Saturday, 24 August 2019 13:44

በሕዝብና በምሁራን ላይ ያመጸ የፖለቲካ ኃይል

Written by  (ከአብዱራህማን አህመዲን፤ የቀድሞ የፓርላማ አባል)
Rate this item
(2 votes)


          የዛሬው መጣጥፌ ትኩረት “የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤና የመፍትሔ አቅጣጫ” በሚል ርእስ በምሁራን የተደረገውን ጥናት በተመለከተ ይሆናል:: ይህንን ጥናት በተመለከተ የተቃውሞም የድጋፍም ድምፆች ይደመጣሉ፡፡ መጯጯሁን ሳይና ስሰማ እስቲ እኔም የበኩሌን “ጩኸት” ላሰማ በሚል መንፈስ ነው ይህቺን ማስታወሻ ለመክተብ የተነሳሁት፡፡ ወደ ጽሁፌ ይዘት ከመግባቴ በፊት ሁለት ነገሮችን ላስቀድም፡፡ አንደኛ፤ መረጃ በማቀበል ብቻ ሳይሆን ሃሳብ በማዋጣት ይህቺን ጽሁፍ ያዳበሯት በዲላ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩ አንጋፋ ምሁራን ጓደኞቼና ወዳጆቼ መሆናቸውን ከአክብሮት ጋር አስቀድሜ መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ሁለተኛ፤ በምሁራኑ የተጠናውን “የደቡብ ብሔር/ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል የአደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤና የመፍትሔ አቅጣጫ - ዳሰሳዊ ጥናት፣ የመነሻ ምክረ ሀሳብ ህዳር 27/2011” የሚል 59 ገፆች ያሉት ሰነድ አንብቤአለሁ:: ይሁን እንጂ፤ በዚህ ጽሁፌ የዚህን ሰነድ ይዘት አንድ በአንድ ለመተቸት ከመሞከር ይልቅ አጠቃላይ እይታዎቼን ማቅረብን መርጫለሁ፡፡ በዚህም መሰረት፤ ስለ አጥኚዎቹ ማንነት፣ ስለ ጥናቱ ይዘት፣ ጥናቱን ስለ ቀሰቀሰው ችግር ያለኝን አስተያየት ለማቅረብ ጥረት አደርጋለሁ፡፡
ጥናቱ ለምን አስፈለገ?
የአደረጃጀት ጥያቄ ሕገ-መንግስታዊ ነው በሚለው ሃሳብ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የደቡብ ክልል ከምስረታው ጀምሮ በርካታ የአደረጃጀት ለውጦች ተደርገውበታል፡፡ በሽግግሩ ወቅት በአምስት ክልሎች ተዋቅሮ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱ ሲወጣ አምስቱ ተጣምረው አንድ ክልል እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ ክልሉ ሥራ ሲጀምር 5 ዞኖች ነበሩት፡፡ በኋላ የዞኖቹ ቁጥር ወደ 9 ከፍ አለ፡፡ ቀጥሎ በ14 ዞኖች ተዋቀረ፡፡ በአሁኑ ወቅት 21 ዞኖች ደርሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወረዳዎችና የልዩ ወረዳዎች አደረጃጀት አለ፡፡ እነዚህ ተጨባጭ የአደረጃጀት ለውጦች ቢደረጉም ጥያቄዎቹ አልቆሙም፡፡
ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የክልልም ይሁን የዞን ወይም ሌላ አደረጃጀት ከልማትና ከመልካም አስተዳደር መስፈን ጋር ቢታይ የበለጠ ሊጠቅም ይችላል፡፡ የቀረቡት ጥያቄዎች ግን አንዳንዶቹ ባለሙያዎቹ የሚሉትን ሃሳብ ግምት ውስጥ ያስገቡ ሳይሆን የእልህ ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት “የአደረጃጀት ጥያቄዎች በሚመለሱበት ጊዜ የህዝቡን የልማትና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንቅስቃሴ፣ ሚናና ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር እንዴት መታየት እንደሚገባው መፈተሽ ያለበት ዋና ጉዳይ” መሆኑን የተገነዘበው የክልሉ ገዢ ፓርቲ ደኢህዴን፤ ዘላቂ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል መደምደሚያ በሳይንሳዊ ጥናት መቅረብ እንዳለበት በማመን፣ በ10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡ በጉባኤው ውሳኔ መሰረት፣ ሰፊና ጥልቅ ሳይንሳዊ ጥናት ለማካሄድና የጉባኤውን ዉሳኔ ለመተግበር፣ በምርምር ልምድና ዕዉቀት ያላቸው ባለሙያዎችን ያቀፈ የጥናት ቡድን በደኢህዴን ሥራ አስፈጻሚ ተቋቋመ። አጥኚው ቡድን የጥናቱ ውጤት የሆነውን ምክረ-ሀሳብ አቀረበ፡፡
የተካሄደው የዳሰሳ ጥናት ነው፡፡ አንዳንዶች ለምን ጥናት ተካሄደ፣ በሀገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ለምን አይፈጸምም? የሚል ጥያቄ ያነሳሉ:: የደኢህዴን አመራር አባላት ጭምር “ጥናቱ አዲስ ነገር አላመጣም፡፡ እኛ በግምገማ ስናየው የነበረውን ነው መልሶ የነገረን” ይላሉ፡፡ እዚህ ላይ መነሳት የሚገባው ሌላው ጥያቄ፣ ጥናቱ ለምን ተፈራ? የሚል ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ጥናቱን የፈሩት የፖለቲካ ልሂቃኑ ናቸው፡፡ ፖለቲከኞቹ የህዝቡን ፍላጎትና የምሁራኑን ሳይንሳዊ የምርምር ምክረ-ሃሳብ ለምን እንደፈሩት እንቆቅልሽ ነው፡፡
ከላይ እንደተመለከተው የጥናቱ አስፈላጊነት ጥያቄ የሚነሳበት መስሎ አይታየኝም፡፡ የቀረበውን የአደረጃጀት ጥያቄ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ለመመለስ መወሰን ደግሞ ከቅሬታ ነፃ የሆነ ምላሽ ለመስጠት ጠቃሚ ነው፡፡ ጥናት ገደብ የለውም፡፡ ይህንን አጥና፣ ያንን ተው ማለት አይገባም፡፡ እንኳን ህገ መንግስት፤ ቅዱስ ቁርዓንና መጽሐፍ ቅዱስን የሚመለከት ጥናት ማድረግ ይቻላል፡፡
አጥኚዎቹ እነማን ናቸው?
አጥኚው ቡድን የተቋቋመው በደኢህዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው፡፡ ሀገራዊ አደረጃጀት የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች የድርድር ውጤት በመሆኑ፣ ፓርቲው፣ አጥኚ ኮሚቴ እንዲቋቋም ማድረጉ ችግር የለውም፡፡ ሁሉም አጥኚዎች የደቡብ ክልል ተወላጆች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ የፓርቲ አባላት ሲሆኑ በሚኒስትር ደረጃ ላይ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር የተካተቱበት ነው፡፡
