Monday, 09 September 2019 11:11

‘ያልተላጠ’ ሽንኩርት፣ ‘የተላጠ’ ኑሮ

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


         “እናም… ከሁሉም በላይ ልንመኝ የምንችለውና ምናልባትም ልንመኝ የሚገባን ሰላምን ነው፣ ከሁሉም በላይ ልንመኝ የሚገባው እላያችን ላይ ሰፍሮ ተራ፣ በተራ እየቆሰቆሰ እያባላን ያለውን መጥፎ መንፈስ ጥርግ አድርጎ የሚወስድልን ተአምር እንዲፈጠር ነው፣ ልንመኝ የሚገባን አልለቅ ያለን የችግርና የመናቆር አዙሪት የሚወገድበትን ጥበብ እንድናገኝ ነው፡፡--”
            
              እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እንኳን ለአዲስ ዓመት ዋዜማ አደረሳችሁ! ምንም እንኳን ኑሮ አንድ ወረዳ የሚክል ቋጥኝ በተራራ ሽቅብ መግፋት ቢሆንብንም፣ መልካም ቃላት በትንሹም ቢሆን መልካም ስሜት መፍጠራቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም…ዘንድሮ ፈረንጅ ‘ክሮኒክ’ በሚለው ደረጃ ያጠሩን ነገሮች በዝተዋልና፡፡ እውነት…የመልካም ቃላት ቋታችንን ማን ወይም ምን አራገፈብን? እንዴት ነው በአንድ ጊዜ እንዲህ ባዶ የሆነው? የማይከፈልባቸው መልካም ቃላት እያሉ ዋጋ የሚያስከፍሉ ክፉ ቃላት መደርደር ከየት የተላለፈብን ወረርሽኝ ነው!? መልካም ቃላት ብቻ የምንለዋወጥበት ዘመን ይሁንልንማ!
በነገራችና ላይ...“ኑሮ እንዴት ነው?” ብሎ መጠየቅ በተዘዋዋሪ አሽሙር ይመስልብን ይሆን እንዴ?! ልክ ነዋ…ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ሠላሳ ሶስትና ሰላሳ አምስት ብር፣ ኩንታል ነጭ ጤፍ ሶስት ሺህ አምስት መቶ ብር፣ ምስር እንኳን በአቅሟ ኪሎ ሰባ አምስት ብር በገቡበት ጊዜ “ኑሮ እንዴት ነው?” ብሎ መጠየቅ ምን እሚሉት አሪስቶትልነት ነው!
“እሱ ፌስታል ውስጥ ምንድነው ያለው?”
“ነጭ ሽንኩርት”
“ሁለት መቶ ብር የተቀበልሽኝ ለዚህ ነበር?”
“እናንተ ምን ታደርጉ፣ የበሰለ ይቀርብላችኋል፡፡ ይገባችሁ እንደሁ፣ አንድ ኪሎ ነጭ ሽንኩርት መቶ ሀምሳ ብር ገብቷል፡፡”
“ሁዋት! ለምን አይቀርም!”
የምር ግን ምን መሰላችሁ… አሁን በየቤቱ የነጭ ሽንኩርት ዋጋ ለመጨቃጨቅስ ይመቻል!
በፊት እኮ “ኪሎውን ሠላሳ ብር ገዛሁት” ሲባል… “ይሄኔ ብትከራከሪ ሀያ ሁለትም፣ ሀያ አራትም ታገኚ ነበር” ማለት ይቻላል፡፡ “መቶ ሀምሳ ብር!” ሲባል ግን “ብትከራከሪ ኖሮ…” ለማለትም ያስቸግራል፡፡ “ገንዘቡ በእንግሊዝኛ ሲጠሩት ነው ክብደቱ የሚሰማው…” ላልከው ወዳጃችን… “ዋን ሀንድረድ ኤንድ ፊፍቲ ብር!” ያውልህ፡፡ አዲዳስ ነጭ ስኒከር ስንት ነው የምትገዙት?
“ስማ ሀምሳ ብር እፈልጋለሁ”
“ለምንሽ?”
“ለዶሮ መግዣ ነዋ…”
“ምን! ሀምሳ ብር! ለአንዲት ዶሮ ሀምሳ ብር! መቶ ሀምሳ ብር ጨምሬበት ጠቦት አልገዛበትም እንዴ!” የሚባልበት ዘመን ‘ሂስትሪ’ እንደሆነ ለመጠቆም ያህል ነው፡፡
መስከረም ለምለሙ መስከረም ለምለም
ብሩህ እንቁጣጣሽ ደስታ ለዓለም፣
ብላለች ጂጂ፡፡ መሬታችንንም፣ ልባችንንም፣ አእምሯችንንም እንደ መስከረም ለምለም ያድርግልንማ!
