Monday, 26 August 2019 00:00

ከተበጣጠሰ ሃሳብ ወደተደመረ ሃሳብ መሸጋገር፣ ስንት ጊዜ ይፈጃል?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(3 votes)


       • የንግግር ነፃነት በኢትዮጵያ ማበብ የጀመረው የዛሬ ዓመት ነው፡፡ አፍኖ የሚቆጣጠር አምባገነን ሲጠፋ፣ የዘረኝነት ጥቃት ተቀጣጠለ፡፡ (ዘ ኢኮኖሚስት)
           ዮሃንስ ሰ


          ዘኢኮኖሚስት፣ ሰሞኑን ያቀረበው ትልቅ ዘገባ፣ “አለማቀፍ የሃሳብ ቀውስን” በሰፊው ያሳያል፡፡ ከኤርትራ እስከ ኢራን፣ ከአፍጋኒስታን እስከ ሳውዲ፣ ከቻይናና ከራሺያ እስከ እንግሊዝና አሜሪካ… አለምን ከዳር እስከዳር ይዳስሳል፡፡
የዘገባው ፍሬ ነገር፣ “ነፃነት ተሸረሸረ፣ ልጓም ከረረ” የሚል ቢሆንም፣ እንደ ድሮው፣ ገሚሱን “የነፃነት ፋና ወጊና የነፃነት ታጋይ”፤ ገሚሱን ደግሞ “የነፃነት አፋኝና አምባገነን” እያለ በግልጽ ለማወደስና ለማውገዝ ቀላል አልሆነለትም፡፡ ለምን?
ዘኢኮኖሚስት፣ ከየትኛውም አለማቀፍ ሚዲያ ጋር ሲነፃፀር፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ነፃነት፣ በህግ የበላይነትና በፍትህ በዙሪያ፣ በጠንካራ አቋሙ የተሻለና የላቀ ቢሆን እንጂ ያነሰ አይደለም፡፡
እንዲያም ሆኖ፣ በነፃነት ጉዳይ ላይ አጥፊውን ከአልሚው እያጣራ ለመዳኘትና ለመፍረድ ተቸግሯል፡፡ የኢትዮጵያ የአንድ ዓመት ጉዞ፣ አንድ ምሳሌ ነው፡፡ “ኢንተርኔት ተዘጋ፤ ፌስቡክ ተቋርጦ ሰነበተ” ብሎ መንግስትን ብቻ መውቀስ ቢከብደው ይገርማል? መንግስት ስለፈለገ ብቻ ነፃነት ይስፋፋል ማለት አይደለማ፡፡ መንግስት አፋኝ አምባገነን ስለሆነ፣ ተቃዋሚ ሁሉ የነፃነት አፍቃሪ ነው ማለት አይደለማ፡፡
ምናለፋችሁ! ነገሮች ተደበላልቀው፣ ሃሳቦች ተበጣጥሰው፣ ለዳኝነት አልመች ብለዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል፤ ሰፊው ዓለምአቀፍ ዘገባ፣ የአሜሪካ ነባር የነፃነት አርአያነትን በመጥቀስ አይጀመርም፡፡ መፈናፈኛ የሚያሳጣ የቻይና የኢንተርኔት ስለላና የአፈና መረብን በማውሳትም አይጀምርም፡፡
ዴንማርክን በማወደስ  ወይም ኤርትራን በመኮነን፣ ኔዘርላንድን ወይም ራሺያን ለንጽጽር በማቅረብ፤ አድናቆት ወይም ወቀሳ በማስቀደም አላስነበበም፡፡ አዎ፤ ብዙ አገራት ተጠቅሰዋል፡፡ ነገር ግን፣ የዘመናችንን አሳሳቢ አዝማሚያና የዓለማችንን የሃሳብ ቀውስ ለማሳየት፣ ኢትዮጵያን ነው የመረጠው፡፡ በዘገባው መግቢያ፣ በቀዳሚነት የኢትዮጵያን አስቸጋሪ ሁኔታ አስፍቶ በመዳሰስ፣ ለመዳኘትና ለመፍረድ እንደሚከብድ በማሳየት፣ ዓለማቀፍ የሃሳብ ቀውስ እየተስፋፋ መምጣቱን ለማስረዳት ይሞክራል - ዘኢኮኖሚስት፡፡
ነፃነት፣ በተለይ ባለፉት 10 ዓመታት፣ በዓለማቀፍ ደረጃ፣ ከመስፋፋት ይልቅ እየተሸረሸረ፣ በበርካታ አገራትም አፈና እየከረረ፣ አምባገነንነት እየጠጠረ መምጣቱ ብቻ አይደለም ችግሩ፡፡ የነፃነትን ፋና ከፍ አድርገው የሚያበሩና እንዲስፋፋ የሚረዱ አገራትም፣ ድምፃቸው እንደሳሳ፣ ብርሃናቸው እንደ ደበዘዘ ይዘረዝራል ዘገባው፡፡