ጥናቱ ለምሁራን እድል የሰጠ ነው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ እንደ ገብሬ እንጢሶ ያሉ አንቱ የተባሉ የማህበራዊ ሳይንስ (ሶሽዮሎጂ) ምሁራን ናቸው ጥናቱን ያካሄዱት፡፡ አበው “የአገሩን በሬ በአገሩ ሰርዶ” እንዲሉ ለደቡብ ችግር፣ በደቡብ ምሁራን መፍትሄ ለመስጠት አጥኚዎቹን ከደቡብ ተወላጆች እንዲሆኑ መደረጉ ክፋት የለውም ሊባል ይችላል:: ይሁን እንጂ ከሌላ አካባቢ ምሁራን እንዲቀላቀሉ ቢደረግ ኖሮ፣ ሁለት ጥቅሞችን ማግኘት እንደሚቻል አስባለሁ፡፡ አንደኛ፤ የጥናቱን ሂደት ለመታዘብ ይረዳል፣ ከሀሜትም ያድናል፡፡ ሁለተኛ፤ ችግሩ ደቡብ ላይ ያጋጠመ ቢሆንም የጋራ ሀገራዊ ችግር በመሆኑ፣ ሁሉም ዜጎች በመፍትሄ ማፈላለጉ ሂደት እንዲሳተፉ ማድረግ አስፈላጊም ጠቃሚም መሆኑ ይታየኛል፡፡
የጥናቱ ይዘት
የጥናቱ ይዘት በሰነዱ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት፤ በመግቢያው ስለ ምርምሩ አነሳሽ ችግር፣ የጥናቱ አላማ፣ ጥናቱ የሚመልሳቸው ጥያቄዎች፣ የጥናቱ አስፈላጊነት፣ ወዘተ. ተካተዋል፡፡ በጥናቱ ምዕራፍ 2 በተለምዶ “Literature review” የሚባለው የጥናት አደረጃጀት ቀርቧል፡፡ በዚህም ስለ ፌዴራሊዚም ጽንሰ ሀሳብና ዓለም አቀፍ ልምዶች፣ ፌዴራሊዝም በአፍሪካ፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓትና ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም አተገባበር ያመጣው መልካም ለውጥና ተግዳሮቶች፣ የደቡብ አፍሪካ፣ የናይጀርያ፣ የኬንያ እና ያደጉ የሰሜን አሜሪካና የአውሮፓ ሀገራት ተሞክሮ ተዳስል፡፡ ከዚሁ ጋር በፌዴራል ሀገራት የተነሱ ጥያቄዎችና ምላሾችን የሚመለከቱ ተሞክሮዎች እንዲሁም የፌዴራሊዝም አተገባበርና ውጤቱ በደቡብ ኢትዮጵያ… በጥናቱ ዳሰሳ የተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የጥናቱ ሦስተኛው ክፍል፤ የጥናት ዘዴዎችን፣ አራተኛው ክፍል መረጃና መረጃ ትንተናን እንዲሁም አምስተኛው ምዕራፍ መደምደሚያና ምክረ-ሀሳቦችን ያስቀምጣል፡፡
አጥኚው ቡድን እንደ ዓላማ አድርጎ የተነሳው “የአደረጃጀት ጥያቄዎች ለምን እንደተበራከቱ፣ ከዚህ በፊት በተሰጡ መልሶች የአደረጃጀት ጥያቄዎች መልስ ለምን ዘላቂ መሆን እንዳልቻለ፣ ከሀገራት ተሞክሮ አንጻር ዘላቂ የሆነ አደረጃጀት እንዴት እንደሚፈጠር፣ ከአደረጃጀት መስፋት ወይም መጥበብ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች ምን ምን እንደሆኑ፣ አደረጃጀት ኅብረ-ብሔራዊ ብዝኃነት ባላቸው ሀገሮች እንዴት እንደተተገበረ ወዘተ... በማሰስ ለውሳኔ ሰጪው አካል ምክረ-ሀሳብ ለማቅረብ” መሆኑን በሰነዱ ላይ ገልጿል፡፡
እነዚህን ዓላማዎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ለመተንተን የተነሱት የምርምር ጥያቄዎች ደግሞ፤ “የደቡብ ክልል አመሠራረት ሂደት ምን ይመስላል? የክልሉ ህዝቦች አብረው በአንድ ክልል በመደራጀታቸው ያገኙት ጥቅምና ያጋጠማቸው ተግዳሮት ምን ምን ናቸው? በክልሉ ህዝብ ዘንድ እየተነሱ ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎች መንኤያቸው ምንድነው? የመንግስታዊ አደረጃጀት ጥያቄዎች መንስኤና ምላሾች፣ በተግባር ከብዝኃነት ጋር ያለ ተሞክሮ ምን ይመስላሉ? እና በክልሉ ለተነሱት የአደረጃጀት ጥያቄዎች ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ምንድናቸው?” የሚሉ ናቸው፡፡
