማው ጀመር፡፡ ስለዚህ ወደ ምርጫ ተንጠራራ፤ ዝም ብሎ መሄድ ፈለገ፡፡ የምሽቱን ትንፋሽ እየማገ ለመጀመሪያ ጊዜ የገጠመውን የህይወት ምናምንቴ ገጠመኝ እያጣጣመ፣ እስኪነጋ ዝምታውንና እግሩን ብቻ እያዘዘ መቆየትን መረጠ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ የቺቺንያ መንገድ ረዥም ነው፤ ለሀምሳ ሰባት አመት ሰው እንደዘፈቀደ ተገፍቶ የሚጨረስ አይደለም፡፡ አቶ ቀረመንዝ አንዲት ቤት ፈልጐ ማረፍ ፈለገ፡፡ ብቻ ከድካሙ መንደር አካባቢ ቀረብ ያለ መቀመጫ ያለበት መጠጥ ቤት ተመኘ፡፡ ቺቺንያ ውስጥ ምኞት ካለ መንገዱ ማስተናገዱን አያቆምም፡፡ ወዲያው ማረፊያ የሚሆን መጠጥ ቤት አግኝቶ ወደ ውስጥ ዘለቀ፡፡ ምሽቱ ልጆቹን የትም ይበትናል፡፡ እዚህም መጠጥ ቤት ውስጥ ሴቶች አሉ፡፡ ነገር ግን ከነዛ ሁሉ ህይወቶች ውስጥ እንደሱ ያለ ህይወት ያየ መሰለው፡፡ ሲመስለው የመጀመያው ነበር፣ መነጽሩን አውልቆ በትኩረት ወደ አንድ አቅጣጫ ማፍጠጥ ሲጀምር የመጀመሪያው ነበር፣ ከሱ እድሜ ከቅርብ ዳርቻ አካባቢ ያለች ሴት ሲመለከት የመጀመሪያው ነበር፡፡ ከቁመቷም ከንቃቷም ያጠረች፣ የሂና ቀለሟን አልፎ እድሜዋን እየነጣ የሚናገርባት ነጭ የፀጉር ዘለላዎች ከጭንቅላቷ የተሸከመች፣ ለድካማቸው መጠለያ እንዲሆን በቀይ፣ በደበዘዘና በነጣ ቀይ ማቀፊያ ወደ ላይ የተንጠለጠሉ ወፋፍራም ጡቶች ከደረቷ ያስቀደመች፣ የማይደነግጥ ደስታንበሚያምታቱ ዳንሶቿ የምትጮህ ሴት፣ አንቱነቷን በገንዘብ ለመሸጥ ለወጣት ገዥዎች ባረጁ ጥርሶቿ ትጥራለች፡፡ ሴትየዋ ስትጥር አቶ ቀረመንዝ ሊጀምር የመሰለውን አዲሱን የገጠመኝ እድሜውን እንደማረጋገጫ የሚወክልለት ሻማውን እየለኮሰ ነበር…ልክ ይህች ሴትዮ መጥታ መልካም ልደት ብላ ሻማውን እንዲያጠፋው ከጆሮው ስር ከጀርባው በኩል እንደምትተነፍስለት አይነት፡፡ ሁሉ ነገሯን ካይኖቹ ቀዝቀዝ ብሎ መከታተል ጀመረ፡፡ ማስተዋል የሚከረፋ መሆኑን የሚያውቀው እዚህ ሰዓት ላይ ነው፡፡ ይህችን ሴትዮ ማየቱን እየተከተለ የሚያስጨንቀው ብስባሽ ሀዘን አለ….ማስተዋሉ ያበደረው ሀዘን፡፡ እያዘነላት ሲያያት እሷ እየጨፈረች ቀረበችው፡፡ እንደጓጐለ ወንዝ ካየሩ ጋር እየተጋጨች ከፊትለፊቱ መጥታ ካይኖቹ ላይ በሀይል ተከመረችበት፡፡ ወጣቶቹ ቤቱን በፉጨት አናጉት፡፡ እሷም ዞራ ደስታቸውን ተደሰተችላቸው፡፡ “ምድቤጋር ደርሻለሁ…በሉ ልጆች…መልካም ጥናት…ትምህርት…ቂቂቂ….”ሴትየዋ ሴት ነበረች፡፡ አሁን ግን ነበረችነቷን የሚያስታውስላት የለም፡፡ ሴትዮ ናት…በቃ፡፡ አቶ ቀረመንዝ በዚህች ሴትዮ ክብር ተደነቀ፡፡ የሆነ ቦታ ክብሯን ደብቃው መጥታ እንደሆነ ገመተ፡፡ የማይታይ ክብር ያጓጓል፡፡ ጉጉት ሸክም ሲሆን ደግሞ ደቂቃዎች ወደ ኋላ ተስበው ቅጽበቶችን አሰልቺና የሚናቁ ያደርጓቸዋል፡፡ በመሆኑም ይዟት ክብሯን ያስቀመጠችበት ቦታ ከልቡና ከነክብሯ ሊያዋያት ፈልጓል፡፡ ሴትየዋ በሃይል እየተንከተከተች ትስቃለች፡፡ ሳቋ የማያልቅ ይህቺ ፍጡር…የሳቋን እድሜ መቁጠር ተመኝቶ ተወው፡፡ “ለምን ማየት የሚያዝናናህ ከሆነ ወደ ውስጥ አልቤርጐ ይዘን በብርሃን አንተያይም….እ….”