እኔ የምለው…እንግዲህ አዲስ ዓመት መግባቱም አይደል… እነ እንትና የ‘ኤጇ’ ነገር እንዴት ነው፣ ‘ማስተካከያ’ ምናምን አይነት ለውጥ ተደረገባት እንዴ?! ምን የሚሉት ነገር አለ መሰላችሁ… “ከኬኩ ዋጋ የሻማው ዋጋ በበለጠ ጊዜ እያረጀህ መሆኑን እወቅ፡፡” (ለኬኩ ሠላሳ አምስት፣ ለሻማው ሀምሳ አምስት እንደ ማለት፡፡)
የምር ግን ምን መሰላችሁ…የሆነ ነገር ትዝ አለኝ…‘ሪያሊቲ’ እና ‘ፋንታሲ’ን የመለየት ችግር አለ:: ‘ፋንታሲ’ ሁሉ እውነት ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ዓለም በሙሉ ምሳሌ የሚወስደው ከእኛ ይሆን ነበር፡፡
ስሙኝማ…በቀደም ሴቶችን በተመለከተ ጀርመኖች ናቸው እነማናቸው ከእኛ ልምድ መውሰድ አለባቸው የተባሉት? ለነገሩ…እኛ ስንት ነገር ስንወስድባቸው ኖረን የለ…አሁን ደግሞ ሴቶችን በተመለከተ ልምዳችንን መውሰድ አለባችው:: አንጌላ ሜርከልን ስላስቀመጡ ብቻ ደረታቸውን ነፋ አድርገው ሊሆን ስለሚችል ‘ልናስተካክላቸው’ ይገባል፡፡ ዘንድሮ ምን ደስ የሚል ነገር አለ መሰላችሁ…ያሰኘንን ማለት ይቻላል፡፡ ምን አለ በሉኝ…ይሄ እያወራንለት ያለውን ሳተላይት ካመጠቅን በኋላ ‘ናሳ’ ከእኛ የሚቀስመው ብዙ ልምድ ይኖራል፡፡
እናማ…መቼም ዘንድሮ ለአዲሱ ዓመት ምኞታችን መለዋወጡ አይቀርም፡፡  (‘እቅድ’ ማለት ስለከበደ ነው! የግላችን ‘ሪሞት ኮንትሮል’ ሳይቀር ከእጃችን እየወጣ ስለሆነ እንዴት ብለን ነው ስለ እቅድ ማውራት የምንችለው!) እንደ በፊቱ “መጠጥ ቀንሼ”፣ “ማጨስ አቁሜ”፣ “በጊዜ ቤቴ ገብቼ” ምናምን አይነት ነገሮች ‘ከጨዋታው ውጪ’ እየሆኑ ነው፡፡ ዘንድሮ ስእሉ ተለውጧላ! ከሀገርና ከህዝብ ህልውና ጋር የተያያዙ ችግሮች በዝተዋልና፡፡ በአንድ በኩል ‘ተስፋ’ የምንላቸው ነገሮች ሲኖሩ፣ በሌላ በኩል የተሳከሩና እየተሳከሩ ያሉ ነገሮች በርክተዋልና፡፡
እናም… ከሁሉም በላይ ልንመኝ የምንችለውና ምናልባትም ልንመኝ የሚገባን ሰላምን ነው፣ ከሁሉም በላይ ልንመኝ የሚገባው እላያችን ላይ ሰፍሮ ተራ፣ በተራ እየቆሰቆሰ እያባላን ያለውን መጥፎ መንፈስ ጥርግ አድርጎ የሚወስድልን ተአምር እንዲፈጠር ነው፣ ልንመኝ የሚገባን አልለቅ ያለን የችግርና የመናቆር አዙሪት የሚወገድበትን ጥበብ እንድናገኝ ነው፡፡
በአዲሱ ዓመት አተካሮ ቢቀንስ እንመኛለን፡፡
ወጥቼ ወጥቼ ሲያልቅልኝ ዳገቱ
ተመልሼ ወረድኩ ከነበርኩበቱ
የምትል ስንኝ አለች፡፡ ምናልባት ወጥተን፣ ወጥተን ዳገቱ እንኳን ሊያልቅ አላጋመስነው ይሆናል:: ግን የጀመርናቸው ነገሮች ነበሩ፤ አሉም፡፡
እናላችሁ ሰላሙን ከቤታችን ይጀመርልንማ! የምር ግን አለ አይደል…በተባራሪ የምንሰማቸው የተረጋገጡም፣ ያልተረጋገጡም የየጓዳዎቻችን ችግሮች… “ነገሮች እንዴት ነው እዚህ ደረጃ ሊደርሱ የቻሉት!” የሚያስብሉ ናቸው፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባላት በትንሹም፣ በትልቁም ጉሮሮ፣ ለጉሮሮ ካልተናነቅን ማለት የተለመደ ሆኗል፡፡ በተለይ ይሄ ‘ውርስ’ የሚሉት ነገር የየቤተሰቡን አባላት በየችሎቱ እያጓተተ ነው ይባላል፡፡
እናላችሁ...በየጓዳችን ምድር ቀውጢ እየሆነ እንዴት ብለን ነው በሀገር ደረጃ አስፍተን ማሰብ የምንችለው፡፡ አዲሱ ዓመት ይህ የሚቀረፍበት እንዲሆን ምኞታችን ነው፡፡     
ሁለት ጓደኛሞች እያወሩ ነው፡፡
“ምን ያህል ታገኛለህ?”