የጥናቱ ድክመቶች
ማንኛውም ጥናት ውስንነቶች ይኖሩታል፡፡ የሚጠበቅም ነው፡፡ አጥኝውም ጥናቱን ከማካሄዱ በፊት የሚገጥሙትን ውስንነቶች ለይቶ በማወቅ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይጠበቅበታል:: ይህም አጥኚ ቡድን አራት ችግሮች ሊገጥሙት እንደሚችሉና እነዚያን ውስንነቶች እንዴት እንደሚያስወግዳቸው መፍትሄ አስቀምጧል፡፡ ይሁን እንጂ በኔ በኩል አጥኝው ቡድን ካስቀመጣቸው ውስንነቶችም ውጪ ሌሎች ችግሮች አስተውያለሁ::
አንዱ ተጠቃሽ ችግር የጊዜ ውስንነት ነው፡፡ ይህንን ሰፊ ጥናት በሰባት ወራት መስራት በውስጡ ጥድፊያ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ በሰባት ወር ውስጥ፣ በዚህ ቀውስ ወቅት ተንቀሳቅሶ ሰርቶ እዚህ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል ወይ? የሚል ጥያቄም ያስነሳል፡፡ ሌላው ችግር ሚኒስትርን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣንና የፓርቲ አባል በሆኑ ምሁራን መጠናቱ የጥናቱን ውጤት ለፖለቲከኞች ሀሜት ያጋልጣል:: ሁሉም አጥኝዎች ከደቡብ ክልል ብቻ እንዲሆኑ መደረጉም የጥናቱ እንከን ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ዘጠና አራት በመቶ (94%) የጥናቱ አካባቢ በጥናቱ ተሸፍኗል ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ የሲዳማ ዞን በጥናቱ አልተካተተም፡፡ እናም የጥናቱ መነሻ የሲዳማ ጥያቄ ከሆነ፣ ሲዳማን ያልጨመረ ጥናት ማካሄድ ችግሩን ይፈታዋል ወይ? የሚል ጥያቄም እንዲነሳ አድርጓል፡፡ የጥናቱ ውጤት ያመላከተው ሦስት አማራጭ ምክረ ሃሳቦችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩ ጎልቶ የተሰማበት ሲዳማ በጥናቱ ቢካተት ኖሮ ምናልባትም አራተኛ አማራጭ ምክረ ሃሳብ ሊያስገኝ ይችል ነበር የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡
የማጠቃለያ ሃሳቦች
እንደ መውጫ አንዳንድ ነጥቦችን በማንሳት ጽሁፌን ላጠቃል፡፡ ጥናቱ “የጥናትን መስፈርት” ያሟላና ሳይንሳዊ መሆኑን አስረግጦ መናገር ይቻላል:: የጥናቱ ውጤት በህዝቡ ውስጥ ያለውን ሃሳብና ፍላጎት በሳይንሳዊ ዘዴ ለማረጋገጥ ያስችላል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ “መልካም አስተዳደር ከተፈጠረ አብረን መኖር፣ አብረን ማደግ፣… እንችላለን” ነው ያለው በጥናቱ የተጠየቀው ህዝብ፡፡ በዚህም መሰረት ህዝቡ ምስክርነቱን የሰጠው፤ ኢህአዴግ በአግባቡ አለመምራቱን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጥናቱ የደኢህዴንን ድክመትና አቅመ ቢስነት ጥሩ አድርጎ አጋልጧል፡፡