 

አቶ ቀረመንዝ የልደት በዓሉን ከዚህች ለህይወት ካረጀች፣ ከደስታ ከተወለደች ሴትዮ ጋር ሊያከብር ታላቅ ፍቃዱ ሆነ፡፡ እንደጀመራት ነው አሁንም የሚያያት፡፡ እያያት በእጁ ምልክት ሰጥቷት አብሯት ወደ አልቤርጐ ገባ፡፡ ሴትየዋ ከመብራቱ እኩል እየሳቀች ተከታትላው ዘለቀች፤ ሳቋ ነው ክብሯ፡፡ እየሳቀች ከላይ የተጣበቀው ናይለን ጨርቋን አውልቃ ወረወረችው፤ ገላዋ ነው ክብሯ፡፡የመሳሳብ ርቀቱ ቅርብ ነው፡፡ ሂደቱን እንዲገፋ የአልኮል ነፍስ እንደአስተባባሪ አይጠራም፡፡ የእድሜ ድምጽ ከየሰው ከንፈር፣ ጉንጭና አይን ላይ ሲዘምር ከሚያደምጡት ጋር ሆኖ ስሜትን አርግዞ ይወልዳል፡፡ አቶ ቀረመንዝ በሴትየዋ ነፃነት ውስጥ የራሱን ነፃነት አምርቷል፡፡ ምርቱን ወደ ጥቅም የሚለውጥበትን ወቅት የሚለየው እሷ ስታወራ ነው…..

