Monday, 09 September 2019 11:14

ሰዎች የዐውዳመት ባሪያ መሆን የለባቸውም!

Written by  ዮናስ ዘውዴ (የፍልስፍና ሌክቸረር)
Rate this item
(0 votes)

‹‹አዲስ ዘመን ሲመጣ አዲስ የሚባል ነገር አለ›› ወይ? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ በፍልስፍና አዲስ የሚባል ነገር አለ? ነገሩ በራሱ አዲስ ነው ወይስ የኛ አስተሳሰብ ነገሩን አዲስ ያደርገዋል? የሚለውን ጥያቄም መመለስ ያስፈልጋል፡፡
ሄራክሊተር የሚባለው ፈላስፋ ሲናገር፡- “everything is in state of change” ይላል:: (ሁሉም ነገር በለውጥ ሂደት ውስጥ ነው፤ የማይለወጥ ምንም ነገር የለም ማለቱ ነው) እኛን ጨምሮ ሁሉም ነገሮች ይለወጣሉ፡፡ ከሚለወጡት ነገሮች አንዱ ዘመን ነው፡፡ የራሳችን አቆጣጠር ስላለን አዲሱ ዘመን፣ አሮጌው ዘመን ብለን እንጠራቸዋለን፡፡ የፍልስፍናም ሰው፣ ሰው በመሆኑ፣ በዚህ አቆጣጠር ጥላ ሥር መግባቱ የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ማህበረሰቡ ስለሚያምነውና ስለሚቀበለው ከዚህ ውጭ መሆን አይችልም፡፡
እንደ ካንት ያሉ ፈላስፎች “ጊዜ የለም” ይላሉ፡፡ ቦታም ጊዜም የሚኖረው አእምሮ ውስጥ ብቻ ነው፤ ከዚያ ውጭ ጊዜም ሆነ ቦታ የሉም፡፡ ምናልባት 2012 ዓ.ም ምንድነው ሊባል ይችላል፡፡
እኔ ግን እንደማስበው፣ አንዳንዴ ጊዜ ትዝታ ይሆንብናል፤ በመኪና ስፖኪዮ እንደምናየው የኋላችንን እናይበታል፡፡ ምክንያቱም የሰው ልጅ የሚኖረው ትላንትናን በትውስታ፣ ዛሬን በመጋፈጥ፣ ነገን ደግሞ በተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ለምን ቢባል? ትናንት የተወሰደ፣ ዛሬ ደግሞ የተሰጠ፣ ነገ በእጅ የተያዘ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለዚህ ነገ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ ዛሬ ላይ ነገንም ጭምር እንኖራለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ የ72 ሰዓታት ጊዜ ባይኖረንም በሃሳብ ግን ትናንት፣ ዛሬ ነገም አለ፡፡ ስለዚህ አዲስ ነገር አለ ማለት ይቸግረኛል፡፡
አንዳንዱ ሰው ዛሬ የሚኖርበት ቀን ትናንቱ ነው:: ትናንት ወድቆ ነበር፣ ተሳስቶ ነበር፡፡ ትናንት የሆነ ነገር በህይወቱ አልፏል፡፡ ትናንቶቹ በትዝታ እየመጡ ዛሬውን ይነጥቁታል፡፡ ስሞታቸውን የሚኖሩትም እንደዚሁ! የሰው ልጅ ውድቀቱ ብቻ ሳይሆን ስኬቱም ጠላቱ ነው ይባላል፡፡
አማኑኤል ካንት ‹‹የህይወት ትርጉሟ ምንድነው?›› ይላል፡፡ ኒቼም አፍላጦንም “What is Good life?”  ይሉ ነበር፡፡ ይህን ሲሉ ጊዜን ጊዜ ሲተካው፣ ቦታ በቦታ ሲተካ፣ የተሳካ ህይወት መኖር የማይፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ሰው ታሪክ መፃፍ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ “እኔ ማነኝ? ከየት መጣሁ? ወዴት እሄዳለሁ? እያለ ሰው ሁሉ ይጠይቃል፡፡ ይሁንና እነዚህን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ የሚመልሱም የማይመልሱም ይኖራሉ፡፡  