ጥናቱ ህግ አይደለም፡፡ የቃል ኪዳን ሰነድም አይደለም፡፡ ምሁራዊ ተግባር (Academic exercise) ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ ለጥያቄው አፈታት ግን ግብዓት ሆኖ ሊያገለግል ይችላል፡፡ እናም የፖለቲካ ኃይሉ ጥናቱ እንዲካሄድ ማድረጉ የሚያስመሰግነው ነው፡፡ ጥናቱ መነሻ ነው እንጂ መድረሻ አይደለም፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ጥናቱ ለምን አቧራ አስነሳ? ጥናቱ የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ የደረሰ ነው ከተባለ፣ ሌላ ጥናት አካሂዶ ጉድለቱን ማሳየት ሲቻል፣ ጥናቱ ለምን ይፈራል? በኔ እይታ ጥናቱ ውይይትን የሚጋብዝ ነው፡፡ እናም ከውሳኔ በፊት ወርደን እንወያይ ማለት ችግር የለውም፡፡
አንዳንዶች የሚያነሱት “ማንነታችን ጎልቶ ሊታይ አልቻለም” የሚል መንፈስ ያለው ስጋት እንደሆነ ይሰማል፡፡ ይህንን በተመለከተ፤ ክልል በመመስረት ብቻ ሳይሆን መልካም አስተዳደርን በማስፈን ስመ-ጥር መሆን እንደሚቻል፣ ከሙስና የጸዳ ዞን በመፍጠር ታዋቂ መሆን እንደሚቻል፣ አካባቢን በማልማት የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት መሳብ እንደሚቻል ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ (የኮንሶ ማንነትና የእርከን ሥራ በዓለም የታወቀው “የኮንሶ ክልል” ስለተቋቋመ አይደለም) በሌላ በኩል፤ የደቡብ ክልል መፈጠሩና አዲስ ማንነት መጨመሩ በተለይም እንደ አሪ፣ ዘይሴ፣ ሙርሲ፣… ያሉ አናሳ የህዝብ ቁጥር ያላቸው “ህዳጣን ማህበረሰቦች” በአንድነት ድምጻቸውን ለማሰማት በመቻላቸው፣ በፌዴራሉ ስርዓት የተደራዳሪነት ኃይል እንዲያገኙ ያደረጋቸው መሆኑም ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ደቡባዊ ማንነት፣ ነባር ማንነትን ያጠናክር እንደሆነ እንጂ ሊጨፈልቅ አይችልም ብዬ አስባለሁ፡፡
የሲዳማ ፖለቲከኞች “ክልል እንሁን” የሚል ጥያቄ ማቅረባቸው ችግር የለውም፡፡ ግን… ግን… በዞን የአስተዳደር ዘመናቸው ለዞኑም ሆነ በዞኑ ስር ባሉት ወረዳዎችና ቀበሌዎች ለህዝባቸው ምን ሰርተው፣ ምን ለውጥ አምጥተው ነው የክልል እንሁን ጥያቄ የሚያቀርቡት? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ግድ ይለናል፡፡ እንደኔ እንደኔ ክልል አለመሆን ለመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ክልል አለመሆን ለሙስና መንሰራፋት ምክንያት ሊሆን አይችልም:: ክልል መሆንም የችግሮች ሁሉ የመፍትሄ ቁልፍ ሊሆን አይችልም፡፡
የክልልነት ጥያቄ ያቀረቡት ፖለቲከኞች፤ ሀገሪቱ በምን ዓይነት አውድ ውስጥ ነው ያለቺው? የሚለውን ማየት አለባቸው፡፡ እንደ ሀገር መኖር ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት “አሁኑኑ ሪፈረንደም ይደረግ” ማለት በየትኛውም የፖለቲካ መስፈርት ትክክለኛ ሊሆን አይችልም፡፡ ጥያቄው ዋል አደር ቢልስ… የዞኑ ህዝብ ምን ያገኛል? ምንስ ያጣል? የሚለው በአግባቡና በጥልቀት መታየት አለበት፡፡ የሚገኘው ጥቅምና የሚደርሰው ጉዳት መመዘን አለበት፡፡