“በናትህ ስንት ልክፈላት ብለህ እንዳትጨናነቅ፤ ያለህን መስጠት ትችላለህ፡፡ ዋጋዋ ካነሰ የምትሰጠው ይቀንሳል በማለትም አትጨነቅ፡፡ ስንቱን ጐረምሳ የነዳሁበት የረዥም ዘመን ልምድ አለኝ፡፡ ስሜን ደግፎ የያዘልኝም የአልጋ ላይ ብቃቴ ነው፡፡ ስለዚህ አትጨነቅ ወዳጄ… ባነስተኛ ወጪ መዝረፍ ያለብህን ዘርፈኸኝ ልቀቀኝ!” እነዚህን የመሰሉ ነፃነቶች ከተራራ ጫፍ ላይ ቢለቀቁ ሞት የሚከዳቸው አይነት የዘላለም ትርጉሞች መሰሉት፡፡ አቶ ቀረመንዝ በዚህች ሴትዮ የሁኔታዎች ድምር፣ የሆነ ሰሞን የተከሰተ የዘመን ምዕራፍ ከፍቶ ያነበበው እንደሆነ የተጠራጠረው ትልቅ ገፆች መሰለችው፡፡ ፈቅዶ ወደ ህይወቱ ከቷት፣ ከህይወት ታሪኩ ውስጥ በኑሮ ቀለም ስለፃፋት ደስተኛ ሆኗል፡፡ በዝግታ እየተራመደ ሄዶ ካልጋው ላይ ተቀምጦ መነጽሩን በዝግታ አውልቆ በጐንዮሽ ከቤቱ መሰረት ላይ የቆመችውን ሴትዮ ተመለከታት፡፡ አጠገቡ እንድትቀመጥ በእጁ ምልክት ሰጥቷት አንገቱን ወደ መሬት ደፋ፡፡ ሴትየዋ እንደተባለች ትሆናለች…ፍቃዷ ነው ክብሯ፡፡ “አንድ ውለታ እንድትውይልኝ እፈልጋለሁ…የሃሳቤን የሞራሌን የስነምግባሬን ጥሪት አሟጥጬ ነው አሁን እዚህ አጠገብሽ መጥቼ ያገኘሽኝ፡፡ እስካሁን ግን የማደርገውን በውል አላውቀውም፡፡ በህይወት ውስጥ የመምረጥ ስልጣኔ እስከየት ድረስ መጓዝ እንደሚችል አላውቅም፡፡ ድርጊቶችን ከመቀመር ይልቅ ከጊዜ ጋር መርባትን እየመረጥኩ ያለሁ ሰው ነኝ፡፡ ውለታ እንድትውይልኝ እፈልጋለሁ…ይስቃል ሲሉኝ ከጥርሴ የማልገኝ፣ አኮረፈ ሲሉኝ እዝነቴ ለራሴ ግራ የሚገባኝ፤ ማንም በቀላሉ ሊገምተኝ የማይችል አይነት ሰው ነኝ፡፡ ይሄ የቀሪው ዕድሜዬ ሩጫ ማረፊያውን ሳልገምት ካሁን በኋላ መንቀሳቀስ አልፈልግም፡፡ ምንአልባት አሁን እያልኩሽ ያለሁት ነገር አልገባሽ እያለሽ መሰለቸትን እየጠራብሽ ሊሆን ይችላል፡፡ እመኚኝ ከሴት ጋር ከዚህ ቀደም በምንም አይነት መልኩ አውርቼ አላውቅም፡፡ ለሴት ልጅ ለወሬዋ ሲባል ጆሮን እንዴት መሰንዘር እንደሚቻል፣ ውበቷን በቅርብ ትውስታ ውስጥ ለማስቀመጥ የሚረዳ ወግ ያለው አተያይ እንዴት እንደሚታይ፣ ካነበብኳቸው መጽሐፍቶቼ በላይ የሆነ መገለጥ ከሴት ጋር እንዳለ እንዲገባኝ የሚያደርገኝ የአዕምሮ ክፍል እንኳን የለኝም…አላውቅም፡፡ ውለታ እንድትውይልኝ እፈልጋለሁ…ይሄ አሁን እየሆነ ያለው ነገር የሚስማማው የህይወት ትርጉም ማግኘት ይችላል…ወይስ የፈራረሰ የህይወት ታሪክ ኪሳራ ነው? የሚቀጥል ቅስፈት አሁኑኑ መያዝ እንችላለን? በራሴ እራሴን መገመት አለመቻሌ ከሚያመጣብኝ ጣጣ እንድታወጪኝ እሻለሁ፡፡ ሳይሽ ገና ቀዘቀዝኩኝ፤ ካዘልሽው ነጻነት ጋር መንትያ ሆኖ መኖርን ለአፍታ ናፈቅሁት፡፡ በመሰለሽ ቃላት አብራሪልኝ…የወሬ ጉዟችንን ስካሩ እንዳይቀማን ለምትጠጭው መጠጥ ትንሽ እረፍት ስጭውና ስብርባሪ ደቂቃዎችሽን አበድሪኝ… ትንሽ አውሪኝ…”አቶ ቀረመንዝ ወሬውን ሲያቆም ሴትየዋ ከምትወጣበት የግርታ ዳገት አረፍ አለች፡፡ ቆይታ…ከዚህ በፊት አስባው የወለደችው ልጇን መሰላት፡፡ ማንም ከዚህ ቀደም ምክር ጠይቋት አያውቅም፡፡ ይሄም ሰው ምን እንደጠየቃት ሳይገባት “ውለታ ዋይልኝ!” የምትለዋን ቃል ብቻ ይዛ፣ ከኑሮ የለቃቀመቻትን ምክር ልትሰነዝር ጓጓች፡፡ እንዳታወሪ እንዳይላት ይመስል ከራሷ ቃላት ጋር ተሽቀዳድማ ንግግሯን ጀመረች፡፡ “እውነተኛ ወሬ ካወራሁ ስንት ጊዜ መሰለህ፡፡ አልዋሽህም የኔ ጌታ…ምን እንዳወራህ አንድም ነገር አልያዝኩም፤ ነገር ግን ዝም ብዬ ዝም ከምልህ የሆነ ወሬ ማውራት አለብኝ፡፡ ታሪኬ አጭር የሆነች ሴት ነኝ፡፡ እናትም አባትም የሌላት ሴት የምትባለዋ የሴት ዘር ውስጥ መመደብ የጀመርኩት ገና ስወለድ ነው፡፡ ስወለድ እናቴ ሞተች፣ ከመወለዴ በፊት አባቴ ሞቶ ነበር፡፡ የቤተሰብ እጥረት ነበረብኝ፡፡ የቅርብ ወዳጄ ትካዜዬ ብቻ ነበር፣ ዝምታዬ ያለኝ ብቸኛው ድምፄ ነበር፡፡ ራሴን እስካውቅ ድረስ የምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ተማሪዎች እንደተማሪ እንደማይቆጥሩኝ ነግረውኛል፡፡ ከሰው ልጅ ያገኘሁት አንድ ጥንጥዬ ድምጽ ብቻ ናት………እሷም ከንፈራቸውን ሲመጡብኝ በጀርባዬ በኩል የምትበጠብጠኝ ትንሽዬ ድምጽ፡፡ ዝም ብሎ መኖር በሚጮህ ማህበረሰብ ውስጥ እንደ ጅልነት እንደሚቆጠር ያወቅሁት እየተማርኩ ነበር……”

