Monday, 09 September 2019 10:36

ድንቅ አገር በውስጣችን አለ፡፡ በገሃድ እንየው፡፡

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በመናገር ብቻ ያሰቡትን ሁሉ መፍጠር፣ ቅንጣት ላባ በማወዛወዝ ብቻ ያሻቸውን ማድረግ፣ የሚመኙትንም መሆን የሚቻልበት ተዓምረኛ ዓለም ውስጥ ነው አሉ፡፡
መቼም፣ ሁሉም የምትሃት ዓለም ሰው፣ አንድ አይነት አይደለም፡፡ የናት ሆድ ዥጉርጉር ይባል የለ፡፡ እናማ አንዷ ታዳጊ የተዓምር ዓለም ልጃገረድ፣ ያልተለመደ ነገር ማድረግ ጀመረች፡፡
በመናገር ብቻ ያሰበችውን ነገር ሁሉ ከመፍጠር ይልቅ፣ የተፈጠሩ ነገሮችን እየመረመረች ስም ታወጣላቸው ጀመር፡፡ ላባ በማወራጨት፣ ያሻትን ከማድረግ ይልቅ፣ ጓሮ ውስጥ እንጨትና ብረት መግጠምና መፍታት አማራት፡፡ ምኞት ብቻ ሳይሆን ችሎታም እፈልጋለሁ አለች፡፡ ተዓምረኞቹን ግራ አጋባቻቸው፡፡ ቤተሰብ ተጨነቀ፡፡ ጎረቤት ተንሾካሾከ፡፡ የሰፈር መጠቋቆሚያ ሆነች፡፡ አንዳንዶቹ ጠሏት፡፡ አንዳንዶቹ መዓት ልታመጣብን ነው ብለው ወነጀሏት፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ፈረዱባት፡፡
ከተዓምር ዓለም ተባረረች፡፡ ሁሌ ብርሃን፣ ሁሌ ምቾት፣ ሁሌ እርጋታ ከሆነበት አለም ተወረወረች፡፡ ተወርውራ፣ ጭቃ ላይ ወደቀች፡፡ የጥቅምቱ ብርድ አንቀጠቀጣት፡፡ ጨለማ ዋጣት፡፡
እንዲህ ሆና ነው፤ ወዲህና ወዲያ ስትንገላታ ቆይታ፣ አንድ ትንሽ መኖሪያ ቤት ያጋጠማት፡፡ በር ከፍታ አየች፡፡ መብራት አለ፡፡ ወደ መታጠቢያ ቤት ስትገባም፣ አምፖል በርቷል፡፡ ተገረመች፡፡ እዚህ ምትሃት የሌለበት ዓለም ውስጥ፤ ድቅድቅ ጨለማን የሚያጠፋ እንደዚህ አይነት ተዓምር አልጠበቀችም፡፡
ለካ፣ የነዚህ ምትሃትም ቀላል አይደለም አለች፡፡ ምትሃት ባይሆንም፣ ከምትሃት አይተናነስም፡፡ እያንዳንዱ ክፍል ውስጥ ፀሐይ ፈጥረዋል፡፡
የገላ መታጠቢያ ቧንቧ ስትከፍት ውሃው ሿ ብሎ ወረደ፡፡ ተደነቀች፡፡ ለካ ተአምረኛ ያልሆነ ዓለም ውስጥም ተዓምር መስራት ይቻላል፡፡ በየቤታቸው ዝናብ ማዝነብ ይችላሉ ብላ ተደነቀች፡፡
*   *   *
በጨለማ ውስጥ ብርሃን ባይኖርም፣ ጨለማ ውስጥ መቅረት ማለት አይደለም፡፡ ብርሃንን መመኘት ብቻ ሳይሆን፣ የየራሳችንን ቤት የሚያፈካ፣ አገርን የሚያደምቅ ብርሃን መስራት እንደሚቻል አለመዘንጋት ነው፡፡
አዎ፣ ከከፍታ እጅግ ወርደናል፡፡ በጭቃ ላይ ወድቀን በማጥ ተጠምደን መራመድ አቅቶናል፡፡ ከፊት የሚራመዱ ሰዎች ታሪክ በሰሩበት አገር፣ ከዓለም ሁሉ የኋላ ሆነናል፡፡ በድህነትና በችግር ተብረክርከናል፡፡ ኑሮ ከብርድ የከፋ ሲሆን የማንቀጥቀጥ ያህል ሊያንገበግበን ይገባል፡፡ ነገር ግን አንርሳ፡፡ በእያንዳንዱ ሕፃንና ታዳጊ አእምሮ፣ ተዓምር የሚያሰኝ እውቀት አቅም ነው፡፡
የእያንዳንዱ ወጣት፣ ምትሃትን የሚያስንቅ የፈጠራ፣ የሙያና የስራ አቅም ነው፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያዊ መልካምን መመኘት፣ ከፍታን መውደድ ማጣጣም፣ ወደ ከፍታ መጓዝ፣ ከከፍታም ወደ ከፍታ እየላቀ በስኬት ላይ ስኬትን እየደመረ ትንግርት የመስራት ብቃትን መቀዳጀት ይችላል፡፡
ድንቅ ብርሃን፣ ድንቅ አገርና ድንቅ ሕይወት፤ በእያንዳንዳችን ውስጥ መኖሩን ልብ እንበል፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!!

Read 7510 times