Saturday, 31 August 2019 12:15

ሁለት ባላ ትከል አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ ደጋ እየኖረ ነበር፡፡ አንድ ቀን ቆላ ገበያ ወረደ፡፡ ሲመለስ ብዙ ብር ይዞ መጣ፡፡ የሳር ቤት ጣራውን ቀይሮ ቆርቆሮ አስመታ፡፡ አጣና፡፡ የጐዳደለውን አጥሩን አጥብቆ ዙሪያውን አሳጠረ፡፡ መሬቱን በሊሾ ሲሚንቶ አስለሰነ፡፡
በጣም አሳመረው፡፡
ይህንን ያየ የጐረቤቱ ገበሬ ወደ ቤቱ ሄዶ፤
“ወዳጄ፤ ምን አግኝተህ ነው ቤትህንና ግቢህን እንዲህ ያሳመርከው?” ሲል ጠየቀው፡፡
ገበሬውም፤
“ከደጋ ብረታ ብረት የተባለ ሁሉ ሰብስቤ ሳበቃ፣ ቆላ ወርጄ፣ ለቆለኞቹ ቸበቸብኩላቸው፤
ከዚያ ገንዘቡን ይዤ ቤቴን አደስኩ፡፡ አጥሬን ጠገንኩ “አለው፡፡
ጐረቤትዬውም የወደቀ የተሰበረ ብረት ሳይቀረው አከማችቶ፣ ሁሉንም ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሄድ፣ ገበያው ዳገት ላይ ስለሆነ ያለው እንዴት ይድረስ? ወገቡ ቅንጥስ አለበትና ወደቀ፡፡
አንድ መንገደኛ በዚህ በወደቀው ነጋዴ አጠገብ ሲያልፍ፤
“ወዳጄ”
“አቤት”
“ምን ሆነህ ነው”
“አዬ ወገኔ አያድርስብህ”
“ምኑን?”
“ያ የጐረቤቴ ገበሬ ቤቴን ያደስኩትና አጥሬን ያስጠገንኩት ባካባቢዬ ያለ የሌለውን ብረታ ብረት ሸጬ ነው ቢለኝ፤ እኔም እንደሱ ሀብታም እሆናለሁ ብዬ፣ ይሄው የብረታ ብረቱ ሸክም ጉድ አደረገኝ! እንደኔ ጐረቤት ትርፉን ነግሮ መከራውን የማይነግር፣ አይግጠምህ!”
***
ያለ መከራ ተድላ ደስታ አይገኝም፡፡ ያለ መስዋዕትነት ድል የለም፡፡
ከጦርነት በፊት የዝግጅት ፋታ
ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ
ዛሬም ያው ህዝባችን የአንድ አፍታ ዝምታ
ነገር ግን ይዋጋል መታገሉ አይቀርም
ታግሎም ያቸንፋል አንጠራጠርም!
አልጋ በአልጋ መንገድ ኖሮን አያውቅም፡፡ ከእርግብ ላባ የተሠራ ፍራሽ የለንም፡፡ የአገር ጉዳይ ሳይቆረቁረን ውሎ አድሮ አያውቅም፡፡
አንዳንድ ቀን አለ
አንዳንድ ቀን አለ
ኮረኮንች የበዛው ሊሾ እየመሰለ
የምንለውም ለዚያ ነው፡፡
ዛሬም የመደራጀት ጥያቄ አልተመለሰም ዛሬም ግልጽነት አልተመለሰም የትውልድ ዕዳ አልተከፈለም ጤና እንደተዛባ ነው፡፡ ትምህርት አላደገም፡፡ ነጋ ጠባ ማህበራዊው ህይወት እየተናጋ ነው፡፡
ህይወት ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሏት፡፡ ገና ብዙ ፈተና፣ ብዙ ትግል ይጠብቀናል፡፡ ያለ ጥርጥር ግን  እንወጣዋለን፡፡ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ኤጭ አይባልም፡፡ ድል የብዙሀን ነውና “ኩሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንዑ” ያልነው ገና ጥንቱኑ ነው፡፡ ሁሉንም ሞክሩ የተሻለውን አጽኑ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አማራጭ እንመልከት፤ እናስላ፡፡ መላ እንምታ፡፡ እንምከር፡፡ በውይይት የማይፈታ ችግር የለም፡፡
“ሁለት ባላ ትከል
አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል”  የሚባለው ለዚሁ ነው፡፡

Read 9541 times