የሰው ልጆች ከፍታና ዝቅታ፣ መነሳትና መውደቅ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፡፡ ሰዎች እነዚህን ጥያቄ በመለሱበት መንገድ ሊወድቁ ወይም ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን በምናወራበት ሰዓት ነገ ብለን ስናስብ፣ ጊዜያችንን አዲስ ማድረግ እንችላለን፡፡ ምክንያቱም አእምሮዋችን ስላለ፡፡ አእምሮዋችን ሁሉን ያስታውሳል፡፡
በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለሰባ አምስት ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች አሉ - “ሕይወት ምንድነው? በሚል:: ጥናቱ እንደሚናገረው፤ ከ80 በመቶ በላይ “ገንዘብ ማግኘት ነው” ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹ ዝናና ታዋቂነት ነው ባይ ናቸው፡፡ ይህ ጥናት ግን የሚያመለክተው ነገር የሚገርም ነው፡፡ የሰው ልጅ በገንዘብ የህይወትን ትርጉም ሊያገኝ አይችልም፤ የሰው ልጅ በዝና የህይወትን ትርጉም ሊያገኝ አይችልም፡፡ በሌላ ቋንቋ ደስ የሚል ህይወት ሊኖር አይችልም፡፡
እነዚህ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱ ሰዎች፣ ዩኒቨርስቲ ጨርሰው ወጥተው፤ በሥራ ያሳለፉባቸውን ዘመናት ያካተተ ቃለ ምልልስ ተደርጐላቸው፣ የተቀመረ ነው:: ከነዚያ ውስጥ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑ ሁሉ አሉ:: በህይወት ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በመጨረሻ ጥናቱ የሚያመለክተው “ከጓደኛ ከቤተሰብ፣ ከህብረተሰብ ጋር ጤነኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ናቸው፣ ህይወትን ያጣጣሙት!” ነበር ያሉት፡፡
ወደ ጥንት ግሪኮችም በምንሄድበት ጊዜ፣ አርስጣጣሊስ ‹‹ጥሩ ህይወት ምንድነው?›› ተብሎ ተጠይቆ፤ “ከአማልክት ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው ህይወት ነው” ብሏል፡፡ “ጥሩ ህይወት ማለት በምድር ላይ ስንኖር፣ ሐዘንን ሥቃይንና መከራን ቀንሰን፣ ደስታን ከፍ የምናደርግበት ነው” ይላል ሌላው ፈላስፋ፡፡ አርስጣጣሊስ ደግሞ “ለማህበረሰብ የቀረበ ህይወት ማለትም የሚፈተሽ የሚዳበስ ህይወት፣ እርሱ ጥሩ ህይወት ነው” ይላል፡፡
እኔም በዚህ ዐምናለሁ፡፡ እኛ የምንኖረው ከኛ ቀድሞ በነበረ ዓለም ውስጥ ነው፡፡ ከእኛ ቀድመው የነበሩ ሰዎች፤ ስኬት፣ አዲስ ዓመት አዲስ አመለካከት ብለው የሳሏቸው ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ ደግሞ አዲስ ዓመት ሊቀርብ አካባቢ!