የእውነቷን የምታወራ አንድ ሴት አግኝቷል…አቶ ቀረመንዝ፡፡ እውነቶቿ ያጓጓሉ፡፡ ትካዜዋ አይዋሽም፡፡ የጊዜ ቀመር ስቦ እስኪነጥቀው ድረስ መስማትን እየጓጓ መረጠው፡፡ “ከትምህርት ቤት ጨርሼ ስወጣ አፉን ከፍቶ ወደ ሴተኛ አዳሪ መንደር የሚወስደው በር ተከፍቶ ተቀበለኝ፤ እስካሁን ድረስ እየኖርኩበት ነው፡፡ ነገር ግን ደደብ አይደለሁም፡፡ ሴት ሆኜ መፈጠሬ ግማሽ በግማሽ ቢያማርረኝም በልጅነቴ የተነጠቅሁትን ግዙፍ ነጻነት ያሁን ደቂቃዎቼን እየተለማመድኩ ምሬቴን እረሳዋለሁ፡፡በየቀኑ እጠጣለሁ፤ በየቀኑ እሰክራለሁ፤ በየቀኑ እተኛለሁ፡፡ የህይወቴ ሂደት ውስጥ ግን ማንም እጁን እንዳይቀላቅል ከሩቅ አቆመዋለሁ፡፡ ሲነጋ ነጻነትን ፈልጌ ሲመሽ አልጋ ካለበት አነፈንፋለሁ፡፡ መተኛት እወዳለሁ፡፡ ቶሎ ቶሎ ይደክመኛል፡፡ ጊዜ ግን ውብ ነው፤ ውበቱ አለማለቁ ነው፡፡ ያለቀብኝ የምለው ምንም ነገር የለም፡፡ ግድየለም ባክህ ተወው የኔ ጌታ እድሜህን አትፍራው፡፡ ይሂድ፡፡ የት ይደርሳል፤ ዋናው ምን እንደምትፈልግ እወቅ፡፡ እኔስ የምፈልገውን መረጥኩኝ………..የቀን ነፃነትና አልጋ ብቻ፡፡”ረጁ ጥርሶቿ ያረጁ አይኖቹን አጥበርብራው ካበቃች በኋላ……………

