Monday, 09 September 2019 11:35

ከአዲስ ዓመት አዲስ ሀሳብ ይበልጣል! (መቀሌ ደርሶ መልስ)

Written by  ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ
Rate this item
(4 votes)


        የሰው ልጅ በዓል ሰርቶ ማክበር ስለሚወድ “አዲስ ዓመት” ብሎ በየነ፡፡ ብያኔውን በየዓመቱ ያከብራል፡፡ አነሰም በዛ በየበዓላቱ እንዳቅሙ ለራሱ ደስታን ይሰራል:: በዚህ ልማዱ ነው አዲስ ዓመትን የሚያከብረው፡፡ ጳጉሜ 6 ከመስከረም 1፣ ነሐሴ 29 ወይም መስከረም 5 የተለዩ ሆነው አይደለም አዲስ ዓመትን የምናከብረው፡፡ ይሁንና በተለይም አንደኛ ጥብቅ ማህበራዊ ግንኙነት ላለው ህብረተሰብ፤ በዓላት በራሳቸው ትርጉም ሳይኖራቸውም ለእኛ የሚሰጡን እሴት ግን አለ፡፡
አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር የእቅዳችን መዓት ተቆጥሮ አያልቅም፡፡ “እንዲህና እንዲያ” እናደርጋለን እንላለን:: ለመተውና ለመጀመር፣ ለማድረግና ላለማድረግ እናቅዳለን:: የሚሳካልንና የማይሳካልን ይኖራል፡፡
2011 እንደ ሀገር ትልቅ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የገባንበት ነው፡፡ ሰው ዘቅዝቀን የሰቀልንበት፣ በድንጋይ ቀጥቅጠን የገደልንበት፣ ገድለን ያቃጠልንበት… ብቻ በትልቁ የከሰርንበት ነው፡፡ እንደ ሀገር ለመቀጠል ከዚህ ኪሳራ ፈጥነን መውጣት ይኖርብናል፡፡ ከተወሰኑ ቀናት በፊት ወደ መቀሌ ተጉዤ ነበር፡፡ በአሮጌው ዓመት የገባንበት ቀውስ ማሳያ ከተማ ናት መቀሌ፡፡ አንዳችም የዕለት ጉርስ ከሌላቸው ጀምሮ ኑሮ የሞላላቸው፣ በዘመናዊ መኪና በህዝባቸው መሀል የሚንፈላሰሱ የክልሉ ተወላጆች መቀሌን መተንፈሻ አሳጥተዋት አይቻለሁ፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሰደው የመጡ ናቸው፡፡
መቀሌ ጥቂት የክልሉ ነዋሪዎች ስልጣንና በስልጣን ንክኪ የሰሩትን ጥፋት ያለ ሀጢያቷ የምትከፍል ከተማ ሆናለች፡፡ ሕዝቡ ከትንሽ እስከ ትልቅ ፖለቲካ ተናጋሪ ሆኗል፡፡ መገፋቱን አምኖ በምሬት ተሞልቷል፡፡ የትግራዋ ሕዝብ አብዛኛው የሀገሪቱ ሕዝብ እንደሚያስበው አይደለም ስለ ሕወሓት የሚያስበው፡፡ እንዲሰማ የሕወሓት ቱባ ባለስልጣናት መቀሌ “ለመሸኑ” ሕዝቡ “እንኳን ደህና መጣችሁ” ብሎ አልተቀበላቸውም፡፡ ጭራሹንም “የት ታውቁንና የት እናውቃችኋለን?” ነው ያላቸው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ “ልጆቻችን የአዲስ አበባውን ስልጣን ይዘው እኛን ረስተውናል” የሚል እምነት አለው፡፡ ይህንኑም የሕወሓት አመራሮች ከም/ርዕሰ መስተዳድሩ ዶ/ር ደብረፅዮን ጀምሮ ታች እስካለው ካድሬ፣ ወደ ህዝቡ ወርደው፣ ለአንድ ወር ገደማ ግምገማ ሲያካሂዱ ሕዝቡ በድፍረት ነግሯቸዋል፡፡