“አምባገነንነትን መቃወም፣ አፈና ላይ ማመጽ” ቀርቷል ማለት አይደለም፡፡ ተቃውሞና አመጽ ሞልቷል፡፡ ነገር ግን “አፈናን መቃወም” ማለት፣ ነፃነትን መፈለግ ማለት አይደለም፡፡ የተቃውሞ መጨረሻ፤ “አንድን የአፈና ሰበብ በሌላ የአፈና ሰበብ መቀየር” ብቻ ሆኖ ሲቀር ታይቷል፡፡
“አምባገነንነት ላይ ማመጽ”፣ የህግ የበላይነትን መውደድ ማለት አይደለም፡፡ እናም አመፁ፣ የሹም ሽር ጉዳይ ብቻ ሆኖ ይቀራል፤ አልያም የባሰ ይመጣል፡፡ “አምባገነንነት በኔ እጅ ያምራል” በሚሉ ደርዘን ተቃዋሚዎች፣ “ለአምባገነንነትማ አላንስም” በሚሉ እልፍ የመንደር ጋጠወጥ ወንጀለኞች፣ አገር ይተራመሳል፡፡ ደቡብ ሱዳን፣ ኮንጐ፣ ማሊ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሊቢያ፣ ሶማሊያ…ለይቶላቸው የተተራመሱ አገራትን ብቻ በማየት፣ የአለማችንን የሃሳብ ቀውስ መገንዘብ ይቻላል፡፡
ተቃውሞና አመጽ በተለኮሰ ቁጥር፣ “አላማቸው ምንድነው? መንገዳቸውስ በየት በኩል ነው? አላማቸው ነፃነትን መቀዳጀት ነው? መንገዳቸውስ ህግና ስርዓትን የሚከተል፣ የህግ የበላይነትን የሚያከብር መንገድ ነው?” ብሎ መጠየቅ ባዕድ ከሆነብን፣ በደፈናው “የህዝብ ጥያቄ”፣ “ለውጥ ፈላጊ”  ምናምን እየተባለ ነገሩ ይጧጧፍና፣ መጨረሻ ላይ፣ ከድሮ የባሰ አምባገነንን በማሸከም ያበቃል::  አልያም ማብቂያው በማይታወቅ ትርምስ አገር እየፈራረሰ፣ እልቂትና ስደት ይነግሳል፡፡ በአዙሪት የመባከን፣ በቁልቁለት የመጥፋት ጉዞ በሉት፡፡
“አፈናን መቃወም”፣ ከነፃነት አላማ ተነጥሎ፣ “አምባገነነት ላይ ማመጽ”፣ የህግ የበላይነትን ከመፈለግ ተገንጥሎ፣ ማለትም “በተደመረ ሃሳብ” ሳይሆን፣ “በተበጣጠሰ ሃሳብ” የምንሄድ ከሆነ፣ ከአዙሪትና ከቁልቁለት የመውጣት ብቃት አይኖረንም፡፡
ታዲያ፣ ለነፃነት የሚመጥን ብቃት ባይኖረንም፣ አንዳንዴ እንደመታደል ሆኖ፣ ነፃነትን የማግኘት እድል ሊገጥመን ይችላል፡፡
የዛሬ ዓመት ገጥሞናል፡፡  
የዛሬ ዓመት፣ አገሬው ከትርምስና ከለየለት አምባገነንነት የተረፈው፣ ሕግና ስርዓት ጨርሶ ያልፈረሰው፣ የነፃነት ጅምር ፈካ ለማለት የበቃውስ፣ በስንቶቻችን ብቃትና ጥረት ይሆን? ‹‹እድል ገጠመን›› አያሰኝም? ይሁን፡፡ መልካም እድል፣ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የነጻነት እድል ሲገጥመን፣ ለነፃነት የሚመጥን ብቃት ለማግኘት ፈጥነን ካልተጋን፣ ነፃነትን የማሰንበት አቅም እናጣለን፡፡
ለነፃነት የሚመጥን ብቃት ማለት፣ በቁንፅል ከመቃወም በፊት፣ የምንፈልገውንና የምንደግፈውን አላማ በቅጡ ማወቅ፣ በብጣሽ ሀሳብ ‹‹ይለወጥ›› ብሎ ከመጮህ በፊት፣ መድረሻ ግባችን ከድሮ የተሻለ፣ መንገዳችንም የተቃናና የተባረከ መንገድ መሆኑን በስርዓት ማወቅን ይጨምራል፡፡ ይሄን አስተሳሰብ፣ የተደመረ አስተሳሰብ ልትሉት ትችላላችሁ - የጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን አባባል በመጠቀም፡፡
“ነፃነት”፣ ለብቻው የተነጠለ፣ ብጣሽ ጉዳይ አይደለም፡፡ ለእውነትና ለእውቀት ክብር የሌለው፣ ነፃነትን ይጫወትበታል፡፡ ሰርቶ መኖርንና በጥረት ተግቶ ንብረት ማፍራትን የማያከብር፣ ነፃነትን ይቆምርበታል፡፡