ምርጫ ቦርድ ለምን ሪፈረንደሙን ያካሂዳል? ማን ስልጣን ሰጠው? የሚሉ ጥያቄዎችም ተያይዘው ሲነሱ ይሰማል፡፡ በየትም ሀገር ሪፈረንደምን ጨምሮ ማንኛውም ምርጫ የሚካሄደው በምርጫ አስፈጻሚ አካል አማካይነት ነው፡፡ የኛ ሀገር ምርጫ አስፈጻሚ አካል ደግሞ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ የተለየ ተቋም ሊቋቋም አይችልም፡፡
ከዚህ በፊት በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣… አጎራባች ቀበሌዎችን በተመለከተ ውሳኔ ህዝብ የተሰጠው በምርጫ ቦርድ አማካይነት ነበር፡፡ ስለዚህ ምርጫ ቦርድ የሪፈረንደም አስፈጻሚ መሆኑ ጥያቄ የሚቀርብበት ሊሆን አይችልም፡፡
ሀገራት የሚተገብሩት የመንግስት ዓይነትና አወቃቀር ለፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ዕድገትና በሕዝቦች መካከል ለሚኖር ጤነኛ መስተጋብር ጉልህ አስተዋጽዖ አለው፡፡ የመንግስት ዓይነትና አወቃቀር ምርጫ፤ የየሀገራቱን ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ በጥልቀት በመገምገም የሚወሰነዉ ከሚያሳድረዉ ዘርፈ ብዙ ተጽዕኖ በመነሳት ነዉ፡፡ ከዚህ አኳያ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት፣ የክልልነት ጥያቄውን ሲወስን በአግባቡ ተወያይቶበታል ወይ? የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ ሌሎች ሰዎችም ይህንን ጥያቄ እንደሚጋሩት አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ፤ ጥናቱ በእውቀትና በጉልበት መካከል የነበረውን ልዩነት ያሳየ ነው፡፡ በጩኸትና በሆያ ሆዬ የቀረበ “የውህዳን የክልልነት ጥያቄ” የብዙሃን ጥያቄ መስሎ እንዳይታየንና እንዳያሳስተን መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የደቡብ ፖለቲከኞች ለብዙሃኑ ውሳኔ ተገዥ መሆን  አለባቸው:: ያስመረጣቸው ፓርቲ አመራር ተወያይቶ ላሳለፋቸው ውሳኔዎች ተገዥ መሆን ብቻ ሳይሆን ወደ ታች አውርደው ማስፈጸምም ግዴታቸው መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡ የፓርቲውን ዲሲፕሊን ካላከበሩ ፓርቲው ወደ ላይ እንዳወጣቸው ሁሉ ወደ ታች አውርዶ፣ ከፖለቲካ ውጪ ማድረግ ይችላል፡፡ ከተሞክሮ አኳያ ህወሓት በ1993 ዓ.ም በውስጡ በተነሳው መከፋፈል የምክር ቤት አባላቱን አግዶ፣ የመተማመኛ ድምፅ ጠይቆ (Recall) ከስልጣን አውርዶ በማሟያ ምርጫ ተክቷቸዋል፡፡ ደኢህዴን፤ በሕዝብ ፍላጎትና በምሁራን ሳይንሳዊ የምርምር ውጤትና ምክረ-ሃሳብ ላይ ባመጹ፣ ፓርቲውንና መንግስትን አልታዘዝም ባሉ፣ አፈንጋጭ አባላቱ ላይ ይህንን አለማድረግ፣ ውጤቱ ሀገርን እስከ ማፍረስ ሊደርስ እንደሚችል ሊገነዘበው ይገባል፡፡ ሀገርን ማፍረስ ደግሞ ደቡብ ላይ ተወስኖ የሚቆም አይደለም፡፡
ጸሐፊውን በEmail: ahayder2000@gmail.Error! Hyperlink reference not valid. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1897 times