ለውጡ እንደመጣ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከፍተኛ የሕዝብ ተቀባይነት ካላቸው ክልሎች ቀዳሚው ትግራይ እንደነበር ተጠንቷል፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት ላይ አቂሞ ዶ/ር ዐቢይን ነው የተቀበለው፡፡ ይሁንና “የቀን ጅቦች” የሚለው አባባልና ሌሎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ትግራዋይን የሚነካ አባባል ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ከሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች መሰንዘር ሲጀምር፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም ትግራዋይ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈፀም ነው ሕዝቡ “ከማያውቁት መልዐክ የሚያውቁት ሰይጣን” ብሎ ለሕወሓት ይቅርታ ያደረገው፡፡ በምርጫ 97ም ይኸው አጋጣሚ በአቶ በድሩ አደም “ወደመጡበት እንመልሳቸዋለን” ንግግር ተደግሟል፡፡
ይሁንና የትግራይ ክልልና ሕዝብ ከሌሎቹ ክልሎች አንፃር መገለል ይታይበታል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው፣ በተለይ የአማራና ትግራይ “አክቲቪስት” የሚባሉት ለትግራይ ሕዝብ መለየትን እስኪበቃው ሰብከዋል፡፡ በዚህ የተነሳም በመቀሌ ከሊስትሮ እስከ ባለሀብቱ፣ ከመሀይሙ እስከ ምሁሩ ድረስ ሁሉም ፖለቲከኛ ሆኗል፡፡ ጫማ እንዲጠርግላችሁ የጠራችሁት ሊስትሮ ስለ ምርጫው መራዘምና በወቅቱ መካሄድ፣ ምርጫው ሲራዘም የሚያመጣውን ጉዳት ሲያብራራላችሁ ታገኙታላችሁ፡፡ እኔን እንደዚያ አጋጥሞኛል፡፡ ከመሀል ሀገር በመሄዳችሁ ብቻ መረጃ ይጠይቋችኋል፡፡
ፖለቲከኞችና “አክቲቪስቶች” ምንም ይበሉ እንጂ ሕዝቡ ላይ ያለው ኢትዮጵያዊ ስሜት በፍቅሩ ይታወቃል:: የትግራይ ሕዝብ ጨዋ ነው፡፡ ባሕል ያለው ሕዝብ ነው፡፡ የሰለጠነ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝቡ የሚወደውንና የሚጠላውን ለይቶ ያውቃል፡፡ ከሌላ አካባቢ በተወሰኑ ሰዎች ጉዳት ስለደረሰበት ሕዝብን እንደማይጠላ በተግባር አሳይቷል:: ዛሬም “በውቢቷ ጐጃሜ” እና “ጐንደር ጐንደር የአንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር” ዘፈኖች ሲጨፍር ታገኙታላችሁ:: በየትኛውም ፈታኝ ወቅት ይህ አይለወጥም፡፡
ኢትዮጵያውያን በሁሉም ክልሎች የምንጋራው ድህነትን ነው፡፡ የብዙዎቻችን ሕይወት በልቶ ማደር (ከእሱም ያነሰ) ነው፡፡ በልቶ ለማደር መኖር ሰውነት አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ከዚያ ለላቀ ዓላማ ነው የተፈጠረው፡፡ እኛ ብዙዎቻችን ግን በልቶ ማደር ላይ ቆመናል፡፡ አዲስ ዓመትን ስንቀበል፣ አዲስ ሀሳብ ልንጨምር ይገባናል፡፡ አዲስ ሃሳብ ካልጨመርን አዲስ ዓመት የለም:: አዲሱ ሀሳባችን ደግሞ ከጥላቻ የራቀ፣ በፍቅር የደመቀ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አዲሱ ዓመት የትግራይን ሕዝብ ከሕወሓት ነጥለን የምናስብበት ይሁን፡፡ ፖለቲካውን ወደ ጐን አድርገን፣ ከሕዝቡ ጐን መቆም ይጠበቅብናል:: ክፋትን መደጋገም መልካምነትን አያመጣም፡፡ መላው ሕዝብ የትግራይ ሕዝብን በፖለቲከኞቹና “አክቲቪስቶቹ” እንዳይለካ አደራ እላለሁ፡፡ አደራ!!     

Read 6417 times