እያንዳንዱን ሰው፣ በዘር በመንደር ሳይሆን፣ በግል ብቃቱ፣ በተግባሩ፣ በባሕርይው ለመመዘን የሚያስችል፣ እውነት ላይ የተገነባ፣ ትክክለኛ የስነምግባር መርህ ከሌለን፣…(ማለትም እያንዳንዱን ሰው እንደስራው የመዳኘት ፍትሃዊነትን ካጣን)፣ ነፃነት ምን ትርጉም አለው?...በሌላ አነጋገር፤…
ነፃነት፣ ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ጋርም አይሰነበትም፡፡
ዘ ኢኮኖሚስት እንደሚለው በጥረት ሳይሆን እድል ገጥሞን፣ አምና ከቀድሞ የተሻለ ነፃነት ብናገኝም፣ ከዘረኝነት ጋር አብሮ ሊቀጥል አይችልም፡፡ እንዴት? ዘኢኮኖሚስት ያቀረበው ዘገባ ሲጀምር እንዲህ ይላል፡፡
የንግግር ነፃነት፣ በትግል መከራ ይቀዳጁታል፣ እንደዋዛ ያጡታል። በኢትዮጵያ፣ በቅርቡ የዛሬ አመት፣ ሊበራል እንደሆኑ በሚታሰቡት በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዐቢይ አህመድ ነው የንግግር ነፃነት ያበበው፡፡ የታሰሩ ሁሉም ጋዜጠኞች ተፈትተዋል፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ድረገጾች፣ ጦማሪዎችና የሳተለይት ቴሌቪዥኖችም፣ ከእገዳ ተለቀዋል፡፡
አሁን ግን፣ መንግስት አሳሳቢ ሆኖበት እያመነታ ነው፡፡ አፍኖ የሚይዝ አምባገነን ሲጠፋ፣ ዘረኛ አመፅና ጥቃት፣ ተቀጣጥሏል፡፡ የመንጋ ፍረጃ አራጋቢዎች፣ ገና ነፃ በተለቀቀው የኢንተርኔት ማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት፣ ዘረኛ የጥላቻና የጥቃት ዘመቻዎችን ቀስቅሰዋል፡፡ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ከመኖሪያቸው ተነቅለው ተሰደዋል፡፡
ኢትዮጵያ፣ የምር አጣዳፊ አደጋ ገጥሟታል። ጥቃትን የሚሰብኩ ቀስቃሾችን ለመግታት፣ መንግስት ቢዘጋቸው ተገቢ እንደሆነ ብዙ ኢትዮጵያውያን ያምናሉ፡፡ ነገር ግን የመንግስት እርምጃ ከዚህ እጅጉን ያለፈ ነው። (ኢንተርኔትን መዝጋት) የሁሉንም አንደበት እንደመዝጋት ነው፡፡
ከጠ/ሚ ዐቢይ በፊት ወደነበረው ሁኔታ፣ የኋሊት ተመልሶ እንዳይጨልም የሚሰጉ አሉ:: መንግስት ከፈለገ፣ ምን ጐድሎት?  ለስለላና ለአፈና የሚያገለግሉ፣ በብዛት ከቻይና የገዛቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች አሉት፡፡ ሞልቶት ተርፎት!
ዘኢኮኖሚስት በእንዲህ አይነት ገለፃና ትረካ ነው ዘገባውን የሚጀምረው፡፡ እንደ ድሮ መንግስትን በማውገዝ፣ አጭር የዳኝነት ፍርድ መስጠት አልቻለም፡፡
መንግስት ስለፈለገ ብቻ፣ ነፃነት ይስፋፋል ማለት እንዳልሆነ እየታየ ነዋ፡፡ ነፃነት ሰፋ ሲል፣ የዘረኝነት ስብከትና የጥቃት ቅስቀሳ እየተግለበለበ፣ አገር በግድያና በዝርፊያ የሚናወጥ፣ በቃጠሎ የሚነድ ከሆነ፣ ምን ተሻለ? ሌላኛው አማራጭ፣ አምባገነንነት አይደለም፡፡
ነፃነትን ለብቻው የሚነጥል የተበጣጠሰ አስተሳሰብን በማስወገድ፣ በምትኩም ትክክለኛ ሃሳቦችን በቅጡ የሚያሰናስል አስተሳሰብን መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ከእውነትና ከእውቀት፣ ሰርቶ ከመኖርና ንብረት ከማፍራት፣ ከግል ማንነትና ከግል ሃላፊነት፣  ከስነምግባርና ከቅንነት፣ ከፍትህ እና ከህግ የበላይነት ጋር ተደምሮ ነው ነፃነት የሚያብበው፡፡ አስተሳሰቦችንም እንደዚያው የሚደምር ይሁን፡፡  



Read 4957 times