አሁንም ይህ ነገር አለ፡፡ በሬዲዮ ስንሰማ፤ አንዳንዶቹ “ሲጋራ አቆማለሁ፣ ጫት መቃሜን፣ መደባደቤን አቆማለሁ፡፡ ሚስት አገባለሁ ወዘተ›› እያሉ ዕቅዳቸውን ይናገራሉ፡፡ ትናንት ደፍቆ የያዛቸው ነገር ዛሬም ደፍቆ ይዟቸው እንመለከታለን:: ከተያዙት ነገር ማን ያወጣኛል? የሚል ብርቱ ጩኸት እንሰማለን፡፡
በፍልስፍናው ዐለም ውስጥ ግን ዋናው ማቀድ አይደለም፤ መሆን ነው፤ ማድረግ፣ ውሣኔን መወሰንና መሆን! ስለዚህ ጥሩ ህይወት የሚጀመረው ከአስተሳሰብ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ወደ ፊት አንድ እርምጃ ካልተራመዱ፣ ወደ ኋላ አንድ እርምጃ መሄዳቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ይሁንና በዚህ አዲስ ዓመት ውስጥ ማሰብ ያለብን ምንድነው? ከተባለ፣ ሁሉም የሚጀምረው ከጥንስሱ ነው፤ ምክንያቱም ህይወት ጨዋታ አይደለም፡፡ እይታዎቻችን፤ ግባችንንና ታሪካችንን ይወስኑታል፡፡ ሁሉም ነገር ደግሞ ያልፋል፡፡ አንድ ወዳጄ ያጫወቱኝ ነገር አለ፡፡ በኦሮምኛ “ኩኒስ ደርባ” ይላሉ፡፡ “ይህም ያልፋል” ማለት ነው፡፡
በድሩ ሁሴን መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት ይመስለኛል፡፡ አንድ በጣም ድሃ ገበሬ ነበረ፡፡ ይህ ደሀ ገበሬ የሚያርስባቸው በሬዎች እንኳ አልነበሩትም:: አንድ በሬ ብቻ ስለነበረው አንገቱን ከበሬው ጋር አጣምዶ ያርስበታል፡፡ አንድ ቱሪስት ሲጓዝ ሁኔታውን ያይና ሰውየውን ይጠይቀዋል፡፡ ‹‹ወዳጄ ምን እያደረግህ ነው?›› አለው፡፡ ሰውየውም ጥልቅ ድህነት ውስጥ ስለሆነ በዚህ አይነት ችግሩን ለማለፍ መገደዱን ይነግረዋል፡፡ ይሄኔ ቱሪስቱ አዘነለት፡፡ ገበሬው ግን መልሶ “አትዘን፤ ኩኒስ ደርባ!” አለው፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አሁንም ያ ቱሪስት ስለዚያ ገበሬ ማጠያየቅ ይጀምራል፡፡ “ያ ሰውዬ እንዴት ሆኖ ይሆን? በሬ አግኝቶ ይሆን? ምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ይሆን?” እያለ አካባቢውን ሲያጠያይቅ፣ “ቤተ መንግስት ገብቷል” የሚል ዜና ይሰማል፡፡ ሰውየው ደስ አለውና ‹‹ቤተ መንግስት የገባውን ሰውማ ማየት አለብኝ” ይላል፡፡ ቤተ መንግሥት ሄዶ ሲያጠያይቅ እውነት ነው፡፡ ገበሬው ንጉሥ ሆኗል፡፡ ለማመን ቢከብደውም እውነት ነው፡፡ አሁንም ንጉሥ ሆኖ ሲያገኘው ግን ‹‹ይህም ያልፋል›› አለው፡፡ ቱሪስቱ በጣም ተገረመ፡፡
አሁንም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ቱሪስቱ ወደ አካባቢው መጥቶ የቀድሞው ገበሬ በኋላም ንጉሥ ያለበትን ሁኔታ ለማጣራት ሞከረ፡፡ “ያ ሰው እንዴት ሆነ? ወንበሩ ፀንቶለት ይሆን?” ብሎ ሲጠይቅ “አልሰማህም እንዴ? ሞተ’ኮ?” ተባለ፡፡ ይሄኔ ሰውየው አዘነ፡፡ ከዚያም “እባካችሁ እርሜን ላውጣ፤ አስከሬኑ ያረፈበትን ቦታ አሳዩኝ?” ይላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወስደው ከብዙ ሀውልቶች መካከል የእርሱን ያሳዩታል፡፡ ወዲያው ቀልቡን የወሰደው  ሀውልቱ ላይ የተፃፈው ጽሑፍ ነበር - “ኩኒስ ደርባ” ይላል፡፡