“በወር ሁለት ሺህ ብር፡፡”
“ባለቤትህስ?”
“በወር ሁለት ሺህ ብር”
“ስለዚህ በጋራ በወር አራት ሺህ ብር ታገኛላችሁ ማለት ነው፡፡”
“ኖ፣ ሁለት ሺህ ብቻ ነው የምናገባው፡፡ እንዴት መሰለህ… ለእኔ ሁለት ሺህ ብር ይሰጠኛል፡፡ እኔ ደግሞ ለእሷ ሁለት ሺህ ብር እሰጣታለሁ…” አለና አረፈው፡፡
በነገራችን ላይ በልክ ይጠጣማ…መሶብ ባዶ በሆነበት የነገን እሱ ያውቃል በሚል ብቻ ቤተሰብን እያስራቡ ራስን ፉል ታንክ መሙላት ልክ አይደለም:: (የመጠጥ ዋጋ የፈለገ ይጨምራ፡፡ ግፋ ቢል ‘ቁልቁል’ መሸጋሸግ ነው… ከፕሬሚየር ሊግ ወደ ናሽናል ሊግ እንደ መውረድ፡፡)
ይቺን ስሙኝማ…ሰውየው ‘ጣጥ’ ብሎ ሲወጣ ሆቴሉ በር ላይ የተንቆጠቆጠ ዩኒፎርም የለበሰ ሰው ቆሞ ያያል፡፡
“ስማ ማነህ… ቤቴ የሚወስደኝ ታከሲ ጥራልኝ” ይለዋል፡፡ ሰውየው ይናደዳል፡፡
“እንዴት ብትደፍረኝ ነው እንዲህ የምታዘኝ!” ይለዋል፡፡
 ጣጤውም…
“ዘበኛ አይደለህ እንዴ! ለምንድነው የማላዝህ?” ይለዋል፡፡
“ስማ፣ እኔ ዘበኛ አይደለሁም፡፡ የባህር ሀይል አድሚራል ነኝ፡፡”
ጣጤው ምን ቢል ጥሩ ነው…
“እንግዲያው ቤት የሚወስደኝ ጀልባ ጥራልኝ፡፡”
አሀ…እውነቱን ነዋ! ሰውየውስ ቢሆን…በተንቆጠቆጠ ዩኒፎርም ሆቴል በር ላይ ምን ይገትረዋል፡፡ (ስሙኛማ…ይሄ ሸላይ እንትናዬዎች ትላልቅ ሆቴል ማኪያቶ ይዘው ‘እያንደረደሩት’ ነው የሚባለው “አይ ላቭ  ሞር ዛን አይ ካን ሴይ” አይነት ቢዙ…አለ አይደል… ጂ ፕላስ ምናምን ቤት ሁሉ  ያስገኛል የሚባለው እውነት ነው እንዴ! ቆይማ…ጥያቄ አለን፤ የፈለገ የኢንቬስትመንት ፈቃድ፣ የአክስዮን ሽያጭ ምናምን ባያስፈልገውም የሚመደበው ከማምረቻ ዘርፍ ነው ከአገልግሎት?! ቂ…ቂ…ቂ…)
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2819 times