Saturday, 31 August 2019 13:24

አዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ ሁለት አዳዲስ ምርቶች ለገበያ አቀረበ

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(1 Vote)

  በ1936 ዓ.ም የተቋቋመው አዋሽ ወይን ጠጅ ፋብሪካ፣ በኅብረተሰቡ ጥያቄ፣ አነስተኛ የአልኮል መጠን ያላቸው ሁለት ዓይነት የወይን ጠጆች ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የፋብሪካው ከፍተኛ አመራሮች በስካይ ላይት ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በ2 ሚሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ሥራ አከናውነው፣ ሁለት ዓይነት “ዳንኪራ” የተባሉና የአልኮል መጠናቸው 6 ፐርሰንት የሆነ የወይን ጠጅ፣ ሰሞኑን ለገበያ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡  
የፋብሪካው የብራንድና የኢኖቬሽን ማናጀር ወ/ሮ ብርሃን መንግሥቱ፤ ‹‹ከ2000 በላይ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄ በትነን፣ተጠቃሚው አነስተኛ የአልኮል መጠን ያለው፣ ለስላሳ ወይን ጠጅ እንድናቀርብለት ጠይቆናል፡፡ በዚሁ የሕዝቡ ጥያቄ መሠረት፣ “ዳንኪራ” የተሰኘና የአልኮል መጠኑ 6 ፐርሰንት የሆነ፣ የወይንና የተፈጥሮ ፍራፍሬ መዓዛ ያለው የወይን ኮክቴል፣ የስትሮበሪና የቮድካ ጣዕም ያለው “ዳንኪራ” የወይን ምርት ለገበያ አቅርበናል” ብለዋል፡፡
በ330 ሚሊ ግራም ጠርሙስ የቀረቡት ሁለት ዓይነቶች “ዳንኪራ” ወይን ጠጅ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ በተመረጡ ሥጋ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶችና ሆቴሎች ሲሸጡ፣ ዋጋቸውም ከ25-30 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
በሁለት ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የማስፋፊያ ሥራ የተገጠሙት እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች፣ የቀድሞውን የፋብሪካውን ምርት በሦስት እጥፍ እንደሚያሳድጉ ተገልጿል፡፡   
ከጀርመን፣ ከኢጣሊያና ከቻይና የመጡት የጠርሙስ ማጠቢያ፣ ማጣሪያ፣ ቆርኪውን የሚከድኑ፣ የብራንድ ስሙን የሚለጥፉና የሚያደርቁ እጅግ ዘመናዊ መሳሪያዎች በቻይና ኩባንያ የተገጠሙ ሲሆን እኒህም ለፋብሪካው ከፍተኛ የጥራት ደረጃ እንደሚያጐናጽፉት ተነግሯል፡፡  
የአዋሽ ፋብሪካ ኮመርሻል ዳይሬክተር ሚ/ር ኒል ኮመርፎርድ በበኩላቸው፤ “የወይን እርሻው ባለበት በአርሲ ዞን መርቲ ወረዳ ማኅበራዊ ግዴታችንን ከመወጣት አኳያ፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የመኖሪያ ቤት፣ የሚጠጣ ውሃ፣ የጤና ሕክምና በነፃ፣ ከነመድኃኒቱና የምግብ ድጋፍ እያደረግን ነው” ብለዋል፡፡  

Read 3794 times