“ዛሬ ላይ ምንም ክፍያ ሳላስከፍልህ ካንተ ጋር ማደር እፈልጋለሁ”አቶ ቀረመንዝ ሁሉንም መልሶች አግኝቷል፡፡ ይህች ሴትዮ የጀመረችለት ታሪክ አለ፤ የታሪኩ ርቀት ራሱ ታሪኩ ነው፡፡ ምንም ነገር አይደገምም፡፡ ኑሮ ትውስታ ብቻ ነው ትርጉሙ፡፡ ይህች ሴትዮ መናገር የቻለችው እስካሁን የያዘችውን ድምርማሪ ትውስታ ብቻ ነው፡፡ አቶ ቀረመንዝ ምንድነው ትውስታዬ ብሎ ከለሰ፤ ሃሳብን መከለስ ይቻላል፡፡ ቢታወሰው ተቃጥለው ሊያልቁ የማይችሉ የመጽሐፍ ገፆች ብቻ ናቸው፡፡ መጽሐፍቶቹ ሲከለሱ ተደጋጋሚ ስሜት ይሰጣሉ፡፡ ስሜቱ ማወቅ ነው፡፡ ማወቅ በሰውነት አይታወቅም፡፡ ሰውነት ከሰው ልጅነት ተቀጥሎ የሚመጣ ውብና ሚስጥራዊ ግኝት ነው፡፡ ሰውነትን ረግጦ በቂ ትርጉም ለማስያዝ እርምጃ ይፈልጋል፡፡ እርምጃው የሚዳስስ ስሜት ማግኘት ነው፡፡ የሚዳሰሰው ስሜት ደግሞ ከሴትየዋ ያረጁ ከንፈሮችና ከጉም የተገነቡ የሚመስሉ ድቡልቡል ገላዋ ላይ ነው ያለው፡፡ የስጋውን ህግ አገላበጠ፡፡ አንቀጽ ተበደረ፡፡ ሰውነቱን ደመረበት፡፡ ትርጉሞች ፈለገ፡፡ መልስ ሳያገኝ ማለቅን መምረጥ ተሳነው፡፡ ነገር ግን ከጥያቄዎች ሁሉ የባሰውን ጥያቄ እንደጠየቀ አልገባውም፡፡ የወንድነት ጉዞ ይሄው ነው፤ ዘመኑ የሚጠይቀው የማይመለሰውን ነው፡፡ አጥሩን አበጃጀ፤ ከሴትየዋ ተጠግቶ ነክቶ የማያውቀውን ድንገት ነካው………….

እስካሁን ሲያጫውቱት የነበሩት የውበት ዝንጣፊዎቹ በዛን ሌሊት በወንድ አዕምሮ ውስጥ ግዙፍ ስፍራን በሚይዝ ፍጡር ተገፍትረው ራቁ፡፡ የሚጣራ ህይወት ያላቸው ዝም ያለው ላይ ይበረታሉ፡፡ የሚቀሙት ነገር የላቸውም፤ መኖራቸው ነው ጥሪው …ሰውነታቸው፡፡

 

 

Read 2244 times Last modified on Saturday, 16 June 2012 10:15