አዲስን ዓመት ስናስብ፣ አብረን ማሰብ ያለብን ‹‹ነገሮች ያልፋሉ›› ብለን ነው፡፡ የሚያስደስቱንም ሆኑ የሚያሳዝኑን ነገሮች ያልፋሉ፤ ግን ሰው እንደ መሆናችን መጠን ‹‹በምድር በኖርንበት ጊዜ የምንታሰብበት፣ ማስታወሻችን ምን መሆን አለበት?” የሚለው ነገር ላይ ነው ማተኮር ያለብን:: በርካታ ፈላስፎች በርካታ ነገሮች ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እነርሱ ስለተናገሩ ሁሉም ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሶቅራጥስ ስለ ሞት የሆነ ነገር ሲናገር፤ “ሞት” ማለት ሶቅራጥስ ያለው አይደለም፡፡
ሁልጊዜ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር፣ ትናንቶቻችን ሁልጊዜ መርሣትና ሁልጊዜ ማስታወስ ብቻ አይደለም የሚኖርብን፡፡ በጐ በጐ ነገሮችን እያስታወስን፣ ክፉ ክፉ ነገሮችንም እያስታወስን ልንማርባቸው ይገባል፡፡ ታሪክ የሚያስተምረን ታሪክ እንደማይደገም ብቻ ሳይሆን ታሪክ እንደሚደገምም ነው፡፡ ስለዚህ ታሪክ አንባቢ ብቻ ሳንሆን ታሪክ ሠሪም መሆን ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ፡፡
በእጆቻችን የያዝናቸው ትንንሽ ባትሪዎች ሀይላቸው ይደክምና ያልቃል፤ ሲያልቅ የሚሞላው  በሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ ደግሞ የሚሻረው በሃሳብ ነው፡፡ ሃሳብ በኒውክሊየር ቦንብ ሊጠፋ አይችልም፡፡ የተሻለ የምናመርተው የተሻለ ነገር ባሰብን ቁጥር ነው፡፡
አንድ የታወቁ የሥነ አዕምሮ ባለሙያ የሰው ልጅ ከ65ሺህ እስከ 70ሺህ ሃሳብ ያስባል ይላሉ፡፡ ‹‹በጣም የሚገርመው ግን ከ45ሺው በላይ አሉታዊ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በጣም የሚከፋው ደግሞ ዛሬ ያሰባችሁት የትናንቱን መሆኑ ነው” ይላሉ፡፡ ስለዚህ ነገን ጥሩ ለማድረግ ጥሩ ማሰብ አለባችሁ፡፡ ጥሩ ለማሰብ ደግሞ ማሰብ ብቻውን በቂ አይደለም:: በምናየው፣ በምንሰማው ነገር መነሻነት ሊሆን ይችላል፤ ምክንያቱም ሃሳብ በነፋስ አይፀነስምና!
በአንደኛው ክፍለ ዘመን ላይ በሮማን አንድ ፈላስፋ ነበር፡፡ ይህ ሰውዬ ባሪያ ነበር፡፡ የራሱ መብት አልነበረውም፤ የሃሳቡ ባሪያ ነው፤ የገዢዎቹም ባሪያ ነው፤ ግን አንድ ነገር አሰበ:: ያለንበትን ነገር ለመቀየር ሃሳባችንን መቀየር እንችላለን:: ስለዚህ ከአስተሳሰባችን ባርነት ነፃ መውጣት እንችላለን፤ ይህን ሲል ካጋጠመን ነገር በላይ ነገሩን የምንተረጉምበት መንገድ ወይም ለዚያ ጉዳይ ያጠለቅነው መነጽር ዋናው ጉዳይ መሆኑን ይገልፃል:: የእኔም ሃሳብ እንደዚያ ነው፡፡ አዲስ ዓመት ለሁሉም አዲስ ላይሆን ይችላል፤ ለአንዳንዱ አሮጌ ሊሆን ይችላል፡፡ በሌላ ቋንቋ አዲስ የምንለው ምን ተለውጦ ነው?
የለም ሌላ ዓመት፣ የለም አዲስ ፀሐይ
ለእኛው እያለቀስን ይሄው በእኛው እንባ
ደግሞ ሌላ ዘመን፣ ሌላ ዓመት ሲጠባ፡፡
እንደሚለው ግጥም፡፡ ፈላስፋ አንዳንዴ ያፈነግጣል፤ የሚያፈነግጥበትም መንገድ አንዳንዴ ይኼ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እንደ ተርታው ሰው አያስብም፤ ወጣ ያለ አስተሳሰብ አለው፡፡ “ለምን?” እያለ ይጠይቃል፡፡ ለምንድነው ዛሬ በግ ወይም ዶሮ የማርደው? ለምንድነው አዲስ ልብስ የምለብሰው? ለምንድነው የምጨፍረው? ወዘተ… ለምን ከትናንትና ወዲያ ወይም ትናንት ይህንን አላደረግሁም? በመስከረም አንድና በጳጉሜ ስድስት መካከል ያለው ልዩነት ለፈላስፋ ምንም አይደለም:: ስለዚህ ፈላስፋ የሚያስበው በነገሮች ሂደት ሳይሆን ለህይወት በሚሰጠው ትርጉም ነው፡፡ እናም አንደኛው የፈላስፋ ሥራ፤ ማኅበረሰቡ የተሸከመውን አመለካከት በመጠየቅ ማፍረስ ነው፡፡ እንዲፈትሸው፣ እንዲጠይቀው ማድረግ ነው፡፡ ሶቅራጥስ ‹‹ያልተመዘነ ህይወት ትርጉም የለውም›› ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ይህን ሁሉ ይጨምራል፡፡
በርግጥ በዓላችን ጥሩ ነው፤ ደስ ይላል:: ሃይማኖታዊ እሴት፣ ባህላዊ እሴት ይኖረዋል፤ መልካም ነው፡፡ ከዚህ ማኅበረሰብ ውጭ ልትሆን አትችልም፡፡ ማፈንገጥ ይቻላል፤ ግን እንደ ዕብድ መቆጠር ደግሞ ይመጣል፡፡ ነገር ግን በማህበረሰቡ ውስጥ ስትኖር ተቀብለህ መኖር ብቻ ነው ያለብህ የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይጠቅማል ወይ? ለምንድነው መስከረም አንድ ያ ሁሉ ፌሽታ፣ ያ ሁሉ ግርግር፣ ያ ሁሉ ኪሣራ የሚያስፈልገው? ያ ሁሉ ገንዘብ ለምን ይፈስሳል? ለምን የሌለህን ነገር ፍለጋ ትዳክራለህ? ለምን ዕዳ ውስጥ ትዘፈቃለህ? ምናልባትም የአንዳንዱ ቤተሰብ በዕዳ ምክንያት ይፈርሳል፡፡
ከማሰብ ይልቅ መብላት መጠጣት፣ የህይወት ትርጉም ማጣፊያ ተደርጐ ነው የታየው፡፡ ፈላስፋ ግን ይህንን ይጠይቃል፡፡ “ለምን?” ብሎ ይሞግታል፡፡ ትናንት በበላኸውና ዛሬ በምትበላው መካከል ምንም ልዩነት የለም ነው ጉዳዩ፡፡ ቀን ቀን ነው፡፡ ባይሆን በቀኑ ታሪክ መስራት ነው ያለብህ፤ አለዚያ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ነገር እንዳለ መቀበል የለብንም፡፡
እኔ መደምደሚያ ቢሆን ይሻላል የምለው፤ በመጠን መኖር፣ በልክ መኖር፣ ደስታን ከአንዲት ቀን ማዕቀፍ ውስጥ አውጥቶ ለቀሪ ዘመን ደስታ መሥራት፡፡ በተቃራኒው ባንድዋ ቀን ምክንያት የህይወት ዘመናቸው የሚፋለስባቸው በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ስለዚህ ቆም ብሎ ማሰብ ይጠቅማል፣ ወይስ አይጠቅምም? ብሎ ነገሮችን ሁሉ መመዘን መልካም ነው፡፡
እኛ በደንብ አልተጠናም እንጂ “ከማን አንሼ” የሚል ፍልስፍና አለን፡፡ ይህ ደግሞ ጤነኛ አስተሳሰብ አይደለም፡፡ ሰው እንደ ቤቱ እንጂ እንደ ጐረቤቱ መኖር የለበትም፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በምክንያትና በምክንያት መመዘኑ መልካም ነው፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣም፤ ጊዜው ተቀይሮ ሰውየው ካልተቀየረ ዋጋ የለውም፡፡ ከጊዜው ይልቅ ጊዜውን የሚገዛው ሰውየው ነው፡፡ እኛ ግን በአብዛኛው የጊዜ ባሮች ነን፡፡ የበዓሎቻችን ባሮች ነን እንጂ የአውዳመቶቻችን ገዢ አይደለንም:: ያ ደግሞ ከሰውነት መውረድ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ሰዎች ከበዓል በላይ መሆን አለባቸው፡፡    

Read 1632 times